በመተከል በተፈፀመ ዘር-ተኮር ጥቃት ከ90 በላይ ዜጎች ተገደሉ
ኢዜጋ ሪፖርተር
December 23, 2020 (Ezega.com) -- በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ በተባለ ቀበሌ ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት ከ90 በላይ ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን በርካታ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የጀርመን ድምጽ ራዲዮ፣ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅትና ቢቢሲ ከአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች አገኘነው ባሉት መረጃ መሰረት ዜጎቹ የተገደሉት ከባድ መሳሪያ ጭምር በታጠቁ ተዋጊዎች ሲሆን በቀስትና በሌሎች መሳሪያዎች የተገደሉና የቆሰሉ በርካቶች መሆናቸውንም አስነብበዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የቡለን ወረዳ ነዋሪ ጥቃቱ ትናንት ሌሊት 11 ሰዓት አካባቢ መፈፀም እንደጀመረ ገልፀው እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ ነበር ብለዋል። በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ለቅሶ ላይ መሆናቸውን የገለፁት እኝህ ነዋሪ "እስካሁን 100 አስክሬኖች ተገኝተዋል የጠፉ አስክሬኖችም አሉ ወደ ቡለንም 70 አስክሬኖች መጥተው ተመልክቻለሁ" ማለታቸው ተዘግቧል። በጥቃቱ የጓደኛቸው አባት መገደላቸውን የተናገሩት ነዋሪው "ቤት እየጠበቀ እያለ ነው ተኩሰው የገደሉት እርሱ መሳሪያ ቢኖረውም እነርሱ ብዙ ስለነበሩ መከላከል አልቻለም ነበር" ሲሉ የተገደሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል። ሌላ ነዋሪ ደግሞ "ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነው ታጣቂዎች ወደ በኩይ ቀበሌ የገቡት" ይላሉ። ጥቃቱ በከባድ መሳሪያ በታገዘ ጭምር መፈፀሙን የገለፁት ነዋሪው እስካሁን ድረስ ከ96 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና 28 ቤቶችና የእህል ክምሮች መቃጣላቸውን አስረድተዋል። ነዋሪው አክለውም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቡለን ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን በስፍራው ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። "አስክሬኖች በሸራ ተጠቅለው በየሜዳው ወድቀው ነው ያሉት ገና ጫካ ያለው አልተሰበሰበም ቡለን የመጡት ቁስለኞችም ከ20 በላይ ይሆናሉ። ሆስፒታል ሄጀ በዐይኔ ነው ያየኋቸው ሆዳቸው የተቀደደ ሁሉ አሉ" በማለትም ጥቃቱ በስለት በመሳሪያም በቀስትም መፈፀሙንና በዐይናቸው 96 አስክሬኖች መመልከታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል ተብሏል።
ለዶይቸ ቬለ ምስክርነታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በጥቃቱ ከ90 ሰዎች በላይ ሲገደሉ ከሀምሳ በላይ የሚሆኑ መኖርያ ቤቶችም መቃጠላቸውን ገልጸዋል። ዛሬ ሲነጋጋ አሰራ አንድ ሰዓት አካባቢ ተጎጂዎች ተኝተው ባሉበት ቤታቸው ከውጭ እየተዘጋ እንዲቃጠልባቸው እና ሌሎች ደግሞ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ መገደላቸውን ከአካባቢው መስማታቸውን አንድ የቡለን ወረዳ ነዋሪ ተናግረዋል። በጥቃቱም ሕጻናትን ጨምሮ 96 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረም ገልጸዋል። "በዓይኔ እንኳ አላየሁም ቢያንስ ጥዋት 11 ሰዓት አካባቢ ሰዎች ተኝተው ባለበት ሰዓት ቡለን ወረዳ በኪጂ በምትባል ቀበሌ ማኅበረሰቡ በድንገት ታፍኖ ብዙ ጥቃቶች ደርሷል። ሰዎች ሳር ቤት ውስጥ በተኙበት በራቸው ከውጭ እየተቆለፈ ሕጻናት፣ እናቶች እና ብዙዎች ሞተዋል። እስካሁን ባይረጋገጥም እስከ 96 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ መረጃዎች አሉን" ሲሉም ተናግረዋል። በመተከል ዞን የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ እና መምህር እንደሆኑ የገለጹ ሌላ ምስክር ደግሞ የጥቃቱ ሰለባዎችን ቁጥር 106 ያደርሱታል። "በመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ ነው ያለሁት። በአንድ ወረዳ ከ106 በላይ ሰው ነው የታረደው እና የተገደለው። እና በጣም ዘግናኝ እና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ድርጊት ነው የተፈጸመው። በተጨማሪም ከ50 በላይ ቤቶችም ተቃጥለዋል። በዚህ ድርጊት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ 96 ሰዎች ነበር አሁን እየተፈተሸ እየተፈተሸ ሄዶ ወደ 106 ሰዎች ደርሷል።" ብለዋል። ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅትም የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ ሌሎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአቅራቢያ እንዳልነበሩ እና ዘግይተው መድረሳቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ በስፍራው የነበሩና ከጥቃቱ የተረፉ ሌላ ግለሰብ ምስክርነታቸውን ለአብመድ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡ ግለሰቡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ጀምሮ በአካባቢው ተሸከርካሪዎች ሲመላለሱ መስማታቸውንና ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ደግሞ ጥቃት አድራሾቹ ተኩስ በመክፈት ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ከባድ መሳሪያ ጭምር የታጠቁ መሆናቸውንና በጥቃቱም በርካታ ንጹኃን መገደላቸውን እንዲሁም ቤትና ንብረትም በእሳት መጋየቱን ነው ምስክሩ የጠቀሱት፡፡ "ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ የጸጥታ ኃይል ቢደርስም ጭፍጨፋውን ማስቆም አልቻለም" ያሉት ነዋሪው ከጭፍጨፋው የተረፉ ሰዎች እሳቸውን ጨምሮ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንደወጡ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ከሰሞኑ በጸጥታ አካላት በተደረገ ስብሰባ ዘርን የለየ ውይይት ሲደረግ እንደነበርም ገልጸዋል ሲል አብመድ አስነብቧል፡፡ "የምናደርገው ጠፍቶን ነው እንጂ ብሔር ተለይቶ የሚደረገው ስብሰባ አልጣመንም ነበር" ያሉት ምስክሩ በእዚህም የተነሳ የአካባቢው ሰዎች ቀደም ብሎም ስጋት እንደነበረባቸው አመላክተዋል፡፡ አብመድ የአካባቢው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌው በየነን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ስልክ ቢደውልም "መረጃ ሲኖረን እንሰጣለን ከሌለን ከየት እንሰጣችኋለን?” በማለት መልሰዋል ብሏል፡፡ "መግለጫ የሚሠጠው ኮማንድ ፖስቱ የተሟላ መረጃ ሲኖረው ነው" ያሉት ኮሎኔል አያሌው ወደ አካባቢው ኃይል መላኩን አመላክተዋል፡፡ "ግድያ መኖሩን አውቃለሁ" ከማለት ውጪ ግን "እነማን ድርጊቱን እንደፈጸሙት፤ ምን ያህል ሰው እንደተጎዳም እውቅና የለኝም" ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ "ችግር ያለ መሆኑን ሕዝቡም ያውቃል እኛም እናውቃለን ግን ደግሞ ኮማንድ ፖስቱ እየሠራ ነው ነገር ግን ካለው ችግር ስፋት አንጻር ችግሩን ለመቆጣጠር ጊዜ ወስዶብናል የደረሰ ጉዳትም ካለ ለሕዝቡ እንገልጻለን" በማለት መልሰዋል የተባሉት ሃላፊው ከሰሞኑ "ዘርን የለየ ውይይት ሲደረግ ነበር" በሚል የተነሳውን ሀሳብ ግን አስተባብለዋል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱ በበኩላቸው ጥቃቱ ስለመፈፀሙ መረጃው እንደሌላቸው የተናገሩ ሲሆን የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ግን ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጠው የሟቾች ቁጥር እስካሁን ድረስ ባይታወቅም "በጣም ከፍተኛ መሆኑን" ለቢቢሲ አረጋግጠዋል ተብሏል። በአካባቢው የመከላከያ፣ የፌደራል፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ተሰማርቶ ሰላም የማስከበር ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተገኝተው ከመተከል ዞን ነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካባቢውን ወደ ሠላም የመመለሱ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ መናገራቸው ተዘግቦ ነበር። ሆኖም ቅሬታቸውን ለቢቢሲ ያስረዱ ነዋሪ ግን "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወያዩት ችግሩ በሌለበት አካባቢ ነው። ችግሩ ያለው ዲባጤ ቡለንን ጨምሮ በሦስት ወረዳዎች ነው። ከሦስቱ ወረዳዎች የተወከለና ሁኔታውን የሚያስረዳ ሰው እንኳን በውይይቱ አልተወከለም፤ ተወካዮች እንዳይሄዱም በክልሉ መንግሥት ተፅዕኖ ተደርጓል" ሲሉ ገልፀዋል።
በመተከል የቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ እና ስማቸው ለደህንነታቸው ሲባል እንዳይገለፅ የጠየቁ ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ወደ ሆስፒታላቸው ከቀኑ አምስት ሰዓት ጀምሮ በጥይት ተመትተው የቆሰሉ ሰዎች የመጡ ሲሆን ብዛታቸው እስከ አርባ ይደርሳል ብለዋል። በጥይት፣ በስለት እና በቀስት ተመትተው ወደ ቡለን ሆስፒታሉ ከመጡ ተጎጂዎች መካከል ከባድ ጉዳት ያስተናገዱ እንደሚገኙበት አክለው ገልፀዋል። ግለሰቦቹ በጥይት እንዲሁም በቀስት መመታታቸውን የሚናገሩት እኚህ የጤና ባለሙያ ሆስፒታል ከደረሱት መካከል አንዲት ታዳጊ ሕጻን መሞቷን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል ተብሏል። ግጭት በተከሰተበት አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ወደ ሆስፒታል ከመጡ ሰዎች መስማታቸውን የገለፁት እኚህ የሕክምና ባለሙያ፣ ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የመጡት ተከብበው ተኩስ የተከፈተባቸው ነዋሪዎች ያሰሙትን የድረሱልን ጩኸት ሰምተው የሄዱት መሆናቸውን መስማታቸውን ተናግረዋል።
የቡለን መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በተደጋጋሚ በአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች ጥቃት የሚደርስባቸውን ሰዎች ተቀብሎ የሚያክም ሲሆን መሰረታዊ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት በፀጥታ ችግር ምክንያት እንዳልቻለ የሕክምና ባለሙያው ተናግረዋል። ለሆስፒታሉ ግዢ የሚፈፀመው ባህር ዳር እንደነበር የገለፁት ባለሙያዎቹ ከቡለን ቻግኒ ያለው መንገድ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ዝግ በመሆኑ ይህንን ማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን ገልፀዋል። በዚህ የተነሳ በሆስፒታሉ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት አስተናግደው የመጡ ሰዎችን ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። በአካባቢው ከጳጉሜ ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚደርስ የሚናገሩት የሕክምና ባለሙያው እንዲህ በጅምላ ጉዳት ደርሶባቸው የመጡት ግን ባለፈው ከቡለን ወደ ቻግኒ የሚሄድ መኪና ላይ ጥቃት በደርሰበት ወቅት እንዲሁም የዛሬው መሆኑን ጠቅሰዋል። በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የመተከል ዞን ውስጥ በታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ወራትን አስቆጥሮ፤ አሁንም ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን