የሁለት “ጁንታዎች” ወግ - የስግብግቡ እና የግብስብሱ!

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

PP-TPLFDecember 8, 2020

“ከእናንተ ኃጥያት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት!”
(ቅዱስ መፅሃፍ)

ከሳምንት በፊት “የሁለት “ጁንታዎች” ወግ” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አስነብበናችሁ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ፅሁፍ ከተነበበ ከጥቂት ቀናት በኋላ አንዱ በትግራይ ክልል ሌላው በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ስርና በሌሎች ክልሎች ታጅቦ ያለውን ጁንታ የበለጠ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች መፈጠራቸውን በማስተዋሌ በዚሁ ርዕስና ሁለቱን በስግብግብ እና በግብስብስ ባህሪያቸው ነጣጥዬ እንዳሳያችሁ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ይልቁንም ሁለቱም አካላት በጠቢቡ “ቢገድሉት ቢገድሉት የማያልቅ” የሚል ትርጓሜ ለተሰጠው ለሰፊው ህዝብ ሠላምና የመንግሥትም ቀዳሚው ኃላፊነት የሆነውን የዜጎች ደህንነት ማስጠበቁ ላይ ከመጨነቅ ይልቅ ስለሥልጣን ያላቸው ቅጥ ያጣ ቀናዒነትን እንመለከታለን - መልካም ንባብ፡፡

ስግብግቡ - የህወኃት ጁንታ!

የህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወኃት) በሌላ ስሟ ትህነግ እየተባለችም ትታወቃለች፡፡ ስለምን በእንስታይ ፆታ እንደምትጠራ ባላውቅም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ከመቀስቀሱ ከጥቂት ጊዜያት በፊት በጦርነቱ ጅማሮ ወቅትና ከዚያም በኋላ ቢሆን በኢህአዴግ ጥላ ስር ባሰባሰበቻቸው ድርጅቶች መካከል በተለይም በራሷ በህወኃት ውስጥ ስር የሰደደና በኢፌዲሪ መኮንኖች ግቢ ሳይቀር ሽጉጥ አታኩሶ እርስ በእርስ ያጠፋፋ ክፍፍል ሲፈጠር እንደማንኛውም ዴሞክራሲ አልባ የፖለቲካ ማህበር ጉዳዩ የተፈታበት መንገድ ፖለቲካችን ላይ ሌላ ፅልመት የጨመረ፤ አምባገነንነትን ያበረታና ሰብዓዊነት የተጣላውም ነበር፡፡

ከተገደሉትና ከታሰሩት ሰዎች በተጨማሪ ከድርጅቱ የተባረሩ፣ የኑሮ ሰቆቃ እንዲገጥማቸው ኢኮኖሚያዊ የበቀል አለንጋ ያረፈባቸውም ነበሩበት፡፡ ኋላ ላይ የኦህዴዱ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለርዕሰ ብሔርነት ክብራቸው በማይመጥን መልኩ ጣራው በሚያፈስ ቤት ውስጥ ምንም መኪና ሳይመደብላቸው እንዲሳቀቁ መደረጉ ለስግብግብነቷ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ህወኃት ስግብግብነቷ ሥልጣንና ኢኮኖሚን አለማጋራቷ ብቻ አይደለም፡፡ ግለሰቦች በርትተው ኢኮኖሚያቸውን ቢያፈረጥሙ እንኳን አትምራቸውም፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙዎች “አንተም ጨካኝ ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ…” እያሉ ባሳደገቻቸው ልጆቿ ስትሳደድ ያልተደነቁት፡፡ ለዚህም ይመስላል በሰፈረችው ቁና ልትሰፈርና በዘመኗ ኦነግን፤ ኦብነግና አርበኞች ግንቦት ሰባትን በሽብርተኝነት በማስፈረጁ በኩል ቀዳሚውን ሚና ወስዳለችና ተረኛ አሸባሪነተቱን የሚሰጧት፡፡

ወደ ቀደመው ነጥባችን ስንመለስ…. በወቅቱ ህንፍሽፍሽ “አንጃ” ተብለው የኢህአዴግ በትር ካረፈባቸው ግለሰቦች አንዱ አቶ ስዬ አብርሃ ነበሩ፡፡ አቶ ስዬ ምንም እንኳን ነባር ታጋይና ወታደራዊ መኮንን ቢሆንም ይህ መሆኑ ከውለታ አላስቆጠረላቸውምና ከእስርና ወከባ አላዳናቸውም፡፡ የህወኃቱ ጁንታ በግለሰቡ ላይ ሁለት ግፍ ሰርቷል፡፡ አንደኛው በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ይመራ ከነበረው ችሎት በዋስትና ሲለቀቁ ከፍርድ ቤቱ ጥቂት ሜትሮች ራቅ አድርጎ ባሰማራቸው የፀጥታ ኃይሎች ዳግም አሳፍኖ ወደ እስር ማጋዙ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካዊ ልዩነቱና ክፍፍሉ ወደቤተሰብ ማምራቱ በተለይም እምብዛም በፖለቲካው አካባቢ የማይታወቁ የቤተሰቦቻቸው አባላት ከመንገላታት አለመዳናቸው ነው፡፡

ብቻውን የበላ ብቻውን እንደሚሞተው ሁሉ በወንጀል ህጋንም አባት ለሰራው ወንጀል ልጅና ሚስት አይጠየቁም፡፡ በፖለቲካችን ግን ቤተሰብን ማሳደድ ብርቅ አይደለም፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ ይህንኑ ጉዳይ መነሻ አድርገው በፃፉትና “ነፃነትና ዳኝነት በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ በሰጡት መፅሃፍ ስር መከላከያ ሠራዊቱ ከዙፋን አስጠባቂነት እንዳልተላቀቀ ጠቅሰው ሲጀምር በህወኃት፣ ሲቀጠል በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍልና ፖለቲካዊ መሰነጣጠቅ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ምክንያት ነበር ይሉናል፡፡

ሲቀጥሉም እርሳቸው አባልና ወታደራዊ አመራር ሆነው ሥልጣን ያስያዙት ድርጅት በዚሁ ፖለቲካዊ ልዩነት ሳቢያ ቤተሰቦቻቸውን ሁሉ ምክንያት እየፈጠረ ወደእስር ማጋዙን ጠቅሰው ለቀደመው ጁንታ እጅ ባለመስጠቷ ያከበርናትን የያኔዋ ዳኛ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ያወሳሉ፡፡ ዳኛዋ የዋስትና መብታቸውን ብታስከብርላቸውም ልክ አሁናዊው ጁንታ አቶ ልደቱ ላይ የመያደርገውን አይነት ነውር ተፈፅሞባቸው እንደነበር በስማቸው ተጠርቶ በአንድ ቀን ጣጣው ያለቀለተን ህግ ጠቃቅሰው ሲያትቱ ይህንን አስፍረው አንብቤያለሁ፡-

“ይህ በእንዲህ እንዳለ የወ/ት ብርቱካን ችሎት በተሰጠው ቀጠሮ መሰረት አለመቅረቤን በመገንዘብ የምርመራ ኃላፊውም ይዞኝ እንዲቀርብ እንደገና አዘው የነበረ በመሆኑ በነጋታው ሰኔ 12 ቀን ጠዋት አራዳ ችሎት ቀረብን፡፡ ችሎቱም ‘ለምን አልተፈታም?’ በሚል ጥያቄ ጀመረ፡፡ ‘ከፍተኛ ፍርድ ቤት እግድ ስንጠይቅ ነው፡፡’ አሉ፡፡ ‘በምን ህግ ነው እግድ የምትጠይቁት?’ ተብለው ሲጠየቁ መልስ አልሰጡም፡፡ የሚሰጡት መልስም አልነበራቸውም… ከዚያ በኋላ ወ/ት ብርቱካን ከባልደረቦቿ ተማክራ ‘በቃ እዚሁ ፍርድ ቤት ልቀቁት፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰውዬው ነፃ ነው ልቀቁት፡፡’ በማለት አዘዘች፡፡” (ገፅ-97) ይሉንና አለመታደል ሀኖ ዛሬ አቶ ልደቱና በሌሎችም ተከሳሾች ላይ እንደሚሆነው ከፍርድ ቤቱ በራፍ ላይ የሥርዓቱ ዙፋን ዘበኛ የሆኑ የፀጥታ ኃይሎች ይዘው በድጋሚ እንዳሰሯቸው ፅፈዋል፡፡

ግብስብሱ - የብልፅግና ጁንታ!

ጁንታነት ባህሪው አንድና ደዌውም የማይለቅ እንደመሆኑ ብልፅግና ሁለተኛው ኢህአዴግ አልያም ተቀፅላ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆኑ ነጥቦችም በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው “ብልፅግና ማለት ህወኃትን የቀነሰና ስግብግቡ አላስቀምስ ያላቸውን ደግሞ የደመረ ኢህአዴግ ነው!” የሚባለው፡፡ ኢህአዴጋዊው ጁንታ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅን ከመሸሹ፣ ሥልጣንን ያለልክ በመውደዱ፣ የኢህአዴግን ገራፊዎችና ሌቦች ከማግበስበሱ አኳያ ደግሞ “ግብስብስ ጁንታ” ቢባል ቢያንሰው እንጂ በምሉዕነት አይገልፀውም፡፡ ቀዳሚው ጁንታ ሲሰራቸው ከቆያቸው ግፎች ይሄኛው ያልደገመው እምብዛም ነው፡፡ “ህዝባችን አድፋጭ ነው!” የሚሉትን ነብያዊ ምስክርነት የሰጡን ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ከማረፋቸው ሳምንታት ቀደም ብሎ “ብልፅግና በአብዮታዊ እርምጃ ካልጠራ በቀር….” ማለታቸው ለዚህ ሙግቴ በቂ ማሳያ ይሆናል፡፡ እርሳቸው የሳቱት አንድ ነገር ቢኖር ቢያጥቡት የማይጠራ ግብስብስ መበርከቱን ነው፡፡

ጁንታው የአዲስ አበባን መሬት ቅርምትና ህገ-ወጥ ዘረፋን አላስቆመም፡፡ ይልቁንም ሊያስቆሙ የታገሉትን “የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ” (ባልደራስ) አመራሮችን በሀሰት ክስ ሲያስር የብልፅግና አጋሮችን “የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ” (ኢዜማ) ሰዎችን ደግሞ መግለጫ ከመስጠት ከልክሏል፡፡ በአዲስ አበባ አንድ ክፍለ ከተማ በአጠራጣሪ ስያሜ በቅሎ ሲያድር ቀዳሚው ጁንታ ህዝቡን በአውቅልሃለሁ እንዳላማከረው ሁሉ ይሄኛውም አላማከረም፡፡ ከህወኃት የተወሰኑ አባላትና አመራሮች በቀር የኢአዴግን ሙሉ ግብስብሶች አግበስብሶ ቢመጣም ብልፅግናው አልጠራም፡፡ ጁንታነት ባህሪው አንድና ተመሳሳይ ነዋ!

ለይስሙላ የሚማልበትና የሚጠቀሰው ህገ-መንግሥት እየተጣሰ የዜጎች በህይወት የመኖር መብት ክብረት አጠራጣሪነቱ አልተቀረፈም፡፡ ድርጅቱ እንደቅንጦት የሚያያቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች ብቻ ሳይሆኑ ሰብዓዊ መብቶችም ይዞታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ የቀደመውን ሥርዓት በዚሁ ሳቢያ ይተቹ የነበሩ ዓለማቀፍ ተቋማት ዛሬም ህያው ምስክር ሆነው በሪፖርትና መግለጫቸው ጉዳችንን እያስተዋወቁን ነው፡ ለላይኛው ጁንታ ማሳያ ያደረግኳቸውን ሁለት ነጥቦች ለዚህኛውም ላስመልክታችሁ፡፡ የሌላው ያልተፈታ ሴራና ጭቦ ጉዳይ ሁሉ ይቆየንና አቶ ልደቱ አያሌውን እናንሳ፡፡

አቶ ልደቱ አያሌው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የፖለቲካ ማህበራት ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን ወደዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲ የሚያደርሳት መንገድ የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ በብሔራዊ ዕርቅ በኩል ማለፍ ነው ሲሉ የማህበራቸውን አማራጭ ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደኃላፊነት ሲመጡ ቃል ገብተዋቸው ቃለ-ዓባይ ከሆኑባቸው ነጥቦች አንዱ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበራትን ለሽንገላም ቢሆን “ተፎካካሪ” ከሰኙ በኋላ አማራጭ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ማበረታታቸው ነበር፡፡ ይህም አቶ ልደቱና ፓርቲያቸው የኢትዮጵያውያን ዴሞካራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ላይ እንዲሁም በታቀፉበት “አብሮነት” ላይ ሲከሽፍ ታይቷል፡፡ በፍርድ ሂደቱ ላይ ተፈጥረው ያስተዋልናቸውን እጅግ አሳፋሪ ነገሮች አንባቢን ላለማሰልቸት አንደግመውም እንጂ የፍትህ ሥርዓታችንን ተቋማዊ ገፅታ ወትሮ ከነበረውም በእጅጉ የቀየረና ለሥርዓቱ ተላላኪ የህግ ባለሙያዎች ሳይቀር አሳቃቂ እንደሆነ የምንዘነጋ አይመስለኝም፡፡

አቶ ልደቱ ስም ስላላቸው ጉዳያቸው ገነነ እንጂ ከሃጫሉ ሁንዴሣ የታሰበበት ግድያ በኋላ ያለህግ አግባብ የታሰሩና ፍርድ ቤትም ያልቀረቡ በሺህ የሚቆጠሩ ስለመኖራቸው ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡ ብዙ ያልተጮኸለትንና እሱም ብዙ የማይጮኸውን አንድ ሌላ ሰው ላስታውሳችሁ፡፡ ሁሴን ከድር (ዶ/ር) ይባላል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ባህርይና ትምህርት ጥናት ክፍል ውስጥ መምህርና ምክትል ዲን ሲሆን ብልፅግና ሊሾመውም ሲያግደረድረው የነበረ ምሁር ነው፡፡ ሆኖም ከአቶ ጀዋር ሲራጅ ሙሐመድ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ምክንያት ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው ቤቱ ተወስዶ ኦሮሚያ ውስጥ ከታሰረ አራት ወራት አልፈዋል፡፡ በመሠረታዊነት የወንጀል ተከሳሾች ሊያገኟቸው የሚገቡ ሰብዓዊ መብቶችን ሲነፈጉ የሚሰሩበትን ተቋም ዩኒቨርሲቲውን ጨምሮ የመብት ተሟጋቾችም ምንም አላሉላቸውም፡፡

እንካችሁ ደግሞ ሌላ ማሳያ፡፡ ስለጀዋር ሲራጅ መሐመድ የተለያየ አመለካከት ሊኖረን ይችላል፡፡ በእርሱ ፖለቲካዊ አቋም ሳቢያ እህቱንና የእህቱን ባል በጠራራ ፀሐይ ማንገላታትም ሆነ መዝረፍ የመንግሥት ፀጥታ አካላት “ስራ” ሲሆን ማየትና ይህንን ህግ አልባነት የማይቃወም ሰው መበርከቱን ማስተዋል ግን አስፈሪ ይሆናል፡፡ ቀዳሚው ጁንታ እንኳን በአቶ ጀዋር ቤተሰቦች ላይ እንዲህ አይነት ግፍ አልፈፀመም ብዬ መከራከር እችላለሁ፡፡ የአሁኑ ኢዜማ የያኔው አርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ምክንያት ወላጅ አባታቸው ሲንገላቱ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ሌሎችም በርካቶች የተመሳሳይ ሰቆቃ ለለባ ነበሩ፡፡ ግለሰቦቹ ወንጀል ሰርተዋል ቢባል እንኳን ወንጀል በባህሪው ግላዊ ነውና ወንጀሉን ሰርቷል ተብሎ ከሚጠረጠረው ግለሰብ ውጪ ቤተሰብና አዝማዶቹን ሁሉ የፖለቲካ ቂም መወጣጫ ማድረግ ፀያፍ ብቻ ሳይሆን በራሱ ወንጀልም ነው፡፡

ፖሊስና በአጠቃላይ በአስፈፃሚው ስር የሚንቀሳቀሰው የፀጥታ አካል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመጤፍ በማይቆጥርበት አገር ይልቁንም እንደ ደርጉ ዘመን ሁሉ እስረኞችን እያወጣ እንደሚረሽን ለሰብዓዊ መብት ተቋማት ቅሬታና ጥቆማዎች በሚቀርቡበት አገር የፖለቲከኞችን አንደበት ለመሸበብ ቤተሰብን ማጥቃት በጋራ ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሰብዓዊነት ቢሆንም በጋራ የሚያቆመን አንድም ነገር አጥተናልና እነሆ ሌላ ማሳያ፡፡ በግፍ የተገደለው የሃጫሉ ሁንዴሣ ወንድም ላይ ቀዳሚው ጁንታ ያደረሰውን እያሰባችሁ ይሄኛውን ጁንታ ደግሞ በደንበኛው መልኩ ተዋወቁት፡፡ ያያ በሽር የሚባለውን የኦሮሞ ፖለቲካ አክቲቪስት እንደምታውቁት እገምታለሁ፡፡ ይህ ግለሰብ በውጭ አገር ሆኖ ፖለቲካውን ያንቀሳቅሳል በሚል ስጋት የመንግሥት አካላት የአራት ልጆች አባትና መምህር የሆነ ወንድሙን አቶ ጋሊብ አባ ሳምቢን ከቤቱ በመውሰድና ጫካ ውስጥ በጥይቶች በመምታት ሄደዋል፡፡

ነብሱ አልወጣችም ነበርና የኮሎኔል ዓብይ አህመድ አካባቢ ሰዎች ጅማ ሆስፒታል ቢያደርሱትም ከቀናት በኋላ ሞቱን ሰምተናል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ሐዘኑን ዋጥ በማድረግ ያያ በሽር ይህንን ፅፎ ነበር፡- “I have received a number of threatening messages from his security over the last few months. However, I have never thought that they would attack my innocent family members back home to revenge on me because family members are pretty neutral of any side of politics. This is Abiy Ahmed's new fascistic and terrorist strategy to silence dissent. It has never happened even during the Marxist Derg rule or under the TPLF-dominated EPRDF regime. The intention is to silence the diaspora Oromo community who are actively challenging his killer regime. State terrorism at it's best.”

ስግብግቡም ግብስብሱም - ያው ናቸው!

በኢፌዲሪ ህገ-መንግሥት አንቀፅ… መሰረትና በመከላከያ አዋጅ…. የተቋቋመው ሠራዊት ትናንትም “ግደል!” ሲለው ለነበረው ሆነ ለዛሬው ጁንታ እየገደለ ነው፡፡ ከሥርዓት አስጠባቂነት ወጥቶ ህዝባዊ ውግንናን በመላበስ የህግ ተገዢነት ውስጥ በቅርቡ ይገባል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ስለተቋማት ነፃነት ከተነሳ አይቀር በትናንቶቹ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት እና በዛሬዎቹ እኚሁ ተቋማት መካከል የተለወጠ ነገር ቢኖር ማሊያውን የቀየረ አመራር መሾሙ ብቻ ነው፡፡ ከማህራዊ ገፆቻችን የባሱት የብዙኃን መገናኛዎቹና የእነሱ ተቆጣጣሪ (Regulator) የሚባለው የብሮድካስት ባለሥልጣን መድፈር ያቃተውና ደጋግመን የሞገትነው ገለልተኝነት ዛሬም አልተነካም፡፡

የመንግሥት የፀጥታ አካላትማ ጠያቂ አልባ ሆነዋል፡፡ ወጣቶችን መግደል ወንጀልነቱ ዛሬም አጠራጣሪ ነውና ማንም ተጠያቂ አልሆነም፡፡ በእርግጥ ተጠያቂነት ከመጣም ይሄኛውን ጁንታ ለሶስት ተጨማሪ ዓመታት ያስጠይቃል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተባለው ብልፅግና ህወኃትን ቀንሶ ህወኃት ሥልጣን አላቀምስም ያላቸውን የዛሬዎቹን አደርባዮች የደመረ ኢህአዴግ ነውና ቆዳውን ከመቀየሩ በቀር አዲስ ነገር የለውም፡፡ የብዙኃን መገናኛዎች በተለይም መንግሥታዊዎቹና የገዢው ፖለቲካ ማህበር ቀላጤዎቹ እንደትናንቱ ሁሉ ሥልጣን ላይ ላለው አካል ከመዘመር ይልቁንም ሙያዊነትን አሳልፎ ሰጥቶ ማደናቆሪያ ከመሆን አልተላቀቁም፡፡ ተቋማት በገለልተኛነት አልተገነቡም ብቻ ሳይሆን እንደትናንቱ ሁሉ ከበቀቀንነት የፀዱ ነፃ ተቋማትን የማቋቋም ውጥንና ፍላጎቱ ያለ አይመስልም፡፡

አዎን! ህዝብ ይሳሳታል ለማለት የሚደፍሩ እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉት ጥቂቶች ቆራጦች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንም ህዝባችን ግፍን ሳይሆን የግፈኛውን ብሔር ለይቶ እንደሚመርጥ መዝግበዋል፡፡ ጭቆናን ሳይሆን የጨቋኙን ጎሳ እንደሚታገልም መስክረው አልፈዋል፡፡ ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ የእንቶኔ ተላላኪ፣ ጠላት፣ ቅጥረኛ፣ የእናት ጡት ነካሽ፣ ባንዳ…. እየተባባልን እንደደርግና ኢህአዴግ ዘመኑ ሁሉ መፈራረጃችን አልተገታም፡፡ እንደህዝብም ለመጣ ባለጊዜ ሁሉ “ንሴብሆ!” እያሉ ማጨብጨብ ይዞን እየጠፋ ስለመሆኑ የሚያስተውል ቁጥሩ ሲያንስ እየታዘብን ነው፡፡ ይልቁንም ትናንት በኢህአዴግ ዘመን አይነተ ብዙ ግፍን ሲያስተናግዱ የነበሩ ስመኛ ግለሰቦች ግፍ እንዳይደገም አንደበት መሆን ሲያቅታቸውና ባስ ሲልም ሲያበረታቱ ማየት ህመሙን ያከብደዋል፡፡

ሁለቱን ጁንታዎች ማማረጥ ለእኔ “ከዝንጀሮ ቆንጆ…” እንዲሉ ነው፡፡ ግብስብሱም ሆነ ስግብግቡ ያው ሁለቱም ጁንታዎች ናቸው፡፡ ስግብግብነት መገለጫው ብዙ ሊሆን ቢችልም ግብስብስነትም በርካታ የራሱ ማሳያዎች አሉት፡፡ ያለንበት ፖለቲካዊ ሥርዓትና ምሁራኑ “ማህበራዊ ድንቁርና” ይሉት ጉድ ብዙ ነገር ቢያሳጣንም ከሁሉም የሚከፋው ግን ጥበብን ለፖለቲካ ተላላኪነት ያዋሏትን ሃሳዊ ጠቢባን ጨምሮ በሙሉ አንደበት “አንቱ!” የምንለው ግለሰብና ታማኝ ተቋም ማጣት ነው፡፡

ፅሁፌን የማገባድደው ከላይ ከዘረዘርኳቸው ግፎች ሁሉ እጅግ የከፋውንና በወገን ጦርነት መሃል የተሸበለቀውን የማይካድራ ንፁኃን ላይ የደረሰውን ኢ-ሰብዓዊነት በማውገዝ፤ አህያ ለአህያ ቢራገጥ ጥርስ ባይሳበርም የዝሆኖቹ ፀብ ለሳሩ አደጋ ነውና ሁለቱም ጁንታዎች ለአገርና ለህዝብ የሚበጀውን እንዲያደርጉ ልቦና ይሰጣቸው ዘንድ በማስታወስ ነው፡፡ እነሆ ባልን ገድሎ ወንድም የሚፎክርበትን፣ ወንድምን ደፍቶ ባል የሚፎክርበትንና ኃዘንን ቅጥ የሚያሳጣበትን የወገን ጦርነት በተመለከተ ባለቅኔውና ፈለስፋው ደበበ ሠይፉ ለቅሶዬን ያልቀስኝ፡-

አታልቅስ አትበሉኝ!
አትሳቅስ በሉኝ - ግድየለም ከልክሉኝ፡፡
የፊቴንም ፀዳል - አጠልሹት በከሰል፣
የግንባሬን ቆዳ - ስፉት በመደዳ፣
ጨጓራ አስመስሉት፡፡
ግድ የለም….
አትጫወት በሉኝ - ዘፈኔን ንጠቁኝ፣
ግድ የለም ብቻ - አታልቅስ አትበሉኝ
አትጩህ አትበሉኝ፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን! -

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :