ፌደራል ፖሊስ ለበርካታ የህወሃት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮችና የእስር ማዘዣ አወጣ

ኢዜጋ ሪፖርተር

November 12, 2020 (Ezega.com) -- የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን "የአገር ክህደት ወንጀል በፈፀሙ የጁንታው ሕወሓት ቡድን አባላት" ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው አስታወቀ። የህወሃት ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ በ64 የፓርቲው አባላት ላይ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው "በትግራይ ክልል በሚገኘው በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀምና ከኦነግ ሸኔ እና ከሌሎች ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ከተለያዩ ክልሎች አገርን የማፍረስ ተልዕኮ ያለቸውን ኃይሎች በመመልመል ትግራይ ክልል ድረስ በመውሰድ ለእኩይ ተልዕኮቸው ስኬት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን በማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ብሄርን ከብሄር በማጋጨት እና በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ በርካታ ንፅሁን ዜጎች እንዲገደሉ፣ በአካልና በንብረት ላይም ከባድ ጉዳት እንዲደርስ በማድረጋቸው በፈጸሙት ከባድ የአገር ክህደት ወንጀል ምክኒያት መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግላጫ አስታውቋል። ከእነዚህ "የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣል እንዲሁም ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል በመናድ" ወንጀል ከሚፈለጉትና የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው የህወሃት አባላት መካከል ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ ጌታቸው ረዳ፣ ፈትለወርቅ ገ/እግዝያብሄር፣ አስመላሽ ወ/ስላሴ፣ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ ኪሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አዲስ አለም ቤሌማ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሐዬ፣ አቶ ስብሀት ነጋ እና ሴኮትሬ ጌታቸው ይገኙበታል። ግለሰቦቹ በከፍተኛ የአገር ሃብት ምዝበራና ዘረፋ እንዲሁም በሰበአዊ መብት ጥሰት ወንጀልም ጭምር የሚፈለጉ መሆናቸውን ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አሳውቋል፡፡

ከላይ ከተዘረዘሩት የህወሃት አባላት ጋር በማበር የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጸመዋል አገር በማፍረስ ሴራ ውስጥም ተሳትፈዋል ባላቸው 32 የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ አመራሮች ላይም በተመሳሳይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ "መንግስት እና ሕዝብ የጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነትና ህገመንግስታዊ ግዴታ ወደጎን በመተው መቀመጫዉን ትግራይ ክልል ካደረገዉ ከወንበዴው የህወሃት የጁንታው ቡድን አባላት ተልዕኮ በመቀበል በሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላት ውስጥ ሴሎችን በማደራጀት ከማዕከል የነበረው ግንኙነት እንዲቋረጥና ጥቅምት24 ቀን 2013 ዓ/ም ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግ የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ" እንዲፈፀም ማድረጋቸውን የኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል፡፡ ባለፉት 21 አመታት በምሽግ አብረው ሲኖሩ የነበሩ ጓዶቻቸውን "የጁንታው ቡድን እኩይ አላማ ማስፈጸሚያ በማድረግ አገር በማፍረስ ተልዕኮው በመምራትና በመሳተፍ" ከሚፈለጉት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የፖሊስ አባላት መካከልም ሌ/ጀኔራል ታደሰ ወረደ ተስፋዬ (ውዲ ወርደ)፣ ሜ/ጄኔራል ዮሐንስ ወ/ጎርጊስ ተስፋይ (መዲድ)፣ ሜ/ጄኔራል ብርሃነ ነጋሽ በየነ (ውዲ መድህን)፣ ብ/ጄኔራል ሀ/ስላሴ ግርማይ ገ/ሚካኤል፣ ብ/ጄኔራል ምግበ ሃይለ ወ/አረጋይ (አባበርሃ) እና ሜ/ጄኔራል ኢብራሂም አብዱልጀሊል መሀመድዙን ይገኙበታል። በፖሊስ ዝርዝር ውስጥ ስሞኑን በቁጥጥር ስር የዋሉት ሜ/ጀነራል ገ/መድህን ፍቃዱ ሃይሉ (ውዲ ነጮ)፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገ/መድህን ገ/ፃድቅ (አስቴር)፣ ብ/ጀነራል ገ/ህይወት ሲስኖስ ገብሩ፣ ብ/ጀነራል ኢንሶ እጃጆ እራሾ፣ ብ/ጀነራል ፍስሃ ገ/ስላሴ እንሁን፣ ኮ/ል ደሳለኝ አበበ ተስፋዬ እና ኮ/ል እያሱ ነጋሽ ተሰማ እንደሚገኙበት ታውቋል።

በተመሳሳይ መረጃ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የ38 ከፍተኛ የህወሃት አመራሮችን ያለመከሰስ መብት አንስቷል። ምክር ቤቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ወንጀሎች የጠረጠራቸውን የእነዚህን ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው የውሳኔ ሐሳቡን በሙሉ ድምጽ ያፀደቀው። በዚህም መሰረት የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ የ38 ግለሰቦች ያለመከሰስ መብት ተነስቷል። ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ከተደረገባቸው ግለሰቦች መካከል የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ፣ አቶ አባይ ፀሐዬ፣ ዶክተር አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ አፅበሃ አረጋዊ፣ አቶ ገብረ እግዚአብሄር አርአያ  ይጠቀሳሉ። ዐቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የጠየቀባቸው ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እነዚህም "ከፍ ያለ የአገር ክህደት መፈጸም፣ በሕገ-መንግስቱና በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ በተደረገ ወንጀልና የጦር መሳሪያ ይዞ ማመፅ" ይገኙበታል። በተጨማሪም "የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት በሚፈጸም ወንጀል፣ የአገር መከላከያ ኃይልን በመጉዳት እና በሽብር ወንጀል በመሳተፍ እንዲሁም ዋና የሽብር አቅራቢ በመሆን" መጠርጠራቸው ለምክር ቤቱ ተገልጿል። የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት አስተያየት የተሰጠ ሲሆን ውሳኔው መዘግየቱንና ይህ ቡድን አገሪቱን "ወደ ቁልቁለት ጉዞ ከመክተቱም ባሻገር ሀገሪቱን በሽብር ለማተራመስ ሲሰራ የነበረ በመሆኑ" የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ እንደሚደግፉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ም/ቤቱም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ያለመከሰስ መብትን ለማንሳት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 4/2013 ሆኖ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :