በመቀሌና በአዲግራት ሰላማዊ ዜጎች በአውሮፕላን ድብደባ ተገድለዋል - ደብረ ጺዮን ገ/ሚካኤል

ኢዜጋ ሪፖርተር

Ethiopia-Fighter-JetsNovember 12, 2020 (Ezega.com) -- የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጺዮን ገ/ሚካኤል በመንግስት ተዋጊ አውሮፕላኖች ጥቃት በክልሉ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ለሮይተርስ ተናገሩ፡፡ ርእሰ መስተዳደሩ በስልክና በአጭር የስልክ ጽሁፍ መልእክት ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ እንዳሉት ሰላማዊ ሰዎቹ በአየር ጥቃት የተገደሉት በተለይ በአዲግራት እና በርእሰ መዲናዋ መቀሌ ከተሞች ነው። ደብረጺዮን ጥቃቱ የተፈጸመው መቼ ነው? እና ስንት ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ? የሚል ጥያቄ ቅርቦላቸው ዝርዝሩን መናገር አልፍልግም ማለታቸው ተዘግቧል። ርእሰ መስተዳድሩ ለክሱ ማስረጃ አላቀረቡም ያለው ሮይተርስ ጉዳዩን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አለመቻሉንም አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የአየር ጥቃቶቹ የተመረጡ የህወሃት የጦር ሰፈሮች ላይ ብቻ እየተፈጸሙ ነው ማለታቸውን ያስታወሰው ዘገባው ከትግራይ ክልል በኩል የቀረበውን ክስ ከመንግስት በኩል ለማጣራት ሞክሮ እንዳልተሳካለት አስነብቧል። በተጨማሪም ደብረ ጺዮን በመንግስት በኩል የቀረበው ውንጀላ ሀሰት ነው ራሳችን ከጥቃት ተከላከልን እንጂ በመከላከያ ሠራዊቱ ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት አልፈጸምንም በማለት ማስተባበላቸውንም ሮይተርስ ጠቅሷል፡፡ የክልሉ ታጣቂዎች ከክልሉ ውጭ ጥቃት እንደማይፈጽሙ የተናገሩት ደብረ ጺዮን ዐለማቀፉ ኅብረተሰብ ጣልቃ ገብቶ ድርድር ካላስጀመረ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ድርድር ይመጣል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መከላከያ ሠራዊቱ በትግራይ ክልል የጀመረውን የማጥቃት ግስጋሴ በመቀጠል ሽራሮ ከተማን ጨምሮ የምዕራብ ትግራይ ቀጣናን ሙሉ ለሙሉ ነጻ አውጥቶ እንደተቆጣጠረ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አስታውቀዋል፡፡ ሠራዊቱ በተቆጣጠራቸው በእነዚህ ቦታዎች የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት የፊጥኝ ታስረው እና በሕወሃት ሃይሎች ተረሽነው ተገኝተዋል ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት አስነብበዋል። ያም ሆኖ በድርጊቱ የተረሸኑት ስንት ወታደሮች እንደሆኑ ግን አልጠቀሱም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ማምሻውን በፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት ሌላ መረጃ ደግሞ የሚንስትሮች ምክር ቤት በፌደሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት በትግራይ ክልል ለሚቋቋመው ጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር ደንብ እንዳወጣ አስታውቀዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት የሆነ ጊዜያዊው አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰኑ የሚታወስ ነው።

በተያያዘ ዜና "የ4ኛ ሜካናይዝድ አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ ሰራዊቱን በማታለልና ደባ በመስራት ጥቃት እንዲፈጸምበት የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል"ሲሉ ጥቃቱን ተከላክለው የተረፉ የሰሜን እዝ አባላት ተናገረዋል።

"በፅንፈኛው የህወሃት ታጣቂ ሃይል የተፈፀመብን ጥቃት ከፍተኛ ክህደት ነው" ያሉት አባላቱ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት "የተፈጸመው ጥቃት በታሪክ ከፍተኛ ክህደት" ነው። ከሰሜን አዝ አባላት መካከል የህወሃትን ሃይል በመከላከል የተረፉት አስር አለቃ ዋለልኝ ወርቅነህ የአገር አለኝታ በሆነው ሰራዊት ላይ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ተግባር የትም አገር ተፈፅሞ አያውቅም ያሉ ሲሆን "በተለይ የ4ኛ ሜካናይዝድ አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ ሰራዊቱን በማታለልና ደባ በመስራት የመሪነቱን ሚና ተጫውተዋል" ብለዋል። ጥቃቱ በተፈፀመበት እለት "የሰሜን እዝ 4ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን መኪና ታርጋ በመቀየርና ሌሎች ተንኮሎችንም በመፈፀም አስጠቅተውናል" ሲሉም ተናግረዋል። በሰሜን እዝ 4ኛ ሜካናይዝድ 2ኛ ብርጌድ የብሬን ምድብተኛ ወታደር አዱኛ እምሩ "የጁንታው ቡድን" ምሽት ላይ ከበባ በማድረግ ያልታሰበ ጥቃት እንደሰነዘረባቸው አስታውሶ ህወሃት ያስታጠቃቸው የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ተባብረው ጥቃቱን እንደፈፀሙባቸውም ተናግሯል።

ከእዙ መካከል አስር አለቃ ወርቅነሽ ሰለሞንም የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በህወሃት ቡድን የተፈፀመው ክህደት የባንዳነት ተግባር መሆኑን ተናግራለች። "ሰራዊቱ ለትግራይ ህዝብ አንበጣን በመከላከል፣ ጤፍ በማጨድ፣ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት በመገንባት አገልጋይ ነበር" ያለችው አስር አለቃ ወርቅነሽ የሰራዊቱ አባላት ካላቸው ገንዘብ በማዋጣት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ያስተምሩ እንደነበርም ገልጻለች። "ነገር ግን በከሃዲው ቡድን በታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ክህደት ተፈፅሞብን ባጎረሰ እጃችን ተነክሰናል የህወሃት ቡድን የፈጸመው አገርን የማፈራረስ አላማ የባነዳነት ድርጊት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያወግዘው ይገባል" ብላለች።

በተመሳሳይ የሰሜን ዕዝን የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ገብረመድህን ፍቃዱን ጨምሮ "ሃገርን በመክዳት ወንጀልና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ በማሰብ" ወንጀል የተጠረጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ፍርድ ቤት ቀረበዋል። የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ገብረመድህን ፍቃዱ፣ የመከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረመድህን፣ የደቡብ ዕዝ ሰው ኃብት ልማት አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ገብረዮኃንስ ሳርሲኒዮስ፣ የሰሜን ዕዝ መረጃ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ኢንሱ ኢጳጆ ረሾን ጨምሮ ሰባት ሃላፊዎች ሀገርን በመክዳት ወንጀልና ህገመንግስትና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ ማሰብ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውለው በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው መቀመጫውን ትግራይ ክልል ካደረገ የፀረ ሰላም ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል በመከላከያ ጦር ውስጥ ሴሎችን በማደራጀት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሬዲዮ ግንኙነት ማቋረጣቸውን ገልጿል፡፡ በዚህም ሰራዊቱ እርስ በርስ እንዳይገናኝና እንዳይቀላቀል በጦሩ ላይም የሞት፣ የአካል ጉዳትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እንዲፈፀም አድርገዋል ነው ያለው፡፡

እንዲሁም በሀገር ውስጥና ከውጭ የሚቃጣበትን ጥቃት እንዳይከላከልና የሰሜን ዕዝ ጦር እንዲፈርስ በማድረግ በተቀናጀ መልኩ ኦነግ ሸኔ ከተባለና ከሌሎች የፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ክልሎችም ሐይማኖትን ሽፋን አድርገው የብሄር ግጭት በማስነሳትም ሀገርን ለመበተን ሲሰሩ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱም የወንጀሉን ክብደትና በሀገር ደህንነት ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ወንጀል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለፖሊስ 14 የምርመራ ቀን ፈቅዷል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ትርምስ ለመፍጠር "የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ያሰማራቸው 242 ግለሰቦችና በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል" ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፋት 5 ቀናት ውስጥ ባደረገው አሰሳ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። የጦር መሳሪያዎቹ በፍተሻ፣ በብርበራ እና በየስርቻው ተጥለው የተገኙ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ በዚህም 18 ቦምቦች፣ 2 ፈንጂ፣ 1 ፀረ ተሽከርካሪ፣ 97 መገናኛ ሬዲዮ፣ 22 የትከሻ ሬዲዬ የተያዘ መሆኑን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። በተጨማሪም 2 ሺህ 686 የክላሽ ጥይቶች፣ 1 ሺህ 942 የሽጉጥ ጥይቶች፣ 1 ጂ.ፒ.ኤስ፣ 4 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 1 ላውንቸር፣ በአጠቃላይ 744 የጦር መሳሪያዎችና 4 ሺህ 628 ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቁት ኮሚሽነር ጌቱ ከዚህ ሌላ131 ሲምካርዶች፣ 6 የውጭ ስልክ መጥለፊያ፣ 74 የፀጥታ ደምብ ልብስ፣ 3 ሳይለንሰርና 600 ተንቀሳቃሽ ስልኮች መያዛቸውንም ገልፀዋል። እንዲሁም "የህወሓት ፅንፈኛ ያሰማራቸው 242 ግለሰቦች ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው" በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቅዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :