ህወሃት በባሕርዳር እና በጎንደር የሮኬት ጥቃት ፈጸመ፣ አስመራን አስጠነቀቀ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Bahir-Dar-AirportNovember 14, 2020 (Ezega.com) -- ህወሃት ትናንትና ምሽት አምስት ሰዓት አካባቢ በአማራ ክልል ዋና ከተማ በባህርዳር እና በአቅራቢያው በምትገኘው ጎንደር አውሮፕላን ማረፊያዎች አቅራቢያ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል። በተለይ በትግራይ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ተያያዥ መረጃዎች ለህዝብ እንዲሰጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ የሮኬት ተኩሱ መፈጸሙን አረጋግጧል። ዛሬ ጠዋት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያው የተሰጠው አጭር መግለጫ እንደሚያሳየው በጥቃቱ በአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ስግብግቡ ጁንታ ብሎ በጠራው ሃይል ጥቃቱ እንደተፈጸመም አስታውቋል። በተጨማሪም "ቡድኑ በእጁ ያሉትን የመጨረሻዎቹን መሣሪያዎች ጠጋግኖ የጥፋት ሙከራውን አድርጓል" ያለው መግለጫው የክስተቱን ዝርዝር መርማሪ ቡድን ተመድቦ እያጣራው መሆኑን ጠቅሶ ሙሉ መረጃው በቀጣይ ለህዝብ የሚገለጽ እንደሆነ ተነግሯል። ኢዜጋ በጎንደር ከሚኖሩ ግለሰቦች እንደሰማው ከምሽቱ አምስት ሰዓት ከ አስር ደቂቃ አካባቢ ሁለት ከባድ የፍንዳታ ድምጽ የተሰማ ሲሆን እርሱን ተከትሎም የአነስተኛ መሳሪያ ተኩስ ሲሰማ ነበር። በስፍራው ነበር የተባለ የቢቢሲ ዘጋቢም የክልሉ መንግሥት ስለክስተቱ መግለጫ እስከሚያወጣ ድረስ በከተማው ነዋሪ ዘንድ ግራ መጋባት ተፈጥሮ እንደነበር ገልጿል።

ያንን ተከትሎ የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምሽት 5:00 ላይ በክልሉ መገናኛ ብዙኀን በኩል በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ መኮድ በሚባለው አካባቢ እና ጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ የተከሰቱ ፍንዳታዎች መኖራቸውን ጠቅሶ "ፍንዳታው በጸጥታ ኃይሉ በፍጥነት" በቁጥጥር ስር ውሏል ሲል ማስታወቁ ተዘግቧል። ትናንት እኩለ ለሊት ላይ የአማራ ክልል መንግሥት ባስተላለፈው መልእክትም ፍንዳታው ከህወሃት ቡድን ጋር ይገናኝ አይገናኝ እየተጣራ ነው በሎ የነበረ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢሮው ግን ጉዳዩ በቀጥታ "በጁንታው"መፈጸሙን በመግለጫው ላይ አመልክቷል። የሮኬት ጥቃቶቹ በሰውና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ የተረጋገጡ መረጃዎች  አልወጡም። ሮይተርስ አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ወደ ጎንደር አየር ማረፊያ የተተኮሰው ሮኬት አየር ማረፊያው ላይ የተወሰነ ጉዳት ሲያደርስ፣ ወደ ባሕር ዳር የተተኮሰው ግን ከአየር ማረፊያው ውጪ መውደቁን ዘግቧል። መንግስት ለደህንነት በሚል ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጎንደር፣ ባህር ዳርና ላሊበላ የሚደረጉ የአየር በረራዎችን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ መወሰኑ ተሰምቷል። ይሁን እንጂ ባሕር ዳርም ሆነች ጎንደር ዛሬ ከጠዋቱ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን፣ ትናንት ምሽት ከተከሰተው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ምንም የተለየ ነገር በከተሞቹ የማይስተዋል መሆኑንና በከተማዋ የተለመደው የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቀጠሉን የከተሞቹ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የሮኬት ጥቃቱ ከተፈጸመ ድርጊቱ ከሰአታት በኋላ የህወሃት ከፍተኛ አመራርና የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል። በክልሉ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው ስለ ጥቃቱ ሲናገሩም "ፋሽስት አብይ አህመድ በተለያዩ የትግራይ ኣከባቢዎች በተደጋጋሚ እያካሄደው ለሚገኝ የአየር ድብደባ ጀግናው የትግራይ መከላከያ ሰራዊታችን አፀፋዊ ምላሽ ሰጥቷል" ነው ያሉት። በመሆኑም "በባህርዳር የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የጦር አውሮፕላን መንደርደርያ እና በጎንደር አየር ማረፊያ ውስጥ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የአየር ሀይል ካምፕ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ተካሂዷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያካሂደው ጥቃት እስካላቆመ ድረስ ጥቃቱ ተጠንክሮ እንደሚቀጥልና በሚቀጥሉት ቀናት በኤርትራ ላይም ጭምር የሮኬት ጥቃት እንደሚፈጸም ተናግረዋል። ከቀናት በፊት ከአንድ የትግራይ ክልል ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጌታቸው በክልሉ የአየር ድብደባ ለማድረግ የሚመጡ አውሮፕላኖችን እንመታለን "በድንገት ሾልኮ ያመለጠ ካለም የሚሄድበትን፣ የተነሳበትን፣ ያረፈበትን አውሮፕላን ማረፊያ የትም ይሁን የት እንመታለን" ማለታቸው ይታወሳል።

በተያያዘ "የትግራይ ህዝብና መንግስት የሰሩት አንደኛው የትግሉ ምዕራፍ በድል ተጠናቋል" ሲሉ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መናገራቸውን ህወሃት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። "በአሁኑ ሰአት ለእነ አብይ አህመድ የሚታዘዝ የሰሜን እዝ የሚባል ሰራዊት ትግራይ ውስጥ የለም በትግራይ ህዝብና መንግስት ቁጥጥር ስር ገብቷል ያሉት ሊቀመንበሩ "የትግራይ ህዝብ ይህንን ገድል መስራት በመቻሉ ለዘመናት ሊወሳ የሚችል አንድ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ አስመዝግቧል" ማለታቸው ተዘግቧል። በተጨማሪም "በዚሁ ደማቅ ታሪክ በተገኘው የመሳሪያ አቅም በቅርብ ጊዜ ጠላቶቻችን ይደመስሳሉ የትግራይን ህዝብ ለመጨፍለቅና የትግራይ ህዝብ መሬት ቆርሰው ለመውሰድ ወደ ትግራይ የገቡ ወራሪዎችም ትግራይን የረገጡባትን ቀን ይረግማሉ እነዚህ ጠላቶች የትግራይን ህዝብ ለመጨፍጨፍ በአውሮፕላን እየተመላለሱ ነው በተደጋጋሚ በትግራይ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ደብድበዋል" ብለዋል። አክለውም "እነዚህ ፋሽስቶች በዚሁ ተግባር ቀጥለው በትግራይ ህዝብ ላይ ለየት ያለ በደል የሚያደርሱ ከሆነ ግን እኛም ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደን ከባድ እርምጃ እንደምንወስድባቸው መታወቅ አለበት። የትግራይ ህዝብና መንግስት የሰሩት አንደኛው የትግሉ ምዕራፍ በድል ተጠናቋል ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር፣ በእጃችን ያስገባናቸውን አቅሞች ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚያስችል ስራም ሰርተናል" ማለታቸው ታውቋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :