በዓለም የፍልስፍና ቀን “ፍልስፍናችን” ቢፈተሽስ? (ማጠናቀቂያ)

Ethiopian Philosophyሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

December 20, 2020

“እንደኔ እምነት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ስድስት ኪሎ ሲሞት
አምስት ኪሎም መጠውለጉ አይቀሬ ነው፡፡”
(ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ)

ጋሽ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) የኔ ዘመን ኢትዮጵያውያን ስለፍልስፍና ያላቸውን አመለካከት እንዲያጠይቁ ካደረጉ ጉምቱ የአደባባይ ምሁራን ውስጥ አንዱና በዚህ ዘርፍ ላይም ቀዳሚው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተከታታይ ቅፆች “ፍልስምና” በሚል ርዕስ የተለያዩ ኢትዮጵያውያንን ምልከታዎች ጨምቆ ከሰጠን ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ በኩል ተነባቢ በነበረችው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ስለፍልስናና በቀደመው ክፍል ስላነሳነው 70/30 የትምህርት ሥርዓተ ፖሊሲያችን ተገቢነት ዙሪያ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ለጥያቄዎቹ ከሰጧቸው ምላሾች ውስጥ ይህንን መግቢያ ላደርገው ፈቀድኩ፡፡

ጋሽ ዳኛቸው ጥያቄውን ሲመልሱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው የስድስት ኪሎ ግቢ ውስጥ የሚሰጡት የማህበራዊና የሥነ-ሰብዕ (Social Sciences and Humanities) የትምህርት ዘርፎች መዳከም በአምስት ኪሎዎቹ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በመጥቀስና ለጥቅስ የሚበቃላቸውን አባባል በማስከተል “ይሄ ጥያቄ ወሳኝ እና ሰፋ ያለ ትንታኔ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ የአንድ ሀገር መንግስታዊ ፖሊሲና የትምህርት ፖሊሲ የተቀራረበ ግንኙነት አላቸው፡፡በመሆኑም ስለኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በምናወራበት ጊዜ ስለመንግሥት ፖሊሲም እያወራን ነው፡፡ሁላችንም እንደምናውቀው ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት “ተቀዳሚ አጀንዳዬ ልማት ነው!” ብሎ ስለተነሳ ማንኛዎቹም ተቋማት የልማት አገልጋይ መሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡” በማለት ማብራሪያቸውን ቀጥለዋል፡፡

ብዙዎች “ዳቦ የማይጋግር ትምህርት” ሲሉ ከሚያሳጧቸው መስኮች የሚመደበው ፍልስፍናንም በተለየ ጠቅሰው “ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልዳበረበት ሀገር “በጀቴን ለሳይንስና ኢንጂነሪንግ ነው የማወጣው” ማለቱ በራሱ ችግር የለውም…… ለሳይንስና ኢንጂነሪንጉ ዘርፍ 70በመቶውን እጅ መስጠቱ ሳይሆን ችግሩ 30በመቶ እጅ የተሰጣቸው ዘርፎች ምንም አገልግሎት አትሰጡም በሚል የተጣበበ መስፈርት እንዲጠወልጉ መደረጋቸው ነው፡፡ አንዲት እናት ከወለደቻቸው አምስት ልጆች ሶስቱን ለይቼ እወዳለሁ ማለት መብቷ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እወዳቸዋለሁ ያለቻቸውን ሶስት ልጆች በአግባቡ እየመገበች ሁለቱን እንዳሻችሁ ካለች ግን ጥያቄው የቁጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱ በህይወት እንዳይኖሩ እያደረገች መሆኑም ጭምር ነው፡፡ በ70/30 ፖሊሲ እየተካሄደ ያለው ሁኔታም ይህን ይመስላል፡፡ የቁጥር ክፍፍሉ ሳይሆን ለሁለቱ ልጆች ምን እየተደረገ ነው? ነው ጥያቄው፡፡” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ሞግተዋል፡፡

የአፍሪካ ፍልስፍና - የኢትዮጵያም ነው!

ፍልስፍና ማለት ያው እውነትን ማፋለግ፤ ሲያጠይቁ መኖር፤ በሚገኘው ምላሽና በምልከታዎችም መደመም እንደመሆኑ ፍልስፍናን የሚሰጉት ቀኖናዊ አቋም በመያዝ ማህበሩ እንዳይናወጥ ይልቁንም አይነኬ (Taboo) የሚሏቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በተጠየቅና አመክንዮን በመሳሰሉ አቀራረቦች የታሸ መሆኑ እውቀቱን እምነትና ተለምዶ ላይ ላደረገ ሥርዓተ ማህበር መክበዱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሆኖም ፍልስፍና ነባር ማህበረሰባዊ ችግሮችንና የተሳሳቱ ምልከታዎቻችንን ያልፈታበት አንዱ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው ዘርፉ አለመበርታቱና አይነኬነታቸውን የደመደምንላቸው ርዕሰ ጉዳዮች መበርከት ነው፡፡

በቀደመው ክፍል ስለ “አፍሪካ ፍልስፍና” አንስተን ህልውናውንና ጥንታዊው የኢትዮጵያ ፍልስፍናም የዚሁ ክፍል አንድ አካል ስለመሆኑ ጠቅሰናል፡፡ በእርግጥ በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የምዕራብ አፍሪካው ክፍል ቢሆንም በአገራችን እንደ ትግራይና አማራ ያሉት የግዕዝና የአማርኛ “ቅኔዎች” በቀሪው የአገራን ክፍሎችም በትረካና ተረክ መልኩ ቃላዊ መሆናቸውና ያለምንም ማጠየቅ ከአባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን መቀባበሉም ሌላው መለያቸው ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦች ሁሉ ተያይዘው የሚመሩን ወደ “አገር በቀል ዕውቀት” ሲሆን በዘመናዊ እሳቤዎች መዳበርና ትምህርቱም መሰጠት መጀመሩን ተከትሎ በ-19ኛው ክፍለ ዘመን መጠነኛ ለውጦች ተስተውለዋል፡፡

በቀደመው ክፍል እንዳወሳነው ጥንታዊውን የአፍሪካ ሥልጣኔ (የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትን የሚጨምሩ ፀሃፊዎችም አሉ) የመመርመር ጅማሮ (African Philosophy in Search of Identity) መነሾም ይኸው ባለሁለት ስለትነት ነው፡፡ በአንድ በኩል ሌላው ዓለም ስለአፍሪካ ፍልስፍና የተረዳውን ማጠየቅ በሌላኛው ደግሞ የእኛ የምንለውን አገር በቀል ዕውቀት ማስተዋወቅ፡፡ ከአፍሪካ ፍልስፍናዎችና ፈላስፋዎችም ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ሲወሳ ቀድመን የምናስታውሰው ከሃምሳ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በኢትዮጵያ የኖሩትን ሰው፣ ካናዳዊውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ፕሮፌሰር ክላውድ ሳምነርን ነው፡፡

እኚህ ጉምቱ ምሁር የኢትዮጵያን ፍልስፍና ከነቋንቋዎቹ አጥንተዋል ብቻ ሳይሆን “Classical Ethiopian Philosophy” እና “Ethiopian Philosophy” በመሳሰሉ ጥራዞች ሰኝተው ለእኛም ለአፍሪካና ለዓለምም አስተዋውቀውታል፡፡ ይልቁንም በተለምዶ “ሐተታ” የምንለውን ተጠይቃዊ ተዋስዖ እንዳስተዋወቁ የተፃፈላቸውን የዘርዓ ያዕቆብ (ወርቄ) እና የደቀ-መዝሙሩንና የሐተታ ፀሃፊውን የወልደ ህይወትን ስራዎች በደንብ ሄደውባቸዋል፡፡ እኚህ ግለሰብን ብዙዎች የሚያውቋቸው ቆየት ባሉትና በደምሳሳው የሰው ልጆች ፍልስፍና “The Philosophy of Man” በተሰኙት ስራዎቻቸው በኩል ይመስለኛል፡፡

በአህጉሪቱ ፍልስፍና ይሉት ነገር እንደሌለ ጥቂት ንቀትና ያልበዛ ዘረኝነትን ቀላቅለው ለነገሩን የአውሮጳና አሜሪካ ሰዎች (ኢንሳይክሎፒዲያዎቻቸውም አይጠቅሱትም!) መልስ የሆኑ አፍሪካዊ ስራዎችን ያዘጋጁት ሳምነርም በአውሮጳዊው ዕውቅ አሳቢ በርትራንድ ራስል “The Western Philosophy” በሚለው ድርሳኑ ላይ ባሰፈረው መመዘኛ መሠረት “ፍልስፍና ሲጠና ፈላስፋው ከኖረበት ዘመንና የማህበሩን አጠቃላይ ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ መሆን አለበት፡፡” የሚለውን በመያዝ ሲሆን የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ጥናት መነሾ ይኸው መሆን እንደሚገባው ሞግተዋል - ተሳክቶላቸውማል፡፡

ሳምነር እና የኢትዮጵያ ፍልስፍና….

ስለኢትዮጵያ ፍልስና ሲነሳ ብዙዎች ቀድመን የምናነሳው ስም “ዘርዓ ያዕቆብ” ነው፡፡ እንዲያውም በልደቱ ቦታ ሁሉ እየተጨቃጨቅን ወደ ብሔር ቋት ልንከተው የምንታገል ሰሜነኞችም ተስተውለናል፡፡ ፍልስፍና በባህሪው የማይጠረቃ የምርመራ ዘርፍ ነውና እንኳንስ ወደብሔር ሊጎተት ዓለማቀፍ ዜግነትም የማይገዛው ስለሆነ ይህ አያሰጋንም፡፡ ፈላስፋው ኢትዮጵያዊ ሊሆን ቢችልም የፍልስፍናው መጥቀምና መጉዳት፤ የርዕዮተ ዓለሙ ንፍገትና ትሩፋት ለሰው ልጆች ሁሉ ነውና፡፡ ምንም እንኳን እንደታሪካችን ሁሉ በደምሳሳው “የኢትዮጵያ” የምንለው ፍልስፍና በራሱ በአጥጋቢነት ያልተፈተሸና በየሃይማኖታቱ እንዲሁም ባህላቱ ውስጥ ያሉት የአገረ-ሰብዕ ዕውቀቶች ያልተመረመሩ ቢሆንም ምልከታው በመኖሩ ይህንኑ ስያሜ የምንሰጠው ነው፡፡

ለአብነትም ክላውድ ሰምነር ሐተታ ዘርዐያዕቆብን ሲያነሱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የምናገኘውን “የአ(እ)ንድምታ” አተረጓጎም አብረው ያወሳሉ፡፡ ይህንን የአተረጓጎም መንገድ ያስተዋወቀው እርሱ ነው ባዮችም አሉ፡፡ የትርጉም ስራዎችንና ከላይ የጠቀስናቸውን የ17ኛው መቶ ክ/ዘመን ዘርዐያዕቆብ ወወልደ ህይወት ሐተታትም እንዲሁ፡፡ በዚህ ረገድ እኚህ የፍልስፍናችን ባለውለታ ወደፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ መተርጎማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከግዕዝ ወደ እንሊዝኛ በአቶ አበበ ረታ ተተርጉሞ እንደነበረ ቢገለፅም አለቃ ያሬድ ፈንታ ወ/ዩሐንስ፣ ዳንዔል ወርቁ እንዲሁም ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ደግሞ በተለያየ ጊዜ እኚህን ሐተታዎች ከግዕዝ ወደ አማርኛ መልሰዋቸዋል - እናመሰግናለን!

በሌላ በኩል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ፊሎሎጂ ጥናት ማዕከል መመህሩ ሐጎስ አብርሃ (ዶ/ር) ሐተታዎቹን “ፍልስፍና ዘርዐ ያዕቆብን ወልደ ሕይወትን” ብለው ወደ ትግርኛ ቋንቋ መልሰዋቸዋልና ልታነቧቸው ትችላላችሁ - የቅነለይ!

እዚሁ ላይ ሳለን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተለያዩ ዕትሞች ፍልስፍናን እያዋዛ ሲፅፍ የምናውቀው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር ብሩህ ዓለምነህ ሐተታዎቹን ከማብራሪያቸው ጋር ቀለል ብሎ ዳጎስ ባለ የመማሪያ መፅሃፍ መልኩ እንዳቀበለንም ሳንዘነጋ ነው - ገለቶማ!

በተለምዷዊ ቅብብል “ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ” የምንላቸው በክርስትና ስሙ “ዘርዐያዕቆብ” እና ስለውዴታው ሐተታ የፃፈለት ደቀመዝሙሩ ወልደህይወት ዘእንፍራንዝ (ምትኩ) ህልውና እውነትነት ሲያጠያይቅ ኖሯል፡፡ የኢጣሊያ ዕውቅ ፀሐፍት የሆኑት እነ ኮንቴ ሮሲኒ ይህንን ክደው በመከራከር የአንድ ሚሲዮናዊ የጣሊያን ሰው (ጃካቦ) ድርሰት ያደርጉታል፡፡ ቄስ ዐለማየሁ ሞገስ በበኩላቸው በሙሉ ልብ ሲቀበሉት አነስተኛ ጥራዝ ያላትን ትችቱን ወደ አማርኛ ያስተዋወቁት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም ምንም እንኳን በአንድ በኩል የበጌምድር ሰው እያደረጉ በሌላኛው ደግሞ ፈላስፋው የአክሱም ሰው መሆኑን እንደሚቀበሉ ቢናገሩና ቢፅፉበትም ከአንድ አደጋ መትረፉን ተከትሎ የፈጣሪን ህልውና በተመለከተ ከራሱ ጋር የተሟገተበትን መንገድ “ካቶሊካዊ” ሰኝተው የእርሱ ስለመሆኑ ሲጠራጠሩ እናነባቸዋለን፡፡

በእርግጥ አማርኛውን አልያም እንግሊዝኛውን ያነበብን ሰዎች እንደግዕዝ አዋቂዎቹ ምሉዕ መንፈሱን ባንቃመሰውም ተጠራጣሪነቱን፣ ጠያቂነቱንና ለፍርድ አለመቸኮሉን ስናስተውል “ፍልስፍና” የሚለው ቃል ትርጉም እዚያው መኖሩን መረዳት አያዳግተንም ብዬ አምናለሁ፡፡ የፍልስፍና ሌላው አገባብ ስለአንድ ነገር በተደጋጋሚ ማሰብና ያንኑ መመርመር ነውና፡፡ በማስተማር ዘዬው “ኢትዮጵያዊው ሶቅራጠስ” ልንለው እንደምንችልና ሳይመረምሩ ማመንንም ፣ ሁሉንም መርምረን ሰናዩን እንድናፀና፣ በነገረን የቅዱስ መፅሐፍ ጥቅስ በኩል የሚያሳልፈንን የሰሰንዮስ ተሳዳጅ ህልውና በተመለከተ ሙግቱ ያላለቀ፣ ምርመራውም ያላበቃ ቢሆንም ከዘመኑ ከፊሉን በዋሻ መኖሩ ግን ያሳምነናል፡፡ ፈላስፋው “ሂሩት” የምትባል ፉንጋ በእርሱ አገላለፅ ፣ውብ ያልሆነች ሴት በጉዱ-ካሳዊ አይነት የሥርዓተ-ፆታ ትችት ጅማሮ አግብቶም አባት መሆኑን የነገረንን አንዘነጋም፡፡ ስለፈጣሪና ስለሰው ልጆች ባህርያትና ስለነፃ ፈቃድ ትችቱና እምነቱም አብሮን አለ፡፡ እውነት ማለት ከህሊና ያልተጣላና ከልቦናም የተስማማ ነገር ነውና መፃህፍቱን ይጠራጠራቸዋል፡፡ ትርጉሞቹንና የሃይማኖታቱን ሰዎችም እንዲሁ ለማመን ይቸገራል፡፡

የኢትዮጵያ ፍልስፍና…. ምርት እና ግርድ!

የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ስለ ዘርዐያዕቆብም ሆነ ስለወልደ ህይወት ማተት አይደለምና ከላይ የያዝነውን ይዘን የእኛ የኢትዮጵያውያኑ ፍልስፍና ከአፍሪካ መለየቱን የሚነግሩንን ሰዎችም ሆነ ሴማዊነት የተጫነው ስለመሆኑ የሚገልፁትን እያስታወስን ከእውነት፣ ከመልካምና መጥፎነት፣ ከተፈጥሮና ውበት፤ ከህይወት ዓላማም ሆነ እርሱ ከመረመራቸው ከሃይማኖታቱ (አይሁድ፤ ክርስትና እና እስልምና) አስተምህሮዎች ባሻገር ያዳበርናቸውን አመለካከቶች (ፍልስፍናዎች) ብንዳስስ ጦርነት፤ መገፋፋትና መገዳደል፤ በጊዜ ብክነት፣ ቁሳዊ ኑሮን የጠላና ከሀብት የተጣላ ምናኔ፤ የስራ ባህል ስኑፍነት ብንመለከት ከመሰረቱ የተበላሸ ነገር መኖሩን መረዳት አይከብደንም፡፡

እንዲያውም የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው መምህር ብሩህ ዓለምነህ (በዶ/ር ዳኛቸው በኩል) ይህንን ሲገልፀው ቅዱሳን መፃህፍቱን ባልተገባ መንገድ ተርጉመን “ከመሮጥ ማንጋጠጥ!” ምርጫችን ሆኖ መቅረቱን ሲገልፅ እናነበዋለን፡፡ በዚሁ “አትሩጥ አንጋጥ!” ሃሳብ ላይ የኩሩውን ፕሮፌሰር የመስፍን ወ/ማርያም ችጋር ተኮር ምርምርን መደመር ይቻልል፡፡ ግሪክን መነሻው ያደረገው የምዕራባውያኑ ፍልስፍና “ዘመነ አብርሆት” ይሉትን (Enlightment) ጊዜ በቅርብ ርቀት አስከትሎ ማህበራዊ ለውጥን፤ ፖለቲካዊ ዝማኔን ከምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ጋር ቢያበረክትም የእኛ ፍልስፍና ሊቀይረው ያልቻለው ነገር ብዙ ነው፡፡

በተለይ እንደ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ ሀዲስ አለማየሁና እኒህን የመሳሰሉት ተራማጅ ምሁራን በሥርዓተ ማህበራችን ላይ አንስተውት የነበረው ማህበራዊ ትችት አለመቀጠሉ የራሱን አሉታዊ ውጤት እንዳመጣ አምናለሁ፡፡ ይልቁንም አሁን የገባንበትን የወገን ጦርነት ያልተገረዘው የውጊያ ናፋቂነት ባህላችን የወለደው ስለመሆኑ ከዘመኔ ፍልሱፍ በዕውቀቱ ስዩም ስራዎች በእነ “ጦር አውርድ”! በኩል አንብቦ መረዳቱ አያዳግትም፡፡ ገዳይ ባል ሟች ደግሞ የሚስት ወንድም ሆኖ የመቸገራችንን ሥነ-ቃል እውነታነት ይዘን ስንቀጥል “በዘመናት መካከል” በሃሳብ የተረማመደው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራር አባሉ አቶ አንዱዓለም አራጌ የሥነ-ምግባር ፍልስፍናችንን ሲያጠይቅ ገዳይን የሚያጀግን ባህል መገንባታችን ገና ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሲገልፅ ካቀረባቸው በሥነ-ቃል የተለወሱ ብሂሎቻችን “ገዳይ እወዳለሁ!” ማለትን በመያዝና በአንፃሩም ገበሬነትንና መሰል ትጉህ ሰራተኝነትን የሚያበሻቅጡ ስለመሆናቸው ይህንን ማሳያ ያደርግልናል፡-

“ገዳይ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል፤
ገዳይ ገዳይ ያልሽው ወንድምሽ አይገድል፤
አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል፡፡”

በእርግጥ ዘርዐያዕቆብን በተመለከተ ዲ/ን ዳንዔል ክብረት “የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ” በሚል ርዕስ በተከታታይ ስድስት ክፍሎች “ወርቄ” የሚለው ስያሜ በአማራ እንጂ በትግራይ አለመለመዱን ከመጥቀስ ጀምሮ ምልከታውን በሰፊው ያቀረበና ይህንኑ ዐብይ ርዕሱ አድርጎ “እና ሎሎችን” በመቀፀል የዘርዐያዕቆብን ማንነት የፈተሸ ስራውን በወጎች ስብስብ መፅሃፍ መልክም የሰጠን ሲሆን ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ በበኩሉ “የሌለውን ሳይሆን የጠፋውን ፈላስፋ ፍለጋ ነው የያዝነው” ሲል ምላሹን አስነብቦ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የፍልስፍና ታሪክ ተዋስዖ ውስጥ ሊነበቡ ከሚገባቸው ሙግቶች አንዱ ይህ የዲ/ን ዳንዔል ፅሁፍ ነውና አንባብያን እንዲያፋልጉትና በንባብ ከጎበዙ ደግሞ በምንጭነት የጠቀሳቸውን ጥናቶችና መፃህፍትንም እንዲያነብቧቸው እጠቁማለሁ፡፡

መጀመር እና መጨረስ….

መግቢያችን ላይ በዘርዐያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋነት የሚያምኑትን ጋሽ ዳኛቸውን ጠቅሰን የሥርዓተ-ትምህርታችንን ነካክተናል፡፡ የፍልስፍና ትምህርት በዓለምም ሆነ በአገር ደረጃ ከቀዳሚዎቹ ረድፈኞች ቢሆንም “የሚጨበጥ ቁሳዊ ነገር የለውም!” በሚለው ስሁት ምልከታችን ሳቢያ ባለበት እንዲረግጥ ሆኗል፡፡ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካዳሚያዊ ቅርፅ ቢይዝም የ70/30 ማህበራዊ የትምህርት ዘርፎች ላይ መነሳሳት ከትምህርት ሥርዓት ያለፈ ሃሳብን የመግደል ዓላማ ነበረው የምንለውም በአመክንዮ እንጂ በዘፈቀደ እንዳልነበር አሁን ያለንበት የሃሳብና አሳቢያን ንጥፈት በቂ ማሳያ ነው፡፡

ለጊዜው ተከታዮቹን ሰዎቻችንን ስለእነዚህ መፃህፍት ስጦታዎቻቸው እያመሰገንን እንሰነባበት፡፡ ከትምህርቱ ዘርፍ ሳንርቅ የአገራችን የትምህርት ሥርዓት መርጦ ሊጠቀምበት ቢሰንፍም “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ምንነቱን ላስተዋወቁን እጓለ ገ/ዩሐንስ ምስጋናችን ብዙ ነው፡፡ ከዓረብኛ ወደ ግዕዝና አማርኛ ከተመለሱ መፃህፍት ውስጥም “መፅሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን” እና የተለያዩ ፈላስፎችን አመለካከትና ንግግር ያቀበለንን “አንጋረ ፈላስፋ” ደራሲ አባ ሚካዔል እንዲሁም የሥነ-ልቦሎጂ ድርሰት ስለሆነው “መፅሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” አለቃን እያመሰገንን ሌሎች በጊዜያዊ ዝንጋዔ ያልጠቀስናቸው እንደሚኖሩም ይታወቅልኝ፡፡

በቀደመው ክፍል ስለ “አፍሪካ ፍልስፍና” አንስተን ህልውናውንና ጥንታዊው የኢትዮጵያ ፍልስፍናም የዚሁ ክፍል አንድ አካል ስለመሆኑ ጠቅሰናል፡፡ በእርግጥ በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው የምዕራብ አፍሪካው ክፍል ቢሆንና እኛ ኢትዮጵያውያኑም አፍሪካዊነትን በአንድ በኩል እየተጠየፍነው በሌላኛው በኩል “Pan-Africanism” እያልን ብንኩራራበትም በጠቅላላው ማመሳሰያ ባህልና እሴቶች ላይ ማተኮራቸው አፍሪካዊ ፍልስፍናዎችን ለአንድ አይነትነት ቅርብ ያደርጋቸዋል፡፡

ይልቁንም የምህረት ደበበን (ዶ/ር) “የተቆለፈበት ቁልፍ” ልብ-ወለድ ድርሰት አልያም አንድ ወቅት ላይ እንደተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ ብሎ ያየነውን የሰርቅ ዳንዔል “ቆንጆዎቹ” ገፀ ባህሪያት ከመፃህፍቱ መመልከት ላልቻለ ሰው ከሰሞኑ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የነበረ የዘረኝነት ጉዳችንን ማስተዋል ያቅተው አይመስለኝም፡፡ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በወፍራም የደም-ወዝ የሚሰሩ አንድ ኢትዮጵያዊ አምባሳደር “ፀሐይ አጥቁሮን እንጂ እኛ አፍሪካዊ አይደለንም!” ሲሉ በድፍረት የተናገሩትን መታዘብ በጣም አሳዛኝ ይሆናል፡፡

ለዚህ በአፍሪካዊነታችን አለመኩራት ይልቁንም በ “ኢትዮጵያኒስትነት” ሽፋን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመዲናው ታቅፎ ከተማይቱንም የአፍሪካ መሆኗን አውጆ “አፍሪካዊነትን” በቆዳ ቀለም ሰፍቶ በንቀት ማራቅ ለማሳያነትም ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡ ከስድሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተቀነቀነው የተማሪዎች ጥያቄና “ኢትዮጵያዊው ማን ነው?” አንዱ ዘርፍ “ሰው ነኝ!” እያለ የሚፎክረውን የኦባንግ ሜቶ አካባቢ ሰዎች “እንደ ኢትዮጵያዊ” እንኳን ለመቁጠር የሚቸገር “ሥርዓተ ማህበር” ስለገነባን ይመስለኛል፡፡ “አሻም ቴሌቪዥን” በዚህ ፍኖት ላይ ከፀና ለምልከታችን መቃናት ሚናው የጎላ እንደሚሆን አምናለሁና ስለአዲሱ ፍኖታቸው እያመሰገንኳቸው እንዲበረቱበትም በመጠቆም እሰናበታችኋለሁ፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን! -

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :