ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እጃቸውን መስጠታቸውን መንግስት አስታወቀ
December 1, 2020 (Ezega.com) -- የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸው ተነገረ፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሃት መካከል እየተካሄደ በከረመው ጦርነት መካከል መንግስት ያለመከሰስ መብታቸውን ካነሳባቸውና የእስር ትእዛዝ ካወጣባቸው የህወሃት አመራሮች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ኬርያ በመንግሥት ውስጥም ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት የነበራቸው መሆናቸው ይታወቃል። ወ/ሮ ኬሪያ የሁለቱን አካላት አለመግባባት ተከትሎ በተለይም በትግራይ ክልል ምርጫ መካሄድ አይችልም የሚለውን የመንግስት አቋም በመቃወም የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባኤነት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው ወደ መቀሌ አቅንተዋል። በወቅቱ ወደ መቀሌ ሲሄዱ አድርሷቸው የነበረው ሾፌራቸው ከስፍራው በመሰወር መኪናውን ይዞ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን ያስታወሰው የመንግስት መረጃ አሁን ወ/ሮ ኬሪያ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት ሰጥተዋል ሲል አስታውቋል። ያም ሆኖ እጃቸውን መቼ፣ የትና በምን ሁኔታ እንደሰጡ ግን የተሰጠ ማብራሪያ የለም። እስካሁን ስለ ሁኔታው ከህወሃት በኩል የቀረበ ምላሽም ሆነ አስተያየት አልተገኘም። የአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት በእዚህ ዘገባ ሌሎችም የሕወሓት አመራሮች የወ/ሮ ኬርያን መንገድ ተከትለው በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡ ተዘግቧል።
በሌላ በኩል የሱዳን ጸጥታ ሃይሎች ከሰላ በሚል በምትታወቀው ግዛት ውስጥ በሚገኘው አልፋሽካ በተባለ አካባቢ አንድ የሚሊሽያ መሪ እንደያዙ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡ በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብ ህወሃትን በመደገፍ ሲዋጋ እንደነበር ያስነበበው ጋዜጣው ሰውየው የተያዘው ከ5 ቢሊዮን የሱዳን ፓውንድ፣ ወርቅ እና ከ2 የቅንጦት ተሸከርካሪዎች ጋር መሆኑን ዘግቧል። በተጨማሪም ቤተሰቦቹ እና በርካታ ታጣቂዎች እና የግል ጠባቂዎቹም አብረውት እንደነበሩ ተሰምቷል። ታጣቂዎቹ አልፋሽካ በተባለው አወዛጋቢ አካባቢ በሱዳናዊያን ከብት አርቢዎች እና አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት በማድረስ ይጠረጠራሉ፡፡ በተጨማሪም ግለሰቡ በድንበር አካባቢ ለበርካታ ዐመታት ሰፊ የእርሻ ማሳ ባለቤት እንደሆነም ዘገባው ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ተሸሽገው ያሉ የህወሃት አመራሮችን በማሰስ ላይ መሆኑን የተናገረው ዘገባው ከሚፈለጉት አመራሮች ጥቂቶቹ የሱዳንና የደቡብ ሱዳንን ድንበር አቋርጠው ሳይገቡ እንዳልቀሩ የሚያሳዩ ሪፖርቶች መኖራቸውን አስነብቧል። በመንግስትና በህወሃት ሃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ እና ከ46 ሺህ በላይ ዜጎችን ደግሞ ያፈናቀለ ነው ሲል ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
በተያያዘ መረጃ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ትግራይ ውስጥ ውጊያው እንዲቆም ማሳሰባቸውን አስታወቀዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ያመለከቱት ማይክ ፖምፔዮ ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረገው ሂደት በመካሄድ ላይ ያለውን ግጭት መፍታት ወሳኝ መሆኑን እና ውይይት እንዲጀመር ብሎም ነፃና ለደህንነት አስተማማኝ የሆነና የማይደናቀፍ የሰብዓዊ አቅርቦት እንዲኖር መጠየቃቸውንም ገልጸዋል። ምክትል ቃል አቀባያቸው ካሌ ብራውን ከዚህም ሌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው የአፍሪቃ ሕብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ለውይይትና እርቅ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆኗን መግለጻቸውንም አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ በሕግ «ተጠያቂ» ካሉት ቡድን ጋር ውይይት እንደማይታሰብ ገልጸዋል። የዩናይትድ ስቴትሱ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ሲቪሎች ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳረጉና ውጊያውን ሸሽተው ወደ ሱዳን ለገቡ ስደተኞች ከለላ ስለመስጠት አጽንኦት ሰጥተው መነጋገራቸውንም አመልክተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይንም ሆነ የሁሉንም ጎሳዎች ሰብዓዊ መብት መከበሩን እንዲያረጋግጥ መማጸናቸውንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። አያይዘውም ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ጉድኝት እንዳላት ገልፀው በውይይታቸው «ታሪካዊ» ያሉትን የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ መደገፍ እንደምትቀጥል በአፍሪቃ ቀንድም ኢትዮጵያ ብልጽግናንና መረጋጋትን ለማስፈን ጠቃሚ ሚና እንደምትጫወት መነሳቱንም ጠቅሰዋል። በተያያዘ ዜና ዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለውን 'ግጭት' አስመልክቶ የፊታችን ሐሙስ በኢንተርኔት ውይይት እንደሚያካሂድ ተዘግቧል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን