ታለ “በሉዓላዊነት” ስም! (አንደኛው ክፍል)

Sovereigntyሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

June 18, 2021

“Sovereignty implies responsibility not just power!”
(Koffi Annan, 26 June 1998)

ደራሲና ሀያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ከሚታወቅባቸው ስራዎች የቅርቦቹ ርዕስ “ታለ” የሰኘውን ገፀ-ባህሪ ስያሜ በማስቀደም ተፈታሹን ጭብጥ እያስከተለ “በፍቅር ስም” እንዲሁም ሐሰተኛውን “በእምነት ስም” በሚሉት ስራዎቹ እጅግ ተነባቢነትን አትርፏል፡፡ ዓለማየሁ በእውነትና “በአንድነት ስም” ወይም “በሉዓላዊነት ስም” እያለ ስለመቀጠል አለመቀጠሉ እርግጠኛ ባልሆንም እነዚህ ታለዎች የሰው ልጆች ህይወትን በየፈርጁ እንድንፈትሽ ገፍተውናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ትናንት በአገር አንድነት ስም ሲፈፀሙ የነበሩ ሰቆቃዎች በሙሉ ዛሬ በአገር ሉዓላዊነት ስም በእኔና በእናንተ ዘመን ሲፈፀሙ እየታደምን ነው፡፡

በተወሰነ መልኩም ቢሆን ዛሬም ስለመኖራቸው ታሪክ ምስክር ሆኗልና መፃህፍትን ጨምሮ በተለያዩ ሰነዶች ተጠርዞ እያነበብናቸውም ነው፡፡ በድምፅ ወምስል ታግዘወም የተመለከትናቸው አሉ፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊና ማህበረሰባዊ ጫናዎች ሳቢያም ወደ ተሳታፊነት የተሳብንባቸው አጋጣሚዎች እየበረከቱ ጦርነትና ግጭት ጠል (Pacifist)  መሆን እንደ አገር ክህደትና ባንዳነት እየተቆጠረ ገለልተኝነትን አልታደልነውም፡፡ አልያም ከ“አንተም ተው አንተም ተው!” ይልቅ “ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ከጠላቶቼ ጎን ነው!” በሚል ስንኩል እሳቤ ተይዘናል፡፡

ስለሆነም አንድም “በሉዓላዊነት” ጋሻነት ስር የሚፈፀሙትን የአረማዊነት ስራዎችና ከሰብዓዊነት የተጣሉ ድርጊቶች በዝምታችንም ቢሆን እንደግፋለን፡፡ ሁለትም ክፉ ሃሳቦቹንና ድርጊቶቹን ተቃውመን ፈፃሚና አስፈፃሚዎቹንም ኮንነን ሉዓላዊነት መደበቂያ እንደማይሆን እንገልፅላቸዋለን፡፡ ይልቁንም ተጠያቂነትን እንደማያስቀር እንመሰክርላቸዋለን፡፡ በዚህ ፅሁፍ በቀደመው ዘመን በኢትዮጵያችንም ሆነ በሌሎች የአህጉራችን አፍሪካና የዓለም አገራት በአገራዊ አንድነት ስም የተፈፀሙ ሰቆቃዎችን መነሻ በማድረግ ዓለማችን አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔ ደረጃ አኳያ እነዚያኑ ሰቆቃዎች (Atrocities)  በዚሁ የሉዓላዊነት ጥላነት ለመድገም የመከጀሉን ዳርዳርታ እንዳስሳለን፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ስሱ ልብና ፅኑ እምነትም አለኝና በዚሁ ርዕስ የፖለቲካዊ ህይወታችንን አንዲት ግርድፍ ጉዳይ እንመረምራለን፡፡ ሉዓላዊነትን፡፡ ከዓለማቀፍም ሆነ ከአህጉራዊና አገራዊ የሠብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች አንፃርም አንድምታውን እንቃኛለን - መልካም ንባብ!

የ“ሉዓላዊነት” ምንነት ሲብራራ….

በህገ ፍልስፍና (Jurisprudence) እና በዓለማቀፉ የፐብሊክ ህግ (Public International Law)  ብየናዎች መሠረት አገር የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብና የጅማሮው የትና እንዴትነት ላይ ያልበረደ የሃሳብ ሙግት እንደቀጠለ ቢኖርም ይልቁንም ከተባበሩት የመንግሥታት ድርጅት የራስን ዕድልና ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ በራስ መወሰን (Self-Determination Right) እወጃ በኋላ በተፈጠሩ የአገር መሆን እሽቅድድሞች ሁለት ነገሮች ጎልተው መታየት ችለዋል፡፡ እነዚህም የአገሮች ሉዓላዊነትና ግዛታዊ ደህንነት (Territorial Integrity)  በአንድ በኩል እንዲሁም በሁለተኛው ወገን ደግሞ የህዝቦች የራሳቸውን ዕድልና ዕጣ-ፈንታ በራሳቸው የመወሰን መብት (Self-Determination) በሌላ በኩል እየሆኑ ተናፅረዋል፡፡ በተለያየ ጊዜም የሁለቱን መብቶች በአግባቡ ለማስታረቅና ለማመቻመች በመቸገር (Failure to Accomodate) ለአስከፊ ግጭቶች መነሻ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ዓለማቀፎቹና አህጉራዊዎቹ ህግጋት እንደየሀጋጊዎቹ ፖለቲካዊ ቁመናና ምጣኔ ኃብታዊ ይዞታ ከአህጉራዊዎቹ ህግጋትጋ እየተሟደዱ ከሁለቱ አንዱንም እየደገፉ ስለመቆማቸው አይታበልም፡፡

ለፍርድ የተቸገሩ መስለው ከሁለቱም ወገን የሚሰለፉበት አልያም በመሀል ቆመው የሚዋልሉበት ወቅትም ብዙ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የምንነጋገረው ስለአገራችን ወቅታዊ ፈተና ነውና አገራችን ኢትዮጵያ በቀዳሚ መስራችና አባልነት የምትሳተፍበትን የአፍሪካ ህብረት አቋም በሂደት እንፈትሻለን፡፡ ለመነሻ ያህል ግን ስለቃሉና ቃሉ ስለተሸከመው መልዕክት ስናወራ ስለ “ሉዓላዊነት/Sovereignty” በተፃፉ የተለያዩየ ዓለማቀፍ ህግጋት፤ ድርሳናትና የህግና ፖለቲካ ብሎም የሥነ-መንግሥት ምሁራን ማብራሪያዎችና አስተያየቶችን እንመለከታለን፡፡

ሉዓላዊነት በዓለማቀፍ ህግ መሠረት ለአገራት አለፍ ሲልም በአገራት ውስጥ ለሚኖሩ ራስ ገዝ ክልሎችና ሌሎች የአስተዳደር እርከኖች የሚታወቅላቸው መብት እና ግዴታ እንጂ ሌላ እንዳይደለ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይልቁንም የሞንቴቪዶ ስምምነት (The Montevideo Convention on the Rights and Duties of States) አገርንና አብሮ-ተከታዩን ሉዓላዊነትን ለመቀዳጀት ያስቀመጣቸው ተለምዷዊ (Traditional) አራት ነጥቦች አሉ፡፡ እነርሱም አገርነትን ለመቀዳጀት ወሰንና ዓለማቀፍ ድንበሩ በታወቀ ቦታ ላይ በቋሚነት የሰፈረ ህዝብ (ህዝቦች) መኖርና ከሌሎች ይህንን መመዘኛ ከሚያሟሉ ሌሎች አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር የሚችል ቅቡልነት ያለው መንግሥት መኖርን መስፈርት ያደርጋል፡፡

በእነዚህ ነባር መመዘኛዎች መሠረት አገራት ሲቆሙ ከሚቀዳጇቸው ነፃነቶች አንዱ በመርህ ደረጃም ቢሆን እንደ አገር በመብት ደረጃ እኩል መሆን ቀዳሚው ሲሆን ሉዓላዊነት ተከታዩ ነው፡፡ ሉዓላዊነት አይነቶቹ ቢበዙም ከያዝነው ርዕሰ ጉዳይ አውድ ስለህዝብ/ህዝቦች ሉዓላዊነት አይደለምና የምንነጋገረው የአገር ሉዓላዊነት (State Sovereignty) ሁለት አይነት ሲሆን ውስጣዊ (Internal Sovereignty) እና ውጫዊ (External Sovereignty) ብለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ውጫዊው የአንድ አገር መንግሥት ያለውጫዊ ጣልቃ-ገብነት ለሚያስተዳድረው ህዝብ ብቸኛ ተወካይ በመሆንና የህጋዊነቱን መስፈርት አሟልቶም የአገሩን ነፃነትና ጥቅም የሚያስጠብቅበት ይሁንታ ሲሆን ውስጣዊው ደግሞ ሌላ የእርሱን መንግሥትነት እና ሥልጣን በበላይነት ወይም በእኩልነት ሊገዳደር የሚችል “መንግሥት” አለመኖርን ይመለከታል፡፡

በሌላ አገላለፅ በአገራችንም ሆኖ በተቀሩት አገራት ሲደረግ እንደኖረው በአንዲት አገር ከአንድ በላይ ንጉሥ የሚኖር ከሆነ አንዱ የግድ “ንጉሠ-ነገሥት” ሆኖ ሁሎችንም ማስገበርና ከ“ንጉሥ” የዘለለ ነገሥትነት እንዳይኖራቸው ማድረግ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ይህንን አፄያዊ አገላለፅ ወደዘመናዊው የመንግሥት ሥርዓት ስናመጣው ክልል የምንላቸው የአስተዳደር እርከኖችን አስተባብሮ ለዓለማቀፍ ግንኙነቶች የሚወከል አንድ ብቸኛ የፌዴራል መንግሥት ማለታችን ይሆናል፡፡ ከግሪክ የነአርስቶትል እና ፕላቶ የጀመረው ፍልስፍና ሮማ ሲገባ ህገ-ፍልስፍናውን አስጀምሯል፡፡ በሀገረ እንግሊዝ ዳብሮ በዘመነ አብርሀት አህጉረ አውሮጳ ዛሬ የምንገለገልባቸውን በርካታ ዘመናዊ የህግ እሳቤና ፍልስፍናዎችን አስገኝቶልናል፡፡ ከወቅቱ ታላላቅ አሳቢዎች አንዱ የነበረው ዦን ዣክ ሮሱ ይህንን የሉዓላዊነት ፅንሰ ሃሳብ “ማህበራዊ ውል” በሚባል የህዝብ ፈቃድ ሉዓላዊነትን ህዝባዊ መሰረት አኑሮለታል፡፡ ቻርለስ ሞንቴስኪው ደግሞ ይህም በቂ አይደለም ሲል የመንግሥትን አምባገነንነትና ሥልጣን ለመቀናነስ ይረዳል ያለውን መግሪያ (Separation of Power) በማስተዋወቅ ሉዓላዊነትን ቀረብ እና ቀለል አድርጎታል ማለት እንችላለን፡፡

ምንም እንኳ ቃሉ በተለያዩ ምሁራን እንደየምልከታና ትምህርታዊ ዘርፋቸው የተለያየ ፍቺ እየተሰጠው ሁሉን አቀፍና አግባቢ ፍቺ ያላገኘ ቢሆንም ከላይ ከጠቀስናቸው የቃሉ መልዕክት ምን ለማለት እንደተፈለገ አንባብያን እንደምትረዱት አምናለሁ፡፡ ይህም ሉዓላዊነት አንድ ምሁር እንዳስቀመጠው በዓለማቀፍ ደረጃ በአገራት መካከል የሚኖር “Sovereignty is Essentially a Matter of Reciprocity.” ነው፡፡ ስለዚህም ባለንበት የሉላዊነት ዘመን (In an Era of Globalization) ምሁራኑ ሉዓላዊነትን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊነቱንም ሲሞግቱ “Globalization; The end of state sovereignty?” ከማለት አልፈው ሉላዊነትን ተስታከው የመጡትና ዓለማቀፍ የሆኑትን ግንኙነቶችና እሴቶች (values dependency and interconnectedness) በማስተዋል ዓለማቀፋዊነት የአገራትን ሉዓላዊነት አሙቷልና “The death of sovereignty” ቅርብ ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡

የመብቶች ጥሰት “በሉዓላዊነት ስም” በአፍሪካ!

የኢትዮጵያ መንግሥትና ለመንግሥቱ አንደበት የሚሆኑ መገናኛ ብዙኃን አሁን እንደሚነግሩን አይነት አይነኬና በተለምዶ ”Effective State Sovereignty” የምንለው ዓይነት ራስን በማጠር መነጠል (Isolation) ማለት አይሆንም፡፡ መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ኮፊ አናን ሉዓላዊነት መብት እንደሚሰጠው ሁሉ ግዴታንም ያስከትላል ማለታቸውን ያጤኗል፡፡ የአፍሪካ አምባገነን ገዢዎች የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች እሴቶችን የባህል ሁለታዊነት (Cultural Relativism) በሚባለው ምልከታ ሸሽገው ከግዴታና ግዴታውን ካለመወጣት ከሚመጣው ተጠያቂነት ለማምለጥ ሁሌም ዝግጁ ሆነው ይታያሉ፡፡

በዚህም አንዱ አምባገነን ሌላውን የጎበዝ አለቃ እየደገፈ ጠቅላይ አምባገነንነቱን በአፍሪካ ህብረት ደረጃ ተቋማዊ ቅርፅ ሰጥተውት አፍሪካውያን በየአገራቸው ከዜግነት መብቶች ሁሉ ተነቅለው የገዢዎቻቸው ምስለኔ (Subject) ሆነዋል፡፡ የፖለቲካ ዕርዳታውና የአህጉራዊው ተቋም ስንፍናም ምንጭ ብቻ ሳይሆን ለአምባገነናዊ አገዛዛቸው ብርቱ ረዳት ሆኗቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደንብን (Charter) በመነሻነት ይዘው በአንድ ወቅት ሰው በላውን ኢዲ-አሚንዳዳን ለህብረታቸው ሊቀመንበር አድርጎ እስከመምረጥ የደፈሩ የአገዛዝ አጋሮች ሉዓላዊነትን መደበቂያ አድርገው ከተጠያቂነት ለመሸሽ ቢሞክሩ የሚደንቅ አይደለም፡፡

በአሁን አጠራሩ የአፍሪካ ህብረት እየተባለ የሚጠራው ስብስብ በሉዓላውያን አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት (Non-nterference) የሚለውን ሐረግና ይሄንን ሐረግ ያዘለውን አንቀፅ እጅግ አድርገው የሚወዱ የአምባገነን መንግሥታት ጥርቅም ሲሆን በሌላ ርዕስ የምንመለስበት ቢሆንም ይህ ጉዳይ በአህጉሪቱ ከሚገኙ የነባር ህዝቦች መብቶች (Indigenous Peoples Rights) ጋር ተያይዞም በብርቱ እያስተቻቸው የሚገኝ ነው፡፡

በመሠረቱ አሜሪካ የውጭ ዕርዳታን በተመለከተ በግልፅ በተቀመጡና በፕሬዚደንቶቿ ግላዊ ወይም ፓርቲያዊ ፍላጎት ሳይሆን አገራዊ ጥቅምን ማዕከል አድርገው የታወጁ የዕርዳታና ድጋፍ መርሆች ያላት አገር ናት፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ካድሬዎች የመንግሥትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፤ ፖለቲካዊ መግባባት ማጣት እንዲሁም አምባመግነኑንና የዲፕሎማሲ ውድቀታቸውን ለመሸፈን ሰሞንኛው ዕቀባ በኮሎኔል ዓብይ አህመድና አስተዳደራቸው ላይ የተጣለና የሚጣል ሳይሆን ከቪዛው ጀምሮ እንደአገር የተጣለብን ወይም የሚጣልብን እቀባና ማዕቀብ ሊያስመስሉት መሞከራቸው አይዘነጋም፡፡

ሉላዊነት (Globalization) ምስጋና ይግባውና በሉዓላዊነት (Sovereignty) ስም ለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በሰው ልጆች ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች እንደጋሻ እንዳያገለግል ሆኗል፡፡ አምባገነን መንግሥታትም በዚሁ መደበቂያ ስር ያልታጠቁ ዜጎቻቸውን ለማሰቃየት እንዳይችሉ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ (International Community) መግቢያ በር ከፍቷል፡፡ ይልቁንም ባለንበት ዘመን ከብዙዎች ተደብቆ ለብዙ ጊዜ የሚቆይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እምብዛም ነው፡፡ የዓለም በተለያዩ መንገዶች መተሳሰርም የአንዱን የብቸኛ ወሳኝነት እያስቀረው ነው፡፡ ስለዚህም በሉዓላዊነት ስም ከተጠያቂነት የምናመልጥበት አጋጣሚ ቀርቷል፡፡

ኢትዮጵያን እወዳታለሁ፡፡ ሌላ አገርም ሌላ ዜግነትም የለኝም፡፡ አሜሪካን የአምባገነንቱን ጥርጊያ በመሸምጠጥ ላይ በሚገኙት የአህጉርና የአገሬ ሹማምንት ላይ በሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ረገድ የምትጥለውን እቀባና ማዕቀብም እደግፋለሁ ብቻ ይሆን ይህንኑ እንድታደርግም ከሚጠይቁት አገር ወዳዶች ጎን በመቀም የበኩሌን እወጣለሁ፡፡ በቀጣዩ ክፍል ኢትዮጵያችንን እየዘወረ ያለውና ይህንን ፅሁፍ ባዘጋጀሁበት ወቅት በሚኒስትር ደረጃ የአስፈፃሚዎች ጉባዔ የተቀመጠውን የመንግሥት አመራር ውሳኔዎች እንመለከታለን፡፡

በዓለማቀፍ ደረጃ በሉዓላዊነት ስም ተፈፅመው ከተጠያቂነት ያልዳኑ መንግሥታትን ማሳያ አንስተንም አሁን በያዝነው የአስመራ መንገድ ከቀጠልን መዳረሻችን የሚሆነውን የወዳቂ መንግሥታት (Failed States) መስፈርቶች በማንሳት ፅሁፌን እስክቋጭ እነሆ መውጫ፡፡ በሞት የተነጠቅናቸውና እዚሁ ገፃችን ላይ ደጋግመን የጠቀስናቸው ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም “እንጉርጉሮ” ሲሉ በተውልን የግጥሞቻቸው መድብል ውስጥ ያካተቱትና “ሞት ማለት” የሚል ርዕስ የሰጡት ግጥም መሰናበቻችን እንዲሆን ፈቀድኩ፡፡ የዚህን ግጥም የመጨረሻዎቹ ስንኞች እንደ ኢህአዴጉ ዘመን ተጧሪ ካድሬዎች “ሁሉ መልካም!” እንደሆነ ለመንግሥት እያሸበሸቡና ከዚሁ ሽብሻቦ በሚያገኟቸው እርጥባን “ሁሉ ደህና!” ለሆነላቸው የብልፅግና ዘመን በቀቀኖች ጥሩ መልዕክትን የያዘ መስሎኛል፡-

“አዕምሮ ፈራርሶ - ህሊና በስብሶ
ሰውነት ረክሶ - እንደግም፤ እንደጥንብ
የጭልፊቶች - ምግብ፤
የሞት ሞት ይሄ ነው፤
ትንሣኤም የሌለው፡፡”

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :