ዕድል ከሌለህ…. ድኃ ትሆናለህ!!!
(ወግ መቋጫ አንድ - ስላቀ ፍቅር ወጦርነት!)
ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
December 31, 2020
“ድህነት በመስኮት ሲገባ ፍቅር በበር ይወጣል!”
(አገራዊ ብሂል)
“የድሃ ልጅ ነው እየታፈሰ ወደጦርነት የሚጋዘው!”
(የኢትዮጵያ መሪዎች)
ይህንን ፅሁፍ ስንጀምረው በገንዘብ ኖቶች ቅያሪ መነሻነት ነበርና ርዕሰ ጉዳዩ “የገንዘብ ኖቶች ወግ” ቢሆንም ብዙ ነገሮችን ነካክቶ እኔም ፅፌው እርስዎም አንበብውታል…. ማለቴ አንተ ዕድለ ቢሱ ድኃ አንብበኸዋል፡፡ በቀጠሯችን መሠረት እነሆ ፅሁፉ መቋጫ ሊያገኝ ግድ ነውና ፍቅርንና የእርሱም ተቃራኒ የሆነውን ጦርነትን ነካክተን ከድህነት ልናሰናብትዎ ባንችልም ከነድህነትዎ እንሰናበትኋለን…! ድህነትን በደንብ አውቆና ተዋውቆት ያለፈው ሞዛቂ ኃ/ኢየሱስ ፈይሣ “ፍቅር” ይሉት ማራኪና አጓጊ ነገር ላንተ ብጤው ድኃ “ዋጋው አይቀመሴ” እንደሆነ እንዲህ ያረዳሃልና እያለቃቀስክ ተቀበል፡-
“ፍቅር ተወደደ
ፍቅር ተወደደ - አወጣ ምሊዮን
የኔ አይነቱን ድሃ - ምን ይውጠው ይሆን?!”
አዎ! ምንም ሳይኖር ፍቅር፤ በባዶ ኪስና ቤት ደግሞ ፍቅርም ትዳርም የለም…. ድኃ ስትሆን መታጨትህም ለፍቅር ሳይሆን ለጦርነት ይሆናል፡፡ የጓድ ሊቀ-መንበር፤ የተጋዳላይ መለስ ዜናዊ፣ የአካዳሚሽያኑ ኃይለማርያም ደሳለኝንም ሆነ የወታደሩን ዓብይ አህመድ (ኮ/ል) ንግግሮች በየተራ ብታደምጥ ምታቸው አንድና አንድ ነው…. ለፖለቲካዊ ትኩሳቶችና ለጦርነቶቻችን ሁሉ የሚማገደው ያንተ ቢጤው ነጭ ድኃ ነው…. ወዳጄ የአገራችን ጦር ኃይሎች ሲመለመሉ የኖሩትና አሁንም ለሞት ዘመቻው የሚታጩት ከጨርቆስና ጉለሌ እንጂ ከቦሌ እንዳይደለ ላስረዳህ አልደክምም…. የቦሌው ወጣት ምን አጥቶ ያኮርፋል?! የአገር ፍቅር ምናምን እንዳትለኝና ያንን ግርማ ሞገሳም የሀብታም ሳቄን እንዳልስቅብህ…. ፖለቲካን ሲቆላ የሚውለውም ያንተ አይነቱ ችጋራም እንጂ ቦሌ ቦሌው አይደለም…. ካላመንክ የእኔና ያንተ ትውልድ ያጣጣመውን የዘጠና ሰባቱን ቦተሊካ ጠይቅ!
አርስቶትል የሚባለው አሰላሳይ “ድህነት የወንጀሎችና የአብዮቶች ሁሉ ምንጭና ወላጅ!” መሆኑን ግሪክ ሆኖ ቢነግርህም እውነታው ለኢትዮጵያም ሆነ ለሩሲያና ለፈረንሳይ አብዮቶች ሰርቷል… ድሆችና አብዮቶች ቁርኝታቸው የጥንት ነውና ነው አንዲቷ ቅምጥል የፈረንሳይ ልዕልት ዳቦ ቸግሮት “ዳቦ!” እያለ ሜዳ ላይ ለተቃውሞ የወጣውን የድኃ ጥርቅም ምን እንደሆኑ ጠይቃ አንዱ አማካሪዋ ቸግሯቸውና የሚበሉት ዳቦ አጥተው እንደሆነ ሲነግራት “ለምን ኬክ አይበሉም ታዲያ?” ስትል በአላዋቂኛ የተሳለቀችበትን አላነበብከው ይሆን?!…. ለነገሩ በየት በኩል መፃህፍትን አጊኝተህ ታነባለህ?! የመፃህፍቱ ዋጋም በእናንተ የሚቀመስ አልሆነም....
እናማ በቃ “ዕድል ከሌለህ ድኃ ትሆናለህ!” ድኃ ስትሆን ደግሞ…. ስለመፃህፍት ከተነሳ ዘንዳ እልል ብለህ ያው መግዛት ስለማትችል በተውሶና በኪራይ ያነበብከውን “ፍቅር እስከ መቃብር” ከሮሚዮና ጁሊየት እያስታከክ ለሰብለ እና ለበዛብህ አድናቆትህን ስትቸር ይልቁንም በተስፈኝነት “ፍቅር ፍቅር” ሲያጫውትህ አስተውያለሁና “ድህነት እና ፍቅር” እንዴት አብረው እንደማይሄዱ ላስመለክትህ የሃብታምነት ሥልጣኔ ያግዘኛል…. ያው ከሀብት ትሩፋቶች አንዱ “ድፍረት” መስጠቱም አይደል?! ካላመንከኝ ናሁ ቴሌቪዥን ላይ እነ ሻለቃ ኃይሌና የጣቢያው ባለቤት የሚሰጡትን ምናባዊና ገንዘብ ጠገብ “ትንታኔ” ተመልከት….!
እናልህ ወዳጄ ወደ ነጥባችን ስንመለስ በእንጉርጉሮ መልኩ የተዜመውን የአበበ ተካን “የድኃ ነገር አንጀት ስትበላ…” እያደመጥክ ተከተለኝማ…. ዕድል ከሌለህ ድሃ ትሆናለህ! ድሃ ስትሆን ደግሞ ተቃራኒ ፆታ ላይ ብዙ አታፍጥጥ…. “እሷ ስትገባ በበሬ በመስኮት ወጣ ችግሬ…” የሚለውን አዝማሪ እንዳታምነው! ችግርህ በመስኮት ሲገባ እሷ በበርህ እንደምትወጣ ግን እመን…. እስኪ የት ልታዝናናት ነው?! አይበልብህና…. እስኪ ቤትህን አሳየኝ ብትልህስ ምን ሊውጥህ ነው?! አንቺስ ጠብሻሚቱ?!
አዎ! ፍቅር ከመሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች አንዱ ቢሆንም እመነኝ ላንተ ቅንጦት ነውና በውስጥህ እያስታመምከው ኑር…. እግረኛ ብትሆንም ለመጓጓዣነት የሚያገለግለው መኪና እንኳን በአገርህ የመደብ መለኪያ ነውና በዚያን ሰሞን ድኃው መንግስትህ ያቀረበውንና በቶሎ ያሰረዝነውን “መኪና አጋሩ!” የሚል መፍትሄ ሰምተን እንዴት እንደተሳለቅን አትጠይቀኝ ወዳጄ… እስኪ እናንተን ማን አምኖ ነው የሚያሳፍረው?! የአጓጉል ክፋታችሁ ደግሞ ጋቢና ላይ መንጦልጦል ስትወዱ ሃሃሃሃ ለማንኛውም “አትመልከቺ ሱፍ አትይ መኪና…” ይሉት ዘፈን ይሁን ማመልከቻ ቅጡ ያልለየለት ነገር ለዘመንህ ሴቶች እንደማይሰራ እወቀው - ከመኪናም ይመረጣልና!
ድኃ ስትሆን…. ፍቅርም ይርቅሃል!
በእርግጥ ፍቅር፣ ትዳር፣ ኑሮ…. ምናምን እንዳያምሩህ ከዚህ በፊትም ነግሬሃለሁ፡፡ ቶሎ አትበስልምና እደግምሃለሁ እነሆ…. የምትወዳቸው ሀዲስ አለማየሁ በበረከቱት ስራዎቻቸው በኩል የክፉውን ምልክዓ ድህነት ቢያሳዩንም ከላይ በጠቀስኩልህ “ፍቅር እስከ መቃብር” በኩል ግን የመልከ ጥፉነቱን ጥግታ አስመልክተውናል፡፡ ድርሰቱን ሲጀምሩ ቀዳሚው ገፅ ላይ ምን ይላሉ፡- “ጎጃም ዳሞት አውራጃ ውስጥ ማንኩሳ ብምትባል ሀገር ቦጋለ መብራቱ የሚባሉ ብዙ ዘመን በብቸኝነት የሚኖሩ ሰው ነበሩ… ከድኃ ቤተሰብ የተወለዱ በዚያውም ላይ ድኆች ወላጆቻቸው ገና በህፃንነታቸው ሞተውባቸው ድህነት ሲያንገላታቸው ያደጉ ነበሩ፡፡ ትንሽ ከፍ እንዳሉ መጀመሪያ የፍየልና የጥጃ እረኝነት እየተቀጠሩ፤ በኋላም እጃቸው እርፍ ለመጨበጥ ያህል መበርታት ሲጀምር ግብርና እየተቀጠሩ ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ እኩል ዕድሜያቸውን ካሳለፉና የምሽት ማግባት ፍላጎታቸው እየተቀነሰ ከሄደ በኋላ……” ይሉሃል ደራሲው፡፡
ሀዲስ ይህንን ካሉ በኋላ እኚህ የውድነሽ በጣሙ ባለቤትና የበዛብህ አባት የሚሆኑት አያ ቦጋለ “የምሽት ማግባት ፍላጎታቸው” በድህነታቸው ምክንያት እየተቀነሰ መሄዱን ነግረውን ይህንኑ ድህነታቸውን ለልጃቸው እንዳወረሱት ፅፈውልናል፡፡ እዚህ ግድም ደርሰህ እንኳን መከራከር ትወዳለህና “ድኃ ሆነህ ብትወለድ ጥፋቱ ያንተ አይደለም፤ ድኃ ሆነህ ብትሞት ግን ጥፋተኛው አንተ ነህ!” ይሉትን ጥቅስ ትጠቅስብኝ ይሆናል…. አባቴ! ስንቱ ስንት ነገር በሚያወርስባት ዓለም ወላጆችህ ድህነትን ካወረሱህ “በመደበኛው መስመር” ሀብታም የመሆንና ድህነትን ከዘር-ማንዘርህ የመፋቅ ዕድል የለህም ይልሃል - በዕውቀቱ ስዩም!
በርከት ያሉ ድህነት ተኮር ሙዚቃዎችን የሞዘቀው አለማየሁ እሸቴም “የአባት ዕዳ ለልጅ” ያለው ይህንንም ከአያት የሚመዘዝ የድህነት እርግማን ይመለከታል፡፡ አፍቃሪው በዛብህ በድህነቱ ምህኛት ላጣት ለተፈቃሪው የጌታ ልጅ ሰብለወንጌል መሸሻ በላከላት የስንብት ደብዳቤ ውስጥ “ተቀማሁኝ ወይኔ ድኃ በመሆኔ!” እያለ ከላከው ዘለግ ያለ ግጥም ውስጥ እኚህን ስንኞች ብታነብ እንዳትገረም እየመከርኩ ከግጥሙ ላስታውስህ:-
“ተቀማሁ ወይኔ - ድኃ በመሆኔ
ጥዬሽ የሄድኩ’ለት - ወንዝ ተሻግሬ
የደም እንባ አልቅሼ - በዕድሌ አማርሬ
የኋሊት ስጎተት - በፍቅርሽ ታስሬ
ወደፊት መራመድ - እያቃተው እግሬ፤
አሁንም አሁንም - ቆሜ እያየሁ ዞሬ
ምን ልቤ ቢፈራ - ባይቀር መጠርጠሬ፤
በተስፋ ነበረ - የወጣሁ ካገሬ፡፡
እስከዛሬም ድረስ - በህይወት መኖሬ
ተስፋ ሆኖኝ ነበር - ፍቅርሽና ፍቅሬ
ግን እውነት ከሆነ - ነገሩኝ ወሬ
ሊያገባሽ ነው ብለው - ባለብዙ በቅሎ ባለብዙ በሬ
በፍቅር ለሞተ መታሰቢያ ሆኖ - እንዲኖር መቃብሬ
መኖር አልፈልግም - ሞቼ ልደር ዛሬ፡፡”
በቀደመው ክፍል ድህነት ማለት “ሳያጠፉ ቅጣት” እንደሆነ “Poverty is like punishment for a crime you didn’t commit.” የሚል የፈረንጅ አፍ ጠቅሰንም አልነበር?! በዛብህም በዚህ ስሞታው ድህነት “ሳይሞቱ ኩነኔ” መሆኑን በማውሳት የሚሞግተው መድልዖ ፈፅመሃል ሲል ፈጣሪን ነው፡፡ ስለምን ሳልኖር እንድሞት ፈረድክብኝ? ባይ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አድሎ የሞላበት ብያኔና ፍርድ ለመቀበል አቅም ባይኖረኝም ዝም ብዬ ከምቀጣ ቢያንስ ፍትሃዊነቱን አጠይቃለሁ ሲል ያለጥፋቴ ነው ድህነት የተፈረደብኝ ሲል ዕድለ ቢስነቱን እንዲህ ሲያማርርና የፈጣሪውን ፍርድ ሲያጠይቅ አንብበሃል፡-
“በማን ደርሶ ያውቃል - እንዲህ ያል ብያኔ?
ሳያጠፉ ቅጣት - ሳይሞቱ ኩነኔ?
ዳሩ ዳኛ የለም! ልተወው ግዴለም!
ጉልበቴን ሳላጥፍ - ወገቤን ሳልፈታ፤
ቀን እረፍት ሳያምረኝ - ወይ ሌሊት ምኝታ
እርም ብዬ ትቸ - ከሰው ጋር ጭዋታ
ስፀልይ ስማለል - ከጥዋት እስከማታ፤
ያሳዬኛል ብዬ - ዓይንሽን ላንዳታ
አጥፊዎችን ሁሉ - ይቅር ባዩ ጌታ፡፡
መቼም ያልፃፈኝ ነኝ - ስፈጠር ለደስታ
አመጣልኝ መርዶ - በምስራች ፈንታ
ዳሩ ዳኛ የለም - ልተወው ግዴለም!
እግዚአብሔር ሲፈጥረኝ - ጥንቱን በዚህ መሬት
ሳለቅስ ተወልጄ - ሳለቅስ ኖሬበት
ሳለቅስ እንድሄድ ነው ወደማልቀርበት?
መከራ ጠግቤ - ደስታ እንድራብበት?
ሌሎች የበሉትን - ዕዳ እንድከፍልበት?
ሌላው ጠግቦ ሲያድር - እኔ እንዳልቀምስበት?”
በእርግጥ ርዕሳችን ስላይደለ እንጂ ይህ “የፈጣሪ ፍርጃ” ሰፊ ፍልስፍናዊ ምልከታ የሚያሻው ነበር፡፡ ዘሪቱ ከበደም “የእኔም ዓይን አይቷል” በሚለው ሙዚቃዋ በኩል ይመስለኛል ለአንዱ ሞልቶለት ሲተርፈው፤ ለምመረጥም ሲቸገር፤ ሌላው ደግሞ ጎድሎበት ሲጨንቀውና ምንም አጥቶ ላይ ታች ሲራወጥ በፈጣሪ ፍርድና በሁለቱ ወገኖች “ፍርቱና” ላይ ጥያቄ ስታነሳ አድምጫታለሁ፡፡ ፍጡር ከፈጣሪው እንደማይበልጥ ጠቅሳ ግን ፍርዱን “ለፈጣሪው” ስትተው እናደምጣታለን…. “ሰሪ አይበልጥም ወይ ከተሰራው?” እያለች ስትሸሽ….
በተያያዘ ዜና….
ገንዘብ የ “ጥረህ ግረህ በላብህ ኑር!” አምላካዊ ተፈርዶን ማቅለያዎች (Technologies) ሊያቀብልህ ቢችልም በዕድለ ቢስ ድኃ አገራት ግን ምኑም አልተያዘምና እንኳንስ ወደ ዘመናዊ አስተራረስ መግባት ቀርቶ መንግሥት የአንበጣ መንጋን ሊከላከልለት ያልቻለው አርሶ አደር ከሰውነት ከፍታ ወርዶና ከአራሹ በሬ ጋር አብሮ ተጠምዶ ሲያርስ ታየዋለህ…. ገንዘብ ጌታም ሎሌም የማድረጉን ጉልበታምነት ታምናለህም፡፡ በገንዘብ ቁልፍነትና ሁሉን ከፋችነት የተማመኑቱ “ገንዘብ ካለ በሰማይም መንገድ አለ!” ቢሉም አንተና መሰሎችህ የምድሩም ግራው ገብቷችኋል.… መፃህፍቱም “ላለው እንደሚጨመርለት ከሌለው ላይ ግን ያ ያለውም እንደሚወሰድበት” ሲነግሩህ አብረው የሚያረዱህ “ድኃ ድህነቱን ይረሳ ዘንድ ይጠጣ!” ማለትን ነውና እየጠጣህ ወዳጄ ሃሃሃ
አሜሪካዊው ሰውዬ “Every village have it’s own idiots. If you fail to know who this ediot is then, you are that ediot.” እንዳለው ነው፡፡ በዚያን ሰሞን አንዱ አድር-ባይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አስር ሚሊዮን የኦሮሞ ወጣቶችን አሰልፋለሁ እያለ የድኃው ልጅ ላይ “ሞት” ሲጠራበት አልሰማህምን?! ከእነዚህ ከተሟረተባቸው ወጣቶች ውስጥ እንኳንስና የእርሱ ልጆች የቅርብ ዘመዶቹ እንደማይኖሩ እወቅና…. ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚመጡ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ (Modes) ለመግዛት እንዴት ይቸገሩ እንደነበር (የእኛዎቹ “መደቦች” ለማስቲካ የሚያወጡትን ያህል እንኳ!) በኃዘን ተውጬ አስተውያለሁና ይህንን ጉድ እያየሁ አገሬ ለወገን ጦርነት ሚሊዮን ብሮችን፤ ከብዙ ሺህ የወጣት ህይወት፣ አካልና ጉልበት ጋር የምትገብርበት ስላቅ ይደንቀኛል…
ይህንን ስትመለከት ነው የሠናይት መብራህቱ ውለታ ገብቶህ ከወገብህ ዝቅ እያልክ የምታመሰግናት፡፡ በድኃ ህፃናትና በሴቶች መብት ላይ እንሰራለን የሚሉህ አንድ ከታቢ “የድህነት ጌቶች” ያላቸው በዶላር የተንበሸበሹ “የበጎ አድራጎት” ድርጅቶች በአንድ የዕለት ውሎ አበልና አውደ ጥናት ምናምን…. የሚያወድሙት ብር ብዙ ህይወቶችን የመቀየር አጋጣሚ ይፈጥሩ ነበር፡፡ ከአለባበስና ሁኔታቸው ጀምሮ የሚሸቅሉበት “ድህነት” እንዳይጠፋ የሚንከባከቡት እንጂ ሊቀንሱት እንኳ የማይፈልጉ መሆናቸውን ስነግርህ አትደነቅ…. የድህነት ቦዲ-ጋርዶች ናቸው ስልህ በሙሉ ልቤ ነው….
ወዳጄ ልቤ ሆይ! ያለአበባ ንቢቷ እንደሌለች፣ ያለቆሻሻም ዝንብ እንደማትኖረው ሁሉ ለፍቅርም ሆነ ለሌላው ሁሉ “ሳቢው ከሌለ ተሳቢው አይኖርም!” ነው መርሁ…. ማግኔቷ ገንዘብ ናት! የዘመናችን ጣዖት ፈራንካ ነው! ፈጣሪ ሁሉንም ፍጥረታት ካስገኘ በኋላ እንደፈጠረው የሚነገርለት “የመጨረሻው ፍጥረት” ሰው ነው ይባላል፡፡ ሰው አምላክነትን ሽቶ ማመፁ አልጠግብ ባይነትንና አይበቃኝ ሰኚነትን ወደ ዓለም አስገብቷል እንዲሉ ሃይማኖታውያኑ፡፡
ሰውም ሟችነቱን ያልተቀበለውና እስካሁንም የሞት መድኃኒት የሚያፈላልገው በአባታችን አደም (አዳም) ስህተት ሞት ባይመጣበት ኖሮ ለዘለዓለማዊ ህይወት ተፈጥሮ ስለነበር ነው የሚሉ ፍልሱፋንም አሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ ድሃ ስትሆን በችጋር ምግብነቱ የሚታወቀውን “ገብስ ቆሎ” እንኳን ፈትገህ እንደማትበላና ክብርህ ነጥፎ፣ ጥላህ እንኳ የማይከብድ ቀትረ ቀሊል እንደምትሆን አማሪካ ከክፉ ድህነቱ መንጭቃ ያዳነችው ይሁኔ በላይ በገድሎ ማዳን ዘይቤ ይነግርሃል፡-
“ባይልለት እንጂ - ኑሮ ቢያሸንፈው
መች ይጠላ ነበር - መከበር እንደሰው?!”
የዛሬን ስንሰነባበት አንድ ወግ ማጠናቀቂያ ቀጠሮ መያዛችን ባይቀርም ገንዘብ የሚፈጥረውን ዘርፈ ብዙ ድሎት ወምቾት፤ ክብር ወፍቅር ስታስብ አምልኮት ሲያንሰው እንጂ እንደማይበዛበት ትረዳለህ…. አንዳንድ የእኛ መደብ ባለሀብቶች (ፀጋው በዝቶልናልና ባለ-ፀጋዎች ልትላቸውም ትችላለህ!) ገንዘብን ቢያመልኩና በእናንተ አገላለፅ ቢስቆነቆኑ አይግረምህ ወዳጄ! ካላመንከኝ “አትሂድ” ከሚለው ዕውቅ የሜሮን ጌትነት ግጥማዊ ሽሙጥ ውስጥ ድሆች የተከለከሏትን አንዲት ኮረዳ ሀብታሞች ከእናትዬው ጓዳ ሊያውም በፈለጉት ሰዓት እንደሚወስዷት የገለፀችበትን ስንኝ ልብ በለው…. በእርግጥ የግበረ-ገብ መምህራችን ጋሼ ከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሳሌ” ላይ እንዲህ ይሉናል:-
“ገንዘብ መፈጠሩ - ለሰው አገልጋይ ሆኖ
ሊሰራበት አልነበረም ወይ?
አሁን ግን መስገብገብ - በጣም ስለበዛ
ሰው ባሪያ እየሆነ - ለገንዘብ ተገዛ፡፡”
- ሠላም ለእናንተ ይሁን! -
_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ
ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣ የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን
ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን
ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን