አሜሪካ በትግራዩ ጦርነት የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፈዋል ብላ እንደምታምን ተነገረ

ኢዜጋ ሪፖርተር

Eritrean-armyDecember 8, 2020 (Ezega.com) -- የኤርትራ ወታደሮች በፌደራል መንግስት እና በህወሃት ሃይሎች መካከል በተከሰተው ጦርነት ውስጥ ተሳትፈዋል ብላ አሜሪካ እንደምታስብ ሮይተርስ ከአንድ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን እና ከ5 የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ዲፕሎማቶች ሰምቻለሁ በማለት ዘግቧል። ኤርትራ ጦሯን ስለማስገባቷ የአሜሪካ መንግሥት ግንዛቤ ያገኘው፣ ከሳተላይት ምስሎች፣ ከተጠለፉ የመልዕክት ልውውጦች እና ከትግራይ ክልል ከሚወጡ ሪፖርቶች እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። ያም ሆኖ በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ መንግሥት ድምዳሜ ላይ ስለመድረሱ እና አንዳች አቋም ስለመያዙ ግን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ማረጋገጫ አለመስጠቱን ዘገባው አመልክቷል። የኤርትራ ወታደሮች በዛላንበሳ፣ ራማ እና ባድመ ከተሞች በኩል እንደገቡ ከምንጮች መስማቱን የገለጠው ዜና ወኪሉ የወታደሮቹ ብዛት እና በጦርነቱ ስላላቸው ሚና በተመለከት መረጃ እንዳልተገኘ አክሏል። ብሉምበርግም ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ፣ የኤርትራ ወታደሮች መቀሌ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች መታየታቸውን ዘግቧል። የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግስታት ከህወሃት በኩል በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበሩ መሰል ውንጀላዎች ሀሰት መሆናቸውን በመግለጽ ሲያጣጥሉት መቆየታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ለሁለት አስርት አመታት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ውዝግብ በስምምነት ለመፍታት ተስማምተው ግንኙነታቸውን ያደሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ህወሃትን የጋራ ጠላታቸው አድርገው መፈረጃቸውን ዘገባው ያትታል። ምንም እንኳን አሜሪካ በጦርነቱ የኤርትራ ሰራዊት ተሳትፏል መባሉ ባያስደስታት እና ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነትም የሻከረ ቢሆንም ኢትዮጵያን በስጋት ቀጠና ውስጥ ያለች ዋነኛ አጋሯ አድርጋ ስለምትቆጥር አንዳች እርምጃ ትወስዳለች ተብሎ እንደማይጠበቅ በዘገባው ተጠቅሷል። ሬውተርስ መረጃውን አቀብለውኛል ያላቸውና ማንነታቸውን ያልገለጸው የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣን "በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ጥርጣሬ ያለ አይመስልም የሀገሪቱ ባለስልጣናት ሁኔታውን አስመልክቶ በስልክ ተወያይተው ኤርትራውያኑ በትግራይ ክልል ይገኛሉ ከሚል ድምዳሜላይ ደርሰዋል። ያም ሆኖ ሁኔታውን በይፋ ማሳወቅ አልፈለጉም" ማለታቸውን አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ማንነታቸው ያልተገለጸ አንድ ከፍተኛ የሌላ ሀገር ዲፕሎማትም "በሺዎች የሚቆጠሩ" የኤርትራ ሰራዊት አባላት በግጭቱ ተሳትፈዋል ተብሎ እንደሚታመን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ሲል ዘገባው አስነብቧል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስትን ድምዳሜ በተመለከተ ያለው ነገር አለመኖሩን ያመለከተው ዘገባው ቃል አቀባዩ ግን የኤርትራን በግጭቱ መሳተፍ በተመለከተ የተረጋገጡ መረጃዎች ከተገኙ አሜሪካ ጉዳዩን በከፍተኛ አትኩሮት እንደምትመለከተው መናገራቸውን አትቷል። የዜና ወኪሉ በጉዳዩ ዙሪያ ባሳለፍነው ቅዳሜ ያናገራቸው የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኦስማን ሳሌህ መሃመድ "እኛ ምንም አይነት ተሳትፎ የለንም ይሄ መሰረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳ ነው" የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተነግሯል። በኢትዮጵያም በኩል ቢሆን ውንጀላው "የህወሃት ጁንታ ግጭቱን አለም አቀፍ መልክ ለማስያዝ የሚያደርገው ተደጋጋሚ ጥረት አካል" መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሲሰጥበት ቆይቷል። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በቅርቡ በምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በህወሃት ሃይል በተፈጸመባቸው ድንገተኛ ወረራ ምክኒያት ሸሽተው ወደ ኤርትራ መግባታቸውንና በዛም ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸው አመስግነዋል። በሌላ በኩል ስለሁኔታው ሬውተርስ ያናገራቸው የጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይም ጥያቄው መቅረብ ያለበት ለኤርትራ ነው ሲሉ መመለሳቸው ተዘግቧል። ሬውተርስ በሁሉም አካላት የሚሰጡ ሃሳቦችን ለማረጋጋጥ የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሶ ለዚህም በትግራይ ክልል ያለው የግንኙነት መቋረጥ ዋና መንሰኤ ነው ብሏል። የህወሃት ሃይሎች ቢያንስ ለ አራት ጊዜ ያህል ወደ ኤርትራ ከተሞች ሮኬቶችን መተኮሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው የኤርትራ ወታደሮች ወደ ክልሉ የገቡትም በህዳር ወር አጋማሽ ላይ እንደነበር ያስነበበው የዜና ወኪሉ ዘገባ ሰራዊቱ በሶስት ሰሜናዊ የጠረፍ ከተሞች ማለትም ዛላምበሳ፣ ራማ እና ባድመ በኩል ሳይገቡ እንዳልቀሩ ጠቅሷል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :