የኤርትራ ሰራዊት ድንበር ጥሶ በመግባት ወረራውን ተቀላቅሏል - ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
ኢዜጋ ሪፖርተር
November 11, 2020 (Ezega.com) -- ከተጀመረ 7ኛ ቀኑን ባስቆጠረው የእርስበርስ ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ተሰምቷል። የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሃይል በትግራይ 8 ግንባሮች ያሰማራ ሲሆን በዚህም በተለያየ አቅጣጫ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑ ይታወቃል።ከዚህ ሌላ የኤርትራ ሰራዊትም ድንበር ጥሶ በመግባት መከላከያውን እያገዘ ነው ሲሉ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከሰዋል። "አምባገነኑ አብይ አሕመድ የትግራይን ህዝብ ለመጨፍለቅ የለኮሰውን ጦርነት ከባድ ኪሳራ ስላጋጠመውና እንደሚሸነፍ ስላወቀ አምሳያው ኢሳይያስን ድረስልኝ ብሏል እኛ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ስንገጥም ኢሳይያስ አብይን ለማዳን ከጀርባችን ውጊያ ጀምሯል" ያሉት ሊቀመንበሩ ያም ሆኖ "የትግራይን ህዝብ ለመጨፍለቅ ተግተልትለው የመጡትን ወራሪ ሃይሎች እስካሁን ከባድ ኪሳራ ተከናንበዋል አሳፋሪ ሽንፈትም እየደረሰባቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ እንዳሉት "ኢሳይያስ አፈወርቂ ከአብይ አህመድ በቀረበለት ግብዣ መሰረት ትናንት ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ትግራይ ምዕራባዊ ዞን ለመተኮስ ተገዷል።" በዚህም "እኛ ከአምባገነኑ አብይ ጋር ፊት ለፊት ስንገጥም ኢሳይያስ ከባድ ሽንፈት መከናነብ የጀመረውን የአብይ አህመድን 'የድረስልኝ' ጥሪ ተቀብሎ ከኋላ ውጊያ እያካሄደብን ነው" ያሉ ሲሆን "ከዚህ አኳያ በአንድ በኩል አምባገነኑ አብይ አሕመድና ትምክሕተኛው ሃይል ከጀርባ ደግሞ አምባገነኑ ኢሳይያስ አፈወርቂ የከፈቱት ጦርነት በባድመ ግንባርም ተጀምሯል" ሲሉ ወቅሰዋል።
ደብረፅዮን አክለውም የሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በሙሉ በትግራይ ላይ ዘምቷል በግላጭም የትግራይ የገጠርና ከተማ ኣካባቢዎች የጦር ጄቶቻቸው ይደበደባሉ ተብሎ በሚድያ ተገልጿል። በተግባርም በትግራይ በገጠርም በከተማም የአየር ድብደባ አጋጥሞናል ብለዋል የትግራይ ህዝብ መከላከያ ሰራዊት እንደ ልጆቹ ተንከባክቦ ድጋፍ ሰጥቶ ሲታገል በግንባርም ሲሰዋ የቆየ ህዝብ ነው አሁን ያለን ልዩነትም ከመከላከያው ሳይሆን ከብልፅግናና "ከአምባገነኑ መሪ" ነው ያለው መግለጫው "ልዩነቱ ፓለቲካዊ ነው መፍትሄውም ፓለቲካዊ መሆን ነበረበት አምባገነኑ ቡድን ግን በጉልበት የትግራይን ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ደፍጥጦ የክልሉን ምርጫ ጥሶ ምክርቤቱን አፍርሶ ከአዲስ አበባ ትግራይን የሚያስተዳድር መንግስት አቋቁማለው ብሎ ጦርነት እንዳወጀ ሁላችን የምናቀው ነው" ብለዋል። አሁን ልዩነቱን ለማጥፋት በሚል በጉልበት ወደ ማምበርከክ ጦርነት ተገብቷል የፈለጉትን በሀይል አደርጋለሁ ወደ ማለት ተሸጋግሯል የሚሉት ደብረጺዮን የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ በርካታ ጦርነቶች እየተካሄዱ ነው ይህ ዘመቻም "ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ከማድረሱም ባሻገር ሄዶ ሄዶ የሃገሪቷ አንድነት የሚጎዳና የሚበትን ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
ይሁን እንጂ "የትግራይን ህዝብ በወራሪ ሃይል ማንበርከክ አይቻልም ታሪክ ምስክር ነው ወራሪ ሃይል የውስጥም የውጭም የትግራይ ህዝብን ማንበርከክ አይችልም ይሄ በተግባርም ይደገማል" ያሉ ሲሆን። አሁን የአብይ ቡድንና ኢሳያስ በጋራ በትግራይ ህዝብ ላይ ወረራ እያካሄዱ ይገኛሉ በባዕኸር አከባቢ ሲደረግ በነበረው ውጊያም ላይም የኤርትራ መንግስት በስተጀርባ ሆኖ ሁመራን በከባድ መሳርያ በመደብደብ አጋርነቱን በተግባር አሳይቷል። ሲደረግ የነበረውን የመከላከል ውግያ ለማክሸፍም ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥቷል ሲሉ ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ያም ሆነ ይህ የትግራይ ህዝብ ወራሪውን ሃይል ክፉኛ ተዋግቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው ይገኛል ለዚህም ነው የኤርትራ መንግስት ድጋፍ ያስፈለገው የሚሉት ደብረጺዮን የኢሳያስ ድጋፍ ካልተጨመረ የትግራይን ህዝብ ማንበርከክ አልችልም አሁን ያሉ ምልክቶች አሳሳቢ ናቸው ተብሎ ኢሳያስን በመማፀን ተኩስ ጀምርልን ነው እየተባለ ያለው ብለዋል። በመሆኑም "በዛሬው ዕለት የኢሳያስ ሰራዊት የሃገሪቱን ድምበር ጥሶ ወረራ ጀምሯል የትግራይ ህዝብ ግን ተጨማሪ መስዋእትነትም ከፍሎ ዳርድንበሩን ለማስከበር ወደኋላ አይልም" የሚሉት ሊቀመንበሩ "የአብይ ቡድን የሃገሪቷን ዳርድንበር ለባእድ አሳልፎ በመስጠት ትግራይን ለመቀጥቀጥ በመምረጥ ከኢሳይያስ ጋር በማበር በቅንጅት ጦርነት ማካሄድ መጀመራቸውን ሁሉም ማወቅ አለበት" በማለት ተናግረዋል። በተጨማሪም "ይህ ጉዳይ የትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም ጉዳዩ የኤርትራውያንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችም ጉዳይ ነው የትግራይ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ብቻ ነው ይከበርልኝ ያለው ተምበርክከህ ሰጥ ለጥ አርገን ቀጥቅጠን እንገዘሃለን ተብሎ ነው በሁሉም አቅጣጫ ወረራው የተጀመረው ትልቅ ክህደት ነው እየተፈፀመበት ያለው" በማለት የሚያትተው መግለጫው "የሃ
ገሪቱን ዜጋ በውጭ ሃይል ለማንበርከክ የሃገሪቱን ዳርድንበር ኣሳልፎ የሰጠ ቡድን" ነው ያለው ሲልም አክሏል።
የትግራይ ክልል ይህን ይበል እንጂ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ግን ወቀሳውን ሀሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
"የኤርትራ ወታደር ጥቃት እያደረሰብን ነው በሚል በደብረፂዮን ገብረሚካኤል የተሰጠው መግለጫ ፍፁም ሃሰት ነው" ያሉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ "ጁንታው በተለያዩ አጋጣሚዎች ህዝብን ለማደናገር ጥረት እያደረገ ይገኛል ቀደም ሲል "በቂ ተዋጊ አለኝ፣ ሰሜን ዕዝም አብሮን ተሰልፏል፣ የመከላከያ ሃይሉን የጦር ጀቶች በሚሳኤል እንመታለን" የሚል ፉከራ ውስጥ" ነበረ "የትግራይ ምድር ለሚዋጉን ሁሉ መቀበሪያ ትሆናለች" የሚል ዛቻም ያሰማ ነበር ያሉት ሜጀር ጄነራል መሐመድ "አሁን ያ ሁሉ ፉከራ አልሳካ ብሎ በመከላከያ ኃይሉ አከርካሪው እየተሰበረ ሲመጣ ሌላ የማደናገሪያ ሃሳብ ይዞ ብቅ ብሏል" ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ላይ ህብረተሰቡ ፅንፈኛ ቡድኑ በሚያሰራጫቸው የሃሰት ወሬዎች እንደይደናገርም ያሳሰቡት ሃላፊው በፅንፈኛ ሃይሉ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ከማለታቸውም በላይ "በቅርቡም በርካታ የድል ዜናዎችን ለኢትዮጵያ ህዝብ እናበስራለን" ማለታቸው ተሰምቷል።
ደ/ር ደብረጽዮን በዚህ ጉዳይ የተናገሩት ለመስማት፣ እዚህ ይጫኑ።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን