ቀኑን ወይስ “ሰብዓዊ መብቶችን” አክብሮ ማስከበር?

Respect human rightsሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
December 10, 2020

“How can you thank a man for giving you
what’s already yours? How then can you thank him
for giving you only part of what is yours?”
(ማልኮልም ኤክስ)

ዓመታትን ወደኃላ….!

እነሆ አስር ዓመታት ሊደፍኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተቀናጀ መልኩ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለመጠበቅ ያስችለኛል፤ ለጥበቃቸውም ስልትና አቅጣጫን ለመንደፍ ያዘኛል ያለችውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ማስፈፀሚያ የድርጊት መርሐ-ግብር (National Human Rights Action Plan 2005-2007) ዝርዝር ጉዳዮችን እንደያዘ ተረቅቀው በሚኒስትሮች ምክር ቤትና የህዝብ መሆን ሳይችል ዘመኑን በፈጀው የተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ፡፡ ሆኖም ተስፋ የተጣለባቸው የሲቪልና ፖለቲካ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚ እንዲሁም ባህላዊ መብቶች ተግባራዊ አፈፃፀምና አስተምህሮ ጉዳይ ባለበት ነው ያለው፡፡

ኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶችን በመቀበል ከአህጉራን ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ የኢፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ከመታወጁ ቀደም ብሎ በነበረው አገራዊ የሽግግር ወቅት “መሰረታዊ መመሪያና መርሆ” በመሆን ባገለገለውና የአሁኑን ህገ-መንግስት መሰረት በጣለው እንዲሁም “እጅግ ዴሞክራሲያዊ ሰነድ ነበር!” ተብሎ በብዙዎች በሚወደሰው “የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር” እና በአሁኑ ህገ-መንግሥት ጭምር የበዙትን አናቅፆቹን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ሆነው ነው የምናገኛቸው፡፡

ሆኖም ከማስመሰልና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን በታይታ ከመደለል ባለፈ አልተተገበረም፡፡ ዛሬም ሰዎች ከህግ አግባብ ውጪ በህይወት የመኖር መብታቸው አላስተማመነም፡፡ አካላዊ ደህንነታቸው አልተረጋገጠም፡፡ ከህግ አግባብ ውጪ እንደማይታሰሩና እንደማይንገላቱ ዋስትና አላገኙም፡፡ ከላይ የጠቀስነው የድርጊት መርሃ ግብር ቀዳሚው ክፍል አልተተገበረምና ሁለተኛው ክፍል መምጣቱም ለውጥ አላመጣም፡፡ ይልቁንም ከአምስት ዓመቱ የዕድገት ውጥንና ልማታዊ ልውጠት ዕቅድ (Growth and Transformation Plan) ውስጥ አንድ ግብዓት ከመሆን ባለፈ ሰብዓዊ መብቶች በራሳቸው አልታሰበባቸውም፡፡

የዓብይ አህመድ (ኮ/ል) አገዛዝ የኢህአዴግን ኢኮኖሚያዊ ርዕዮት “ቆሞ-ቀር” ሲል በመንቀፍ “አገር በቀል” ያለውን መንገድ ተልሟልና የዕድገት ውጥንና ልማታዊ ልውጠት ዕቅዱ ከመንግሥት አጀንዳነት ሲወጣ አብሮ እንደሚተገበር ተነግሮለት የነበረው የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይም አብቅቶለታል፡፡ ከ-2004-የሠነድ ዝግጅቱ ጀምሮ ትግበራው ተጀምሮበታል እስከሚባለው-2006- ድረስ “ሰብዓዊ መብቶችን” ተስታከው ይሰሩ የነበሩ የስበትና መጠቃቀም ጉዶችን ለጊዜው ተወት አድርገን ሠነዱ ኢትዮጵያችን ውስጥ የነበሩትንና ሳይፈቱ የቀጠሉትን ችግሮች በነባራዊ እውነታነት አልያዘም፡፡

ከክሽፈት ወደ ክሽፈት?!

ሰነዱ ሆነኝ ተብሎ በጣም የዘመነ እንዲመስል መደረጉም ተግባራዊነት እንዲርቀው አድርጓል፡፡ ቀላሉ ማሳያ አሁንም ድረስ “ዶክትሪን” እንዲሸፍነው የተደረገውና መፍትሄ የጠፋለት “የፀጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀም” ልኬት ጉዳይ ነው፡፡ ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት “Amnesty International” አሁን በቀጠለው የወገን ጦርነት ወቅትም ሆነ ከጥቂት ወራ በፊት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የአገሪቱ የፀጥታ አካላት የፈፀሟቸውን አይነተ ብዙ ግፎች ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በተቃራኒው ቄሮ፣ ፋኖ እንዲሁም በቅርቡ በማይካድራ ግድያዎች ላይ መሳተፉን የሰማንለት “ሳምሪ” ተብሎ የተጠቀሱት መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች በህዝብ መብቶች ላይ የደቀኑት የሰብዓዊ መብቶች ገፈፋና የዘር ማጥፋት ፈተና እንደዋዛ በቀላሉ የሚታለፍ አለመሆኑንም ተቋሙ በመግለጫው አብሮ ጠቅሷል፡፡

ለገፅታ ግንባታና ለሥልጣን ዘመኑ ርዝማኔ ሲደክም የኖረው ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችን (International Human Rights Documents) በመቀበል ከአህጉራችን ቀዳሚ አገራት ተርታ ውስጥ ከፊተኞቹ ቢሰለፍም መሬት የረገጠው እውነታ አስከፊም አስፀያፊም ነበር፡፡ በህ-መንግሥቱ አንቀፅ-9/13(2) መሰረትእነዚህ መብቶች የአገሪቱ ህግ አካል ሆነው ሶስቱ የመንግሥት አካላት ማክበርና ማስከበርን በኃላፊነት ቢወስዱም በዓለማቀፉ የመብቶች አጠባበቅ ግምገማ (Universal Periodic Review) ከአገራትና አለማቀፍ ተቋማት አስተያየቶችን ከትችት ጋር ከሚያስተናግዱ አገራት ተርታ አልተላቀቅንም፡፡

በተለይ ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅና ከዴሞክራሲ ማስፈን ጋር ተያይዞ ከስራ ተከለክለው የነበሩ የበጎ አድራት ድርጅቶች፣ የሙያ ማህበራና የነፃ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶች (Civic Societies) በሰብዓዊ መብቶች ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እንዳይሰሩ ከመከልከል ጀምሮ ማስፈራሪያና የንብረት ንጥቂያም ሲደረግባቸው ኖሯል፡፡ በህገ-መንግሥቱ የታወቁ ሰብዓዊ መብቶችን ለመተግበር መንግሥትና መንግሥታዊውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጨምሮ በመስነፋቸው “አስቻይ ሁኔታዎችን” ለመፍጠር ተልሞ ቢዘጋጅም በሁለተኛው ክፍልም (ከ2008-2012) የቀዳሚውን ክሽፈት ደግሞታል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የወቅቱ ተቃዋሚየፖለቲካ ማህራት በነበሩበት አንድ መድረክ ላይ ሁሌ እንደሚደረገው ለግብዓት የሚሆን ሃሳብ እንዲሰጡ ሠነዱ ከተዘጋጀ በኋላ “ለይስሙላ” ተጠርተው ሠነዱን በተመለከተ ከሰጧቸው አስተያየቶች ክሽፈቱን መረዳት ቀላል ነበር፡፡ ለአብነትም ዛሬ “ተፎካካሪ” እየተባሉ የሚሸነገሉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበራት ለጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች (ቨልነረብል ግሩፕስ) ውስጥ እንዲካተቱ እስከመጠየቅ ደርሰው ነበር፡፡የወቅቱ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮች የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ በፅሁፍ እሳተፍበት ለነበረችው “ሰንደቅ” ጋዜጣ ሃሳባቸውን ሲያካፍሉ አሁን ካለንበት ሁኔታ አኳያም የተለወጠ ነገር ስላለመኖሩ ማሳያ ይሆነናልና እንዲህ ነበር ያሉት: -

“በመጀመሪያ ደረጃ ችግር እንዳለበት መንግስት የሚቀርቡበትን ችግሮች አምኖ መቀበል ይኖርበታል… ለምሳሌ በህይወት የመኖር መብት የሚለው ላይ እንደ እኛ እይታ በቅርቡ በተፈጠሩ ችግሮች ላይ እንኳ የብዙ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። ህይወታቸው ከጠፉ ዜጎች መካከል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተገደሉት ቁጥራቸው ብዙ ነው። እንደ ሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር መንግስት ይዞ ሲነሳ ያንን ማጣራት ነበረበት። ያንን ያህል ሰው በመንግስት የጸጥታ ሀይል ሲገደል የሰዎችን በህይወት የመኖር መብት ነጥቋል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜዎችና አካባቢዎች በመንግስት ላይ በሚነሱ ታቃውሞዎች ምክንያት በሚፈጠር ግጭት የብዙ ሰዎች ህይወት አልፏል። ያንን አጣርቶ ተጠያቂ የሚሆኑ የመንግስት አካላትን ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ መካተት ነበረበት…. የድርጊት መርሃ ግብሩን ሰነድ ካየህ ችግሮቹ መኖሩን አለማመን ነው ያለው። እንዲያውም የመጀመሪያው የድርጊት መርሃ ግብር ሙሉ በሙሉ መሳካቱን ብቻ ነው የገለጸው… በሁሉም ችግሮች ላይ የሚሰጠው ችግሩን ክዶ ስኬቱን ብቻ መግለጽ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ሰነድ ከመጀመሪያውም አያስፈልግም። ምክንያቱም መግቢያው ላይ የተቀመጠው ማብራሪያ እውነት ቢሆን አስፈጻሚው አካል ስራውን በአግባቡ የሚሰራ ቢሆን የድርጊት መርሃ ግብር ለምን ያስፈልጋል። የልማት መብት የመምረጥና የመመረጥ መብት ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ቢከበር እኮ በሰነድ አዘጋጅቶ ማቅረብ አስፈላጊም አይሆንም፡፡”

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሰነዶቹ ወደትግበራ ይገባሉ የተባለበት ወቅት ላይ ገና ምኑም ያልተያዘ “ውይይት” ላይ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ የመብቶች ሁሉ እናት (The Mother of all the Rights) ከሚባለው በህይወት የመኖር መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት እንኳን ሳይከበሩ የቅንጦት የሚመስሉና ሆን ተብሎ ለገፅታ ግንባታ የገቡ መብቶችንም ተመልክተናል፡፡ የመኢአዱ ተወካይ ሲቀጥሉ ደግሞ፡- “ለምሳሌ አመለካከትን እና ሃሳብን የመግለጽ መብትን በተመለከተ ነጻ ሚዲያን የማስፋፋት የሚል አንድም ቦታ አልተገለጸም። እንደ አገር ስናየው አንዱ ትልቁ ችግራችን ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻ የሚገልጹበትና የመንግስትን ድክመቶች የሚያሳውቅ ሚዲያ አለመኖር ነው። መንግስት ከልቡ መሻሻል ከፈለገ የነጻውን ሚዲያ ማስፋፋት ይኖርበታል። የግሉ ፕሬስ ከገበያ የወጡበት ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ማጣራት አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ግን ለማድረግ መንግስት ድፍረቱ ያለውም አይመስልም፡፡”

መብቶቹ እና ቀኑ በኢትዮጵያ….

ኢህአዴግ ፖለቲካዊ መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን አምጥቻለሁ ባይ ነው፡፡ ሆኖም በሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝና ነፃነቶች ጥበቃ በኩል ስራውም ፕሮፖጋንዳዊ ልፈፋውም አልተሳካለትም፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ሰብዓዊ መብቶች ሲባል ሰዎች “ሰው” በመሆናቸውና በዚሁ የእኩልነት ፍጥረትነታቸው ብቻ (Universal) በተቸራቸው ክብር (Inherent) የሚኖሯቸው ናቸው፡፡ እነዚህን መብቶች በተመለከተም የዘር፤ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የፆታ፣ የፖለቲካዊ አመለካከትና መሰል መስፈርትና ቅድመ-ሁኔታዎች ከግምት ሳይገቡ ቢያንስ በመርህ ደረጃ በህግ ካልሆነ በቀር በማይነጠቁበት ሁኔታ (Inalienable) የሚከበሩላቸው ናቸው፡፡

መብቶቹ ከፍጥረታችን ጋር አብረው ቢኖሩም የዘመናዊ መንግሥት ምስረታ ከፊሎቹን በአደራ እንድንሰጠው አድርጓል፡፡ በሂደት ከመንግሥታዊ አምባገነንነት ጋር አደራዎቹ እየተበሉ የእኛ የሆነውን መብት እየሸራረፈ ስለመለሰልንአመስግኑኝ ባይ ሆኗልም፡፡ መብቶቹ በዓለማቀፍ ስምምነቶችና ሰነዶች በኩል ተዋውቀውና በህግነት ደረጃ ለዓለም የተስተጋቡት በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር-1948- ላይ በአስረኛው ታህሳስ (December-10) ስለነበር ይህ ሰላሳ አናቅፅን የያዘው ሁሏቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እወጃ (Universal Declaration of Human Rights - UDHR)የተዋወቀበት ቀን ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ቀን (Intrenational Human Rights Day) ሆኖ ስለመብቶቹ ግንዛቤን በማስፋፋት እንዲታሰብ ሆኗል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጠቅላላ ጉባዔው ይህንን ከሶስት መቶ ስልሳ በላይ ቋንቋዎች የተተረጎመ የሰብዓዊ መብቶች ሰነድ ካወጀ በኋላ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ በኩል ስለሰብዓዊ መብቶች ትይይዝ ሲያስረዳ ይህንን አስፍሮ አንብቤያለሁና እንካችሁ፡- “Human rights are indivisible, interrelated and interdependent, for thereason that it is insufficient to respect some human rights and not others. In practice, the violation of one right will often affect the respect of several other rights. All human rights should therefore be seen as having equal importance and of being equally essential to respect for the dignity and worth of every person.”

በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ከኃላፊነትና ግዴታ ጋር የምናያይዘው መብት (Right) ልዩነት (Privileges) ችሎታ (Capacity) እንዲሁም እኚህን የመሳሰሉ ቃላት በርካታ ቢሆኑም በተፈጥሮ ከመገኘቱ ባሻገር በስልጠን አገራት ህግ-ሰራሽ (Legal Rights) መብቶችም አሉ፡፡ ሁልጊዜም ከተፈጥሮ የመነጩ ናቸው እንዳይባሉ የሚያደርገውም ይኸው ነው፡፡ ህገ-ፍልስፍናው (Philosophy of Law and Jurisprudence) እንደየአገራቱ ማህበራዊ እውነታና የዕድገት ሁኔታ የራሱን መልክና ቅርፅ ይይዛል፡፡ ከሰሞኑ ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተወካዮች ምክር ቤት ንግግራቸው ትኩረት ያላደረግንበት ቢሆንም“ኢትዮጵያን የሚመስል ዴሞክራሲ እንገነባለን!” ሲሉ የገለፁት ይህንኑ ለአምባገነንነት በር ከፋች የሆነ ሃሳብ ነበር፡፡ ከላይ የጠቀስነው የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሃ ግብር እንደሚገልፀው መንግሥት ላይ ኢኮኖሚያዊ መብቶች (Economical Rights) በሂደትና በአቅሙ ልክ የሚሟሉ እንጂ ወዲያውኑ የሚሳኩ እንዳልሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አለመታደል ሆኖ “ኢትዮጵያን የሚመስል ዴሞክራሲ ምን አይነት ይሆን?.” ብሎ የጠየቀ አለመኖሩ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ቀን በተለያዩ አውደ ጥናቶችና መፈክሮች እያሰበች ዓመታትን ብታስቆጥርም በሰብዓዊ መብቶች ይዞታ በኩል በተለይ አሁን “ህግ ማስከበር” በሚል የዳቦ ስም ከተሟሸው የወገን ጦርነት (Civil War) ጋር ተያይዞ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቀኑ በሳምንትነት አድጎ መታሰብ ከጀመረ ቢቆይም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት አንቂና አስጠባቂ ተቋማት ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና “የኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ የተነጠቀውና በመንግሥት ሚዲያዎች የአስር ደቂቃ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት ጠይቆ የተከለከለው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ጋር በጋራ በመምከር የዘንድሮውን አስሽለውታል ለማለት እደፍራለሁ፡፡

አለመታደል ሆኖ ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔትና ሌሎች በዓለማቀፍ ደረጃ ከሰብዓዊ መብትነት የተመደቡ ግንኙነቶችን በተደጋጋሚ በማቋረጥ የቀጥታ ተሳታፊ ቢሆንም ተቋማቱ ደፍረው ሲተቹት አይስተዋልም፡፡ የመብራት አገልግሎቱንም እንዲሁ፡፡ አሰቃቂው የሰው ልጆች ታሪክ ያደረሰውን ሰቆቃ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኩል የታዘቡት ቀኑ እንዲከበርና ሰብዓዊ መብቶችም ትምህርታቸው እንዲስፋፋ ቀስቃሽ ሆኗቸዋል፡፡ የዕለታቱ መታሰብ መልካም ቢሆንና ቢፈይድም ወደተግባራዊነት መቀየሩ ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ነውና “Addis Standard” መፅሄት በአንድ ዕትሙ ላይ “Human Rights Day in Ethiopia; Make It Count Please” ሲል መንግሥት ለተግባራዊነቱ እንዲተጋ ጥቆማውን የለገሰው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰብዓዊ መብቶች ማዕከል ቀኑን ከሚያከብሩት ተቋማት አንዱ ቢሆንና በነፃ የህግ ድጋፍ ማዕከላቱ (Free Legal Aid Center) በኩል ቢሰራም ገና ብዙ ብዙ እጅግ ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ለሰላሳ ደቂቃ ያሰራጨው የነበረው ግንዛቤ ማስጨበጫም ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ራዲዮ ቢኖረውም እየተሰራበት አይደለም፡፡ ደህነት በራሱ አንዱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነውና በተለይ እንደ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ያሉ አካላት በነፃ የህግ ድጋፍ በኩል የሚያሳዩት ጅምር መበረታታትና መንግሥታዊ ዕውቅናን ማግኘትም ይኖርበታል ብዬ አምናሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ ተመስርቶ ውጤታማ ስራ እየሰራ ያለውን (Center for Advancemenet of Rights and Democracy-CARD) ማበረታትና እናመሰግናለን ማለትም ይኖርብናል፡፡

ማብቂያ!

ሃገራት የእርስ በእርስ ግንኙነቶቻቸውንም ሆነ ከዜጎቻቸው ጋር የሚኖሯቸውን የተናጠልና የጋራ ግንኙነት በተመለከተ የሚያደርጓቸው ስምምነቶች፣ የሚገቧቸው ውሎችና በረዥም ጊዜ ሂደት ያስለመዷቸውን አሰራሮች እንዲሁም እንደ “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት” አይነቶቹ አለም ዓቀፍ ተቋማት የሚያወጧቸውን የህግ፣ የመርሆና የመግለጫ ሰነዶችን አለም ዓቀፍ ህግጋት አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡ እንደ ሌሎች ሰዋዊ መብቶች ሁሉ ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ መብት ህጋዊ ዕውቅና በመስጠቱና ጥበቃ በማድረጉ በኩል የ-1945-ቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማቋቋሚያና መተዳደሪያ (The ‘UN’ Charter) ቀዳሚው ሲሆን ይኸው ተቋም በጠቅላላ ጉባዔው “ሁሉ ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ” ወይም በእንግሊዝኛ አህፅሮቱ UDHR የሚባለውንና እንደ ምዕራባውያኑ የዘመን ቀመር በዲሴምበር 10, 1948 አጽድቆ ይፋ ያደረገው ባለ 30 አንቀጹ ታሪካዊ ሰነድም ከዚሁ ምድብ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡

ይህ መግለጫ የልማዳዊ አለም ዓቀፍ ህግ (Customary International Law) አካል ሆኖ ሃገራት ላይ የገዢነት ስልጣንና ውጤት ያለው ሲሆን ከሁለቱ የቃልኪዳን ሰነዶች (ICCPR/ICESCR) ጋር በመሆን የመብቶች መሠረት (Bill of Rights) ሆኗልና በሃሳቡ ላይ ለደከሙ ሁሉ ምስጋናችን እንዲደርስ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ይልቁንም የብዙኃን መገናኛዎቻችን ነቅተው ካላነቁ ቀኑን ከማክበርና አበል ከመተሳሰብ የዘለለ ቁም-ነገር ሳንፈይድበት እንዳንቀር ያሰጋልና ቢታሰብበት መልካም ይሆናል፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :