ዕድል ከሌለህ…. ድኃ ትሆናለህ!!!

Poverty-Ethiopiaዕድል ከሌለህ…. ድኃ ትሆናለህ!!!
(ወግ መቋጫ ሁለት - ስላቀ ኑሮ!)

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

January 11, 2021

“I am neither an Optimist nor a Pessimist. But a Possibilist.”
(Hans Rosling)

አገርህ እንዲህ እንደዛሬው የጠቢብ እጥረት ሳያጋጥማት በፊት እንደሳቅ ንጉሡ ቻርሊ ቻፕሊን ሁሉ ድህነቱንና ድህነትህን በምሬት ሳቅ የሚያዋዛልህ ተስፋዬ ካሳ የሚባል ሰው ነበረ… ይህ ቀልዱ ብቻ ሳይሆን ድምፁም ያማረለት ሰው በአንድ የበዓል ጨዋታው ላይ ህፃን ልጅ “እማዬ ፆም ሲፈታ….?!” ብሎ ድኃ እናቱን ይጠይቅና የእናትዬውን ምላሽም ያቀብለናል፡-

“ልጄ! ፆም ሲፈታማ ሌላ ፆም እንይዛለና!”

እነሆ…. አንተም ዕድለ ቢሱ ወዳጄ ፆም ተፈታልህና ሌላ ፆም ይዘሃል... በቀደሙት ክፍሎች ይልቁንም ድህነትን ከፍቅርና ጦርነት ጋር እያሰናሰልን በተሳለቅንበት ክፍል የሀዲስ ዓለማየሁን “ፍቅር እስከ መቃብር” ዋቢ አድርጌ የበዛብህን ድህነት የተጫነው ብሶት አስመልክቼህም አልነበር?! አዎ! ብዙ ተመልካችና አጀብ ያላትን ሴት ልብህ እንዳይከጅል በአሸናፊ ከበደ “አንቺን የብቻዬ ቢያደርግልኝ… አይ ዕድሌ!” እንጉርጉሮ በኩል ተግሳፄን አቀብዬህም አልነበር?! እስኪ “ህያው ፍቅር” ከተሰኘው ቆንጆ የፍቅር ተረክ መፅሃፍም ይህንኑ ደግሜልህ ወደዛሬው ስላቀ ኑሮ አሳልፍሃለሁ…. ደራሲው “ቻርሊ” በሰኘው ቺስታ ገፀ-ባህሪው በኩል “አብነት” ለሰኛትና እንደስሟ አብነት ለሆነችው የሞላለት ቱጃር ልጅት ድህነትን እንዲህ ሊያስረዳት ሲሞክር የአብነትን አስተዳደግ በቅድሚያ ይነግርሃልና ይህንኑ እያሰብክ አንብበኝ ወዳጄ ልቤ:-

“አብነት… የዚያ መንደር ጠባይ ይገርማታል፡፡ ጎረቤት ከጎረቤት አቦል ቡና አይቃመስም፡፡ የሰፈሩ ህፃናት ግቢያቸው ውስጥ ተገልለው እንጂ በጋራ ሆነው አይቨቦርቁም፡፡ እድር፤ እቁብ፣ ሰንበቴ፤ ዝክር የሚባሉት የማህeበራዊ ግንኙነቶች አይታወቁም፡፡ መንደdሩ አብዛኛውን ጊዜ ጭር እንዳለ ነው፡፡ የሰው ዘር በአካባቢው ለመኖሩ የሚታወቀው ከቪላ ቤቶቸ ጀርባ ከተሰሩት የጭስ ቤቶች ሽቅብ የሚትጎለጎል ጥቁር ጭስና ጣፋጭ መዓዛ ያለው ምግብ ሽታ በመኖሩ ብቻ ነው… እንደአባቷ አገላለፅ ግን ያ መንደር ከምድራዊው ሲዖል ያመለጡ ብልሆች የራሳቸውን ምድራዊ ገነት ፈጥረው የተሸሸጉበት አምባ ነው፡፡ በምድር ሲዖል የሚጠበሱ ጎስቋሎች ገላ እንዳይሸታቸው፤ ዋይታቸው እንዳያደነቁራቸው፤ እንደከሩቤል ሠይፍ የሚቆጥሩትን ረዣዣም የግንብ አጥር ከለላ አድርገውታል… ፡፡”

እናልህ ወዳጄ አብነት ያደገችው እዚህ የሞጃዎች ግዛት ውስጥ ሲሆን ያፈቀረችው ቻርሊ ደግሞ እንዳንተው የኑሮ ውጣ-ውረድ የቆጋው መናጢ ድኃ ነበርና የቤተሰቦቿ ሀብት በፍቅር ግንኙነታቸው ላይ የሚፈጥረወ ችግር እንደማይኖር ቃል ለምድር ለሰማይ ብትገባለትም ለፍቅር ጥያቄዋ ምላሽ ከመስጠቱ በፊት በዚህ ይንደረደራል:- “አየሽ አብነት የንዋይ ፈተና ከፈተናዎች ሁሉ የላቀና በዋዛ የማይታለፍ ነው፡፡ በሁለታችን መካከል ያለውን የአስተዳደግና የአኗኗር ልዩነት ስገምተው….” አዎ! መጨረሻውን አልነግርህም፡፡ ግን ገምት….

ድኃ አይጣላ ከውኃ?!

በዚህ ወጋችን ውስጥ ከሙዚቃና ግጥሙም፤ ከሥነ-ቃልና መፃህፍቱም፤ ከፊልምና ከኪነቱም ድህነትንና ድሆችን ርዕሰ ጉዳያቸው ያደረጉ ጥበባዊ ስራዎችን በማዋዣነት ከዚህም ከዚያም እያፋለግኩ እንደድኃ የበዓል ቅንጣቢ ስጋ አቀብዬሃለሁ…. ድኃ ከብሮ ባያውቅም “የከበረ ድኃ” የሚለውን ፊልም በስሌት እንድትመለከተው “ድኃ አደግ” የሚለውን የአያልነህ ሙላተ ባለአንድ ገቢር ተውኔት በወቅቱ ለመመልከት አቅም ባይኖርህም በመፅሃፍ መልክ ስለቀረበልህ አፋልገህ እንድታነበው እነሆ በድጋሚ ጠቁሜሃለሁ….

ስለውኃ ብዙ ላወራህ አልፈለግኩም ነበር…. እኛ ለጤናችን በጣም ስለምንጠነቀቅ “ከውስጥ ይሁንልህ ወይስ ከውጭ?!” ተብለን በክብር እየተጠየቅን በማዕድናት በልፅጎ፤ ባማረ አስተሻሸግ ታግዞ የሚቀርብልንን ውኃ ገርገጭ አድርገን ያለስጋት ስንጠጣ ትዝ ትለናለህ… በዛገ የብረት ቧንቧ በኩል እሱንም “ውኃ የበላው ተዝካር!” እንዲሉ ከስንት አንድ ጊዜ እየመጣ “የእግዜር ውኃ” ስትለው እየሰማሁ እንዴት ስለውኃ ለማንሳት ልድፈር?! ነገሩ “በዶሮና በጫጩቶቿ ፊት ስለፈንግል አይወራም!” ይሉት አይነት ነገር ነዋ….

አገርህ “የአፍሪካ የውኃ ማማ” እየተባለች ህዝቦቿ በውኃ ችግር የሚንከራተቱባት “ውኃ አለ! ግን ውኃ የለም!!!” የመሆኗ ስላቅ ግን አይገርምህም ወዳጄ?! የአህዮችን ጀርባ በቢጫ የዘይት ደንበዣን ጭነት አጋግጦ ሴቶችንና ህፃናትን ለአቅማቸው የከበደ፤ ለጀርባቸውም የፈተነ ሆኖ ከትምህርት ማስታጎሉ ሳያንስ ከተጠጣ በኋላ ወትሮም የተረበሸ ሆዳችሁን መረበሹስ?! ለነገሩ እንዲህ ያለውን ውኃ እኛ ሞጃዎቹ ለአትክልቶቻችን እንኳ ላለማጠጣት በጣም ነው የምንጠነቀቀው…ካላመንክ እኛ የምንበረክትባቸው አካባቢዎች ብቅ በልና ያንተ ቢጤው ዘበኛችን ለአትክልቶች ውኃ ሲያጠጣ ተመልከት…. ደግሞ’ኮ “ውኃ ህይወት ነው!” ይባልልኛል፡፡

መሆኑንስ ውኃ ከእስትንፋስ ሲለጥቅ ህይወት ነው… ሁሉንም ነገር ህያው አድርጎ እያኖረ ያለው የፈጣሪ ፀጋ ውኃ ነው… የዓለም ስሪት በአብዝኃው ውኃ፣ የእኛ ሰውነትም ለመቶ ሩብ ፈሪው ሲቀር ብዙ እጁ ውኃ ነው፡፡ እዚሁ ግድም “ምግብማ ሞልቷል” እያለ ጥላሁን ገሠሠ በዘፈነባት አገር በምግብ እጦት የሚቀነጭሩና የሚሞቱ ድሆች ህፃናት ሚሊዮናትን ቢያስቆጥሩና አገርህ በምግብ እንኳ ራሷን ሳትችል ብትቀርም… እዚህ ግድም የቴዲ አፍሮን “ፍቅር አጥተን እንጂ በርኃብ የተቀጣን አፈሩ ገራገር ምድሩ ምን አሳጠን?” ሲል ስለአረንጓዴው ምድር ያንጎራጎረውን የስቃይ ጣር ተጋበዝልኝማ…. እናልህ ይኸው ምግብ እንኳ ከትክለት እስከ ብቅለቱ፤ ከፅድቀት እስከ ብስለቱ በውኃ ተራዳኢነት እንጂ በሌላ እንዳይደለ አለመዘንጋትም ቁም-ነገር ነው…. ደግሞ ይቺን ሰበብ አገኘሁ ብለህ “እንራ ሚሰራው ከውኃ ነው ብዬ ውኃን አስቀደምኩኝ እንጀራውን ጥዬ….” ብለህ ለድኃ በታዘዘው ወይን ፈንታ አምቡላህን እንዳትጋት!

ለአገርህ የበረከቱ ዝማኔዎችን ያቀበሏት አጤ ምኒሊክ የጣይቱን ምግብ ቤት ሲያስተዋውቁና ባላባቱን ለማስለመድም እየከፈሉ መብላት ሲጀምሩ ምግብ ለሽያጭ በመቅረቡ ወቅታውያኑ እንደተደመሙ ሁሉ ስራ ፈጣሪው ኤርሚያስ አመልጋ የውኃውን መፍለቂያ ይዞ “Highland” ሲል በመጥራት ዛሬም ድረስ ለታሸጉ ውኃዎች በቅፅል መጠሪያነት የምንጠቀምበትን ስያሜ ሰጥቶ ሲያቀብለን ጉድ መባሉ አልቀረም ነበር….

ይህንን ሁሉ የማነሳው ለምን መሰለህ ወዳጄ?! የዘፈኑ ግጥማዊ ስንኞች እምብዛም ባይማርኩኝና ግልፅነትም ቢጎድላቸው ዳዊት ፅጌ “ድኃ አይጣላ ከውኃ” በሚለው ዘፈኑ “ባላገሩ” ይሉትን የሙዚቃ ተሰጥዖ ውድድር ከማሸነፉጋ “የኔ ዜማ” የሚል ርዕስ በሰጠው ቀዳሚ አልበሙ ስርም አካትቶታል… ዘፈኑን ርዕሱ እንደከበደው ተሰምቶኝ ሳውጠነጥን እውነትም “ድኃ አይጣላ ከውኃ!” ባልኩበት ቅፅበት “ውኃን ለድኃ ያለው ማን ነው?” ይሉ የነበሩ እቴጌና ባለቤታቸው ታወሱኝ… እቴጌይቱና ባለማዕረግ ባለቤታቸው ውኃን ንቀው በጉሮሯቸው የሚንቆረቆር ጠጅ ብቻ ነበር…. ሊያውም የማሩን ጠጅ!

ከቀናት በአንዱ ቀን…. በቀደመው ክፍል ዳቦ ተርበው አደባባይ ለአብዮታዊ ተቃውሞ ሲሰባሰቡ “አክሳሪዋ እመቤት/Madame Deficit” የሚል ቅፅል በፈረንሳውያን የተሰጣት ብኩን ልዕልት (ንግሥት) ሜሪ አንቶይኔት/Marie Antoninette “ለምን ኬክ አይበሉም?!” ብላ መሳለቋን እንደነገርኩህ ሁሉ ይህች ያንተ እቴጌና ባለቤቷም ገረዶቻቸውና አሽከሮቻቸው “የድኃ መጠጥ” እያሉ ውኃን በፍቅር ሲጠጡት ተመለከቱና ምንነቱን ጠየቁ…. ያኔ እንደዘንድሮው ውኃ ያልተበከለ ነበርና “የድኃ መጠጥማ ንፁህ ውኃ ነው!” ተባሉ፡፡ አጅሬዎቹ በትዕዛዝ አስመጥተው ቢቀምሱት በእርካታው ተደንቀው “ውኃን ለድኃ ያለው ማናባቱ ነው? ይሄማ የእኛ ነው!” ማለታቸውን አንብቤያለሁ፡፡

እዚህ ጎረቤትህ ሱዳን ለዘመናት መንበሩ ላይ የሰለጠኑበትን ኦማር ሐሰን አል-በሽር ከወንበር ያፈናቀለው “የዳቦ ጥያቄ” እንደነበረ ትረሳለህን?! አገርህ “አባይ ወንዛወንዙ ብዙ ነው መዘዙ!” ከተባለለት ጀምሮ በርከት ያሉ ወንዞችና ሐይቆች ባለቤት ብትሆንም “የሚበሉት ውኃ የሚጠጡት ውኃ” የሚለውን የእጅጋየሁ ሽባባው አባያዊ ስንኝ ተነፍጋለችና “ውኃን ለድኃ ያለው ማን ነው? ይሄማ የእኛ ነው!” እየተባልክ ዛሬም ከግብፅና ሱዳን በኩል ቢዛትብህ እንዳይደንቅህ ወዳጄ ልቤ…. አየህ! የውኃን ጉልበት?! ውኃ ፖለቲካህንም ህይወትህንም መልካም ጉርብትናህንና ወዳጅነትህንም ነው የሚያሾረው…. እናማ “ጭሮ አዳሪ ነኝ!” የሚለው ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ አለማየሁ እሸቴ በርካታ ድኃ ተኮር የሙዚቃ ስንኞችን ያሰናኘና በድምፁም የተጫወተ ሲሆን ሲያገኝ በልቶ ሲያጣ ጦሙን እንደሚያድር በሚያወሳበት አንድ ሙዚቃው፡-

“ጥራጥሬም ቢሆን - ቆልተን እየበላን
ተመስገን እያልነው - ውኃን እየጠጣን፤
ስቀን ተሳስቀን - ካልኖርን እኔና አንቺ
ክፉ ቀን አያልፍም - እስከጊዜው በርቺ፡፡”

እያለ ፈረስን ያለልጓም ለመጋለብ ቢሞክርና በሌላ ተቀራራቢ የሙዚቃ ግጥሙ በድህነትህ ቁስል ላይ እንዲህ እንጨት ሲሰድበት ታደምጠው ይሆናል፡-

“አንድ እፍኝ ቆሎዬን - እቆረጥምና
አንድ ኩባያ ውኃ - ችልስ አደርግና
ተመስገን እላለሁ - ኑሮ ይባልና!”

አሌክሶ እንዲህ እያለ “በድህነት ኩራት” እና “በድህነት ስላቅ” መካከል ሲመላለስ ብታስተውለውም “ድኃ የሚበላው ቢያጣ የሚገብረው አያጣም!” በሚለው ነባር ፈሊጥ ሳቢያ ይሄንኑ ኑሮህን የሚፈልጠው ብዙ ነውና የችጋሩ ገብስ ቆሎ እንኳ ቅንጦት የሚሆንበት ይበዛል… ስለውኃ ከተነሳ ዘንዳ… ዓረቦቹ “እጅህን ወደባህር ስደድ፤ ከሆነልህ ዓሳ ይዘህ ትወጣለህ፡፡ ያ ባይሳካልህ ደግሞ እጅህን ትታጠባለህ!” ይሉት ብሂል አላቸው፡፡ ይህንኑ ሲያጠነክሩትም “ዕድለኛ ሰውን ወደባህር ብትወረውረው እንኳ በአፉ ዓሳ ይዞ ይወጣል!” እስከማለት ይገፋሉ፡፡

ይቺ ከፊል እውነት ስትሆን የተዘነጋው ከፊል “The Remaining Half” ደግሞ… ዕድለ ቢስ ስትሆን ለዓሣ መያዝ አልያም ለትጥቢያ ወደባህር የዶልከውን እጅህን ከፊል ጣቶች አልያም ሙላውን በባህር ውስጥ እንስሳት ንክሻ ልታጣ መቻልህ ነው… የወግ አባቱ መስፍን ኃ/ማርያም ይህንን አይነቱን እውነታ “ጨለምተኝነት/Pessimism” ቢለውም እውነት እውነት እልሃለሁ ወዳጄ… ተስፈኛም ጨለምተኛም አይደለሁም… ሃንስ ሮሊንግ መግቢያዬ ላይ እንደነገረህ “I am neither an Optimist nor a Pessimist. But a Possibilist.”

በተያያዘ ዜና….

በእርግጥ “Luck is where preparation meets opportunity!” ምንም ብትማር ብትመረመር አልያም ጠንክረህ ብትሰራ ዕድል ብሎልህ ሁኔታዎች ካልፈቀዱ አትበለጥግም…. ኃብታም የመሆን አንዱ ትኬት የሚገዛው ደግሞ ከቤተሰብ ነው ካላመንከኝ እነሆ ሌላ ንንብ ልጠቁምህ እገደዳለሁ “Rich dad, poor dad" ይሉትን መፅሃፍ ወኦዲዮ አገላብጥ፡፡ ሀብት ሁሉ በዕድል አጋጣሚ ብቻ ይመጣል እያልኩህ አይደለም፡፡ ጠንክሮ መስራት ሀብትን የሚፈጥርባቸው ጊዜያቶች ቢኖሩም ቴነኛ ኢኮኖሚያዊ ስርዓትን ግድ ይላሉ… በአገርህ ከባለሠማያዊው ኮሌታ ላብ-አደር (blue-collars) በላይ የሚፈጋ ባይኖርም ኑሮውን የምታውቀው ነው…. እናስ ድሆች በዕድል ቢያምኑ ተፈርዳለህን….

አገርህ ከአህጉረ አፍሪካ ብሎም ከዓለም በድህነት የሁለተኝነቱን ቦታ ስለመያዟ ታዋቂውና በአዋቂነትም የተመሰከረለት ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥናት ሲያረዳት በወቅቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የተግባቦት ተሹዋሚ የነበሩት ሀጂ ኢብሳ “ጥናቱን አንብቤዋለሁ! እኛ እንደመንግሥት ማንም እብድ ከመሬት ተነስቶ አጠናሁ ብሎ የሚያውጣውን ሪፖርት አንቀበልም!” ብለው ሲየያስቁንም ሲያስለቅሱንም ነበር…. በዓለማችን እጅግ ድሆች የተባባ ሰዎች በብዛት ከሚኖሩባቸው አምስት አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያችን ሆና ሳለ ሰውዬው ወፍራሙን እንጀራ ይበላሉና እንዲህ ቢሉ አይድነቅህ….

በእርግጥ ድህነት ክብረ-ነክ ነውና መንግስትህ ለእርዳታ ሲሰለፍ አፍታም እንደማይፈጅበት ትመለከትና ራስህን ትጠላለህ… ድህነት ክፉ ባለጋራ ነው፤ ክብርህንና ስብዕናህን ብቻ ሳይሆን ወዳጆችህንም ያሳጣሃል፡፡ ከማትቃቃረው አቃቅሮ ከማትቆራረጠው ያቀያይምሃል… ፈረንሳዮቹ ህሊና ካልኮራ ሆድ አይጠግብም! እንደሚሉት ካልሆነ በቀር ሰው አይጠግብም፤ አይጠረቃምም፡፡ ድህነት ደግሞ ይበልጥ ንፉግና ስስታም ያደርጋልና ነው የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ረገድ የማይሳካላቸው ይላሉ የሥነ-ሥሥት ልሂቃን ሃሃሃሃ

የሆነው ሆኖ… ሰው ምንም ይዞ አልመጣምና ምንም ይዞ እንደማይሄድ ሲታወቅ፤ እኛ ሰፈር ውስጥ እየኖረ በፍቅር እጦት የተመታ፤ ኑኑና መደቡን ከእናንተ ሰፈር አድርጎም ፍቅር የሞላው አይጠፋም፡፡ ሀብታሞች ለስጋቸው ሆድ እንደሚፈልጉ ስነግርህ ድሆች ለሆዳቸው ስጋ ይፈልጋሉ ብዬህም አልነበር… ይህንን ደግሞ ደበበ ሰይፉ “ለራስ በተፃፈ ደብዳቤ” ይልቁንም “በደል” የሚለው ግጥሙ በደንብ ይገልፀዋልና እስከቀጣዩ የመጨረሻ ቀጠሯችን አነሆ:-

“ዝናብ ቢኖር በእጃችሁ - ምን ያደርጋል?
አንዲት ጠብታ ሞታችሁ!
አዝመራችሁን - ወፍ አይቀምሰው
የለማኝ አቁፋዳ አያውቀው፤
እንደሌላው አንድ አፍ ሲፈጥርላችሁ - አይደል የበደላችሁ?!
ያዘመራችሁትን እንዳትበሉ - የሮሯችሁ ጥበቱ
ያላችሁን እንዳተድሉ - የእጃችሁ እጥረቱ!”

-ሠለም ለእናንተ ይሁን-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :