የሁለት “ጁንታዎች” ወግ!

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

Ethnic-war-EthiopiaNovember 17, 2020 (Ezega.com) -- ኢትዮጵያን የዘር ሐረግ እየቆጠረ ለረጅም ጊዜ ከተንፈላሰሰባት የዘውዳዊ ሥርዓት ወደ ወታደራዊው የጁንታ አገዛዝ ትሸጋገር በነበረችበት ወቅት ላይ ነበር የኤርትራና የትግራይ በረሃዎችን መነሻቸው ያደረጉና ሥርዓታቱ ያነበሩት ዘርፈ ብዙ ጭቆናዎች ላይ ያበዩ የነፃነት ሸማቂዎች የመጀመሪያዋን የዓመፃ ጥይት ያጮሁት፡፡ እነሆ ያ የበረሃ ትግል የወቅቱን ወታደራዊ ጁንታ ገርስሶና በመሃል አገር ከቤተ-መንግሥት ደጃፍ አድርሶ የያኔዎቹን አማፂዎች በህጋዊ የፖለቲካ ድርጅትነት አስመዘገበ፡፡ የመንግሥትነት በትረ ሥልጣንንም አስቀበለ፡፡

ምንም እንኳን ሥልጣኑ የተገኘው በወታደራዊ ድል ቢሆንም የ“ጁንታ”ነት ስያሜውን ለማስቀየርና ቅቡልነትን ለመቀዳጀት የይስሙላ ምርጫዎች ተካሂደውም ፍፃሜውን ሳያሳምሩ ቀሩ፡፡ ትግሉ በመረብ ምላሸዋ አገረ ኤርትራ “ህግደፍ” የተባለ የአንድ ፖለቲካ ማህበርን ይልቁንም የአንድን ግለሰብ የፈላጭ ቆራጭነት ሥርዓት ሲያዋልድ በኢትዮጵያችን ደግሞ የከሸፈ ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ አስተዳደርን አስተዋወቀ፡፡ ዓላማውን የሳተው አስተዳደርም ስር የሰደደ ንቅዘትንና ሥርዓታዊ አምባ-መግነንን አስከትሎ ለዜጎች ሰቆቃው ተረፈ፡፡

ይህ ሥርዓት ይሻላል ተብሎ በተተሰፈበትና የራሱ ሌላ ተቀፅላ በሆነ ሥርዓት እንደተተካ ነበር ብዙም ሳይቆይ “ጁንታ” የሚለው ስያሜ የተደመጠው፡፡ ይህ ቃል ኢህአዴግን ፈጥራ ለሥልጣን ካበቃችውና ከፍርሰቱም በኋላ በኢህአዴጓ አስኳል ህወኃት መግለጫዎችና ብዙኃን መገናኛዎች እንዲሁም አክቲቪስቶች በኩል ሲደመጥ ቢቆይም ትኩረት አጊኝቶ የተደጋገመውና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን የተቆጣጠረው ግን ዓብይ አህመድ አሊ (ዶ/ር) ህወኃት የሰሜኑመከላከያ ዕዝ ላይ “ጥቃት እንደፈፀመ” በገለፁበት ወቅት ቃሉን ከተጠቀሙበት በኋላ ነው፡፡

በእርግጥ የቃሉን ትክክለኛ ትርጉምና መሠረት የነገረን ባይኖርም የስፓኒሽ ወይም ከፖርቹጋል የተገኘ ቃል ስመሆኑና ላቲን/እንግሊዝኛውም በውርስ ወስዶት “ወታደራዊ” የሚል ትርጉም እንደሰጠው የሚመሰክሩ ሰነዶች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህች አጭር መጣጥፍም የኢህአዴግ ውልድ የሆኑትን የመቀሌውን “ህወኃት” እና ማዕከሉን አዲስ አበባ ላይ ያደረገውን “ብልፅግና” ነገረ ስራና ባህሪ በማወዳደር ነው የሁለቱን ጁንታዎች ወግ ፍርድ ለአንባብያን የምንተወው - መልካም ንባብ፡፡

የህወኃቱ ጁንታ- ፍጥረተ ባህሪ!

ዛሬ የህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወኃት) አስፈሪ ግርማ ሞገስ ተገፍፎ አብሯት ሲዘርፍና ሲገድል እንዲሁም በአድር ባይነት ተሰልፎና አፉን ቆልፎ ተቀምጦ የነበረ ሁሉ በሙሉ አፍና በአንቋሻሽ አገላለፅ “ትህነግ” እያለ ሊያሳቅላት ከመጀመሩ ጥቂት ዓመታት በስተፊትስም አይጠሬና ተፈሪ ነበረች፡፡ በ-1968 ማኒፌስቶዋ አካትታው ነበር ከሚባለው አማራን በነፍጠኝነት እና በሁልጊዜ ቋሚ የትግራይ ጠላትነት የመፈረጅ መርኋ በጠላትነት የሚኮንኗት መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በትግል ዘመናቶቿ ትጠቅሳቸው የነበሩትን አልባኒያዊ፤ ስታሊናዊም ሆነ ማኦይዝምን የነካኩ ህብረተሰባዊነቷን የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በሩሲያ ሽንፈት መጠናቀቅ ገደል ከትቶባታል፡፡ ዓላማዋንም አስቀይሯታል፡፡

ኢኮኖሚን በተመለከተ ከዕዝም ሆነ ከቅይጥ ምጣኔ ሃብታዊ የግንባታ መስመር ይልቅ ወጥነት የሌለውንና ምንነቱ በደንብ ሳይበየን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የታጀለ መርህን ስታራምድ ቆይታለች፡፡ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ!” ምን አይነት የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ ያልገባቸው የኢህአዴግ አባላትና አመራሮችም ሚሊዮኖች ነበሩ፡፡ የአንድ ወቅት የኢፌዲሪ ርዕሰ ብሔር የነበሩት የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለሶሻሊዝም ቆርበው ከነበሩ የፖለቲካ ሰዎቻችን አንዱ ናቸው፡፡ የነጋሶን ህይወት በሚተርከውና ዳንዔል ተፈራ ባሰናኘው“ዳንዲ - የነጋሶ መንገድ” በኩልይህንኑ የፓርቲውን ፕሮግራም ጉዳይ አንስተው የወቅቱን ርዕሰ መንግሥት አቶ መለስ ዜናዊን ሲሞግቱ አቶ መለስ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ እንደተቀያየረው ዓለም ሁሉ ተቀያይረው ነበር “ፕሮግራማችን ነጭ ካፒታሊዝም ነው!” ሲሉ የቀደመው ዓላማ በጊዜያዊነት መሳቢያ ውስጥ እንደተቆለፈበት የነገሯቸው፡፡

ፖለቲካን በተመለከተ ታጋዮቹ ከተማ ሲገቡ ከኢምፔሪያሊስቱ ዓለም ጋር መጣላት የማይታሰብ ነበርና በወቅቱ የተሰናዱት ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች በቀጥታና በማይታመን መልኩ ሊበራል አንቀፆችን ሳይቀር በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ብሎም በህገ-መንግሥቱ በማካተት የታይታ ዴሞክራሲን መተግበር የጀመረችበት ወቅት ነው፡፡ እያደር ኢትዮጵያ በርካታ ዓለማቀፍ ስምምነቶችን በህጓ በማካተት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስመሆኗ ቢመሰከርላትም በተግባር ረገድ ግን ከኋለኞቹ ሰፈር ነበር ምድቧ የሆነው፡፡ ይባስ ብሎም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ የዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነት አፈናዎች በሚጠበቀው መልኩ ባልታየው ቁሳዊ ልማት ይሸፈኑ ነበር፡፡

በኢትዮጵያችን ለረጅም ዓመታት ሲብላላ የቆየውን የብሔሮችና ሃይማኖቶች ጭቆና ለእኩልነት ለማብቃት የተዋለደው የአብሮነት (ፌዴራሊዝም) ሥርዓት ለከፋፍለህ ግዛው መርህነትና ለሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ በመዋሉ ግልፅ አደጋ ይደቅን ያዘ፡፡ ፕሮፖጋንዲስቶቹም ህወኃት ኢህአዴግ በሥልጣን ካልቀጠለ “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች!” ማለትን ዘወትራዊ መዝሙራቸው አደረጉት፡፡ በሂደት እንደሚገነባ የተተሰፈበት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት (Multi party Democratic System) ውሃ በልቶት በወረቀት ላይ ቀረና በምትኩ ኢህአዴግን ዘለዓለማዊ ለማድረግ ያለመው የአውራነት ሥርዓት (Dominant Party System) ከሩቅ ምስራቅ ተቀዳ፡፡ አለመታደል ሆኖ ልማቱም፣ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲውም ነበር የጠፋው፡፡

ከእነዚህ ሁሉ ችግሮችጋ ነበር ህወኃት መራሹ ኢህአዴግ ሚሊዮኖችን በአባልነትና ደጋፊነት መልምሎ የጥቅም ተጋሪ ያደረጋቸውና የአገሪቱ ሃብት የእነዚህ የጥቅም ተጋሪዎች የጋራና የግል ርስት ሆኖ ለቅርምት መዳረጉ የኢህአዴግን መፍረስ አይቀሬነት አሳብቀው ፍረሰቱንም ያፋጠኑት፡፡ በተለይ በተላላኪነት እዚያና እዚህ ሲሉ የነበሩ የያኔዎቹ ጭፍሮች የዛሬዎቹ ጌቶች በዚሁ የዝርፊያ ሃብት መድለባቸውና ተነስ፣ ተቀመጥ፣ ፍለጥ፣ ቁረጥ…. የሚሉትን ወፈሰማይ ስራ አጥ ወጣት ማግኘታቸው ጌትነቱን አስናፈቋቸው ነበርና የሆነው ሁሉ ሆኖ ኢህአዴግ ታሪክ፣ የኢህአዴግ ውልዱ ብልፅግናም እውነት ሆኑ፡፡ ከዚያስ?!

የብልፅግናው ጁንታ - ነገረ ስራ!

ጁንታነት ባህሪው አንድ ነው፡፡ የማይለቅ ደዌ እንደመሆኑቆዳውን እንጂ ጁንታዊ አቋሙን አይቀይርም፡፡ በበረከቱት የአፍሪካ አገራት የሥልጣን ርክክቦች በወታደራዊ ጁንታ መገልብጠ መንግሥት አልያም ደም አፋሳሽ በሆነ የጭቦ መንገድ ካልሆነ በቀር የማይታሰበውም በዚሁ የስልቻና ቀልቀሎ የቀልቀሎና ስልቻ ባህሪ መነሾ ነው፡፡ አንዱ በአማርኛ ሌላው በኦሮሚኛ፡፡ እንደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያና እንደ ጎረቤቶቻችን ሱዳንና ግብፅ ያሉ አገራት በዚህ መንገድ ውስጥ በርካታ መንግሥታትን ቆጥረዋል፡፡ በማሊ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ ወታደሮች እየተፈራረቁ መንበረ ሥልጣኑን ከበትረ መኮንኑ ጋር የሚቀባበሉትም በዚሁ ጁንታዊ ወግ ነው፡፡ ኢትዮጵያችን ከ-1953-የጀመረ የከሸፉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ታሪክ ቢኖራትም የተሳካና ሙሉ መንግሥታዊ ታሪክን ከሥርዓትጋ መቀየር ያስቻለ መፈንቅል ያደረገችው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው - በ1967!

ከላይ ለህወኃት መራሹ ኢህአዴግ የሰጠነው የጁንታነት ግብር ለኢህአዴግ ብልፅግናም በልኩ የተሰፋ ሲሆን ብልፅግና የራሱ የሆኑ ልዩ ባህሪያት አሉት፡፡ ለአብነት ያህልም ህወኃት ኢህአዴግ በታይታ ህግጋት ይሸፍናቸው የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የበለፀገው ኢህአደግ ምንተ-እፍረታቸውን ቀርጥፈው በበሉ ተከፋይ ጡሩምባዎቹና በወረሳቸው ብዙኃን መገናኛዎች በኩል ይሸፍናቸዋል፡፡ አለፍ ሲልም ሰቆቃዎቹን በብልጭልጭ እየሸፋፈነ ህዝቡን ያጀልባቸዋል፡፡ በአንድ ራስ ሁለት ምላስነትን ከማይታመን አስመሳይነትና ከልስሉስ ሴረኝነት ጋር በተቀባው መሪው በኩል ኢትዮጵያ በመፈክር የምትድን በመፈክርም የምትፈርስ ይመስል “ኢትዮጵያ አትፈርስም!” እያለ ህዝብ ያማልልባቸዋል፡፡

የበረከቱት ኢትዮጵያውያን በዝምታ ድባብ ውስጥም ሆነው “አህያ ለአህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም!” እያሉ በጁንታዎቹ የሥልጣን ጠብ የዜጎች መማገድ እንደሚያሳስባቸው አሳይተዋል፡፡ አለመታደል ሆኖ ገዢዎቻችን አድማጭም ሆነ የቅርብ ገሳጭ ያገኙ አይመስልም፡፡ እንዲያውም ባነበርነው የጦረኝነት ባህል “በለው በለው!” እየተባለ ዘመቻው ከህግ መስመር ወጥቶ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት የመግቢያ ጥርጊያው አቅንቷል፡፡ ወደቀደመው ነገሬ ስመለስ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአሮጌው ወይን ማሸጊያ ስለደበራቸውና ሥልጣን ላይ በንግሥና ዙፋን ለመክረምም አዛላቂ ሆኖ ስላላገኙት “በወዳጃቸው” ምርጫ ቦርድ በኩል ከህወኃት በቀር ያለውን የኢህአዴግን ሁለመና አዲስ ወይን-ጠጅነት አውጀዋል - አስክረውንማል፡፡

ኢኮኖሚን በተመለከተ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተሽሮ በአገር በቀል ስያሜ የሚሽሞነሞነው የነፃ ዓለሙ ሥርዓት ቢጀመርም ግልፅ ያለ ነገር ባለመኖሩ “መኪናችሁን ለእግረኞች አጋሩ!” እስከማለት የሚደርሱ ሶሻሊስታዊ ውጥኖች ታይተዋል፡፡ የቀደመው ኢህአዴግ እስከ ዘጠና ሰባቱ ምርጫ ማግስት ድረስ ከተሜውን ቸል ብሎት ዕዙን ገጠርና ግብርና ላይ ቢያደርግም አገሪቱ ከርሃብ፤ ከጥንታዊው አስተራረስናከችጋር እንዳልወጣችው ሁሉይሄኛውም በመሠረታዊነት የቀየረው ነገር የለም፡፡ በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዚህም ከዚያም ተቀምሮ እንደተደራጀ የተነገረለት “መደመር” ዛሬ ላይ ከነአካቴው የገባበት ከመጥፋቱ በፊትም ቢሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከመንቀፍ በዘለለ ግልፅ አድርጎ ያስተዋወቀው የኢኮኖሚ መርህ የለም፡፡

ፖለቲካን በተመለከተ ብልፅግናና መሪው ወታደርና ወታደራዊ እንደመሆናቸው ዓብይ አህመድ (ኮ/ል) የመጀመሪያ መደበቂያቸውና የስራቸው መጀመሪያ ያደረጉት ይህንን ምሽግ ለሥልጣን በማያሰጋ መልኩ ማደላደል ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ “መከላከያ ሠራዊት” እየተባለ የሚሞካሸው የመንግሥት ቅልብ ጦር ተቋማዊ አደረጃጀትና ህዝባዊ አመኔታን ያተረፈ ሳይሆን በየትኛውም አቋራጭሥልጣን ላይ ለወጣ ባለጊዜና የግደል ትዕዛዝ ለሰጠው ሁሉ ያለማቅማማት ቃታውን የሚስብ ጁንታ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሰራዊት ክብሩን መልሶ እንዲጎናፀፍ ከጭብጨባ ይልቅ ህዝባዊነትን እንዲላበስ የሚነግረው ፖለቲከኛና ህዝብ ነው የሚያሻው፡፡

መከላከያ ሠራዊቱን በተመለከተ እጀ መንገዴን አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ይኖርብኛል፡፡የወላይታ ህዝብ የክልልነት ጥያቄን ሲያነሳና ይህንን ጥያቄውንም ፍፁም ጨዋነት በተመላበት መንገድ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ከሳምንታት በፊት ይህንን ህገ-መንግሥታዊ ጥያቄ በህገ-መንግሥቱ መሠረትና ህገ-መንግሥቱን እንዲጠብቅ የተቋቋመው ሠራዊት “የመለሰበትን” ኢ-ህጋዊና ኢ-ሰብዓዊ መንገድ ብዙዎች አይረሱትም - አንረሳውም፡፡ በአዲስ አበባና ቡራዩ ዙሪያ የተጨፈጨፉ ወገኖችን ለማሰብ በተደረገው ሰልፍ ላይ በዚሁ ሰራዊት የወደቁትንም አንዘነጋም፡፡ ብልፁጉ አቶ ታዬ ደንደዓ ህወኃት በሞቃዲሾ ፈፅማለች ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተደምሮ በከፋ፣ በሲዳማ፣ በኦሮሚያና በአማራ እንዲሁም በጋምቤላ ክልሎች ይሄ ኃይል ሲፈፅማቸው የኖሩ ኢ-ሰብዓዊነቶች የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ትኩረት ያገኙ ናቸውና ከማንቆለፓፐስ ተወጥቶ የሠራዊቱን ህዝባዊነት ጉዳይ መስራቱ የተሻለ ይሆናል፡፡

የብልፅግናው ጁንታ ከነስያሜው “አሻግሬ” ነበር፡፡ እያደር አሻጋሪነቱ ተረሳና ዘመን ተሻጋሪ ለመሆን መደላድሉን አመቻቸ፡፡ ወታደሩን አመቻቸ፣ ፖሊሱን አዋቀረና እግሩን አንፈራጠጠ፡፡ የቀድሞውን ማስፈራራት በለዘብታ ጀምሮ በድንፋታ ገለጠው፡፡ ተቀምጠው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ እንዲከብድ ተረድቷልና እነ ፖለቲካዊ ድርድርን፣ የነፃ ተቋማት ግንባታንና ብሔራዊ ዕርቅ ከአገራዊ መግባባትን እንደወላጁ ኢህአዴግ ይሸሻቸው ያዘ፡፡ ሽግግሩ የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ (Roadmap) የሚጠይቁት ንቁአን እየተፈረጁ የተለየ ሃሳብ የሚያቀርቡ እየተዋከቡና እየታሰሩ የሽቅበት ጎዳናውን ተያያዘ፡፡ ብዙኃን መገናኛዎቹም “ንሴብሆ!” እያሉ ንጉሡ ሺህ ዓመት እንዲነግሡ ህብረተሰቡን ያስፀልዩ ገቡ፡፡ ከዚያስ?!

እግር ከተንፈራጠጠና ግለሰባዊ አምባገነንነት በእርካብ አልባ መንበር ላይ ከተዋደደ በኋላ ሞት፣ እስር፣ ስደት፣ መታፈንና ሌሎች ጁንታዊ ባህርያት ጎሉ፡፡ የህዝብ ፈቃድ በአውቅልሃለሁ ተተካ፡፡ አገራዊና ህጋዊ ቅቡልነት በመሳሪያና በዓለማቀፍ ዝና ላይ ተመሰረተ፡፡ ኢትዮጵያም ፈፅሞ ያልታሰበ ችግር ውስጥ እየገባች ስለመሆኑ ብዙዎች ሳይረዱት ተገባ፡፡ የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ነገሮች በንግግርና በድርድር እንደሚፈቱ በብዙ ቢተስፍም ሁለቱም ጁንታዎች የትናንትን ቁርሾ ለማወራረድ አገርና ህዝብን መማገድ ይዘዋልና ሠላም የሩቅ ህልማችን መስሏል፡፡ ለአገራችንና ለህዝቦቿ ሠላም ይሁን ከማለት በቀር የምለውም የለኝም፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :