ሃያ ሰባት ሲደመር - ስንት?!

Lidetu Ayalew bookሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

February 16, 2021

“በታሪክ የሚታወስ መሪ ለመሆን ከፈለግክ ራስህን ሁን - አታስመስል!”
(አቶ ልደቱ አያሌው - ለኮ/ል ዐቢይ አህመድ እንደፃፉላቸው)

የአቶ ልደቱ አያሌው ምህረቱን ፖለቲካዊ እስር መነሻ አድርገን “ሰቆቃወ ልደቱ በአዳማ በቢሾፍቱ!” በሚል ርዕስ በሶስት ክፍል ያስነበብናችሁ መጣጥፍ እንደተጠበቀ ሆኖ እዚሁ ገፃችን ላይ የተነበቡ ሌሎች ፅሁፎች የአቶ ልደቱንም ሆነ የሌሎች አያሌ ኢትዮጵያውያን የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን እስራት ስንቃወም፣ ሰብዓዊ መብታቸውን ያከበረ አያያዝ እንዲደረግላቸው ስንወተውት፣ አቅማችን በፈቀደ ሁሉ ኢ-ሰብዓዊነትንና ጭፍን ወገንተኝነትን ስንተች እንደቆየን ማሳያ ይሆናሉ ብለን እናምናለን፡፡

የነገ ከነገ ወዲያ መንገዳችንም ይኸው ነው፡፡ ለተበደሉትና ለተገፉት ሁሉ ድምፅ መሆንና ለሁሉም እኩል ተቆርቋሪነትን በማሳየት በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እግሩን እንዲተክል መትጋት፡፡ አቶ ልደቱ አያሌው የፍትህ ሥርዓቱን ተቋማዊ የውድቀት ልክ አስመልክተውንም ቢሆን በሐሰት ከተደረቱባቸው ፖለቲካዊ ክሶች በህግና በህሊናቸው እንጂ በሥርዓቱ ባልታሰሩ ነፃ ዳኞች ነፃ ተብለዋል፡፡ ጠበቆቻቸውም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ አይመስልም እንጂ የሌሎች ህሊናና ፖለቲካዊ እስረኞችም ጉዳይ እንዲሁ በፖለቲካዊ መፍትሄ አልቆ አገራችን አብረን ወደምናሸንፍበት (Win-Win) ሥርዓት ብትገባ እንመኛለን፡፡ ለዛሬ የአቶ ልደቱ አያሌውን አዲስ መፅሀፍ “27 ሲደመር 2… ኢትዮጵያ - አዲስ አምባገነናዊ ስርዓትን በማዋለድ ሂደት” መነሻ በማድረግ ውስን ሃሳቦችን አንስቶ ለማሳየት ያህል ሙያዊ ያልሆነ ወፍ በረራዊ ምልከታ (Birds Eye View) እናደርጋለን፡፡ ከቀደመው ተነባቢ ስራቸው “መድሎት፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሶስተኛ አማራጭነት ሚና” አንፃርም ምልከታዬን ላጋራችሁ እሞክራለሁ - ሰናይ ንባብ!

“ኑ ሀገሬን እናዋልዳት!” ሲባል?!

የትኛውም ሥርዓት ለትውልድ ልውውጦሽ መሆን እያቃተው “በአዲስ ሥርዓት” መተካቱ ያለና የነበረ ነው፡፡ ወደፊትም ኗሪነቱ አያጠያይቅም፡፡ ኢትዮጵያችንም ከየትውልዱ የለውጥ ምልከታ አኳያ የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዳች፡፡ የቀዳሚዎቹን አቆይተን የዘመናት የህዝብ ብሶት ወልዶኛል ባዩ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አዲስ አበባ ሲገባ ስጋቱም ተስፋውም አብሮ ነበር፡፡ እያደር ያ “አዲስ” የተባለው ሥርዓት ቢያጥቡት የማይጠራ እስኪሆን ድረስ “አሮጌ” ሆነና በውስጡ ጭቦ በዛበት፡፡ በውጪ ተቃዋሚዎች አየሉበት፡፡ በውስጥ ምንም እንኳ መዳረሻቸውን ያላወቁ ቢሆንም ወጣቶች ታገሉትና ተንገዳግዶ አገራችንንም አንገዳገደ፡፡

ይልቁንም የወጣቶቹ ዓመፃ በአዲስ አበባ ዙሪያ ማነቆውን ሲያጠነክር በአገረ ኢትዮጵያ “ለውጥ” የመምጣቱን አይቀሬነት የተረዱ አንዳንዶች የተረገዘው ልወጣ ዓይነት ላይ እርግጠኛ ባይሆኑም “ከአሮጌው” መሻሉን በማመን ለማዋለዱ አልሰነፉም፡፡ በስጋትና ተስፋ መካከል ሆነውም ቢሆን ሳይነጋገሩ ተግባብተው እንደነበር ብፅፍም አልስትም፡፡ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ለረጅም ጊዜ በሃይማኖታዊ ስብከቶቹና ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን ከዓለማዊ ቁም-ነገሮች ጋር በሰፉ አስደማሚ ወጎቹ የምናውቀው ዲያቆን ዳንዔል ክብረት ነው፡፡

በወቅቱ ዳንዔል “ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት” ሲል የወጎች ስብስብ አሳትሟል፡፡ የዓብይ አህመድ (ኮ/ል) የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪነትንና ፕሬሱንም በአገራችን ታሪክ ታይቶ ይታወቅ በማይመስል የድምፅ ልዩነት ተሹሞበታል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያችን እርሱ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች እየቀረበ እንደሚነግረን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳይሆን አምባገነናዊነት እየተዋለደ ስለመሆኑ ምስክሮች ሆነናል፡፡ ይህንንና መሰል አማካሪዎችን በመንተራሻነት ይዘው ነው “አማካሪነት ሳይሆን ጥሩ አሸርጋጅነት….” ብለው የገለፁት አቶ ልደቱ “27 ሲደመር 2…” በሚል ዓቢይ ርዕስና “ኢትዮጵያ - አዲስ አምባገነናዊ ስርዓትን በማዋለድ ሂደት” በሰኙት ንዑስ ርዕስ ስር የለውጥ ሂደቱ ሽል ጨንግፎብን እንግዴ ልጁን ታቅፈን እንደቀረን የሚነግሩን፡፡

በእርግጥ ሀሳብን ከመ-ጦር የሚፈራው ሥርዓተ ማህበራችንና ሥርዓተ-መንግሥታችን አቶ ልደቱን ለእስር ያበቃቸውም ይህንኑ እምነትና አቋማቸውን በፅሁፎቻቸውና በየቃለ-ጭውውቶቻቸው በድፍረት ከመሞገታቸው ባሻገር ምሁራዊ ትችታቸውን በመፅሐፍ መልኩ ሊጀቡን እየተሰናዱ የነበር በመሆኑ ነው፡፡ የአቶ ልደቱን መፅሐፍ የሽፋን ሥዕል ስመለከት ኮ/ል አስናቀ እንግዳ “ሸክም የማይከብደው ህዝብ” ሲሉ የተውልን ድርሰት ነው የታወሰኝ፡፡ እግሩን ተቀይዶ ዳገት ለመውጣት የሚንገታገት በዚያውም ላይ በነጂው ዱላ እየተነረተ ሸክም ከብዶት የሚታየው የአህያ ምስል ስለእንስሳዋ ካለን ምልከታ ጋር ሲዳመር መልዕክቱ ብዙ “ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ!” እንተባለው ይመስለኛል፡፡

በእርግጥ አቶ ልደቱ “አሽቃባጭ” ካሏቸው አማካሪዎችና “አድር-ባይ” ከሰኟቸው ባለሀብቶች ባልተናነሰ ህዝብንና ሥርዓተ ማህበራችንን እየተቹ ችግራችንን ለማሳየት ችግር የለባቸውም፡፡ “መድሎት - በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሶስተኛ አማራጭነት ሚና” ባሉት ተነባቢ መፅሃፋቸው ስርም “ህዝብ አይሳሳትም!” እያሉ ህዝብን ስለሚያሳስቱ ፖለቲከኞች ባቀረቡት ትችት ህዝብ ድብን አድርጎ እንደሚሚሳት፡- “የኢትዮጵያ ህዝብ በርካታ ጎኖች ያሉት ጠንካራ ሕዝብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁለንተናዊ መልኩ የበቃና የመጠቀ፤ ምንም አይነት እንከን የማይወጣለት ህዝብ እንደሆነ ተደርጎ ያለመጠን እየተሞካሸ የአገሪቱ ችግሮች አካል ሆኖ እንዲቀጥል እየተደረገ ይገኛል፡፡” በማለት ሽፍንፍን ያልጎበኘውን እውነታ አሳይተዋል - ለሚያይ፡፡

ሙግት - የልብና የአዕምሮ!

መታሰቢያነቱን “በስጋ ብቻ ሳይሆን በባህሪም ለወለደኝ አባቴ ለአቶ አያሌው ምህረቱ ይሁን!” ብለው ከሰጡ በኋላ ይህ በመጣጥፍ መልክ ተጀምሮ ለአቅመ መፅሃፍትነት የበቃው ስራ በዘጠኝ ክፍሎች እንደተዋቀረ ማውጫው ይጠቁመናል፡፡ ሆኖም በተለምዶ ከምናውቀው ቀዳሚው ክፍል በፊት የተሰደሩት እነ “የባለአደራው ማስታወሻ” “ምጥን ሃሳብ” “ብለን ነበር እንደመንደርደሪያ” “ሙግት የልብና አዕምሮ” እንዲሁም “መግቢያ”ን እናገኛለን፡፡ እኒህን ልዩ ልዩ ቋጠሮዎች አንባቢ ቢያፍታታቸው ብዙ እንደሚያተርፍ አምናለሁ፡፡

ለአብነትም ከዚህ በፊት በመጣጥፍና በአማራጭነት አቅርበዋቸው በዚህ መፅሀፍ ውስጥም አስፈላጊነታቸውን አምነውበት በስድስተኛው እና ሰባተኛው ክፍል ስር ያካተቷቸው “የዕርቅና የሽግግር መንግሥት” እና በተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ልክ የተሰራው “ሻሞ…! ‘274’ የቅድመ ምርጫ ትንተና” የተሰኙት ስራዎቻቸው መጠቀስ ይችላሉ፡፡ “መግደል” ወንጀል መሆኑን በፖለቲካዊ ድለላ እያለባበሱ ያሉት ገዢያችን መዋዕለ-ዜና ፀሐፊ የሆነው መሐመድ ሰልማን “ሰውየው” ካለው መፅሐፍ በኋላ ሰሞኑን “መግደል መሸነፍ ነው” በሚል ስራ ብቅ ብሏል፡፡ ምናልባትም ሃሳቦችን መሸፈኛ ስትራቴጂ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ አይከፋም…!

የከዚህ በፊቶቹን መጣጥፎች አርትዖት የሰራውና “የባለአደራው ማስታወሻ” ሲል በዳዊት ፅጌ “ጦር ይሰበቃል ወይ ጋሻ በሌለው ሰው” የሙዚቃ ስንኝ አዝማችነት የተከተበውን የጥላሁን አበበ (ወለላው) መልዕክት ሲሻገር በምናገኘው “ምጥን ሃሳብ” ስር መሠረታዊ የፖለቲካ ስንጥቆቻችንን ለመድፈን ሳንሞክርና ቅራኔዎቻችንንም መፍታት ቢያቅተን እንኳ ለማቻቻል ሳንስማማ የምንገባበት ምርጫ መርገምት እንጂ በረከት እንደማያመጣልን ሲገልፁ “ብለን ነበር” ያሉትን ማሳያዎች ነጥብ በነጥብ እየዘረዘሩ ነው፡፡ ይህንኑ ሃሳብ በኋለኛው ገፅ ላይ ከዘረዘሯቸው የአገራችን ችግሮች አኳያ ገምግመቀው፡- “ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምናካሂደው ምርጫ የለውጥ ሂደቱ የመጨረሻ የክሽፈት ማረጋገጫ ማህተም ከመሆን አልፎ ወደዘላቂ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ሊያሸጋግረን አይችልም፡፡” (ገፅ-205) ብለውታለል፡፡

በልብና አዕምሮ ሙጋታቸው “ዐቢይ ካልዲስ” ሲሉ በስልክ ደብተራቸው ከአስር ዓመታት በፊት ስሙን የመዘገቡለት ወዳጃቸውና የዛሬውን ባለጊዜ በመተቸት እና ባለመተቸት መካከል ከራሳቸው ጋር ሲሟገቱ መክረማቸውን ያስመለክቱናል፡፡ አልሆንልህ ብሏቸው በመደመርና ባለመደመር አጥር ላይ ቆመው ግን አልቀሩም፡፡ “በእኛ ሀገር ለሥልጣን የሚበቁ የሀገር መሪዎች ሕጉና መዋቅሩ ከሚፈቅድላቸው አግባብ ውጪ ለራሳቸው ከልክ ያለፈ የሥልጣን ድርሻ ስለሚወስዱ የእነርሱን ስምና ሚና በስፋት ሳይጠቅሱ ሥርዓቱን በጥቅል መተቸት አስቸጋሪና ብዙም ትርጉም የማይሰጥ…” ስለሆነባቸው የልብ ስቅየታቸውን ቀንሰው የአዕምሯቸውን በመጨመር “…በታሪክ የሚታወስ መሪ ለመሆን ከፈለግክ ራስህን ሁን - አታስመስል!” ሲሉ በኢህአዴፈግ ሊቅነትና እርሱን በሚከተለው የአገር ገዢነት ቦታ ላይ ለተቀመጡት “ዐቢይ” የፅሁፍ መልዕክት በመስደድ መጀመራቸውን ይነግሩናል፡፡

በእርግጥ ከዶ/ር ዓብይ እስስታዊና አይጨበጤ ባህሪ እንዲሁም ይፋዊ አቋምን ያለማሳወቅ ኢህአዴጋዊ ድንቅነት አኳያ እርሳቸውንም ሆነ ድርጅታቸውን ለመደገፍም ለመቃወምም የሚቸገሩ የአጥር ላይ ተንጠልጣዮች ብዙዎች ናቸው፡፡ በመግቢያና አንደኛው ምዕራፍ ስር ከለውጡ ሂደት ማን ምን ጠብቆ እንዳገኘና እንዳጣ “የጎራ መደበላለቅ” ሳይፈጥሩ ባይነግሩንም በአመዛኙ “የአንድነት ኃይል” ለሚባለውና እርሳቸውን ጨምሮ ግብሩን የማይመጥን ስም የተሰጠውን ስብስብ ጥበቃ (Expectation) ግን አስነብበውናል፡፡

አቶ ልደቱ በመግቢያቸው በኩል “የሀገራችን ፖለቲካ ቀልሎ የሚያቀል፤ ቆሽሾ የሚያቆሽሽ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡” ካሉን በኋላ የሀገር ጉዳይ አዝማሪው እንዳለው አልተመቻትም ተብሎ በሌላ እናት አትቀየርምና ከራሳቸውና ከሥርዓተ ናህበራችን ግምገማ ሲቀጥሉ የመጪውን ምርጫ ጉዳይ ያነሱና የለውጥ ሂደቱ ክሽፈት የሚረጋገጥበት ማህተም እንደሚሆን ይገልፃሉ፡፡ እዚህ ግድም ደራሲው “ጨለምተኛ!” እንደሚባሉ አላጡትም፡፡ ይልቁንም ተጋፍጦውን ይቀበሉትና አማራጮችን ለውይይትና ገበያ በማቅረብ “ከተራ ዜጎች ጀምሮ የታላቁን የኖቤል የሠላም ሽልማት አዘጋጅ አዘጋጅ ኮሚቴን ጭምር ለማሳሳት የበቃ እጅግ አስቸጋሪና ልዩ ባህሪ ያለው ክስተት!” ያሉትን ሂደት በበጎ ጎን ማውሳቱ ነው የሚጀምሩት፡፡

ደራሲው “የምንጠብቀው ለውጥ ምን ነበር?” ሲሉ በመጠየቅ ምን ጠብቀው ምን እንዳጡ ባብራሩበት በዚህ ክፍል ስር ሁሉም ከየፖለቲካ ምልከታውና አቋሙ በመነሳት ይጠብቀው የነበረው “ለውጥ” መራራቅ ሳቢያ “የለውጥ ሂደቱ ደጋፊዎች” በስድስት ፈርጆች የተከፈሉና “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ንግግሮች ብቻ ረክተው ጥሩ እንቅልፍ የሚተኙ…” ከተሰኙት ጀምሮ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው!” እስከሚሉት ድረስ በባህሪ ዘርዝረዋቸዋል፡፡ በሌላኛው ወገንም “የለውጡ ሂደት ተቃዋሚዎች” የተባሉ ስብስቦች ስርም እንዲሁ አራት ባህርያት ተሰድረዋል፡፡ አንባብያን ከአንዱ ወይም ከሌላው ምድብ ስራ ራሳቸውን ያገኙበታል፡፡

በፅሁፍ የተገለፀው ሃሳብ የእርሳቸው ግላዊ ሃሳቦችና ከፊሎቹም በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በኩል ድርጅቲያዊ አቋም የተወሰደባቸው ስለመሆናቸው የሚገልፁት አቶ ልደቱ ይጠብቁት የነበረው ለውጥ “የአሸናፊነትና ተሸናፊነትን አዙሪት የሚሰብር” እንደነበር አውስተው የሂደቱን ጠንካራ ጎኖች ሲጠቅሱም መልካሞቹን የፖለቲካ ወረቶች “የለውጥ አመራሩ” በአግባቡ እየመነዘረ አልተጠቀመባቸውም ይላሉ፡፡ ሆኖም ከሠላማዊነቱ፣ ከኢህአዴግ ይሁንታ፣ ከአዲስ ትውልድነትና አመራሩም ከኦሮሚያ መገኘቱን እንዲሁም ለታይታ የተደረጉ ቢሆኑም ያስከተላቸውን የበጎ አድራጎት ስራዎች ያነሳሉ፡፡

ለውጡን ምን አከሸፈው - ከዚህስ ወዴት?!

አቶ ልደቱ አያሌውን ከማከብርበት ብዙ ምክንያቶች አንዱ ሰውን በስራው ለማመስገንና ዕውቅና ለመስጠት ንፉግ በቃልና ተግባሩ መዝነው ለመተቸትም ስኑፍ አይደሉምና ነው፡፡ የለውጥ ሂደቱን ምን እንዳከሸፈው ከመመልከታችን በፊት እነሆ ማሳያ ስለስምረቱ፡- “ከሁሉም በላይ ግን የለውጥ ሂደቱ ዋና ውለታ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ከነበረው እጅግ አስፈሪ የፖለቲካ ውጥረት ለጊዜው ወጥተን ስለወደፊት ዕጣ-ፈንታችን እንደዚህ ለመነጋገር የሚያስችል ፋታ ያስገኘልን መሆኑ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ዶ/ር ዐቢይ እንደመሪ ያረከቱት ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በዚያች ዕለት መሪ ሆነው ባይመረጡ ኖሮ፤ ከተመረጡም በኋላ ከላይ የተዘረዘሩትን በጎ እርምጃዎች በፍጥነትና በተከታታይ ባይወስዱ ኖሮ ሀገሪቷ ወደምን አይነት ቀውስ ልትገባ እንደምትችል መገመት ከባድ አይመስለኝም፡፡” (ገፅ-40)

አለመታደል ሆኖ መልካሙ ጅማሮ በሥልጣን አለቅጥ መውደድ ሳቢያ በጅምር መቅረቱን የሚያወሱት አቶ ልደቱ በሂደቱ ውስጥ አራት ወገኖች ተገቢው አክብሮትና ዕውቅና ሳይቸራቸው እንዳለፉ በመጥቀስ የፖለቲካ ባህላችን ከሥሪቱ ተበላሽቶ አጉል ጀብደኝነት ከአሻጥር፣ ወንዳዊነት ከነጋሲ ወዳድነት ጋር የተዛመደበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፉት የግማሽ ክፍለ ዘመን ዓመታት የተከሰቱ የለውጥ ዕድሎችን ማክሸፍ ለኢትዮጵያውያን “ልማዳችን” ሆኖ የፖለቲካ ፅንፈኝነትና ብሔርተኝነት፣ የአመራር ድክመትና አቋም የለሽነት፣ የቃልና ተግባር አለመጣጣም፣ በመሠረታዊ ቅራኔዎቻችን ዙሪያ ያለው የዕውቀትና ልምድ እጦት ላይ የሐቀኝነት እጦትና የቅንነት መጉደል ተደምሮበት የተጀመረው የለውጥ ሂደት መክሸፉን ፅፈዋል፡፡

ደራሲው “ሁሉንም በማስደሰት ማንንም አለማስደሰት!” ይሉትን (To Satisfy all is to Satisfy None!) ምዕራባዊ ብሂል ይዘው በተለየ ሁኔታ ሥልጣን ይወዳል ያሉትን አመራር ሲገመግሙ “ከአማካይ በታች” እንደሰጡት ነግረውን ትንቢት የሚደፍሩ ቢሆን እንዲህ ሲሉ ከመተንበይ እንደማይመለሱም ፅፈውልናል፡- “ብልፅግና ፓርቲ በታሪካችን አይተነው በማናውቅ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ የለየለት አምባገነን የሚሆን፣ ከሥልጣን ወዳድነቱ፣ መከርህ የለሽነቱና ከድርጅታዊ ድክመቱ በመነጨም ‘የፈሪ ዱላ’ በመጠቀም የራሱን ሥልጣንም ሆነ የሀገር ህልውናን በቀላሉ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አደገኛ ፓርቲ ነው፡፡” (ገፅ-175) በማለት ከህግና ሥርዓት ይልቅ ጭቦን ያዘለ የልወደድ ባይነት ፖለቲካ (Tyranny of Popularity) ከራስ ተርፎ ለሀገር የሚከፋ ተረፍ ሊኖረው እንደሚችል በማስጠንቀቅ ምዕራፉን ይዘጉታል፡፡

አቶ ልደቱ በሶስተኛው ክፍል ስር ስለወደፊቱ የአገራችን ዕጣ-ፈንታ ቢሆኖችን (Scenarios) ዘርዘር አድርገው ያስቀመጡ ሲሆን ቀዳሚውና ተፈላጊው ሁሉን አቀፍ በሆነ አካታች የዕርቅና የአንድነት ሽግግር መንግሥት በኩሉ ወደዘላቂና መዋቅራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር መሠረቱን ማኖር ሲሆን ቀሪዎቹ ቢሆኖች ግን ባለንበት የሚያኖሩን አልያም ለአምባገነናዊነት አለፍ ሲልም እጅግ ለከፋ ግጭት የሚዳርጉን ስለመሆናቸው ፅፈዋል፡፡

ሲቀጥሉም “አንድ ህዝብ አንድን ለውጥ ለማግኘት ፈልጎ ትግል ሲያካሂድ ከአሸናፊነት በኋላ ሊያገኘው ስለሚችለው ተጨባጭ ለውጥ አስቀድሞ ማሰብና መጨነቅ የሚያስፈልገው ወደዚህ አይነቱ የባሰ ጣጣ ውስጥ ላለመግባት ነው፡፡ አንድን ህዝብ ከሌላ ህዝብ በበለጠ ብልህ ወይም አዋቂ ሊያስብለው የሚችለውም በዚህ ረገድ የሚኖረው የማስተዋል አቅም ነው… ችግሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ አይነቱ አስተሳሰብ አልታደልንም፡፡ ሁልጊዜም ጭንቀታችን ስለምንጥለው ወይም ስለምናስወግደው መንግሥት እንጂ በምትኩ ስለምናገኘው እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ሆኖ አያውቅም፡፡” (ገፅ-182) በዚህ ብቻ አያበቁም አቶ ልደቱ፡፡ እውነታውን እንዲህ ከገላለጡት በኋላም ቀድመው ያሰፈሯቸውን አራት ቢሆኖች እያጣቀሱና በማሳያዎች እያብራሩ በቃል “ኢትዮጵያ አትፈርስም!” ቢሉንም በተግባራቸው ከሚያፈርሷት “የፖለቲካ ባህታውያን” በተቃራኒ በመቆም የወቅቱ ጥያቄ መሆን ያለበት “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ወይስ አትፈርስም?” ሳይሆን የኢትዮጵያን መፍረስ ሂደት እንዴት አድርገን እናስቁመው? የሚል ነው ይሉናል፡፡

ነገረ ምርጫ - የአሻጋሪና ተሻጋሪ ተውኔት!

የለውጡ ሂደት ያስገኛቸው በጎ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ከአጠቃላይ ውጤት አኳያ ግን “ከድጡ ወደማጡ” ስለመሸጋገራችን የሚያስታውሱ ሃያ ያህል ወሳኝ መመዘኛዎችን ማንበብ አቶ ልደቱ ላይ የሚሰበቀውን ጦር ምንጭ ከወዴትነት እንደሚጠቁም ግልፅ ያደርግልናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እርግጥ ነው በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሣ ዘዋሪነትና በወ/ት ሶልያና ሽመልስ አፈ-ቀላጤነት የቀጠለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅራዊ ችግር ተደባብሶ ለምርጫ እንድንዘገጃጅ ተነግሮናል፡፡

ከለውጡ ወዲህ “ምርጫ ካልተደረገ ሞቼ እገኛለሁ!” ሲል የነበረው ኢህአዴግ-ብልፅግና ቢሆንም አሁን አብሶታል፡፡ ቀድሞም ያለብሔራዊ መግባባት ምርጫውን ማድረግ ጦስ አለው ሲሉ የነበሩት ኢዴፓዎች በምክንያትነት የሚተቅሷቸውን አምስት ያህል መሟገቻዎች አቶ ልደቱ በዚሁ መፅሃፍ በኩል አቅርበውልናል፡፡ ይልቁንም “እንዲህ አይነት አቅጣጫ የጠፋበትና በሐቅም ሆነ በማጭበርበር ምርጫን ለማሸነፍም ሆነ ለመሸነፍ ዝግጁ ያልሆነ፤ ነገር ግን በማንኛውም መንገድ በሥልጣን ለይ መቀጠል አለብኝ ብሎ የወሰነ ፓርቲ በሥልጣን ላይ በሚገኝበት ሁኔታ ወደምርጫ መግባት ሀገራዊ ቀውስን የመምረጥ እንጂ ህጋዊ መንግሥትን ለመምረጥ የሚያበቃ ምርጫ አይሆንም፡፡” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

አቶ ልደቱ ለአዲሱ አይነት አምባገነንነት መዋለድ አበርክቷቸው ቀላል እንዳልሆነ የገለፁላቸውና አቋም አለመያዝን አቋማቸው ያደረጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበራት፣ አድር-ባይ ባለሀብቶች፣ ወዶ-ገብ የብዙኃን መገናኛዎች፣ አሽቃባጭ ምሁራንና አሸርጋጅ አማካሪዎች በቁጥር የበዙ የሚመስሉ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ሲያስተውሉ “ሥርዓቱ አምኖበትና አቅዶ ራሱን ወደአምባገነናዊነት እየቀየረ ብቻ ሳይሆን ሀገሩ እንደሀገር አዲስ አምባገነናዊ ሥርዓት በማዋለድ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑን…” በመጥቀስ የመጪው ትውልድ ተጠያቂነታችንን አይቀሬነት በትዝብታቸው ሲያትቱ በዚህ ሂደት ውስጥም የዘጠና ሰባቱ ቁርሾ እንደተደመረበት ገልፀዋል፡፡

በመፅሃፉ ቀዳሚ ገፅ በብለን ነበር እንደመግቢያ የገቡት አቶ ልደቱ በስምንተኛው ክፍል ስር እንደመደምደሚያ ባቀረቡት “እያልን ነው!” በኩል ለለውጡ ሂደት መክሸፍ “ግንባር ቀደም ተጠያቂ!” እና “የኢህአዴግ ቅሪተ አካል” ሲሉ ከሰየሙት ብልፅግና ፓርቲ ጀምሮ ግራ ለተጋባው የተቃውሞ ጎራና የአምባገነኖችን ጥቅምና ፍላጎት ደግፎ መቆም ለማይገደው የህዝብ ክፍል መልዕክት በማስተላለፍ ይዘጉታል ምዕራፉን፡፡ ደራሲው ለመፅሃፋቸው የመጨረሻ በሆነው ዘጠነኛው ክፍል ላይ ከመፅሃፉ አጠቃላይ ይዘት የተወሰዱትን ሃሳቦች በጨመቅ (Essence) ለመወያያነት በዓብይ እና ንዑስ ርዕሶች ስር ከማቅረባቸው አራት ገፅ ቀደም ስንል “የአጎት ለቅሶ - እንደመውጫ” ሲሉ የተዉልንንና እርሳቸው ወደገቡበት የልብና አዕምሮ ሙግት የሚዶለንን ሃሳብ እናነባለን፡፡

ይህን የፅሁፍ መልዕክት እዚህ ሸርፎ ማቅረቡ ሃሳቡን ማቃለል ይሆንብኛልና አቶ ልደቱ ከአስር ዓመታት በፊት በፃፉትና ለረዥም ጊዜ ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ ለተጋለጡበት አሉባልታ እርጋቤ በፃፉት የአረም እርሻ መፅሃፋቸው በኩል ለህዝብ ካደረሷቸው መልዕክቶች በአንዱ ኃይለቃል ብሰናበታችሁ ወደድኩ፡- “ከዚህ ሁሉ የትግል ሂደት በኋላ እኔ በገዢው ፓርቲ፣ በተቃዋሚው ጎራና በህዝቡ ዘንድ ያለኝን ቦታ ስገመግመው እራሴን እንደገና ዳቦ ከታችም ከላይም በእሳት የምለበለብ ሰው ሆኜ አግኝቼዋለሁ… በቀጣዩ የትግል ሂደት እኔ ኖርኩም አልኖርኩም ከእንግዲህ ትግሉም ሆነ የትግሉ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ያልዘሩበትን የማያበቅል፣ የበቀለውም ሁሉ የማይበላበት የአረም እርሻ ከመሆን እንዲድን ከልቤ እመኛለሁ፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :