ዕድል ከሌለህ…. ድኃ ትሆናለህ!!! (ወግ መቋጫ ሶስት - ስላቀ ምግብ ወልባስ!)

No luckሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

February 4, 2021

“ሀብታሞች ለስጋቸው ሆድ ሲፈልጉ
ድሆች ደግሞ ለሆዳቸው ስጋ ይፈልጋሉ!”
(የሕይወት ተቃርኖ)

“ሱፉን ግጥም አርጎ ተከርክሞ ፀጉሩን
መልዓክ መስሎ ታየኝ ወይ ያለው ማማሩ!”
(አስቴር አወቀ - በህዝብኛ)

አገርህ በንዋዩ በኩል ባትታደልም የበዓላት ሀብታም ነችና በቀደመው ፅሁፌ በተሳልቆ ውኃ ከነቋቆርኩህ በኋላ ተጣፍተን ከረምን፡፡ እንደምን አለህልኝ ወዳጄ ልቤ?! በዓላትን መለዮዋ ባደረገች ቺስታ አገር ላይ በዓሉስ እንዴት አለፈልህ ይሆን?! ያው የገናን ቅንጥብጣቢ ለጥምቀት ከሚያሻግሩት እንጂ ጥምቀትንም ራሱን የቻለ በዓል ከሚያደርጉት ወገን አይደለህም ብዬ ነው…. አልሞላ ያለ ኑሮህስ እንዴት ይዞሃል…?! ለነገሩ የድኃ ነገር ሆኖ ጠግባችሁ የበላችሁና ከርሳችሁ የሞላ ቀን የዓመት ርኃባችሁን ትረሳላችሁና አይዞን! “ያልተፈተነ አያልፍም!” ነው ነገሩ፡፡

በቀደመው ክፍል “ድኃ አይጣላ ከውኃ!” ይሉትን በተሟላ መልዕክት ስር ያልተሟላ ሆኖ የቀረበልንን የሙዚቃ ግጥም ስናነሳሳ በድምፅም በቀልድና ጨዋታውም አይጠገቤ ከመሆኑም በላይ ድህነቱና ድህነታችን ላይ “እህ!” በሚያስብል ግራሜ ሳቅ ይፈጥርልን የነበረውን የካሳ ልጅ ተስፋዬን ከቻርሊ ቻፕሊን ጋር አማስለን አውስተነውም አልነበር?! ሌላ “ድኃ-ተኮር” ጨዋታውን ደግመን ወደቀጣዩ ወጋችን አሻግርሃለሁ - እመነኝ ሃሃሃ

በነገርህ ላይ “አሻግርሃለሁ!” ስትባል ከምን ወደምን እንደምትሸጋገር ካልጠየቅክ ችግሩ ካንተ እንጂ ከአሻግሬ አይደለም… አገርህ እንደዘወትሯ “አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታና ሰብዓዊ ድጋፍ” ከመጠየቅ ባሻገር ጦርነትና ግጭቱም የተረጂውን ቁጥር አንሮታል እልሃለሁ…. እናልህ… ጓድ ተስፋዬ ካሳ በሌላ ጨዋታው አንዲትን ችግረኛ እናት ጠቅሶ ከአይረቤዎቹና ሀያሲና ደራሲ ብርሀኑ ደቦጭ “የድንቁርና ጌቶች” ሲል ወደ አማርኛ የተረጎመልህ የድህነት ዘበኞች (Lords of Poverty) ከሚባሉት የፈረንጅ ባህል አስታጣቂ መያዶች (NGO’s) አንዱ ፈንዱን ይበላበት ምክንያት ሲያጣ “የእጅ መታጠብ ቀን!” ይሉትን አጓጉል አመጣ ይልሃል….

አበሉን በዶላር የበሉ የድርጅቱ “አባላት” እኚህን ችግረኛ እናት መንገድ ላይ ያስቆሟቸወና ካሜራ ደግነው እጅን መታጠብ ስላለው ጠቀሜታ እንዲሁም ዘወትር ምግብ ከመበላቱ በፊት እጅን መታጠብ አስፈላጊ ስለመሆኑ ሲደሰኩሯቸው ሴትዮይቱ “ምግብ ባገኝማ ኖሮ እንኳንስና እጄን ገላዬንም በታጠብኩና በበላሁ ነበር!” ብለው መልሰውላቸዋል ስለማለቱ አንብቤያለሁ…. አይመምህ ወዳጄ! የተራራቅነው ይህንን ያህል ነው… ካላመንከኝ ለቁራስ ዳቦ የቁሻሻ መጣያ ገንዳ የሚፈትሹና ኑሯቸውንም እዚያው ያደረጉ ወገኖችን ቁጥር ማሻቀብ ተመልከት! ይሄ አይስማማኝም ካልክ ደግሞ በአምስቱም አቅጣጫ ከአዲስ አበባ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ርቀህ ተመለስና ድህነትን ከጓደኞቼ ድንቁርናና ኋላቀርነት ጋር አይተኸው ተመለስ… አየኸው የድህነትን ፉንጋነት?!

የበላ ባይጥል - ይገለብጣል!

በእርግጥ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “ሀበሻ ሆዱን ይወዳል!” ሲሉ በነቆሩት ሥርዓተ ማህበር ውስጥ “የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም!” እየተባለልህ ያደግህ ነህ…. ይኸው ሥርዓት “የበላ ባይጥል ይገለብጣል!” እያለ ሲፅናና ሰምተኸውም ይሆናልና በሽበሽ የሆኑለትን በዓላትን እያመካኘ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ቢሮዎችን ሲያራቁትና ይበልጥ ለመደህየት ከዚያችው ላይ ማባከኑ የሚጠበቅ ነው…. የተማረ ሲወድቅ በዚሁ ባንተው የወጣኒነት ዘመን ስለማየትህ እርግጠኛ ነኝና “የበላ” የሚለው እውነትነቱ ዘል-ዓለማዊ ነውና እሱን ላስመልክትህ… ተከተለኝ!

አንተ ዶ/ር ብርኃኔ ረዳኢን የምታውቀው “በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ” ውስጥ ባለው የስራ ኃላፊነት ሊሆን ቢችልም በዝነኛዋ “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት እንዲሁም በታዋቂዋ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ ሙያውን የተመለከቱ ቁም-ነገሮችን እያዋዛ በአምደኝነት ይፅፍ እንደነበር ላስታውስህና “የዕንቁላል ነገር” የሚል ርዕስ የሰጠውን አንድ መጣጥፉን ከሁለቱ ህትመቶች የመነሻና መድረሻ ቃላት ወስዶ ባሳተመው “አዲስ እና ጉዳይ” በተሰኘው መፅሐፉ በኩል ያቀበለህን እንካ…. ዶክተርዬ “ለምለሚቷ” ሲላት ከኖረው አገረ ጦቢያ ወጥቶ ራሽያ ለትምህርት ሲሄድ ልምላሜዋን አስተውሎ በመደነቅ “ኢትዮጵያ ከሶቪየት ህበረት ቀጥላ…” ለምለም መባል እንደሚኖርባት ገልፆ በህበረቱ የፍርሰት ዋዜማ ላይ ምቾት ወድሎቱ መቀነሱን ጠቃቅሶ ለቤተሰቦቹ ሲፅፍ ይህንን ነበር የከተበው፡- “አሁን ትልቅ ችግር አለ፡፡ ምግብ በራሽን ሆኗል፡፡ ለወር የተፈቀደልን ሰላሳ እንቁለካል ብቻ ነው…” የሚል ነበር፡፡

ሆኖም ከለምለሚቱ ኢትዮጵያ… የደረሰው የቤተሰቦቹ መልስ ይህ እንደነበር በኃዘን ውስጥ ሆኖ አስፍሯል…. “ልጃችን ሆይ! ምነው እባክህ? እንዲህ ማማረርህ ደግ አይደለም፡፡ ጡር አለው፡፡ አንተ እዚህ እያለህ በወር አይደለም ሰላሳ እንቁላል ሶስት እንቁላልስ ትበላ ነበር ወይ?” እናልህ ወዳጄ…. ዕድል ከሌለህ ድኃ ትሆናለህና “በወር ውስጥ ምን ያህል ዕንቁላል ትበላለህ?” ብዬ አልጠይቅህም ሄደህ “ስጋና ዕንቁላልን የሚተኩ ምግቦች!” እየተባልክ ሽንብራና አሹቅህ ላይ እንደምትሰፍርባቸው አውቃለኋ… እሱንም ከታደልክ ነው!

ይልቅ ወደ ዶ/ሩ ዋዘኛ ልመልስህ ይህንን ከኢትዮጵያ የተሰደደለትን ምላሽ ከተሳለቀበት በኋላ ልጅነቱን ሲያስብ “…እውነትም ለካ ብዙ ዕንቁላል አልበላም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነው መሰለኝ አንዴ 5ኛ ክፍል እያለሁ ከአንድ የክፍል ጓደኛዬ ጋር ጠብ ገጠምን፡፡ ተሸነፍኩ፡፡ ስንገላገል እንደገና ካልገጠምኩ አልኩኝ፡፡ ከዚያ አገላጋዮች ‘ይቅርብህ! እሱ እንዳንተ ቂጣ በሻይ እየበላ አይደለም የሚመጣው፡፡ ዕንቁላል ጥብስ ነው ቁርሱ!’ አሉኝ፡፡ ያኔ በቂጣ እና በዕንቁላል መካከል ያለው ልዩነት ከጣዕምና ከሽታ መለያየት በስተቀር ብዙም የማይገባኝ ቢሆንም፤ አሁን ሲገባኝ ደግሞ በእውነትም በእናቴ ማህፀን ውስጥ እያለሁ ጀምሮ ዕንቁላል ብመገብ ኖሮ በአዕምሮም በአካልም የት በደረስኩ አስብሎኛል…” ይልሃል፡፡

ዶ/ር ብዙም ቂጣን እንዳላሰደበ ለመፅናኛና ማፅናኛ የከተባት ትቆየንና “ዛሬ ደግሞ በምን ትውስ አልኩህ?” ብትለኝ ኤልያስ ተባባል ይሉት ድምፀ ቆንጆ ዘፋኝ ምን አግኝቶት እንዳዜመው ባላውቅም የ40ቀን ዕጣ ፈንታውን ከዕድሉ ጋር ሰፍቶ እንዲህ እያማረረ ሲረግም አገኘሁትና ነው የሚል ይሆናል መልሴ “ዕድሌ ዕድሌ ጠማማ ጠማማ…” ስለምግብ ከተነሳ ዘንዳ በዚያን ሰሞን “ለምን ኬክ አይበሉም?” ብላ ዳቦ የራበውንና “ቢገድሉት ቢገድሉት የማያልቅ!” ሲል አቤ ጉበኛ የቀፀለለትን ሰፊ ሰልፈኛ ድኃ ህዝብ ላይ ስለተሳለቀችው ንግሥት ትሁን ልዕልት አውግቼህ ነበርና ከላይ ከጠቀስኩልህ ህትመቶች የአንደኛው ተረፍ በሆነችልን “ፒያሳ ማህሙድ ጋር ጠብቂኝ” ውስጥ እንዲህ ሲሳለቁብህ አነበብኩ፡-

“ፒያሳ የኬክ አገር ናት …. በተለይ የ‹‹ኤንሪኮ›› ኬክ ይምጣብኝ፡፡ እስኪ በሞቴ ከዚህ ቤት ሂዴና ኬክ እዘዝ፡፡ ኪኒን ኪኒን የሚያካክለ ኬኮች ይቀርቡልሀል፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልሆንክ ታኮርፋለህ፡፡ አንተ የለመድከው ድፎ ዳቦ የሚያካክሉ ኬኮችን ነዋ… እስኪ በሞቴ ቅመሰው! ከዚያ በአድናቆት ጭንቅላትህን ትወዘውዘዋለህ፡፡ ካልጣመህ ግን በኬክ አላደግክም ማለት ነው፡፡ ሂድና ሸዋ ዳቦ ተሰለፍ……” ይልሃል ጋዜጠኛ መሐመድ ሰልማን፡፡ ምን ትጠብቃለህ? በል ሂደህ ተጣድ!

ለነገሩ ደራሲውም እንዳንተው ጥናዣም ድኃ መሆኑን በመፅሃፉ ላይ አምኗልና ሲቀጥል “ኤንሪኮ ውስጥ ዞር ዞር ብለህ ከጎንህ ያለውን ሰውዬ ገሌመጥ ለማድረግ ሞክር፡፡ የሆነ ሰውዬ በትኩረት ኬክ ሲበሊ ታየዋለህ፡፡ በእርግጠኝነት ስለሰውዬው ብትጠይቅ ከተማዋ ውስጥ ካየሃቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች የአንዱ ባለቤት ሆኖ ታገኘዋህ፡፡ ፎቅ ባይኖረው እንኳ ፎቅ የሚሰራ ብር ያለው ለመሆኑ አትጠራጠር፡፡ ይህም ባይኖረው አንድ ቀን የማግኘት ተስፋ ያለው ነው፡፡ የኤንሪኮ የውስጥ ገፅታ አለመጮህ ተራ ቤት እንደሆነ ሊያስገምትህ ይችላል፡፡ አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልህ፣ ይህ ቤት የሞጃዎች መናኸሪያ ነው፡፡ ስለዚህ አትንቀዥቀዥ!” ይልሀል፡፡

መፅኛኛም አለው ወዳጄ! እንዲህ የሚል፡- “አንተም ኪስህ ቢነጣ፣ መሄጃ ብታጣ ፒያሳ እንደ ቦሌ “ሂድ ከዚህ!” ብላ ውሻ አታደርግህም፡፡ ቦሌ ብዙ ፎርጅድ የቦሌ ልጆች እየተሳቀቁ የሚስቁባት ሰፈር እንደሆነች ልንገርህ፡፡ ፒያሳ ግን 32 ጥርስና 12 ጥርስ ያሏቸው ዜጎች እኩል የሚስቁባት ቦታ ናት፡፡ “የቦሌ ሌጅ የለውም አባይ” ሲባል ሰምተህ ይሆናል፣ የፒያሳ ሌጅ ደግሞ የለውም ፎርጅድ - ድኃና ሀብታም እየተጋፉ የሚዝናኑባት ድንቅ ስፍራ፡፡” ይልህና “ፒያሳን በካፌዎቿ እንጂ በምግብ ቤቶቿ የሚያውቃት ሕዝብ እምብዛም ነው፡፡ ይህ ግን ድንቁርናና ድህነት ያመጣው ጣጣ እንጂ የፒያሳ ችግር አይደለም፡፡ እመነኝ፡፡ በከተማችን ትልቁ፣ ዝነኛው፣ ውዱና ተወዳጁ ምግብ ቤት የሚገኘው በፒያሳ እንደሆነ የፒያሳ ልጆችም አንዳንዴ ይዘነጉታል፡፡ የከተማችን ዲፕሎማቶች፣ ባለሀብቶች፣ ዘናጭ ምግብ መብላት ሲሹ የት የሚሄዱ ይመስሃል?! ቦሌ እንዳትለኝና እንዳልስቅ፡፡ ፒያሳ ነው የሚመጡት - ካስቲሌ!”

በእርግጥ ደራሲው እንዳለው ካስቲሌን የሚያውቀው ጥቂት ሰው ነው፡፡ ምግብ ቤቱ ያንተ አይነቱ መናኛ የሚገባበት አይደለም ወዳጄ…. ድምፁን አጥፍቶ ነው የሚሰራው፡፡ ስታየው ምግብ ቤትም አይመስልም፡፡ እርሱ እንደሚልህ እንደማንኛውም ምግብ ቤት መስሎህ ዘው የምትልበት አይደለም፡፡ ያንተው ቢጤ ድኃ ዘበኛ ወዝህን አይቶ ያባርርሃል፡፡ አዎና! እዚህ ቤት መብላት ካማረህ አስቀድመህ በስልክ ቦታ አስይዘህ ነዋ የምትሄደው፡፡ ደግሞ ዘንጠህ ካልሄድክ አስተናጋጅ መስለሃቸው “ሄሎ! ማነህ… እዚህጋ እስኪ የዳቦ ክሬም ጨምር፡፡” ይሉህና ከፍተኛ የሞራል ኪሳራ ደርሶብህ በልቼ እወፍራለሁ ያልከው ሰውዬ ከስተህ ልትመለስ ትችላለህ ይልሃል….

ተኖረና ተሞተ - ድንቄም!

ድሆች የገበታው ራት አይነት ባይበዛውም “ከፍትፍቱ ፊቱ!” እያሉ ፊታቸውን እንደሚያወዙ ቢደመጥም ያው ድኃ ናቸውና ፊትም ፍትፍትም የሚሰጣቸው የለም፡፡ ላለው የሚጨምርለት ብሔራዊ ሎቶሪ እንኳን ማረፊያውን የሚያደርገው ሀብታሞች ላይ ነው፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል!” ሲሉስ አልሰማህምን?! እንካልህ ተደገም፡-

“ያለው ጮማ ይቁረጥ - የሌለው ባቄላ
ሲያሻው አነፍሮ - ሲያሻው እየቆላ!”

የድሮዎቹ ያንተ ቢጤ ባዶ ኪሶች “አትመልከቺ ሱፍ አትይ መኪና እኔም እገዛለሁ ዕድሌ ሲቃና!” እያሉ በማንጎራጎር ነበር የእንስቷን አንጀት የሚያባቡት፡፡ ያንተ ዘመኗ ሱፉም መኪናውም ከሌለህ እሷም አንጀት የላትም ወዳጄ አትድከም! ከፈለግክ “እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ድኃ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል!” ማለት ትችላለህ… ደጋግሜ እንደነገርኩህ ቀዳዳውን እያሰፋ የሚሄድ እንጂ ትንሽ የሚባል ሽንቁር በህይወት ውስጥ የለም - ድህነትህ ያስገምትሃል - ላለው እንጂ ለነበረው እንደማይሰራ አብዱ ኪያርን መርካቶአዊ የአራዳ ምክር ልትጠይቀው ትችላለህ፡፡ ታሪካዊ ፍቅሮች ሂሳባዊ ሲሆኑ መምስክር ነበራ እሱ… እና ደግሞ አንተን ገንዘብ ባይቀይርህ እንኳ “Money changes the people around you!” ነው ነገሩ…. ይታደሉታል’ንጂ አይታገሉትም!

ካልተዋጠልህ የኤፍሬም ታምሩን “የሰው መሰረቱ” እያደመጥክ በነፃነት መለሠ “ፍርቱና” አወራርደው፡፡ ሙዚቃም ፍልስፍናም ነው፡፡ ሀብት የመታደል፣ የከፍታና የትልቅነት ምልክት ሲሆን ድህነትና ችጋር ግን የማነስ፣ የመውረድና መዋረድ ማሳያና የትንሽነትም ማስረጃው ነው ይልሃል፡፡ ወዳጄ ልቤ…. ዕድል ከሌለህ ድኃ ትሆናለህ፡፡ ድሃ ስትሆን ደግሞ አትመኝ! በእርግጥ ምኞት አይከለከልም፡፡ ሆኖም ግን “ገንዘብ ሳገኝ….” እያልክ ያጠራቀምካቸው ዕቅዶች ብዛት ሊደፋህም ይችላላ… ስለዚህ ፍላጎቱን የገታ መሞት የጀመረ ነው እያልክ ፍላጎቶችህን ሁሉ ጨቁናቸው! ገንዘብ ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን አሁንና እዚህ የሚያሟሉልን ለእኛ ለባለገንዘቦቹ ብቻ ነው፡፡ ለእኛ - ለፍርድ ባለመብቶቹ!

አንተማ “የፍርድ ባለዕዳ!” ተብለሃልና “ባለህ መደሰት” ምናምን ሲሉህ እንዳይሞቅህ ወዳጄ… ምን አለህና በምንህ ትደሰታለህ?!.... የገንዘብ ኃያልነቱ ሰዎች ባለህ የሀብት መጠን የሚሰጡህ ቦታና ክብር መኖሩ ላይ ነው፡፡ ሀብታም ስትሆን የምትገዛቸው ነገሮች መጠቀሚያ ብቻ አይሆኑም፡፡ መገለጫም ናቸው እንጂ፡፡ በዚያ ላይ “brand” ይሉት የሳልቫጅ ተቃራኒ አለልህ፡፡ እስኪ ማን ይሙት አንተ በህይወት ዘመንህ ለእግር ሹራብ (ካልሲ) ከአንድ ሺህ ብር በላይ አውጥተህ ገዝተህ ታውቃለህ?! እኮ! ከላይ እስከታች ያለው “ልባስህ” ቢገመት እንኳ ሺህ አይሞላም!

አሁን ነው “የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ!” እያልክ ካንተ በታች ያሉትን ቁልቁል ማየት…. ድሮ ድሮ ንግሥና በገንዘብህ ልክ ነበር፡፡ በእርግጥ ዘንድሮም ቢሆን አንጋሾቹ እኛው ነን… ትንንሽ ንግስናዎቻችን እንዳሉ ሆነው ማለቴ ነው፡፡ አንተ መቶ ብር ያረረብህ ድኃ ነህና ልጅህን “ሚሊዮን” ብለህ ብትሰይመው አልፈርድብህም፡፡ እናማ… ሌሎች ሰርቀው ሲከብሩ፣ ከታችኛው ምድብ በድንገት ተፈትልከው ከላይኛው ሲሰኩ፣ የምትኖርበት ህብረተሰብ ተሸናፊ ነህ ብሎ ሲሳለቅብህ ፣ አንተም ሽንፈት ይውጥሃል፡፡ ስለዚህ ላለመሸነፍ ስትል አንተም ትገባበታለህ፡፡ ሲሰርቁ ትሰርቃለህ፡፡ ተራ ሌባም ባትሆን፣ ያንተ ባልሆነው መክበርን መሻትህ ግን ከተራዎቹ ተርታ ያስመድብሃል፡፡

ሥርዓተ ማህበርህ… ሰርቀው ላልተያዙ ሲጨበጨብ አብረህ ታጨበጭባለህ፡፡ የተያዙትን ሲረግም ትረግማለህ፡፡ መስረቅን ሸሽተው ከድሃው ተርታ በተመደቡ ሲሳለቁ፣ በስንፍናቸው ሲገረሙ ትታደማቸዋለህ፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል!” እያለ አይደል ያሳደገህ?! ብዙዎች የሚያከብሩህ ባለህሊና ድኃ ስትሆን ሳይሆን ባለገንዘብ ሞራለ-ቢስ ስትሆን ነው፡፡ ሁለቱ ደግሞ አንድ ላይ የሉም!!!

ሥርዓተ ማህበርህ… ለስርቆት ቅጣትን ሳይሆን ሽልማትን ሲያድል…. ግራ ይገባህ ይሆናል፡፡ እያደር ግን ትቀበለዋለህ “የማጣት ፍርሃት” ደግሞ የበለጠ ሀብታም መሆንን እያስመኘ በቃኝን ያርቅብሃል፡፡ የቤንጃሚን ፍራንክሊንን “ገንዘብ ደስተኛ እድርጎን አያውቅም፣ ሊያደርገንም አይችልም!” የሚል ሹፈት እንተወውና አጠቃቀምህ እንደሚወስነው እንግባባ… የቃላት ማምታታት ካልሆነ በቀር በገንዘብ ጊዜያዊ ደስታንም ሆነ ዘላቂ እርካታን በአንፃራዊነት ማግኘት ይቻላል፡፡ የንዋይ ነገር ዕድላችንንም ለሌሎች ማካፈል የምንፈልገው ዕድለ-ቢስ ስንሆን ብቻ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡ እናማ… አንተን ድሃውን ማየት የሚደብራቸው ህይወትን በምሉዕነት ለመኖር ነው፣ ታላቁ የማህበራዊ ጥናት ፈላስፋና መምህር የሆነው ጆን ድዊ ፤ድሃ የመኖር መብት የለውም!፤ ያለው ጠልቶህ አይደለም… ጠገራ፤ ሽልንግ፤ ዱዱ፤ ጢና፤ ሀንቲ፤ በከና፤ ቤሳ-ቤስቲን፤ ይሏቸው ክፍልፋዮች እንኳ ከኪስህ ስለራቁ እንጂ!

ድኃ - አይጣላ ከሰልቫጅ?!

በዚህ ወጋችን ስማቸውን ካወሳሳናቸው ተሳላቂዎች ውስጥ አንዱ “ተኖረና ተሞተ - ድንቄም!” ሲሉ የምናውቃቸው አለቃ ገ/ሃና ናቸው፡፡ ድህነት የእጅና እግረ-ሙቅ ነው፡፡ አለቃም በአንድ ወቅት ድግስ ተጠርተው ሲሄዱ በአዳፋ ልብሳቸው ሳቢያ በር-አስከልካዩ “በዚህ ውራጅዎ ገብተውማ የጌታዬን ድግስ አይበሉም!” እያለ ሲያካልባቸው የሰሩትን አስተማሪ ጀብድ አልደግምልህም… ይልቁንም እኔና አንተ እኩል አባል የሆንንበት ማህበረሰብ ለልባስ እንጂ ለነብስ ቦታ አይሰጥምና አንተ ከሆነ ፈረንጅና ዓረብ አገር ፈግቶ እየመጣ “ሰለሞን” ስትል በንጉሡ ስም እያቆላመጥክ ለምትለብሰው ልብስ ኬረዳሽ ነው…

ይህንን “salvaj” አገርህ በመኪና ቢያጥለቀልቃት ከልክላዋለች፡፡ የልብሱን ውራጅ ግን አልቻለችውም፡፡ ዕድለኞቹ “የእራት፤ የክት፤ የአዘቦት፤ የሰንበት፤ የበዓል፤ የሌሊት….” እያልን ስንንበሸበሽበት አንተ ብራንዳቸውን እንኳ ማንበብ ተስኖሃል ወዳጄ! ሂደህ የእሁድና ቅዳሜ ገበያ Sunday Market ተሰለፍ…! ወዳጄ ልቤ ልባስህ ከዘመን አመጣሽ ሌሎች መለኪያዎች ጋር ተዳምሮ በማህበረ-ሥርዓትህ ውስጥ የሚያሰጥህ ቦታ አለና ነው አስቴር አወቀን የጋበዝኩህ፡፡ እናማ… ድህነቱን አማሪካ የፋቀችለት ክበበው ገዳ ፤፤ሰልቫጅ ሰልቫጅ አሉት ስሙን አሳንሰው ከቡቲክ ይበልጣል አጥቦ ለለበሰው!፤፤ እያለ ስለሰልቫጅ ፤ኳሊቲ፤ የዘፈነው መፅናኛ ለአገርህ አይሰራም፡፡ ምናልባት በጭርንቁሷ የኬንያ ናይሮቢ መንደር ኪቢራ “የዓለም የድህነት ጉባዔ” ወቅት የተለወጠ ነገር ኖሮ ለነጨርቆስህ ደርሷቸው እንደሆነ ግን አላውቅም ሃሃሃሃ

የዓለም ባንክ ለድህነት በሰጠው ትርጉም ውስጥ “የህይወትን መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት አለመቻል!” ቢለውም ድህነት በህይወትህ ውስጥ ትናንትን ከዛሬ ጋር እንጂ ነገን እንዳትተስፍ የሚያደርግ የድንቁርና አጋር ነው… አገርህ ለም መሬት ከውኃ ጋር፤ በጋን ከክረምት ጋር፤ ጉልበትን ከችሎታ ጋር ብትይዝም ከረኃብና ችጋር ተምሳሌትነት ያለመውጣቷ ምክንያቶች ዘውዱ ላይ ዕድሜ ልክ ሊደላደሉበት በሚፈልጉ የአህጉራዊ በሽታ ተጠቂ ፖለቲከኞች ሳቢያ ነው… እንደልባሱ ሁሉ የአመለካከቱ ሳልቫጅ ነው ስንዴን እንኳ በውጭ ምንዛሬ እያመጣህ ለሸገር ዳቦ ብታቀርብም ከአገራዊ ኪሳራ ያልዳንከው… የእናቶችን ቡኃቃ መሙላት የሚሳንህ… ከቃሉ ዓመታት በኋላም የዜጎችን ሆድ በቀን ሶስቴ የመብላት ተስፋ ማደላደል የሚያቀትህ… የአርሶና አርብቶ አደሩን ብርታትና ሌማት ማደርጀት የማይሆንልህ…!

በዋነኝነት በፖለቲከኞቻን ሳልቫጅ ሳቢያ - የአመለካከት ሳልቫጅ - ሳቢያ ነው ኑሮህ ካለበት ፈቀቅ የማይለው፡፡ እዚህ ግድም አንድ አፍሪካዊ ቢሊየነር ላስተዋውቅህ፡፡ ሞ ኢብራሂም ይባላሉ፡፡ ሱዳናዊ የቴሌኮም ቢዝነስ ቱጃር (ከበርቴ!) ናቸው፡፡ እናልህ የአፍሪካ ገዢዎች ሥልጣንን እንዲህ በቀላሉ ከሌብነት ያፀዱት፤ በሠላምም ይለቁት መስሏቸው “ፋውንዴሽን” አቋቁመው ሥልጣኑን ያለግርግር ላስረከበ ገዢ አምስት ቢሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ቢሉም እስካሁን ድረስ ሥልጣን በሠላም ማስረከብ ብሎ ነገር የለም This is Africa!

ለዚህም ነው ኢትዮጵያህ በዓለማችን እጅግ ድኃ ሰዎች ከሚኖሩባቸው አምስት አገራት ዝርዝር የምትጠቀስልህ… በዚህ ሳቢያ ነው አገርህና አገሬ ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ ለግጭት እጅግ በጣም የቀረበች ስለመሆኗ የሚነገርህ… ዳሩ “እንኳንስ ዘንቦብሽ…” እንዲሉ አምባገነንነቱን በማበርታት ችጋሩን የምታረዝመው ትከሻህ የማይዝል አንተም አይደለህ?! ብልፅግና ይሉት ከድህነት ሳይሆን ከድሆች ጋር የተጣላ የፖለቲካ ድርጅት ለአገርህ ከድህነት አለመውጣት እስልምናንና ኦርቶዶክስ ክርስትናን በደምሳሳው ተጠያቂ ያደረገበትን ሠነድ እንደተመለከትከው ተስፋ አደርጋለሁ…. እውነት የለውም አልልህም! እውነቱ ግን ከሃይማኖቶቹ እንጂ ከሃይማኖተኛ ነጋዴዎቹ አለመሆኑ ተዘንግቷል… የሆነው ሆኖ የድህነትን ጉዳይ አንስቶ ደራሲው እንደከተበው “ሃይማኖቶች ምን ሰጡን?! ምንስ አሳጡን?!” ብሎ መጠየቁ አይከፋም እላለሁ!

በዕንባ ተለያየን ድኃ በመሆኔ?!

ይህንን ዘፈን መልካሙ ተበጀ ሲጫወተው “የወደደና ያበደ…” ሆኖብህ ሆድህን የሚቦረቡረው ከሆነ እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ችጋራም ድኃ ነህ… በድኃ አገር ድኃ ሆኖ መገኘት ወንጀል እንደሆነ የሚሰብኩ ደፋር ፃድቃን ሀብታሞችን ምንም ልታደርጋቸው ባትችልም በኃይሉ ገ/እግዚአብሄር በተባለው ወግ አዋቂ እንደተሟረተብህ ድንገት ስታፋሽክ በህብረቱ ጥቆማና በፖሊሱ ያላሰለሰ ጥረት ተይዘህ “ድህነት ኃጢያት ነውና ስለድህነት አታውሩ፤ ስለድህነት አትመራመሩ፤ ስለድህነት በማሰብ የበለፀገ የለም! ለራሳችሁም ሆነ ለቀረው ዓለም የምትበጁት ስትበለፅጉ ብቻ ነው!” ይሉት የብልፅግና መፅሐፍ በአስረጅነት ተጠቅሶብህ “የብልፅግና ሊቆች አባት” በሚባለው አሜሪካዊ ደራሲ ዋትልስ ዲ. ዋትልስ ቋንቋ “The Science of Getting Rich” የማይገባህ ተሰኝተህ ከርቸሌ ልትወርድ ትችላለህ….    

የመፅሃፉ ተርጓሚ ኢዮብ ካሣ መፅሃፉ “መጀመርያ በልፅገው በኋላ መፈላሰፍ ለሚሹ…” የተተረጎመ ስለመሆኑ ይነግርሃልና ከመበልፀግህ በፊት እንዳትፈላሰፍ! በእርግጥ ሀብታም ሁሉ አይፀድቅም… ሁሉም ድኃም አይኮነንም! ወጋችንን ስንጀምር ምክንያተ ድህነትን አለማየሁ ገላጋይ “አጥቢያ” በሰኘው ድርሰቱ በአንዱ ገፀ-ባህሪ ስር ተደብቆ ለድኃ ውግንና ቆሞም አልነበር?! ዘሬ ፤ውኃ የሚደንስባትን፤ የአራት ኪሎ ፈረሳ ተከትሎ በየወገኑ ድህነትንና ሀብትን የፅድቅና ኩነኔ ተምሳሌት ሊያደርጉ የተጉም ብዙ ባለብዕሮች ነበሩ… የጠገበና የሞላለት፤ የተራበና የጎደለበት ሁለቱም አንድ አገር ውስጥ…. ሀብታም በበላው ስጋ አጥንት ድኃው በጉንዳን እየተሰቃየ!

በእርግጥ ድኃ ለሀብታም የዓይን ቁስል ነው… እመነኝ ሀብታሞች አንዴ ብቻ የምንኖረውን ህይወታችንን በምልዓት እንዳንኖረው ጉድፍ የሚሆንብን ድኃ ነው፡፡ የሆነው ሆነና ለሀብታም ዓይናችን ከሚደብሩን ብዙ ነገሮች አንዱ የሰፈሮቻችሁ እርጅና ነው፡፡ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ድህነትን እንጂ ድኃን አይጠየፍም ነበር ይላሉ የሚያውቁት፡፡ ዓለማቀፉ ተፅዕኖ ግን እንደዛሬው ብልፅግናህ ሊያስወግደው ባይችል እንኳ ቢያንስ ድህነትን እንዲሸፍነው አስገደደውና በወቅቱ የሆነውን ሲገልፀው ከፎቆቻችን ጀርባ ጭርንቁስ ሰፈር እንጂ ሌላ ፎቅ እንደማታገኝ በመሐመድ ሰልማን የብዕር አንደበት ልጥቀስልህ፡-

“…ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የፎቅ ጥቅም በስንት እንደሚከፈል ታውቃለህ? በሁለት ካልክ ትክክል ነህ፡፡ የመጀመርያው የፎቁ ባለቤት ብ…ዙ መስታወት እንዳለው ማስመስከር ሲሆን ሁለተኛውና ዋነኛው ግን ከፎቁ ጀርባ ያለውን ገመና መሸፈን ነው…. ቆራጡ መንጌ ፎቅ አልደርስልህ ሲለው አይደልንዴ ወሎ ሰፈር ህንፃ ፊት ለፊት ያሉትን ገመናዎች በግንብ ፕላስተር የጋረዳቸው?! መሌ እሳቱ ግን ረጋ ብሎ አሰበ “ችግሩን መቅረፍ ያለብን ከምንጩ ነው!” አለ፡፡ ጭርንቁስ ሰፈሮችን ቡልዶዘር ላከባቸው፡፡ የተማረ ይግደለኝ!!” እናማ… በድህነት ላይ አብዝተው ካዜሙ ሙዚቀኞች አንዱ ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ በአንድ ሙዚቃው እንዲህ ሲል ያቀነቀነው ወዶ እንዳይደለ ትረዳለህ፡-

“ብትውልም መልካም ውለታ - ስለሰው ብትንገላታ
ከሌለህ ማን አለ ደጅህ - ኪስህ ነው የቅርብ ወዳጅህ፡፡”

ሲፈርድብህማ ከአንቀልባ እስከ ቀብርህ (From Cardle to Grave - እንዲሉ) ከገንፎ እስከ ንፍሮህ (ስትገባ አልቅሰህ ስትወጣ የሚያለቅስልህ አጥተህ!) ድሃሃሃ ሆነህ ኖረህ ነጭ ድሃ ሆነህ ትሞታለህ-ዕድልህ ነው ወዳጄ-የተፃፈ የአርባ ምናምን ቀን እጣ ፈንታህ፡፡ ምናልባት ይህንን ማሸነፍ ከቻልክ ብቻ ነው ከ“ንፋስ ነው ዘመዴ!” ተላቅቀህ እንደ አረጋኸን ወራሽ:-

“ያኔማ እንደሰው ስቀየር ሲሞላልኝማ
ያኔማ ተስፋዬ ሲፈካ ሲነጋልኝማ
ያኔማ ፈላጊዬ በዝቶ በዓይን ስታይማ…
ያኔማ ውበቴ ከሆዴ የወጣ ጊዜማ
ያኔማ ቀና ስል ካንገቴ ዓይኔን ስገልጥማ፤
ያኔማ እንባዎቼ ደርቀው ፊቴ ሲጠራማ
ያኔማ ፈተናው ይበዛል ከላልተቋቋምሽማ!”

በቀደመው ክፍል “ህያው ፍቅር” ከተሰኘው የደረጀ በቀለ ድርሰት ላይ ስለሀብታም ልጇ አብነታዊ አኗኗር ቆንጥሬልህም አልነበር?! ዛሬ ደግሞ ደራሲው “ቻርሊ” በሰኘው ቺስታ ገፀ-ባህሪ በኩል ድህነትን ላስመልክትህማ ወዳጄ ልቤ! አብነት “ድህነትም እንደሀብት ህይወት የጣለችልን ዕጣ ነው!” ስትል የድልድሉን ፍትሃዊነት ስትሞግት ቻርሊ ደግሞ እንዲህ ይጠይቃታል:- “አብነት… የምትለብሺው ነገር አጥተሸ በርዶሽ ያውቃል? ወይም የምትጫሚው ጫማ አጥተሸ እግሮችሽ በቀን ሀሩርና በምሽት ቁር ተቃጥለውና ተኮማትረው ያውቃሉ?!… አንቺ ድህነትን እንደጥሩ ዕድል ብትቆጥሪ አልፈርድብሽም፡፡ ከሰይፍ ስለት የሰላ ጥፍሩ አልቧጠጠሸም፤ ከጦር የሾሉ ጥርሶቹ አላኘኩሽም፡፡ ነዲድ እሳቱ አልፈጀሽም፡፡ እና አይፈረድብሽም አብነት፡፡ ተፈጥሮ ከለገሰችን በረከት ጣፋጭ ጣፋጩን እንጂ መራራዋን አልቀመስሽም፡፡ ግማሽ ህይወት እየኖርሽ በመሆኑ ድህነትን ብታሞካሺ አልፈርድብሽም… የምትይው ቢጠፋሽ ድህነትና ድንቁርናም ሊኮራባቸው ይገባል አልሽኝ?”

- ሠላም ለእናንተ ይሁን! -

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :