ልጄ በምን ምክኒያት እንደታሰረች ማወቅ አልቻልኩም - ወ/ሮ አዜብ መስፍን

ኢዜጋ ሪፖርተር

Semhal MelesDecember 22, 2020 (Ezega.com) --- የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሴት ልጅ ሰምሃል መለስ መቀሌ ከተማ ውስጥ ተይዛ እንደታሰረች እናቷ ወይዘሮ አዜብ መሰፍን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ያም ሆኖ ልጃቸው ሰምሃል በምን ምክንያት ለእስር እንደተዳረገች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ወ/ሮ አዜብ ለቢቢሲ ተናገረው ወደ መቀለ የሄደችው ወታደራዊ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል። አዲስ አበባ የሚገኙት ወ/ሮ አዜብ እንደሚሉት ከሆነ ሰምሃል ወደ መቀለ ያቀናችው በአባቷ የህይወት ታሪክ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ ላይ ተንተርሶ የተዘጋጀን ቲያትር ለማስመረቅ ሲሆን አካሄዷም በርካታ ሰዎች ካሉበት ቡድን ጋር በመጣመር ነው ብለዋል። ሰምሃል "የፖለቲካ አቋም ሊኖራት ይችላል ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ አመራርም፣ አባልም፣ ደጋፊም አልነበረችም" የሚሉት እናቷ ወ/ሮ አዜብ መስፍን የልጃቸው እስር ምክንያት ምን እንደሆነ እንደማያውቁ ነው ለቢቢሲ የተናገሩት። ወ/ሮ አዜብ ከቀናት በፊት ልጃቸው ሰምሃል እየተፈለገች እንደሆነ በመስማታቸው አርብ ዕለት ወደ መቀሌ ለመሄድ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ፈቃድ ባለማግኘታቸው እንደቀሩና እሁድ ዕለት በቁጥጥር ሰር እንደዋለች እንደሰሙ ነው የተናገሩት።

ሰምሃል በየትኛው አካል እንደተያዘችና ምክንያቱ ምን እንደሆነ "ከአንዳንድ አካላት" ለማወቅ ጥረት ማድረጋቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ አዜብ ነገር ግን ምላሽ ለማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል። እርሳቸው አንዳንድ አካላት ያሏቸውና መረጃ ሊሰጧቸው ፈቃደኛ አልሆኑም የተባሉት በትክክል እነማን እንደሆኑ ግን በዘገባው ውስጥ አልተካተተም። ከሰምሃል መለስ በተጨማሪ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት የጀነራል ኃየሎም አርአያ ልጅ የሆነው ብርሐነመስቀል ኃየሎምም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል። ቢቢሲ ሰምሃል መለስ በቁጥጥር ስር ስለዋለችበት ምክንያት ለማወቅ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አወል ሱልጣን እና የፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄይላን አብዲ ምላሽ ጠይቆ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እንደነገሩት አስነብቧል።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን አንድነትና መረጋጋት ለማረጋገጥ የወሰደው እርምጃ ቆራጥነት የተሞላበት ነው ሲሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ተናገሩ። ሊቀመንበሩ ይህንን የተናገሩት ትናንት እሁድ ጂቡቲ ውስጥ በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 38ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው። የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የወሰደው እርምጃ "የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስከበር" መሆኑን ጠቅሰው ይህም ሁሉም አገራት የሚጠበቅባቸው ሕጋዊ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል። ሙሳ ፋኪ እንዳሉት በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ከፍተኛ መጠን ያለው ህዝብ መፈናቀሉን ገልጸው በዚህ ረገድ ኢጋድ ለስደተኞችና ለተፈናቀሉ ሰዎች የተለየ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከምታደርገው የሰብአዊ ድጋፍ ጥረት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ኮሚሽነሩ ከዚህ በፊት የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ወደ ድርድር እንዲመጡና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የኢጋድ አባል አገራት ከአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር በተጨማሪ ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፋቸውን መግለጻቸው ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የአገራቱ መሪዎች "የሕግ ማስከበር እርምጃዎቻችንን ሕጋዊነት በመረዳታቸውና እውቅና በመስጠታቸው እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን በመግለጻቸው" ምስጋና አቅርበዋል። በጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት ላይ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ከኢትዮጵያ አልፎ በአካባቢው አገራት ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ሲነገር የነበረ ሲሆን፤ የኢጋድ አባላት ጉዳዩን አንስተው መወያየታቸው ተነግሯል። የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ባካሄደው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባው ላይ በአባል አገራቱ ውስጥና በአገራት መካከል ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር አፋጣኝ እርምጃ በሚያስፈልጋቸው ላይ ውሳኔዎችን ሰጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ፣ ከኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሞሐመድ ፋርማጆ፣ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም ጅቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ጋር ተወያይተዋል። መሪዎቹ በአባል አገራት ውስጥ እንዲሁም በአንዳንድ አገራት መካከል ስላሉ ጉዳዮች አንስተው መወያየታቸው ተገልጿል።

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :