ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማና የአቶ ስዩም መስፍን ቤተሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ኢዜጋ ሪፖርተር

AddisAlem Balema in CourtDecember 10, 2020 (Ezega.com) -- መንግሥት በበርካታ ከባድ ወንጀሎች ውስጥ ተሳትፈዋል በማለት ያለመከሰስ መብታቸውን ካነሳባቸው ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት  ዶ/ር አዲስአለም ባሌማ ዛሬ ሐሙስ ታኅሳስ 01/2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። በዚህም በትግራይ ክልል ውስጥ ከተካሄደው ወታደራዊ ግጭት በኋላ ፍርድ ቤት በመቅረብ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል ዶ/ር አዲስአለም የመጀመሪያው ሆነዋል። በትግራይ ክልልም ሆነ በፌደራል መንግሥት ደረጃ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉትን የአዲስዓለም ባሌማን ጉዳይ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የእስር ትዕዛዝ ከወጣባቸው የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ የነበሩት አዲስዓለም በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት። ፖሊስ ሰውዬውን የጠረጠረበትን የወንጀል ዝርዝር ያቀረበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈፀምና ከባድ የጦር መሳሪያዎች እንዲዘረፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በማይካድራ በንፁሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማመቻቸት እንዲሁም ግለሰቡ አምባሳደር በነበሩበት ዘመን አገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲበላሽና እንዲቋረጥ ተጽዕኖ በማድረግ መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለችሎቱ ማስረዳቱ ተዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም አዲስዓለም ባሌማ ከባድ የመንግሥት መረጃና ምስጢሮችን አሳልፈው በመስጠት እንዲሁም ከኦነግ-ሸኔ አመራሮች ጋር በመገናኘት የተለያዩ የጥፋት ተልእኮዎችን በመስጠት ከዚህ ባለፈም የመንግሥትን ምስጢር አሳልፈው እንደሰጡና ከቡድኑ ጋር ሲሰሩ እንደነበርም ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል። ተጠርጣሪው ዶ/ር አዲስዓለም ከህወሓት አመራሮች ጋር በመተባበር የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም፣ ሁከትና አመጽ እንዲፈጠር የተለያዩ ድርጊቶችን በማስተባበር መጠርጠራቸውም ተነግሯል። ከተጠቀሱት የወንጀል ድርጊቶች በተጨማሪ በርካታ የአፍሪካ ሕብረት ባለስልጣናት ጋር በመሄድ ከህወሃት ጋር በነበረው ጦርነት በመንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ግፊት በማድረግ እንዲሁም ከአንድ የቻይና አምባሳደር ጋር በመገናኘት የቻይና እና የህወሓት ኮሙኒስት ፓርቲ እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ሲጥሩ እንደነበርም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ መግለጹ ተነግሯል። ተጠርጣሪው አዲስዓለም ባሌማ በበኩላቸው የተባሉትን ወንጀሎች አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናገረው "ሰኞ ዕለት ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር በሽምግልና ጉዳይ ስነጋገር ቆይቼ ረቡዕ በቁጥጥር ስር ውያለሁ" በማለት አስረድተዋል።

እርሳቸው ከሌሎች አምባሳደሮችና ከተጠቀሱት ባለስልጣናት ጋር የተነጋገሩት ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት በማሰብ በሽምግልና ጉዳይ ላይ እንደሆነ መግለፃቸውን የፋና ዘገባ አስነብቧል። ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱ በቂ መረጃዎች እንዳሉት ገልጾ ወንጀሉ ሰፋ ያለ በመሆኑ ምርመራውን በሰፋት ለማካሄድ ተጨማሪ 14 ቀናት ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱንም የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ ፈቅዷል። በተመሳሳይም ለረጅም አመታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት የአምባሳደር ስዩም ባለቤትና ልጃቸው በፖሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት መቅረባቸውም ተሰምቷል። ሐሙስ እለት ፍርድ ቤት የቀረቡት የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት የስዩም መስፍን ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ፈለገህይወት በርሔና ልጃቸው አጋዚ ስዩም ሲሆኑ ፖሊስ ግለሰቦቹን በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ጠርጥሮ በቁጥጥር ሰር እንዳዋላቸው ለፍርድ ቤት አስረድቷል። ሁለቱ ግለሰቦች የተጠረጠሩበት ወንጀል በተለይ 'ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም' የሚለውን የሕወሃት እና ኦነግ ሸኔ ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ ብጥብጥ ለመፍጠር ለጸረ ሰላም ሃይሎች ገንዘብ አሰራጭተዋል፣ ወጣቶችንም ለሁከት ዐላማ መልምለዋል የሚል ነው። በተጠርጣሪዎቹ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ላይ ፖሊስ ምርመራ አድርጎ ሁለት ሽጉጦችን ጨምሮ ሌሎች ማስረጃዎችን መያዙንም ለፍርድቤቱ አስታውቋል። ፖሊስ በወንጀል ተግባራቱ ዙሪያ የጀመረውን ምርመራ ለማካሄድም ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ስምንት ቀናት እንደተፈቀደለት ተዘግቧል። የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት መሸጋገሩን ተከትሎ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እንደሚፈለጉ በተ
ገለጹ የቡድኑ አመራሮች ላይ ፖሊስ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ የሚታወስ ነው። ለወታደራዊው ግጭት ምክንያት ከሆነው በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ጨምሮ በበርካታ ከፍተኛ ወንጀሎች ጠርጥሮ መንግሥት እፈልጋቸዋለሁ ካላቸው የህወሓት አመራሮች በተጨማሪ በከፍተኛ ወታደራዊና የፖሊስ መኮንኖችም ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል። ያም ሆኖ አስካሁን በቁጥጥሩ ስር እንደዋሉ በይፋ የተገለጹት ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና አምባሳደር የነበሩት ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ እና የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ናቸው። መንግስት የክልሉ ርእሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት ከፍተኛ አመራሮችን ለመያዝ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆኑኑንም በተደጋጋሚ አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በትግራዩ ጦርነት ስለመሳተፋቸው ማረጋገጫ እንደሌለው  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ድርጅቱ በዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኩል ባስተላለፈው መረጃ በህወሃትና በሌሎች አካላት በተደጋጋሚ የሚነሳውን ውንጀላ መሰርት አድርጎ ባደረገው ማጣራት ድርጊቱ ስለመፈጸሙ ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጿል። "ስለዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ጠበቅ አድርጌ ጠይቄያቸው የኤርትራ ወታደሮች የትግራይን ምድር እንዳልረገጡ አረጋግጠውልኛል" ሲሉም ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናግረዋል። የኤርትራ ወታደሮች በተወሰነ ደረጃ ገቡ ከተባለም የገቡት አወዛጋቢ ወደነበሩት እና ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነቱ መሠረት ለኤርትራ በምትመልሳቸው አካባቢዎች ብቻ መሆኑን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ዶ/ር ዐቢይ እንደተነገራቸውም ጉተሬዝ አክለዋል። ተመድ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ከመንግሥት ጋር የደረሰው የመጀመሪያው ስምምነት ባለመተግበሩም በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታው በጋራ ለመገምገም ሌላ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ዋና ጸሃፊው ጨምረው አረጋግጠዋል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :