በኢትዮጵያና ሱዳን ሃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት አለፈ
ኢዜጋ ሪፖርተር
December 20, 2020 (Ezega.com) -- የኢትዮጵያ ሚሊሻና ወታደሮች ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው ጥቃት ፈጽመዋል ሲል የሱዳን መንግስት ጦር ከሰሰ። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክም ከሀገሪቱ ጦር ጋር ተመሳሳይነት ያለው መግለጫ በማውጣት በጥቃቱ የሰዎች ህይወት ማለፉን እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች በሱዳን ጦር ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሃምዶክ በመግለጫቸው "ሀገራችን ምስራቃዊ ድንበሯን አቋርጠው የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላለች ህዝባችንም በአስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም በሚታወቅ ልግስናው አስተናግዷቸዋል" ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማክሰኞ ታህሣሥ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የሱዳን ወታደሮች በ 'ጃባል አቡጢዩር' አካባቢ ቅኝት አድርገው ሲመለሱ "ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው አድፍጠው በነበሩ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ሚሊሺያዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡ በዚህም ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋት እና የንብረት ጉዳት መድረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው የገለጹት፡፡ እርሳቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጦሩ ጎን መሆኑን እና ድጋፍ እንደሚያደርግም የገለጹ ሲሆን የሱዳን ታጣቂ ኃይሎች የሀገሪቱን ዳር ድንበር የመጠበቅ እና ማንኛውንም ጥቃት የመከላከል አቅም እንዳላቸው እምነታቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ የተከሰተው ግጭት "በስፍራው ባለ የሱዳን መንግሥት መዋቅር ውስጥ በተከሰተ ችግር ምክንያት" ያጋጠመ መሆኑን ገለጿል። በድንበር አካባቢ ስለተከሰተው ጉዳይ በቢቢሲ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ "የተወሰኑ የሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የአርሶ አደሩን ንብረት ለመውሰድ ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት ለመከላከል የተደረገ ክስተት ነው" ሲሉ ግጭቱን ገልፀውታል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ አለመረጋጋት ስለመኖሩ የተለያዩ መረጃዎች ቢወጡም ሁለቱም ሀገራት በይፋ ችግሮች ስለመኖራቸው ሳይገልጹ ቆይተዋል። አምባሳደር ዲና ስለክስተቱ ጨምረው እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ "የአርሶ አደር ማሳ ውስጥ ገብተው አንዳንድ ነገሮችን የመውሰድ፣ ወደ እዚያ የማስፋፋትና ከሕግ አግባብ ውጪ የመሄድ ሁኔታ ስላሳዩ ይህንን ነገር መመለስ ስለሚያስፈልግ እርምጃ ተወስዷል" ብለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። ግጭቱን ተከትሎ የሱዳን መገናኛ ብዙሃን በጥቃቱ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጨምሮ አራት የሱዳን ወታደሮች መሞታቸውን ዘግበዋል።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች የድንበር ጉዳይ አንዱ ነው። የሱዳን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጦሩ ጎን መሆኑን እና ድጋፍ እንደሚያደርግ የዘገቡት መገናኛ ብዙሃኑ የሱዳን ታጣቂ ኃይሎች የአገሪቱን ዳር ድንበር የመጠበቅ እና ማንኛውንም ጥቃት የመከላከል አቅም እንዳለው እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት በጉዳዩ ላይ በመንግሥት ደረጃ ግንኙነት ማድረጋቸውን ገልፀው ግጭቱን "ይህ የሱዳን መንግሥት ፍላጎት አይደለም" ብለዋል። እንደ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ጥቃቱን በፈፀሙት ታጣቂዎች ላይ የሱዳን ሠራዊት እርምጃ እንደሚወስድ የተገለጸ ሲሆን የሱዳን ብሔራዊ ዜና ወኪል የሆነው ሱና መከላከያ ኃይሉ "የሱዳንን ድንበር ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ወታደር እንደሚመደብ" መግለፁን ዘግቧል።
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ የተሳካ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለፁት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይህ ችግር "የሱዳን መንግሥት የታችኛው እርከን ችግር ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት በአጭር ጊዜ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ አመራሮች ለመነጋገር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል። አምባሳደሩ ግጭቱ የተፈጠረው የመንግሥት ትኩረት ሌላ ቦታ ላይ መሆኑን ከግምት በማስገባት ነው ካሉ በኋላ ከዚህ ቀደምም ድንበሩ አካባቢ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያም ወደ ሱዳን እንቅስቃሴ እንደነበር ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር አካባቢዎቻቸው ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ መፍትሄ የሚሰጥ የጋራ የድንበር ኮሚሽን ያላቸው ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባና በካርቱም እተገናኙ ሲመካከሩ መቆየታቸው ይታወቃል።ሱዳን ትሪቡን ረቡዕ ዕለት በሱዳን መከላከያ እና በኢትዮጵያ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደነበር ዘግቦ ግጭቱ የተካሄደው በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ስደተኞችን በሚቀበል ጣብያ አቅራብያ ነበር ብሏል። ግጭቱ በምሥራቅ ሱዳን አል ቀዳሪፍ ግዛት ቁራይሻ መንደር ዋድ አሩድ ከተማ አቅራብያ መከሰቱንም አክሎ ዘግቦ ነበር።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን