ህወሃት አስመራን በርቀት ሚሳይሎች ደበደበ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Asmara-AirportNovember 14, 2020 (Ezega.com) -- የኤርትራዋ ርእሰ መዲና አስመራ ማምሻውን ከትግራይ ክልል በተተኮሱ ሚሳኤሎች መመታቷን የተለያዩ ምንጮች እየዘገቡ ይገኛሉ። ታዋቂው የብሪታኒያ እለታዊ ጋዜጣ ዘ ቴሌግራፍ (The Telegraph) ወደ አስመራ የተተኮሱት ሚሳኤሎች ከሁለት የማያንሱ ናቸው ብሏል። ጋዜጣው ከስተቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተከፈተው የእርስበርስ ጦርነት ቀጠናዊ መልክ ይዟል ነው ያለው። ኤርትራን ሀብ (Eritrean Hab) የተሰኘው ጋዜጣ በበኩሉ የተተኮሱት ሶስት ሚሳኤሎች መሆናቸውንና የከተማዋ አየር ማረፊያና የመረጃ ሚኒስቴር ሳይመቱ እንዳልቀረ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ዘመዶቻቸው ጋር ደውለው ማረጋገጣቸውን ጠቅሷል። በጥቃቱ ወቅት በአስመራ ከፍተኛ ድምጽ ያለው ፍንዳታ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች መናገራቸውን የዘገበው ሪፖርቱ አንድ የመኖሪያ ህንጻ መመታቱንም ጽፏል። ተኩሱ በከተማዋ መብራት እንዲቋረጥ አድርጓል ያለው ዘገባው ከጥቃቱ ቀደም ብሎ የትግራይ ቴሌቭዥን ኤርትራ ቀጣይዋ ኢላማ ልትሆን ትችላለች ሲል መዘገቡን አስታውሷል።  

የተፈጸመው ድርጊት ግጭቱን ወደ አለምአቀፍ ደረጃ ሊያሳድገው ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩንም ኤርትራን ሀብ አስነብቧል። ሌላው ስለ ክስተቱ የጻፈው ደግሞ ኤርትራን ፕሬስ (Eritrean Press) ነው። በዚህኛው መረጃ መሰረት የተተኮሰው አንድ ሚሳኤል ሲሆን እርሱም ከአስመራ ወጣ ባለ ቦታ ላይ ወድቋል። ዘገባው እንዳስነበበው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም የአየር ማረፊያውም አልተመታም። ድርጊቱ ህወሃት ኤርትራ ወደ ጦርነቱ እንድትገባ ያቀረበው "ይፋዊ ግብዣ" ነው ያለው መረጃው ያም ሆኖ የአገሪቱ መንግስት 'ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ስንል እንታገሳለን' የሚል አቋም ይዟል ብሏል። ትንኮሳው ጦርነቱን አለማቀፋዊ ገጽታ ለማላበስ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ያለው ጽሁፉ ኤርትራ ጥቃቱ ከምእራባውያን አገራት በኩል እንደሚወገዝ ትጠብቃለች ሲል አስነብቧል።  

በትናንትናው ምሽት በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች ላይ የሮኬት ጥቃት የፈጸመው ህወሃት ጥቃቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ቀጣዩ እርምጃ ኤርትራንም እንደሚመለከት አስታውቆ ነበር። የትናንቱ ጥቃት ከተፈጸመ ድርጊቱ ከሰአታት በኋላ የህወሃት ከፍተኛ አመራርና የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው  "ፋሽስት አብይ አህመድ በተለያዩ የትግራይ ኣከባቢዎች በተደጋጋሚ እያካሄደው ለሚገኝ የአየር ድብደባ ጀግናው የትግራይ መከላከያ ሰራዊታችን አፀፋዊ ምላሽ ሰጥቷል" ነው ያሉት። በመሆኑም "በባህርዳር የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የጦር አውሮፕላን መንደርደርያ እና በጎንደር አየር ማረፊያ ውስጥ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የአየር ሀይል ካምፕ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ተካሂዷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያካሂደው ጥቃት እስካላቆመ ድረስ ጥቃቱ ተጠንክሮ እንደሚቀጥልና በሚቀጥሉት ቀናት በኤርትራ ላይም ጭምር የሮኬት ጥቃት እንደሚፈጸም መናገራቸው ይታወሳል።  

በተመሳሳይ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ባሳለፍነው ሳምንት የኤርትራ ሰራዊት ድንበር ጥሶ በመግባት መከላከያውን እያገዘ ነው ሲሉ  መክሰሳቸው አይዘነጋም። በወቅቱ "አምባገነኑ አብይ አሕመድ የትግራይን ህዝብ ለመጨፍለቅ በለኮሰው ጦርነት ከባድ ኪሳራ ስላጋጠመውና እንደሚሸነፍ ስላወቀ አምሳያው ኢሳይያስን ድረስልኝ ብሏል እኛ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ስንገጥም ኢሳይያስ አብይን ለማዳን ከጀርባችን ውጊያ ጀምሯል" ያሉት ሊቀመንበሩ ያም ሆኖ "የትግራይን ህዝብ ለመጨፍለቅ ተግተልትለው የመጡትን ወራሪ ሃይሎች እስካሁን ከባድ ኪሳራ ተከናንበዋል አሳፋሪ ሽንፈትም እየደረሰባቸው ነው" ካሉ በኋላ "ኢሳይያስ ከባድ ሽንፈት መከናነብ የጀመረውን የአብይ አህመድን 'የድረስልኝ' ጥሪ ተቀብሎ ከኋላ ውጊያ እያካሄደብን ነው" ሲሉ ወቅሰዋል። ያም ሆኖ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግስታት ከሱ የተለመደ የቡድኑ የማምታታት ሴራ መሆኑን በመጥቀስ አጣጥለውታል። ይልቁንም ህወሃት በአልመዳ ጨርቃጨርቅ አማካኝነት የኤርትራ ሰራዊትን መለዮ በማምረትና የራሱ ሰዎች እንዲለብሱት በማድረግ "የተማረኩ የኤርትራ ሰራዊት አባላት' በሚል ሊያስወራ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :