በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ የተዘጋጁ 14 የአልሸባብ እና የአይ ኤስ አባላት ተያዙ

ኢዜጋ ሪፖርተር

ISIS-EthiopiaNovember 14, 2020 (Ezega.com) -- በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ 14የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ። አልሸባብ እና አይ ኤስ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት በመፈፀም "በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ ለማድረስ እንዲሁም የሀገራችንን በጎ ገፅታ ለማበላሸት በዝግጅት ላይ እንዳሉ" ብሄራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን 14 የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል ተብሏል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው አባላትን በመመለመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ኢላማዎችን በመለየት እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥቃቶችን ለመፈጸም ስምሪት ወስደው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የነበሩት ተጠርጣሪ የሽብር ቡድኖቹ አባላት በዛሬው እለት እንዲያዙ ተደርጓል። ይሄንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ሀገር ውስጥ የገባው አንደኛው የአልሸባብ የሽብር ቡድን አብዱል አብዲ ጀማል በቅፅል ስሙ አብዱልቃድር የተባለ ተጠርጣሪ ሲሆን በኢትዮጵያ የአልሸባብን የሽብር ህዋስ ሲያስተባብር የነበረና በሶማሊያ ከሚገኘው ጃፋር ወይም ጉሬ ከተባለ የአልሸባብ ከፍተኛ አመራር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና ስምሪት በመቀበል በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ወደ አዲስ አበባ ገብቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የግንኙነት መረቡን ሲያጠና ቆይቶ አብዱል አብዲ ጀማልን ጨምሮ አብዱራህማን አደን አቡበከር፣ ሙክታር ጋብ ጎሳ፣ ጋማዕ ድርዬ አብዲ፣ ሼህ አህመድ ኑር መሀመድ ኡስማን፤ኩሶው አደን ሁሴን፤ መሀመድ ሀሰን አደንና ኡመር ሬዲዋን ሙሃዲ ከተባሉ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ሲል አስታውቋል፡፡ በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ "በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እንደሚፈጽም ሲዝት የነበረው የአይኤስ የሽብር ቡድንን ህዋስ በአገር ውስጥ ሲያስተባብር የነበረው አማን አሰፋ ገዲምወርቅ የተባለው ተጠርጣሪም" ባደራጃቸው የጥፋት ቡድኖች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በተደረገበት ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ተብሏል፡፡ ተጠርጣሪው ለረጅም ጊዜ የአይኤስ አባል የነበረና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የጥፋት ቡድኖችን ሲያደራጅም የቆየ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ አይ ኤስ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መረጃው የደረሳቸው የኢትዮጵያ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ባደረጉት ክትትል የቡድኑ ህዋስ አስተባባሪ የሆነውና ከሶስት በላይ የሀሰት ስሞችን የሚጠቀመው አማን አሰፋ ገዲምወርቅን ጨምሮ የሽብር ቡድኑ አባላት የሆኑት ፉአድ ሽፋ ከድር፣ አብዱልጀባር አብደላ ኢብራሂም፣ ሰይድ ሙስጠፋ ኢብራሂም፣ መሱድ ሳጂቦ ገበየሁና ተፈራ በላይ ተሾመ ወይም እድሪስ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የአልሸባብና የአይኤስ ቡድን አባላቱ የወጠኑትን የሽብር ጥቃት ለማሳካት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ ስምሪት በመስጠት እንዲሁም የእነርሱን አስተምህሮዎች ለማስረጽ ሲሰሩ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል። የሽብር ቡድኖቹ አባላትና ግብረ አበሮቻቸው ጥቃት ለመፈጸም ዒላማ ያደረጓቸውን ስፍራዎች ቅኝት አድርገውና መርጠው የሚጠቀሙባቸውንም መሳሪያዎችም አዘጋጅተው እንደነበር የጠቆመው መግለጫው የሽብር እቅዱ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ክትትል ይደረግበት ስለነበር ምንም አይነት ጥቃት ሳይፈፀም ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ ይገኛል ሲል አስታውቋል፡፡ የአልሸባብም ሆነ የአይኤስ ቡድኖች በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ ዕቅዶችን የሚያወጡት፣ ስምሪት፣ አመራርና ድጋፍ የሚሰጡት በተለያዩ አገራት የሚገኙ አካላት መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫው በኢትዮጵያ የተመለመሉ የቡድኑ አባላትም በአገሪቱ ጥቃት ለመፈጸም እንዲያስችላቸው ወደ ሶማሊያ ተልከው ስልጠና እንዲያገኙ እቅድ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ የአልሸባብና የአይኤስ የሽብር ቡድኖች ለመፈጸም ያቀዱትን ጥቃት ለማክሸፍ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ረዘም ላለ ጊዜ ጥናታዊ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱንም መግለጫው አያይዞ አመልክቷል። የሽብር ቡድኑ አባላት አሁን ላይ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቅት ለመፈፀም እንቅስቃሴ ለማድረግ የሞከሩት "በጁንታው ጥቂት የህዋሃት የጥፋት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ" እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በማሰብ እንደነበርም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ በቀጣይም የሽበር ቡድኑ በሀገራችን ጥቃት ለመፈፀም ካለው ዝግጅት አንጻር ህዝባችን ይሄን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና የተ
ለየ ነገር ሲመለከትም በአካባቢው ላለ የፀጥታ አካል መረጃ እንዲሰጥ አገልግሉት መስሪያ ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ በድሬዳዋ ከተማ የጥፋት ተልዕኮ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ ሲል የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ገለጿል። የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በህዝብ ጥቆማ መሰረት ሰሞኑን በተለያዩ ቀናት በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል። እነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ዘጠኝ ሽጉጦች፣ ተተኳሽ ጥይቶች፣ የተለያዩ ሀገራት ፓስፖርቶችና ሰነዶች እንደተገኘባቸውም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የጥፋት ቡድኑን ለመደገፍ በለገሀሬና ጀርባ በሚባሉ ሰፈሮች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነር አለሙ ገለጻ "ድሬዳዋን ከህወሃት ጁንታና ሌሎች ሽብርተኛ ቡድን ተላላኪዎች ለመጠበቅ ምክር ቤት ተዋቅሮ ከኢሚግሬሽን፣ ኤርፖርት፣ ጉምሩክ፣ ፌደራልና ከተማ ዋና ዋና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር የጠበቀ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል" ከፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ከሚሊሻ ጋርም ተመሣሣይ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነሩ በተለይ ማህበረሰብ ዓቀፍ የፖሊስ ተቋማትና ወጣቶች ለአካባቢው ፀጥታ መጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ድሬዳዋን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኟት መሠረተ ልማቶችንና የወጪና ገቢ ንግድ መስመሮችን ያገናዘበ የመከላከል ሥራ ከምስራቅ ተጎራባች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :