ከዓድዋ እስከ ማይጨው… ከካራማራ እስከ ባድመ!

Adwa victory 1896ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

March 8, 2021

“We sleep peaceably in our beds at night only because rough men stand ready to do violence in our behalf!”
(ሰር ዊንስተን ቸርችል)
“ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!”
(ቀኝጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ)

ወግ መያዥያ…

ይህ ያለንበት ወር ከግንቦት ሲለጥቅ በኢትዮጵያችን በርካታ ሁነቶች የተስተናገዱበት ወር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተርፎ ለመላው አፍሪካውያንና ይልቁንም ለጥቁሮች ሁሉ የነፃነት ምልክትና ጭቆናን ያለመሸከም ትዕምርት ሆኗል፡፡ ድሉን ድህነታችን ላይ መድገም ቢያቅተንም አንገታችንን በእኩልነት ቀና አድርገን እንድንሄድ ያስቻለ ታሪክም ተከትቦበታል፡፡ ስለዚህም ብዙ ክብርና ምስጋና ስለነፃነታቸውና ነፃነታችን፤ ስለአገራቸውና አገራችን ሲሉ ለተዋደቁ ሁሉ ይሁንና “የድል በዓል!” እንጂ ከቅኝ ግዛት እንደተላቀቁ ወገኖቻችን የምንዘክረውና “የነፃነት ቀን!” ብለን የምናከብረው በዓል የለም - ኢትዮጵያውያን!

የካቲት ወር ሙሉውን ለዚሁ ድል ዝከራ ቢበረከትም በዚሁ የካቲት ወር አስራ ሁለተኛው ዕለት ላይ በየዓመቱ የምናስበው “የሰማዕታት ቀን!” ግፉን ቢያስታውሰንም እጅ ያለመስጠትንም አስተምሮናልና በተከታዩ ገጠመኝ ወጋችንን እንቀጥላለን፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አካባበቢ ባስገነባውና በ“ገዛኸኝ ይልማ” በሰየመው ቅርንጫፉ በኩል ለመስተናገድ ተራዬን እየጠበቅኩ ነበር፡፡ ሁለት ወጣቶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያወሩ ተከታትለው ሲገቡ መጠነኛ ትኩረትን አገኙ፡፡ ሞቅ እንዳላቸው ያስታውቃሉ፡፡ አንዱ የግራ ሌላኛው ደግሞ የቀኝ እጅ ከክንድ በታች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ልብሳቸው በጣም አድፎ ስለነበር የኔ ቢጤ ይሆናሉ በሚል ግምት ነው መሰል አግኝተውት የነበረው ትኩረት አልዘለቀም፡፡ እንዲያውም የባንኩ ሰራተኞች ጥበቃ ጠርተው እንደሚያስወጧቸው ሊነግሯቸው ሲጀምሩ ጠጋ ብዬ ችግራቸውን ጠየቅኩ፡፡ “ኢሳያስ ወዳጅ ሆነ እኛ ጠላት ሆንን!” አሉኝ፡፡ “ጥበቃ ጠርቼ እንዳላስወጣችሁ!” ያላቸውን የባንኩን ሰራተኛ beመስኮት አሻግረው እየተመለከቱ፡፡ ከዚያ በኋላ ነበር ችግራቸው ገብቶኝ በሀዘን የተመታሁት፡፡ ከዚያ በኋላ ነበር “ለምን ትጠጣላችሁ?” ብዬ ልጠይቅ የነበረውንም በድፍረት ማጣት የተውኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ነበር ስራ ላይ ሆኜ እንኳ ስለ ሀገረ ኢትዮጵያ የጦር ጀግኖች እያብሰለሰልኩ የዋልኩት፡፡

ኢትዮጵያውያን መገራት ያለበት “የጦር ባህል” እንዳለን አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች እስካሁን ድረስ ሁነኛ ማሰሪያ ባልተበጀለት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተሳተፉና ስለሀገረ ኢትዮጵያ ሲሉም የአካል ዋጋ የከፈሉ ባለውለታዎቻችን ናቸው፡፡ አንዱ ከደቡብ ሌላው ከሰሜን ናቸው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ግን በቃ ያው እንደከዚህ በፊቱ ጀግኖቻችን ሁሉ ከወር ወር የማታደርስና እዚህ የማልጠቅሳትን ወርሃዊ የመንግስት ተቆራጭ እየጠበቁ እንዲኖሩ ተገደዱ፡፡ ነገሮች መሻሻል ቢጀምሩም ፍፃሜ አላገኙምና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖችም ሆኑ የቀድሞ ጦር አባላትን ጥቅማ ጥቅም ከነሙሉ ክብሩ ለማስጠበቅ የነበረው ፈተና ከባድ ነበር፡፡ አሁንም ያልተጠናቀቁ ስራዎች አሉ፡፡

ኢትዮጵያዊ ጀግንነት በየዘመኑና በየጊዜው የሚኖር ቢሆንም በተለይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ መሆን ያልነበረባቸው ብዙ ኢ-ሰብዓዊ ነገሮች መሆናቸውን አስተውለናል፡፡ መለዮ ለባሹ በየጎዳናው አንጥፎ ይለምን እንደነበርም የልጅነት ትዝታዬ ይነግረኛል፡፡ ምሽቱን ከስራ መልስ ወደ ብሔራዊ ቴአትር ጎራ ብዬ በዕለቱ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር “ዝክረ የኢትዮጵያ ጀግኖች!” በሚል መሪ ቃል አዘጋጅቶት የነበረውን የሥነ-ፅሁፍ ምሽት ታደምኩ፡፡ በመሰናዶው ጅማሮ ላይ በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሰብሳቢ ልጅ ጆቴ መስፍን እየተመሩ የገቡትንና ከዝክረ-በዓላት ማዳመቂያነት የዘለለ ክብር ያልሰጠናቸውን ጀግኖች አርበኞቻችንን ቆመን አክብረን ተቀበልናቸው፡፡

በተለይ በዕለቱ የመድረክ አጋፋሪ የነበረው ጋሽ ተስፋዬ ማሞ “የደርግ” እየተባለ ይጠራ የነበረውን “የኢትዮጵያ ሰራዊት!” በተመለከተ ትዝታና ትዝብቱን ካወጋጋን በኋላ የጋበዛቸው ታላቅ ጀግና ያደረጉት ንግግር በአዳራሹ የተገኘነውን ሁሉ እንደ ዕድለኛ አስቆጠሩን፡፡ እኚህ ሰው የአብዮታዊት ኢትዮጵያን የላቀ ጀግና ሜዳይ ከተቀበሉት ሁለት ሰዎች አንዱ የሆኑት ጄኔራል ተስፋዬ ሀ/ማርያም ነበሩ፡፡ የጄኔራሉን የጦር ሜዳ ጀብዱ መፅሃፍ ደጋግሜ ባነበውም እሳቸውን በአካል አጊኝቶ ማየትና ማድመጥ መቻል ለኔ ትውልድ መታደል እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ጄኔራሉ ብዙ ቁም ነገሮችን ካስተማሩን በኋላ የቀን ትዝብቴን እንደታዘቡ ሁሉ አንድ የቀድሞ ጦር አባል የነበረን ጀግና አወሱ፡፡ ይህ ግለሰብ አሊ በርኬ ይባላል፡፡ ሚሊሺያ ሆኖ የዘመተ ቢሆንም በጦር ሜዳ ውሎው ባስመዘገበው ውጤትና በፈፀመው ጀብዱ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚ ነው፡፡ ስለሀገር ክብርና ስለዜጎቿ ነፃነት የጀገነው ይህ ሰው ታሪኩ በተለያዩ ጋዜጣና መፅሄቶች ቢነበብለትም ኑሮውን የሚገፋው በድንጋይ ፈለጣ የቀን ስራተኝነት መሆኑን ከጄኔራሉ አንደበት ስንሰማ አንገታችንን ደፋን፡፡

ስለሀገር ነፃነት ዋጋ የከፈሉትን ፊት በምትነሳ ሀገር ውስጥ ሀገርን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ “ወዳጅ!” ሆነው የሀገር ጀግኖች ላይ በቁም እንዲሞቱ መፍረድ ህሊናዊ አይሆንም፡፡ ልድገመው?! ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት ይፋ ይሁን ብዬ ብሞግት ትርጉም ላይኖረው ይችላል፡፡ ያለነው ገዢዎቻችን እንደፈቀዱ በሚያደርጉበት አህጉረ አፍሪካ ነውና፡፡ ኤርትራ በትግራይ ውስጥ ዛሬም ለምትፈፅመው በደል ስለሉዓላዊነት ጮክ ብሎ የሚያወራ እምብዛም አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ የሁለቱ አገራት ገዢዎች ላይ የተንጠለጠለው “የሠላም ስምምነት” ግን ቢያንስ የጀግናውን ኮ/ል በዛብህ ፔጥሮስ የት-መድረስ በተመለከተ ግልፅ ያለ ነገር ሊነግረን፤ ለቤተሰቦቹም እረፍት ለአገርም መታፈሪያ በሆነም ነበር፡፡

ከሶሎዳ ተራራ ግርጌ… ዓድዋ እና ኪነት!

ገጣሚ፣ የቲያትር አዘጋጅና ፀሃፊ ተውኔቱ በስራው እንደነገረን ጀግና በማይከበርባት አገር ጀግና አይበቅልም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ዋጋ የከፈለውና የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር በቀዳማይ መሰናዶው ያስመለከተን ጀግናው በላይ ዘለቀ በክህደት የተሰቀለበትን አደባባይ ቁሳቁስ ስናስተዋውቅበት እንጂ በስሙና ሀውልቱ አስጊጠን ስንዘክረው አለመታየታችን ውርደት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ኢትዮጵያ ነገስታቶቿን ብቻ ሳይሆን የየዘርፉ ጀግኖቿን ይልቁንም የጦር ጀግኖቿን የምር ማክበር ይኖርባታል፡፡

የዓድዋው ጀግና አባ ነብሶ ባልቻ አባ ሳፎ በህይወታቸው የመጨረሻ ዘመናት ላይ ከአገዛዙ የጠበቃቸውን የክብር ጉድለት የምታውቁት ነውና አልፅፈውም፡፡ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) ሽልማቱ በአደባባይ መታነቅ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀግኖቻችን አንዱ የሆነው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በረኃ ሲኳትን ከርሞ የተበረከተለት ምስጋና ቢኖር ጥይት ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ…” እንዲሁ በከንቱ የተገጠመ አልነበረም፡፡

ወደነጥባችን ስንመለስ የዓድዋ ድል ኪነትን አድማቂ ነው፡፡ ኪነትም የዓድዋ ድልን አድምቃለች፡፡ በሙዚቃና ግጥሞች፣ በቴአትርና ፊልሞችም ሆነ በሌሎች ስራዎች ውስጥ ዓድዋ ድርሻው እየጎላና አድማሱም አፍሪካዊነትን እየያዘ መጥቷል፡፡ ከነችግሮቹ መነሻውን ከአቧራማዋ ሰፈር አቧሬ የሚያደርገው “ጉዞ ዓድዋ!” ከአገር ተሻግሮ አህጉራዊነትን መተለሙም ለዚህ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ኪነት ዓድዋን የህዝብ ልብ ውስጥ አኑሯል፡፡ ዓድዋ ሲነሳ ከሸዋ ንጉሥነት ተነስተው የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥትነትን የደረሱበት ዓፄ ምኒልክ አብረው ይወሳሉ፡፡ ይህ ማለት በእርሳቸው ላይ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ቅሬታቸውን ይዘውም ቢሆን ለጋራ አገርና ነፃነት የተዋደቁ በርካታ ነበሩና፡፡

ይልቁንም ስለኪነጥበብና ዓድዋ ሲነሳ “ዓድዋ” ከሚለው የፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ፊልም ባልተናነሰ መልኩ የሚታወሰን ፀጋዬ ገ/መድኅን ቀዌሳ ነው፡፡ ፀጋዬ ማይጨውን በነካካበት የ“እሳት ወይ አበባ” መድብሉ ስር ብዕሩ የጴጥሮስን የመጨረሻ ሰዓት አስመልክቶን ወደ ዓድዋ ይዞን ሲሻገር “ዋ!... ያቺ ዓድዋ” ሲል እንዲህ እናነበዋለን:-

“…ዋ ዓድዋ
የዘር ዐፅመ ርስቷ - የደም ትቢያ መቀነቷ፤
በሞት ከባርነተ ሥርየት - በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ዕለት…
ሲያስተጋባ ከበሮዋ - ሲያስገመግም ዳኘው መድፏ፤
ያባ መቻል ያባ ዳኘው - ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው - በለው - በለው ሲለው
በለው - በለው - በለው ዋ!... ዓድዋ…”

በአገራችን በተደራጀ መልኩ ለህዝብ ማቅረቡ የተለመደ ስላልሆነ የስዕልና ፎቶውን እናቆየውና በሙዚቃው ረገድ እጅጋየሁ ሽባባውን የቀደመ ልጠቅስ አልችልም፡፡ ጂጂ “ሙሽራዬ” በምትላት ኢትዮጵያ ስለሆነው የዓድዋ ድል ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬና ነገም እንደሆነ ስትገልፅ ስለእኛም ስለራሳቸውም፣ ስለአገራችንና አገራቸውም ነፃነት ተዋድቀው ቀና ያደረጉንን ጀግኖች በማክበሩ ረገድ የተዋጣለት ስራ መስራት ችላለችና በየዓውዳመቱ ይሄ ሙዚቃዋ ከሌሎች ስራዎች ሁሉ ከፍ ብሎ ይደመጣል፡፡ ሰው ሰውን ሊያድን ስለመሞቱና ስለክብር ፍጥረትነቱ ካወሳሳችና የጥቁር ድል አምባነቷን ካስታወሰችን በኋላ ይህንን ትለናለች:-

“የተሰጠኝ ህይወት - ዛሬ በነፃነት
ሰው ተከፍሎበታል - ከደምና ከአጥንት
ስንት ወገን ወደቀ - በነፃነት ምድር
ትናገር ዓድዋ - ትናገር ትመስክር
ትናገር ዓድዋ - ትናገር አገሬ
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ!
ነኩራት - በክብር- በደስታ በፍቅር
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን
ደሞ መከራውን - ያን ሁሉ ሰቀቀን፡፡
ዓድዋ ዛሬ ናት - ዓድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት
ምስጋና ለእነሱ - ለዓድዋ ጀግኖች
ለዛሬ ነፃነት - ላበቁን ወገኖች፡፡”

ከጂጂ ሲቀጥል ለዓድዋ ድምቀት ሰጥቶ ዝክሩን የሚያደምቀው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ ዘ አፍሮ ባንድ) ሲሆን “ጥቁር ሰው” በማለት የዓድዋውን ጌታ ዓፄ ምኒሊክን አስተዋውቆ በመጀመር የጦሩን አዛዦች ውሎ እንዲሁም የንግሥቲቱን ሚና በተዋጣለት የምስል ቅንብር ሊያሳየን ችሏል፡፡ ቴዲ “ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ!” ይሉትን የወቅቱን ብሂል ዘወር አድርገጎ ሲነግረን ምኒሊክ በማርያም ምሎ ሲጠራኝ አቤት ሳልል ቀርቼ ቢሆን ኖሮ “እኔን አልሆንም ነበር እኔ!” በማለት ነው፡፡

ይህ የምንሸኘው የየካቲት ወር የጥቁሮች ታሪክ የሚዘከርበት (Black History/ African-American History Month) ወር ነው፡፡ ጂጂ እንዳለችው ነፃነቱን በቀን ቀን ብንኖረውም ያንን ክፉ ሰቀቀንም አብረን እንኖረዋለን፡፡ ከወደድኳቸው ፊልሞች አንዱ የሆነውና “Troy” ከሚለው ፊልም “History remembers kings not soldiers.” የሚለውን ኃይለ-ቃል መሰናበቻዬ ላደርገው ወደድኩ፡፡ ፊልሙን እንደወደዳችሁት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከግሪክ ጦር ጋር ትሮይንe ለማስገበር የሚዘምተውና አኪለስ በሚለው ስሙ በአፈ ታኮች በኩል የተዋወቅነውን ጀግና ንጉሡ እንዲህ ሲለው እንሰማለን፡- “You came here because you want your name to last through the ages… history remembers kings! Not soldiers… My name will last through the ages. Your name is written in sand for the waves to wash away.” እኔም እላለሁ ለንጉሡና መኳንንቶቻቸው እንዲሁም ስማቸው ላልታወቀና ላልተዘመረላቸው ግን ደግሞ ዛሬን በነፃነትና እኔን ሆኜ እንድኖር ላበቁኝ ሁሉ ክብርና ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :