ከሰልፉ ክልከላ ማግስት የታወጀው - የወገን ጦርነት!

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

Ethnic-war-EthiopiaNovember 17, 2020 (Ezega.com) -- “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሠላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሠላማዊ ሰልፍ ሠላምን፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የህዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብነት ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡”
(የኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ-30)

ስለ መብቱ!

በኢትዮጵያ ህገ-መንግሥት ውስጥ መብቶች በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ክፍፍል ውስጥ መውደቃቸውን፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የሃሳብና ንግግር ነፃነትም ሆነ የዚሁ መብት ተቀፅላ የሆነውንና ይህንኑ መብት የሚከተለውን የመሰብሰብ፣ በሰላማዊ መልኩ ሃሳብንና ተቃውሞን የመግለፅ መብትም ከአነጋጋሪዎቹ ምድብተኖች ውስጥ ሆኗል፡፡ አቤት-ኡኡታዎችንም ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የማቅረብ መብቶች ከመሰረታዊ የሰብዓዊ መብትና ነፃነትነታቸው ይልቅ “ዴሞክራሲያዊ መብቶች” ስር መሰለፋቸውም እያወዛገበ ቀጥሏል፡፡

ሆኖም ግን ይበልጥ አነጋጋሪ የሆነው ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በብዙ ተተስፎበት መጣ የተባለውን፣ በገና ለገና የሠላም ታሳቢነትም የኖቤል ሽልማት ያሰጠውን “ለውጥ” ተከትሎ ለድጋፍና ጭብጨባ እንጂ ለተቃውሞና ስለመብት የመሰለፍ ህገ-መንግሥታዊነቱ አይቀመሴ መሆኑ ነው፡፡ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች “ከወረቀት ላይ ነብርነት ወርደው በተግባር እንዲገለፁ እሰራለሁ!” በሚለው “የተስፋ ቃል” የሥልጣን ጊዜው ያከተመለትን ኃላፊነት የተቀበሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቀድሞው በባሰ መልኩ ተቃራኒ ሃሳቦችን የማይታገሱ፣ የሃሳብና ንግግር ነፃነትን ከነጉዝጓዙ የማያከብሩ እንዲሁም የዜጎችን በሠላማዊ መንገድ ተደራጅቶ ተቃውሞን ስለመግለፅ የሚደረጉ ቅድመ-ዝግጅቶችን ሳይቀር ከፊሉን በደባ፣ ቀሪውን በዳቦ ምንዳና በደቦ የሚያምሱ ሆነዋል፡፡

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ምለው ተገዝተው ሥልጣን የያዙበት ህገ-መንግሥትም መሠረታዊ የሰው ልጆችን መብቶች በተመለከተ ዋነኛውና የመብቶች ሁሉ እናት (the mother of all ዘ rights) ከሚባለው በህይወት የመኖር መብ ጀምሮ በርካታ ዓለማቀፍ ዕውቅና የተቸራቸውን መብቶች አካትቷል፡፡ ለትግበራው ቢሰንፍም የቀድሞው ኢህአዴግ እነዚህን መግለጫ የመስጠትና የመንግሥት ላይ ተቃውሞ ሰልፍን በመሠረታዊነት ሲያስተጓጉል እንጂ ሲከለክል እምብዛም አይታወቅም፡፡ በአንፃራዊነት ህጉ የሚሰራው ዓመፃዊ (Non-Violent) ላልሆኑት ስብሰባዎች እንደመሆኑና ከነስያሜውም “ሠላማዊ ሰልፍ” እደመሰኘቱ ኃላፊነቱን ወስደው ለምናልባቱ የመስመር መሳት የሚጠየቁ አካላት ማስፈለጋቸውም አሌ አይባልም፡፡

በቅርብ ጊዜ ሃሳቡን በሰልፍና አንድ ላይ ሆኖ ከመግለፅ ይልቅ ዓላማው መልዕክት ማስተላለፍ እስከሆነ ድረስ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች በኩል ይህንኑ መግለፅ ይቻላል የሚሉ ድምፆች ቢኖሩም በኢትዮጵያችን ያለው የብዙኃን መገናኛዎች መንግሥታዊ ወገንተኛነት ይህንን አማራጭ ፉርሽ ያደርገዋል፡፡ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የህ-መንግሥቱ ድንጋጌ በመጨረሻዎቹ ሐረጎቹ ካስቀመጣቸው በስተቀሮች (exceptions) በተጨማሪ በሁለተኛው ንዑስ አንቀፅ ስር “ይህ መብት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ህጎች መሠረት ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፡፡” ሲልም አካትቷል፡፡

በዚህ በዜጎች መብትና በመንግሥት ኃላፊነት መካከል ስለሚኖረው ሁለትዮሻዊ ግንኙነት ላይ ከጦርነቱ ጅማሬ በኋላ እንዳነሳ የተገደድኩት ከሰሞኑ በሥልጣን ላይ ያለው የፌዴራልና የአንዳንድ ክልሎች ስብስብ “ጦርነቴን ደግፉልኝ!” ሲል በዘመነ ኮሮና ለተቃውሞ ከልክሎት የከረመውንና ለጦርነቱም መንደርደሪያ ያደረገውን ሰልፍ ጠርቶ መመልከቴ ነው፡፡ በዓለማቀፍ ተሞክሮዎች የፀረ-ጦርነት ሰልፎች የተለመዱ ቢሆኑም በአስተሳሰብ ደረጃችንም ሆነ በመዋዕለ ንዋይ አቅማችን የዓለም ጭራ በሆንነው በእኛ ዘንድ ጦርነትን ማበረታታትና ለዚህ ዓላማም መሰለፍ እንደተራ ነገር በመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ሲቀጣጠል ማየት ከማስገረምም የበለጠ ይሆናል፡፡

በእርግጥ በህዝብና በህዝብ ስም መንግሥታዊ አስተዳደሩን በሚይዘው ቡድን መካከል የሚኖረው ሁለትዮሻዊ ግንኙነት የሚገዛበት የህገ-መንግሥታችን ሠነድ ውስጥ ከሌሎች ገዳቢዎች (limiting freedom of assembly) በተለየ ሁኔታ የዘረዘራቸውና በዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሠነዶች ውስጥም ሆነ በዴሞክራሲያቸው ሰልጥነዋል በሚባሉት አገራት ህግጋት ውስጥ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍን ለመገደብ የህዝብ እንቅስቃስ (public convenience) እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለመጠበቅ ሲባል (protection of democratic rights) የሚሉ አይገኙባቸውም ይሉናል በዚህ ዘርፍ ላይ ሁለት ታዋቂ ጥናቶችን የሰሩት የሰብዓዊ መብቶች ምሁር ፀጋዬ አንዷለም ገላዬ፡፡

ስለ ባለመብቶቹ - ስለ ባለግዴታዎቹም!

በመሰረቱ ህገ-መንግሥቱን የማክበር፣ የማስከበርና ለእርሱም “ተገዢ” የመሆን ይልቁንም በዚሁ ህግ ሶስተኛው ምዕራፍ ስር ከአንቀፅ 14 እስከ 44 ተሰንደው የሰነዱን አንድ ሶስተኛ የሆኑትን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች  በተመለከተ ቀዳሚው ኃላፊነት የተጣለው በተለምዶ “ሶስቱ” እየተባሉ በሚጠሩት የመንግሥት አካላት ላይ ሲሆን የድንጋጌዎቹን አተረጓጎም በተመለከተም ሰፋ ተደርገው ከዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግጋት አኳያ እንዲተረጎሙ ይኸው ሰነድ ያዝዛል፡፡  ስለዚህም ምንም እንኳን ይህንን ፅሁፍ እያሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት ጦርነቱን እንዲደግፉ በአበል፣ በትራንስፖርት ማመቻቸትና ልቦናዊ ጫናን በመፍጠር ጭምር ዜጎች ያለፈቃዳቸው የድጋፍ ሰልፍ እንዲወጡ እየተቀሰቀሱና በአንዳንድ ቦታዎችም በትናንሽ ቁጥር እየወጡ ቢሆንም ለተቃውሞ ሰልፍም ባለመብቶች ዜጎች ሁሉ ስለመሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

መብት የሚሰጥ ነገር አይደለም፡፡ የሚኖረን ነገር ነው፡፡ በተለይ መሠረታዊ መብቶችን የምናገኛቸው ነገሮች አይደሉም፡፡ አንድም እንደዜጋ ግለሰብ ሁለትም እንደቡድንና ሶስትም በሁለቱ ቅልቅሎሽ የሚከበሩልን ናቸው መብቶች፡፡ ይህ ማለት ገን የእነዚህን ተፈጥሯዊ መብቶች ቅፅርና አጠባበቅ ለማስፋት ሰው ሰራሽና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አይጨመሩልንም ማለት አይደለም፡፡ እንደመንግሥታቱ ዴሞክራሲያዊና ለዜጎች ነፃነት እንዳላቸው ፍልስፍናዊ ምልከታም እነዚህን መብቶች ወደመሠረታዊ ሰብዓዊ መብትነት የሚያሳድጉበት ጊዜም አለ፡፡ የመሰብሰብና ተቃውሞን በሠላማዊ መንገድ የመግለፅ ነፃነት (The right to protest) ከእነዚሁ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ስር ምድብተኛ የተደረገው በዚሁ እሳቤ ነው፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶችና በእኛ አገር ስያሜና ሚናቸው እንዲጠላ የተደረጉት የማህበረሰብ አንቂዎች (Activists) እንዲሁም በተቋም ደረጃ በህጋዊ ሰውነት የሚመዘገቡ ሁሉ እንደዜጋ ግለሰብ ሁሉ ኃላፊነትና ተጠያቂነቱን ወስደው ይህንን የመምራት መብት ያገኛሉ፡፡ ሰልፎች ሲጠሩም በተለምዶ የሚካሄዱባቸው የህዝብ መሰብሰቢያዎች አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜው የግብፅ አብዮት ወቅት ከአንደበታችን የቀረውና የነፃነት አደባባይ የሚል ትርጉም የሚሰጠን ታህሪር ማሳያ ይሆነናል፡፡ በኢትዮጵያችንም አብዮት አደባባይ ተብሎ የተሰየመው ቦታ በርካታ ሰልፎችን ያስተናገደና ወደፊትም የሚያስተናግድ ነው፡፡

ይህ አብዮት አደባባይ (ለሃይማኖታዊ ዓላማ ሲሆን መስቀል አደባባም ይባላል) በኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ጥሪ ወቅት፣ በታሪካዊው የዘጠና ሰባት ምርጫ በአንድ ቀን ልዩነት የተቃውሞና ድጋፍ ሰልፎች፣ እንዲሁም ሆን ተብሎ ዓብይን ለመደገፍ እንጂ እንደመርሁ “ዴሞክራሲን እናበርታ!” ተብሎ እንዳይደለ በመንግሥቱ ቀላጤዎች የሚገለፀው የሰኔ አጋማሹ የዴሞክራሲ ድጋፍ ሰልፍ ተካሂደውበታል፡፡

ሁልጊዜም ቢሆን ዜጎች “መብት” እንዳላቸው በሚገለፅባቸው ጉዳዮች ላይ በተቃራኒው መንግሥት የሚባለው አካል ቀዳሚ ስራው ተደርጎ የሚሰጠው እነዚህን የዜጎች መብቶች ማክበርና ማስከበር ይሆናል፡፡ ይህ “ግዴታ” ደግሞ ለዜጎች ንባቡ እንደመብት ነው የሚሆነው፡፡ በአገራችን ሰልፍ ለተቃውሞ ሲሆን የሚከለከልበትና ለድጋፍ ሲሆን ትራንስፖርትና ከህዝቡ ከራሱ በግብርና መዋጮ መልክ የሚሰበሰበው ገንዘብ በአበል መልክ ለተሰላፊዎቹ እየተቆረጠላቸው የሚፈቀድበት አሰራር ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡

ሆኖም እንደድጋፉ ሁሉ ዜጎች የመንግስት አሰራር ላይም ሆነ የተቀረፁ ፖሊሲዎችን በተመለከተ አልያም የሰብዓዊ መብቶችን ይዞታና የዴሞክራሲያዊ ልምምድ ምህዳሩን በማስመልከት የተቃውሞና መልዕክት ማድረሻ ሰልፎችን መጥራት፣ ማስተባበርና መሰለፍ መሰረታዊ መብትነቱ ለመንግሥት ባለሥልጣናቶቹና ለፀጥታ አስከባሪ ኃይሎቻችን ተብራርቶ አልተነገራቸውም፡፡ ዜጎች በግለሰብ ደረጃ የሚቀርቧቸው ተቃውሞዎችና ተገቢ ትችቶች የመንግሥት የሥልጣን ኃላፊነት ላይ በተቀመጡ ግለሰቦችና ቡድኖች በኩል ሳይደመጡ ሲቀሩ ጫና መፍጠሪያው መንገድ በቡድን ይህንኑ ትችትና ተቃውሞ ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ መንግሥታዊ ጆሮን መነፈግና ጉዳዮቹ ተከመቻችተውና በስለው የተቃውሞ ሰልፉን በብስጭት የመሙላትና ወደህዝባዊ አመፅነት መቀየራቸውም የተለመደ ነው፡፡ ብሶቶች የሚደመጡት በአንዲት አጋጣሚ በምትገኝ የዚሁ መወጫ ሰልፍ የሚሆነውም ሰልፎች እየተከለከሉ በመቆየታቸው ሳቢያ ነው፡፡ ለአብነትም እስካሁን ላለንበት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል የዳረገንን ያለህዝብ ይሁንታ ሊተገበር የተወጠነው የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ዞኖች እቅድ አንዱና አይነተኛው ማሳያ ነው፡፡

ማብቂያ!

ስለተቃውሞ ሰልፍ መብትና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በሰፊው የምንመለስበት ቢሆንም አሁን ያለንበትን የወገን ጦርነት በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ልዘጋው ወደድኩ፡፡ ጦርነቶች ቀድመው የሚፈጠሩት በተበላሸ አዕምሮዎች ሲሆን ወደተግባር የሚለወጡት ደግሞ በአይዞህ ባዮች ነው፡፡ ለሠላማዊ ሽግግር ተተስፎባቸው የኖቤል ቀብድን ቀርጥፈው የበሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እዚህ ምስቅልቅል ውስጥ ይከቱናል ብሎ ማሰብ ቀርቶ የገመተውም እምብዛም ነበር፡፡ አሁን የማንክደው ነገር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መግባታችንና መውጫውም እጅግ እየከበደ መሄዱን፣ የተሳታፊዎቹ ቁጥርና የግጭቱ አድማስ መስፋቱንም ነው፡፡

ጦርነት ለየትኛውም ችግር መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፡፡ በተለይ የህዝብና ሃይማኖት ብዝኃነት ባለባቸውና እንዚህ ብዝኃነቶችም ታሪካዊ ቅራኔን ይዘው በቆዩበት ድባብ ውስጥ የሚደረግ ጦርነት እያደር ነው አክሳሪነቱ የሚገለፀው፡፡ የብልፅግናና የህወኃት ሰዎችን አይዟችሁ የሚሉ ሁሉ እሳቱን የሚሞቁት ዳር ሆነው ስለሆነ ተለብላቢው ህዝብ ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ አካታችን አግባቢ ውይይት በማድረግና የምር በመደራደር ብቻ ነው ችግሮች የሚፈቱት፡፡ ጦርነትና ፉከራ የኣለም ጭራ አድርጎ አስቀረን እንጂ ምንም የፈየደልን ነገር የለምና እንደሥልጡን ዜጋ በማሰብ በሁለቱም መንግስታት ላይ ጫና መፍጠርና ግጭትን እምቢ ማለት እንደሚኖርብን ይሰማኛል፡፡ በሌሎች አገራት እንደሚደረገው የፀረ-ጦርነት ሰልፍ አደርጋለሁ የሚል አካል ከተነሳም አብሬው ለመሰለፍ በዚሁ አጋጣሚ ዝግጁነቴን እገልፃለሁ፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :