አንዳንድ ነጥቦች - ስለሰሞንኛው ፖለቲካችን

Why we hate each otherሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

April 1, 2021

የዳያስፖራው ፖለቲካ - እንደግመል ሽንት?!

የኢትዮጵያች ፖለቲካ በብዙዎች እንደተተሰፈው ሳይሆን በጥቂት ሩቅ ተመልካቾች ቀድሞም እንደተፈራው “ከድጡ ወደማጡ” እየገባ ስለመሆኑ በድጋፍም ተቃውሞውም ጎራ የተሰለፉ ወገኖቻችን ልቦና የሚረዳው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለእኩልነትና ነፃነት፤ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ለአካታች አገራዊ አንድነት የተደረገውን ትግል በመጥለፍ “የለውጥ ኃይል” ነኝ ብሎ ብቅ ያለውና በኋላ ላይ በኮ/ል ዓብይ አህመድ አሊ የአምባገነንነት ፍላጎትና የንግሥና ምኞተ ፈቃድ ስር ያደረው ኢህአዴጋዊ ስብስብ ከአመራር ክህሎት እጦት ባልተናነሰ በሥልጣን ሽኩቻውና ባደረ የቂም መንገዱ አገራችንን ቁልቁል ይዟት መንደርደር ከጀመረ ሰንብቷል፡፡

አለመታደል ሆኖ ትናንት በዚያ ክፉ የሰቆቃ ዘመን ሽፋን ያልቀየረውን ኢህአዴግ በብርቱ ሲተቹና የተሻለ አገራዊ ፍቅርን ሲያሳዩ የነበሩ ሰዎች፤ ትናንት የበቁ፤ የነቁና ያወቁ ይመስሉ የነበሩ ሰዎች ይልቁንም በምሁሩ አካባቢ የነበሩቱ ጃኬት ቀይሮ የመጣውን ኢህአዴግ ለማገልገልም ሆነ “የንጉሠ ነገሥትነት ቅዠት” ላይ ያለውን መሪ ይሁንታ ለማግኘት መርህ አልባነትን እንደመርህ፤ አቋመ ቢስ መሆንን እንደ አቋም ሲይዙ መመልከቱ በዝቷልና በርካቶች ወደቀደመ ዝምታቸው እንዲመለሱ ሆነዋል፡፡ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኙና መሀንዲሱ ሳሙዔል ብርሃኑ ዘነገደ ዳን (ሳሚ ዳን) ከራሱ ጋር በተነጋገረበት አንድ ሙዚቃው እንደገለፀው ይህ ዝምታን መምረጥ አልያም “ጅቡ እግሬን እየበላው ስለሆነ ዝም በሉ!” ማለት ከጥቅሙ ጉዳቱ በልጦ ክፉ ግብዣውን ወደቤት መጋበዝም ሆኗል፡-

“ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል - ይጠይቀኛል
ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል - ያሳድደኛል
ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል
“ለምን ዝም አልክ?” ይለኛል፡፡
ዝምታዬ መልሶ እኔው ላይ ይጮሀል…
የተራበውን አይቼው ሳልፈው - የተጨነቀውን ሳልሰማው
ለቸገረው ምንም ሳላካፍለው - ለራሴ ብቻ ነው ለካ የምኖረው፡፡
ጉልበተኛው ደካማውን ሲረግጠው
ድምፁ እንዳይሰማ ሲያደርገው
አንድ ቀንም ሳልዋጋለት - ለካ ትቼው ነው ጥዬው ያለፍኩት፡፡
ቸልተኝነቴ ለካ በዝቶ ነው - ለውጥ የሌለው
ቸልተኝነቴ ለካ አርጎኛል - ድምፅ አልባ ሰው፡፡
ቸልተኝነቴ ለካ በዝቶ ነው - መኖር ያስጠላው
ቸልተኝነቴ ለካ አርጎኛል - የዳር ተመልካች ሰው፡፡
ድምፅ አልባ ሰው - የዳር ተመልካች ሰው
ራስ ወዳድ ሰው - ድምፅ አልባ ሰው፡፡
ቁጭት የሚሉት - የህመም ጣጣ
ተነስ እያለ - ወደኔ መጣ
ሰላማዊ ምድር በል ገንባ እያለ
ከህሊናዬ ሲሟገት ዋለ
አፍንጫን ሲሉት - አይን እንደሚያለቅሰው
ዛሬ ወንድሜ ቤት ነገ ራሴ ቤት ነው…!”

በሸኘነው ሳምንት በተለያዩ ጊዜያትና ምክንያቶች ወደተለያዩ የዓለም ይልቁንም የአውሮጳ አገራትና አሜሪካ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ የኤርትራ ጦርና የአማራ ክልል ኃይሎች በጋራና በተናጠል ፈፅመውታል ተብሎና በምስል ታግዞ የቀረበውን ሪፖርት ከመመዘን ይልቅ ለሰብዓዊ መብቶቹ ጥሰት የሰጡትን “የድጋፍ ሰልፍ” ትርዒት በመንግሥታዊና ብልፅግናዊ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር እንደደህና የቡና ቁርስ ሲደጋገምልን ቆይቷል፡፡ በግሌ የዳያስጶራውን ፖለቲካ ከበፊትም እጠየፈዋለሁ፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ፅንፈኝነቱና ምድር ላይ ከረገጠው እውነት በተቃራኒ መቆሙ ነው፡፡ እውነታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምዱ (Political Diaspora) በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ ባውቅም የሰሞንኛው ክስተት ይህንኑ አስረግጦልኛል፡፡

አብዛኛው የዲያስጶራ ፖለቲከኛ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ አንድም ጭፍን ድጋፉን በካፈርኩ አይመልሰኝ መርህ የሚቸር አልያም በልወደድ ባይ ጭፍንነት የሚቃወም እንጂ መርህ ይዞ ለዚያ መርሁ እስከመጨረሻው የሚቆም ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እዚሁ ላይ ከዚህ ይዞት የሄደውና በሥልጡን አገራት እየኖረ ያልጣለው የጀብደኝነት ባህሉም ይደመርበታል፡፡ እዚህ ያለ ወገኑ በኦሮሚያ እንደሚደጋገመው የድጋፍ እንጂ የተቃውሞ ሰልፍ ተከልክሎ ማንቁርቱን እንደተያዘ ልቦናው ቢያውቅም፤ ከጥቂቶች በቀር የሚጮህለት የጠፋው እስክንድር ነጋና ጓዶቹ በኢ-ፍትሃዊነት እንደታሰሩ ቢያምንም ድምፅ ላለመሆን ወዲያውም ኮሎኔሉን ላለማስቀየም ጨምቷል፡፡ ይልቁንም “ለበጎ ነው!” ሲልና ለአገር እንደተከፈለ ዋጋ ይሳለቅበታል፡፡ ትናንት ከትናንተ ወዲያ “We need freedom more han food!” ሲል እንደነበር ዘንግቶ አገራችን ችግር ላይ ነችና ያገኛችሁትን በልታችሁ ኑሩ ነፃነቱ ነገ ይደርሳል ለማለትም ዓይኑን በጨው አጥቦ በተደጋፊ ተደማሪዎች ሚዲያ በኩል ብቅ ይላል፡፡

ሰቆቃወ አምሃራ - በመተከል በማይካድራ!

በኢትዮጵያችን ፖለቲካ ውስጥ ተወደደም ተጠላ ሶስቱ ብሔሮች ቀዳሚ ተዋንያን ከመሆናቸውም ባሻገር ፖለቲካውንና ቅርፀ-አገር ወመንግሥቱን በቀዳሚነት ተሰልፈው ሲያስኬዱት ነው የምናውቀው፡፡ ምንም እንኳን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግሥት መምጣት በስተፊት አማራነት በክልል ደረጃ የሚታወቅ ባይሆንና በይፋም የሚቀነቀን ብሔርተኝነት ባይሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት የዚህ ታላቅ ህዝብ አባል መሆናቸው ብቻውን ለመርጦ ግድያና ማፈናቀል ምክንያት ሆኖ ከደቡብ ክልሏ የጉራፈርዳ መፈናቀልና ጥቃት ጀምሮ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከልና ድባጤ ወረዳዎች እንዲሁም ዛሬም ድረስ ያላባራው የወለጋው ግፍ ህይወትና ንብረቱን ነጥቆታል፡፡ አሟሟቱ ብቻ ሳይሆን ቀብሩ እንኳ በወግ ያልሆነለት አማራ በምዕራባዊዋ ትግራይ ማይካድራም ብዙዎቻችንን አብዝቶ ያሳዘነና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈፅሞበታል፡፡

የመንግሥት ቀዳሚው ስራ የበጎ ስራዎች አይደሉም፡፡ ይሄ የግለሰቦችና መንግሥታዊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስራ ነው፡፡ የመንግሥት ቀዳሚ ስራ ድኃው ህብረተሰብ የኑሮ ውድነት እንደመርግ ከብዶት ሳለ፣ ወጣቱ ከተለያዩ የትምህርት መካናት ተመርቆ ስራ አጥ ሆኖ እየተንቀዋለለና ለክፉ ፖለቲከኞችም መጠቀሚያ ሆኖ ሳለ መናፈሻዎች ላይ ጠያቂ የሌለበትን ሚሊዮን ብሮችን ፈሰስ ማድረግ አይደለም፡፡ የመንግሥት ቀዳሚ ስራ ታይታ ላይ መጣድና የሀዘን አልያም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትን በአማላይ ቃላት ማስተላለፍ አይደለም፡፡ አብሮ ማልቀስና ማቃበርም አይደለም፡፡ በተለምዶ “መንግሥት” እየተባለ የሚጠራው አካል የስራ ኃላፊነት ሲዘረዘር ቀዳሚው ነገር የእኔና የእናንተ እንዲሁም እስካሁን ድረስ በተለያዩ ጥቃቶች ህይወትና አካላቸውን፤ ንብረትና ተስፋቸውን የተነጠቁ ብዙ ሺዎችን ከጥቃት መከላከል ነው፡፡

መንግሥት ይህንን መከላከልና ማስቆም ሲያቅተው እንደየአገሩ የህግ ሁኔታ ሥልጣን ከመልቀቅ እስከ የስራ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት በህግ እስከመጠየቅ የሚሻገሩ እርምታዊ እርምጃዎችን በመሪዎቹ ላይ ይወሰዳል፡፡ የብዙኃን መገናኛዎችም ጉዳዩ እዚህ እስኪደርስ አወዳሽና አፋሽ አጎንባሽ አይሆኑም፡፡ አለመታደል ሆኖ የህዝብና መንግሥት ከሚባሉት ባለፈ የሚበዙቱ የአገራችን የግል ብዙኃን መገናኛዎች “የእህል ውኃ” ጉዳይና የፖለቲካዊ አሰላለፍ ነገር ሆኖባቸው ሚናቸውን በአግባቡ ሲወጡ አይታይም፡፡ እንዲያውም በንዑስ ርዕስነት በጠቀስነውና በአማራው ላይ በተለያዩ ክልሎች የሚደርሱትን ጥቃቶች አንድ ጊዜ “ግጭት” እያሉ ሲዘግቡት በሌላ ጊዜ ደግሞ እስከነአካቴው ተጠቂውን ጥፋተኛ ሲያደርጉና ሲስሉት፤ ይባስ ሲልም ባላየ ባልሰማ ጥቃቱን ሲያልፉት ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡

የአማራው መጠቃት፤ የኦሮሞው መገፋትም ሆነ የትግሬው መጨፍጨፍ ደስታን የሚፈጥርላቸው ሰዎች ቁጥር ማሻቀብና ይህንን የተቃወምነውን ደግሞ በጁንታነት የሚፈርጁ ሰዎች መበርከት የሚነግረን የክሽፈት ደረጃ ያለ ቢሆንም ያለንበትን እውነታ ግን አመልካች ነው፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ግፍን ሳይሆን የግፈኛውን ብሄርና ተክለ-ስብዕና የምንተች ሆነናል፡፡ በደልን ሳይሆን የበዳዩን ማንነት እየተመለከትን የምንጨምት አልያም የምንጮህ ሆነናል፡፡ እዚህ ልጠቅስላችሁ ከምችላቸው በርካታ ማስረጃዎች ለመቀንጨብ ያህል ዓለም አቀፍ ተቋማትን እማኝ ላድርግ፡፡ ዳያስፖራውም ሆነ አንዳንድ ነዋሪ ፖለቲከኞች ከእነዚህ ተቋማት ጀርባ ያለውን ዕውቅ ግብ ቢረዱትም በዘመነ ኢህአዴግ እነዚህ ተቋማትና እንደ አና ጎሜዝ ያሉ ግለሰቦች ከኢህአዴግ ጋር ሲናጩ ትክክል ነበሩ፡፡ ዜና ዘገባዎቹ፤ ሐተታዎቹና ግርምቶቹ ሁሉ የእነዚህን ተቋማት ትክክለኛነት የሚያሞቁ ነበሩ፡፡

ኢህአዴግ ጃኬት ሲለውጥ ተቋማቱም ለውጥ ጠበቁ፡፡ ለውጡ የውኃ ሽታ ሲሆንና ይልቁንም የቁልቁለት ስንዳፋ በሪፖርትና መግለጫቸው ማስተካከያ ጠየቁ፡፡ መርህ አልባነት ልብሳችን ሆኗልና ተቋማቱ የሚሰነዝሯቸው ክሶች ኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሳይሆን እንደ አገር እየተሰነዘረብን ያለ ጥቃት አስመስለነው አረፍን፡፡ ዓለማቀፍ ህግጋትን ረስተን ዓለም በእኛ የውስጥ ጉዳይ ምንም አባቱ አይገደውም ባዮች ሆንን፡፡ በተለይ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ መኖሩ እየታወቀ ያንን ለማስተባበል ከተኬደበት ርቀት ባልተናነሰ የተሰነደ ዘረፋና ድፍረታቸውን፣ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝና ግድያዎቻቸውን ለመሸፈን ዳያስጶራውን ጨምሮ የተኬደበት ርቀት በእጀጉ አሳፋሪ ነው፡፡

ሜጀር ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት እና ፃድቃን ገ/ትንሳዔ የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ በተለያዩ ፅሁፎቻቸውና ንግግሮቻቸው እንደተረዳሁት በአገዛዝ ዘመናቸው ከሚፀፀቱባቸው ጉዳዮች አንዱ “በጫጉላ ሽርሽሩ” ወቅት በተኬደበት የተሳሳተ መንገድ ዘላቂ ጥቅማችንን እንዳጣን ገልፀዋል፡፡ ይልቁንም አበበ ተ/ሃይማኖት (ጆቤ) “ለውጡ” የመጣ ሰሞን ሁለተኛው ዙር የጫጉላ ዘመንም ችግር እንዳይፈጥርብን ተደጋጋሚ ውትወታዎችን ሲያደርጉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የዓድዋ ድልን 125ኛ ዓመት ዝክር ስናስታውስ ድንበራችን በሱዳን ጦር መደፈሩና ብዙኃኑ ማህበረሰብ መወረሩን እንኳ አለማወቁ አልያም በመወረሩ ለመቆጨት የምንግሥቱን ፊሽካ መጠበቁ ቢያስተዛዝብም “የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ!” የሚል የዳቦ ስም በተሰጠው የወገን ጦርነት (Civil War) ውስጥ ለኢትዮጵያ መልካም እሳቤ ኖሮት የማያውቀው ሻዕቢያ በውስጥ ጉዳያችን መሳተፍ ጉዳይም አስተዛዝቦናል፡፡ በፅሁፍ በምሳተፍበት “ሪፖርተር” ጋዜጣ ላይ መምህሬ ሱራፌል ወንድሙ ከሰሞኑ ያሰፈረውን ሸግዬ መጣጥፍ ሳነብ ያጋጠመኝም ይኸው አይነት ሃሳብ ነበር፡፡

ብዙዎች በሙዚቃውና መዝናኛው ዘርፍ (Infotaiment) የሚያውቁትና “አሻም” ላይ በሚያቀርባቸው መሰናዶዎቹ የሚታወቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ሱራፌል ወንድሙ “ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም› - ከኤርትራ ጋር ዘላቂ ሰላም ፈጥረናል?” በሚል ርዕስ ስር ድምዳሜውን አስቀድሞ ሐተታውን ሲያስከትል አምባገነን ግለሰብና አጫፋሪዎቹ በሚዘውሩት አገር ይህንን ማሳካት እንደማይቻል አስነብቧል፡፡ ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያን የኤርትራ ጦር በውስጥ ጉዳያችን እንዲጠልቅ ተደርጎ ወገናችን የሆነውን የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ እንዲያበዛበትና እንዲዘርፍ በዝምታው ይሁንታውን መስጠቱም አሳዛኝ ነው፡፡ ጥቂቶች የዚህ መዘዝ ነገ ከነገም በስተያ የሚያመጣው ገብቷቸው ከማለዳው “ከአስመራ ይልቅ መቀሌ ከኢሳያስ በስተፊትም ደብረፅዮን ይቀርበኛል!” ሲሉ መቃወማቸው ትክክል እንደነበር ያስገነዝባል፡፡

በግጭት አፈታት ዙሪያ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ፅሁፉን በሰራና በጅማሮውም ትልቁን የዓለም ሠላም ኖቤልን እንደቀብድ በተቀበለ ገዢ በምትዘወር አገር ግጭቶች ሲወሳሰቡና ሲበረክቱ እንጂ ሲቀንሱ አለማየታችን አልታወቀንም፡፡ ምሁራኑም ምክር ቤት ገብቶ ለመቁለጭለጭ እንጂ የአቅምን ሙያዊ ሙግት ከማድረግ ሰንፈዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ይዞታችን ከቀድሞው ከፍቷል፡፡ ምንም እንኳን ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ መጠነኛ የፖሊሲ ነፃነት እጦትን ቢፈጥርብንም አሜሪካንን፤ የመንግሥታቱ ድርጅትን እና የአውሮጳ ህብረትን ጨምሮ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሰቆቃችንን ከእኛ እዚህ ካለነው በተሻለ ተረድተው የየራሳቸውን ሚና ለመወጣት መንገድ ላይ ናቸው፡፡

በቀዳሚው ኢህአዴግ ዘመን እነዚህ አገራትና ተቋማት መግለጫ ሲያወጡና የሰብዓዊ መብቶች አያያዛችን እንዲስተካከል በተለያየ መንገድ ግፊት ሲያደርጉ ትክክል እንደነበሩ ይነግሩን የነበሩ ሰዎች ዛሬ ሚዛናቸውን ቀይረው ኢ-ትክክለኝነታቸውን ሊግቱን ሲንደፋደፉ ማየቱ ቢያስተዛዝብም የገዛ ወገንህን እየጨፈጨፍክና በባዕድ እያስጨፈጨፍክ ሉዓላዊነትን ጋሻ የምታደርግበት ዓለማቀፍ ህግ እንደሌለ ማወቁ ይጠቅማል፡፡

የዘፈቀደ ግድያና ወታደር ያልሆኑ ዜጎችን ማፈናቀል፣ ከፍርድ ውጪ መግደልና በጦርነት ውስጥም ቢሆን ዓለማቀፉን የሰብዓዊነት ህግ (International Humanitarian Law) የጣሱ ተግባራት ሲያጋጥሙ ይልቁንም መንግሥታችን ሪፖርቶቹ በትክክለኛ መረጃ ያልተደገፉ ናቸው ብሎ በደከመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ቢዘባበትበትም በሰብዓዊ መብቶች ተቋማቱ በትክክል እንደተቀመጠው ኢትዮጵያችን ውስጥ “በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል” ስለመፈፀሙ ከፍንጭ በላይ የሆኑ ማስረጃዎች ስለመገኘታቸው አይካድም፡፡ ኢትዮጵያ በአፅንኦት ብትቃወመውም የትግራይ ተወላጆች ከመጀመሪያው “የቀን ጅብ” የአፍ-ድልጠት ጀምሮ እስከ የመጨረሻው መጀመሪያ “ጁንታ” ልጠፋ ድረስ በአንቶኒ ብሊንክ አገላለፅ “የዘር ማፅዳት/Ethnic Clinsing” የሚመስሉ ነገሮች በይፋ ተስተውለውበታል፡፡

ፅሁፌን ለማጠናቀቅ ያህል ብልፅግና ኢህአዴግ “ያለንም እኛ የሞትንም እኛ!” በሚለው ቀዳሚ ብሂላችን የቀዳማይ ኢህአዴግን መስመር ሲሄድበትና ለውጡ ከለውጥነት ወደነውጥነት ሲቀየር እምብዛም ያላሳሰበን ብንኖርም ድርጅቱ የኢህአዴግን ባህል፤ ማዕከላዊነቱንና ጥርነፋውን ከመዋቅሩ ጋር ወርሷልና ከዚህም ሊከፋ እንደሚችል መገመቱ አይከብድም፡፡ የምንተዛዘበው በምሁራኑና ማህበረሰቡ ላይ በሚታየው መደናቆር እንጂ በፖለቲከኞቹ አቋም አይሆንም፡፡ የትግሬው ህመም ካላመመን፤ የአማራው ሞት ካላሳሰበን፣ የኦሮሞውን እስራት ካልተቃወምን አብረን ኖረናል ማለታችን የከንቱ ሽንገላ ይመስለኛል፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :