ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ባስቸኳይ እንድታቆም ኢትዮጵያ አሳሰበች
ኢዜጋ ሪፖርተር
December 23, 2020 (Ezega.com) -- በኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን በኩል እየተደረጉ ያሉ አዳዲስ ለውጦች እና እንቅስቃሴዎች የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥሱ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙ ኢትዮጵያ አሳሰበች። ማሳሰቢያው የተሰጠው በሱዳን ካርቱም ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳዮች ከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ውይይት በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅትም ሁለቱ ወገኖች በጋራ የድንበር አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳብ የተለዋወጡ መሆኑን የዘገበው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ በጋራ ድንበር አካባቢ በሱዳን በኩል የተደረጉ አዳዲስ ለውጦች እና እንቅስቃሴዎች የቀደሙ ስምምነቶችን የሚጥሱ መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል ብሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም ድርጊቶቹ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚለውጡ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲቆሙና ወደቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ አሳስባለች ተብሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በገበሬዎች እና ባለሃብቶች ንብረት ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና የዜጎች መፈናቀል ትኩረት እንደሚያሻውና በአስቸኳይ መታረም እንዳለበት ማሳሰቧም ተገልጿል ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ ሃገራት የጋራ ድንበርን በተመለከተ ያሉ ማናቸውም አይነት ልዩነቶች ሁሉንም በሚያስማማ መንገድ በውይይት ስለ መፍታትና የወደፊት አቅጣጫውም ምን ይሁን በሚለው ዙሪያ መሪዎቹ በሁለቱ ቀናት ውይይት መክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የድንበሩን ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ መልኩና ከቀደሙት ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ ከድንበሩ ጋር በተያያዘ የተቋቋሙና ስራቸውን ያላጠናቀቁ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ስራቸውን እንደገና እንዲጀምሩ በማድረግ መፈታት እንዳለበት ተገልጿል፡፡ ይህም የሁለቱን ሃገራት ስትራቴጂካዊና ወንድማማቻዊ ግንኙነት እንዲሁም የሁለቱን ህዝቦች ፍላጎትና ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሚሆንም ነው የገለጸችው፡፡ ሁለቱ ወገኖች ቀጣይ ምክክራቸውን ወደፊት በአዲስ አበባ ለማካሄድ እና ለመሪዎቻቸው የዚህን ስብሰባ ሂደት እና ውጤት ሪፖርት በማቅረብ በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት ምክክራቸውን ለመቀጠል በመስማማት ስብሰባቸውን አጠናቀዋል ሲል ዘገባው አስነብቧል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ስብሰባ በአካባቢው ያሉ ለውጦችን በመገምገም የድንበር ኮሚቴዎች ስራቸውን በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡ በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው ልዑክ በሱዳን ቆይታው ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ባለፈው ሳምንት በርካታ የሱዳን ወታደሮች ከኢትዮጵያ በኩል በተሰነዘረ የሚሊሻ ጥቃት መገደላቸው ተዘግቧል። ካርቱም ክስተቱን "የደፈጣ ጥቃት" ስትል ጠርታዋለች በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል ክስተቱ ያልተስተባበለ ሲሆን "ድንበር ጥሰው በገቡ ኃይሎች ላይ የተወሰደ ራስን የመከላከል አስፈላጊ እርምጃ ነው" ተብሏል። እንዲህ ዓይነት የድንበርተኞች ግጭት በተደጋጋሚ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ይከሰታል። ግጭቱ ቦታው የእኛ ነው በሚሉ ኢትዮጵያዊያን አራሽ ገበሬዎች እና "የለም አካባቢው የእኛ ነው" በሚሉ የሱዳን ጎረቤቶቻቸው መካከል የሚከሰት ነው ሲል ቢቢሲ አስነብቧል። ይህ ክስተት የተሰማው ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕግን የማስከበር ወታደራዊ እርምጃ መጠናቀቁን በገለጹ ማግስት መሆኑ ነገሩን ላልተረጋገጡ ፖለቲካዊ ትርጓሜና መላምቶች አጋልጦታል ተብሏል። የድንበር ግጭቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትዊተር ሰሌዳቸው "እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በሁለቱ አገሮች ያለውን ጥብቅ ቁርኝት አይበጥሰውም እኛ ሁልጊዜም ችግሮቻችንን በውይይት ነው የምንፈታው" ብለዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጋሩት ድንበር ርዝመት 750 ኪሎ ሜትር ያካልላል። ነገር ግን ይህ ድንበር አብዛኛው ርቀት ግልጽ በሆነ መንገድ መሬት ላይ አልተመላከተም። ይህን ለማሳካት ተደጋጋሚ ንግግሮች ተጀምረው በተደጋጋሚ ተቋርጠዋል። አሁን ኢትዮጵያና ሱዳን ያሉበት አካባቢ ታሪካዊ ሁኔታዎች ከብሉ ናይል እና አትባራ ወንዞች ጋር በአንድም በሌላም መልኩ የተጋመዱ ናቸው። እነዚህ ወንዞች ሁለቱ ሕዝቦች በንግድና በሌሎች መልኮች እንዲገናኙ ለዘመናት ምክንያት ሆነው የቆዩ ናቸው። ነገር ግን ንግድ ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ግጭቶችም መነሻ ናቸው፡፡ በተለይም ድንበር ላይ ለሚነሱ ግጭቶች። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የቅኝ ገዢዎች ያበጇቸው ድንበሮች ሱዳንን፣ ግብጽንና ሌሎች የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ አገራትን የአሁን ቅርጽና መልክ ፈጥረውላቸዋል።
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን