በዓለም የፍልስፍና ቀን “ፍልስፍናችን” ቢፈተሽስ?! (ቀዳሚው ክፍል)

world-science-day“I Think! Therefor I am”
(Rene Descartes)

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

November 24, 2020

ጋዜጠኛና ደራሲ ኃ/ጊዮርጊስ ማሞ (ጲላጦስ) ለትውልዴ ወጣቶች ሩቅ ይመስል የነበረውን ፍልስፍና ቀረብና ቀለል አድርጎ “ጥበብ” በሚል ርዕስ ንዑሳን አርዕስቶችን እያስከተለ ያስተዋወቀ ባለውለታችን ነው፡፡ ከመፃህፍቱ ቀደም ብሎም ቢሆን እንደ ኔሽን እና ዜን በመሳሰሉት የህትመት ብዙኃን መገናኛዎች በኩል ብዙ የፃፈ ሲሆን አሁንም ፍትህ በተሰኘችው ተነባቢ መፅሄት ላይ ይህንኑ አምድ ይዟል፡፡ በአንድ ወቅት የህንዳዊውን አሰላሳይ ቻንድራ ሞሃን (ኦሾ) መፃህፍት ማንበብ “የአዕምሮ ጤናን ያቃውሳል!” በሚል ስሁት እሳቤ እነዚህ መፃህፍትም አብረው ተመድበዋልና በወቅቱ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቃለ-ጭውውት አድርጎ ነበር፡፡

ኃ/ጊዮርጊስ እውነት እንደዚያ አይነት ነገር ተከስቶ ወጣቶች መስመር ስተው ከሆነ እጅግ አድርጎ እንደሚያዝን ሲገልፅ “ፍልስፍና” ግን ለአዕምሮ ጤና መቃወስ ምንጭ እንደማይሆን በመግለፅ “በእርግጥ በመፃህፍቱ ላይ የተደራጁት ሃሳቦች የአሳቢያኑ እንጂ የኔ አይደሉም…. እኔ ያደረግኩት ነገር ቢኖር ሃሳቦቹን በየዘርፋቸው ማደራጀት ብቻ ነው፡፡” ብሎ ነበር መልስ የሰጠው፡፡ ይህ ማለት ግን አባባሽ ምክንያት ሊሆን አይችልም ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያችንና በሌሎችም ቦታዎች “የፍልስፍና መፃህፍትን ማንበብ ያሳብዳል!” ከሚለው የተሳሳተ ምልከታ እኩል ስለፍልስፍና ምንነት በጥቂቱም ቢሆን ያለመረዳት ይስተዋላል፡፡

ፀጉርን አንጫብሮና ልብስን አዝረክርኮ ንግግርን ከማሰማመር ይልቅ “ለመሆኑ ፍልስፍና ምንድን ነው?” ብሎ የሚጠይቅ አንድ ሰው እየተፈላሰፈ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ሃሳባዊ ተፈላሳፊ የተፈጠረውን በአግባቡ ማወቅ እንጂ እንደ ፈጠራ ሰው (Innovator) አልያም እንደ የንግድ ሰው (Entrepreneur) የግድ አዲስ ነገር መፍጠርና ወደ የንግድ ሃሳብነት መቀየርም አይጠበቅበትም፡፡ ቁሳዊ ጥቅም የሚያስገኙ ነገሮች ላይ እንዲያተኩርም አይገደድም፡፡ በዚህ ሳቢያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደታሪክ የትምህርት ክፍል ሁሉ በሙሉ ባይዘጋም “ዳቦ አይሆንም!” ተብሎ በትምህርት ሥርዓቱ የ70/30 አካሄድን የተከተለ የትኩረት ቅንስናሽ ተደርጎበታል፡፡

“ሰው” የምንለው ፍጥረት አካልም ነብስና መንፈስም እንደመሆኑ በቁሳቁስና በምግብ ብቻ አይኖርም፡፡ ታሪክም ሆነ ፍልስፍና በሥርዓት ከተመራ ዳቦ ባይሆኑና ባይጋግሩም የሥርዓተ ህብረቱንና የጋጋሪውንም ስብዕናና አስተሳሰብ በመገንባት በኩል መሳተፋቸው፣ የዳቦውን ጥራና ብዛትም ማበርከታቸው አይቀርም፡፡ ጀሶን ከጤፍ ዱቄትጋ ቀላቅሎ የሚያበላን ኢትዮጵያዊ ለዚህ ፍልስፍና ማጣት ወይም የምልከታው መበላሸት አይነተኛ ማሳያ ይሆነናል፡፡ አለመታደል ሆኖ ህዝባችን ለደራሲያንና “ለመፃህፍት ሰዎች” ጀምሎ እንደሚሰጠው ሁሉ “ፈላስፋ” ለሚለው ቃልና ቃሉንም ለሚሸከመው ግለሰብ መልካም ምልከታ አለው ለማለት አልደፍርም፡፡ እንዲያውም ሃይማኖት አልባና አለፍ ሲልም ነቃፊ ብቻ አድርጎ ነው የሚስለው፡፡

ለመሆኑ “የዓለም የፍልስፍና ቀን” ለምን ይዘከራል?!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሐምሌ 29/2015 ሰላሳ ሶስተኛው የፓሪስ ጠቅላላ ጉባዔው በሳይንስና ባህል ማዕከሉ በኩል ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ በየዓመቱ የህዳር ሶስተኛ ዕረቡ ላይ ሲታሰብ የቆየውንና 2004/5 ላይ በሞሮኮው የባህል ሚኒስትር አቶ ሞሐመድ አቻሪ በኩል ተጠቁሞ በድርጅቱ በኩል የታወጀውን “የዓለም ፍልስፍና ቀን” ክብረት መነሻ በማድረግ ስለፍልስፍናችን ልናወራ ከሆነ የክብረት ቀን መነሻው እሳቤንና የነገርዬውንም ስረ መሰረት ከዓለም፣ ከአህጉረ አፍሪካና ከአገረ ኢትዮጵያ አኳያ በደንብ ማስገንዘቡ ጠቃሚ ነው፡፡

በየዓመቱ የህዳር ወር በገባ ሶስተኛው ሐሙስ ላይ ዕለቱ መዘከር የጀመረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) ከተዋወቀ በኋላ ሲሆን ዓላማዎቹ የነበሩትም በተለያዩ አገራት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ከማሳሰብና ለዘመናዊው ሥርዓተ ማህበር የሚበጁ ዘርፋዊ ጥናቶቸን አስተዋውቆ ከማበረታታት ባለፈ ትምህርትንና ንቃትን ለመፍጠር በመተለም ነው፡፡ ዘንድሮም በኮሮና ተህዋሲ ዙሪያ “The health crisis” ሲል በጠራው ጉዳይ ከጤናው የሚከተለው ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ ሆኗል አትኩሮቱ፡፡

የአፍሪካ “ፍልስፍና” ምንጩ ከወዴት ነው?!

ስለ “የአፍሪካ ፍልስፍና” መነሻ የሚሆኑንን አፈ-ታሪኮች የምናገኘው ፍልስፍናው ከሚገኝባቸው የአህጉሪቱ ሃይማኖቶች ነው፡፡ በድጋሚ እንደ አህጉራችን ታሪክ ሁሉ የፅህፈት ልምድ ያልዳበረ መሆኑ ይህንንም ዘርፍ ይቃኘዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ የፃፉ ሰዎች አህጉረ አፍሪካን ለሁለት በመክፈልና ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የሰሃራ አካባቢ በመተው ስልጠቱን ለሰሜን አፍሪካውያን ያደርጋል፡፡ ምክንያቴ የሚለውም የፍልስፍና ምንጭ የሆነውን ግሪክን ይዞ፣ ሂንዱይዝምን ከእስልምናና ከክርስትና አስተምህሮዎችጋ ጨምሮ በአይሁድ እምነት በኩል በአካባቢው የተስፋፋ መሆኑ ነው፡፡

በሌላ አነጋገር “አፍሪካዊ ፍልስፍና” የሚባል ነገር ስለሌለ የምዕራብና ምስራቁ ፍልስፍና ግልባጭ ያደርጉታል፡፡ በእርግጥ በሃይማኖቶቹ በኩል ከክርስትናው የሂፖው ኦገስቲንና አኩዩናስ ከእስልምናውም የእነ ኢብኑ ራሺድ ስራዎች በስፋት ተሰራጭተዋል፡፡ ይህ መሆኑ ግን አፍሪካውያን የዳበረ ፍልስፍና የላቸውም ወይም ፍልስፍናውን አደርጅተው ለዓለም አልገለፁትም ሊያስብል ቢችል እንጂ ፍልስፍና አልቦ አያደርጋቸውም፡፡ አፍሪካውያን ብሔርተኞችና ወዳጆቻቸው በዚህ ዘርፍ ላይ ባይሳካላቸውም እንደ ፀረ ቅኝ-አገዛዙ (decolonization) ሁሉ የራሳቸውን ምልከታ ለማሰናጀት በወሰዱት ጊዜ የምዕራቡ ፍልስፍና ተቆጣጥሯቸዋል፡፡ ተቆጣጥሮናል፡፡ ስለዚህም የአፍሪካ ፍልስፍና በተከላካይነት መቅረቱን መመስከር እንችላለን፡፡

ለዚህ አብነት እንዲሆነን የኢትዮጵያዊውን የፍልስፍና መምህር ዮሴፍ ሙሉጌታ (ዶ/ር) መሟገቻ ማሳየት በቂ ነው፡፡ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው በማሟያነት በሰሩትና “Meta philosophy or Methodological Imperialism?  The Rationale for Contemporary African Philosophy with Reference to Oromo Philosophy” የሚል ርዕስ በሰጡት ጥናታዊ ስራቸው በኩል “አገር በቀል ዕውቀቶችን” በማስፋፋት የእጅ አዙር ቅኝ ተገዢነትን (neo-colonization) ከትውልዱ ላይ ማስወገድ ካልተቻለ ለምዕራብና ለምስራቁ ዓለማት የገበሩ አፍሪካውያን (Westernized Africans) ይበዛሉ የሚል ስጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የአስተሳሰብ ገባሪነትን (decoloniation) እሳቸው “የፍልስፍና ዘዴ” ሲሉ ባቀረቧቸው የአመክንዮ ሐተታት (logic) ማስወገድ ካልተቻለ ሠላምና ዕድገት በአፍሪካ የማይታሰቡ ስለመሆኑ ሞግተዋል፡፡

ዶ/ር ዮሴፍ በተለይ “አለርጂ” ሆኖብናል የሚሉት የአውሮጳውያኑ ፍልስፍና ስለሰው ልጆች ያዳበረው ምልከታና ስለፍልስፍና ዘዴ (metaphilosophy) ያኖረው “የተዛባ” ምልከታ አመክንዮ የሌለው (Illogical) በመሆኑ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ዛሬ ያሉት አፍሪካዊ ፍልሱፋን (Continental philosophy) እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህንን ዘርፍ የሚያስተምሩቱ ትውልዱን ከህሊና ቅኝ ተገዢነት ለማላቀቅ የምዕራቡን ፍልስፍና በማሄስና የአገር በቀሎቹ ፍልስፍናዊ ዘዴዎች ላይ አተኩሮ መመራመር ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡

በእርግጥ ይህ ምልከታ ከአፍሪካ ፈላስፋዎች እንደ አንዱ የሚቆጠረው የሞግቤ ራሞስና የሌሎቹ እንደ ሴዳር ሴንጎር ያሉ ዘመነኞቹም ነው፡፡ ሞግቤ አፍሪካ የዚሁ የእጅ አዙር አዕምሯዊ ጭቆናና የሌሎችም አይነተ ብዙ ችግሮች ቀጥተኛ የምዕራቡ ተጠቂ መሆኗን ሲያምን “ጥቃትን መከላከል ተፈጥሯዊ ነው!” በማለትም የአፍሪካን ፍልስፍና ምንነትም ይህንኑ የጥቃት ተከላካይነት ያደርገዋል፡፡ በሌላ አገላለፅ እነሱ ያላዩትንና በወጉም ያልገለፁትን “ማንነት” በመፈለግ ውስጥ የእነሱን “ናችሁ” ብያኔ እየተከላከሉ የመቆየት ትግል እንደማለት ነው፡፡

የቃሉ ከየት መጣነት (etymology) የግሪክን ቋንቋ መነሻው ያደረገ ሲሆን “ፊሎ-ሶፊያ” ከተሰኙ የሁለት ቃላት ጥምረት የተቀነበበ ነው፡፡ ሌጣዊ ትርጓሜያቸውም ቀዳሚው “ፍቅር” ተከታዩ ደግሞ “ጥበብ” የሚል ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት “ፍልስፍና” ማለት “የጥበብ ፍቅር” አልያም ለጥበብ የሚኖር ውዴታ እንደማለት ነው፡፡ የምንነጋገረው ስለፍልስፍና ነውና ፍቅርና ጥበብም በራሳቸው ተርጉሙኝ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ለጊዜው አይመለከትንም፡፡ እየተረጎምን እንቀጥል ብንልም ውቂያኖሱ ውስጥ እንቀራለንና ይህንን የመግቢያ ሃሳብ “የፍልስፍና መግቢያ” ከሚለው መፅሀፍ ወስደንና ደራሲውን አመስግነን ከላይ የጠቀስነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ቅርንጫፍ የሰጠውን ድፍየና ከእንግሊዝ-አፍ በመመልከት እንቀጥላለን፡፡

የድርጅቱ ህትመት ፅንሰ ሃሳባቱን “Philosophy is the study of the nature of reality and existence, of what is possible to know, and of right and wrong behavior. It comes from the Greek word phílosophía, meaning 'the love of wisdom.' It is one of the most important fields of human thought as it aspires to get at the very meaning of life.” ሲል ነው ከቃላቶቹ ስርወ ምጣት እስከ ጥናት መስካቸው ድረስ ያለውን ሂደት የሚያስቀምጠው፡፡ ሆኖም ዘርፉ ንዑሳን ክፍልፋዮች አሉትና “…and of right and wrong behavior…” የሚለው አገላለፅ ህሊናዊ ፍርድን (Moral) የሚመለከት ክፍል ውስጥ የሚጠቃለል ነው፡፡

በመሠረቱ ፍልስፍና አገርና ድንበር የሚለየው ባይሆንም ስለኢትዮጵያ ፍልስፍና ለማንበብ የሚነሳ አንድ ሰው ፍልስፍና አልባ አህጉርና ፈላስፋ አልባ አገር ውስጥ እንዳለ ሊሰማው ይችላል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ እንደጥንታዊና እንደታሪካዊ አገርነቷ በሃይማኖቶቿም በባህሎቿም ጠብቃ ያቆየቻቸወው ምልከታዎች አሏት፡፡ በቀጣዩ ፅሁፍ የአፍሪካን ፍልስፍና በመጠኑ በመቃኘት የአገራችንን ፍልስፍናዊ ምልከታ ለመዳሰስ አንድ ቀጠሮ ይዤ ልሰናበታችሁ፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :