ታለ “በአገር ሉዓላዊነት” ስም! (ማጠናቀቂያ - አንድ በሉ!)

Failed Statesሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

June 18, 2021

“There are two kinds of Injustice: the first is found in those who do an injury; the second in those who fail to protect another from injury when they can.”
(Cicero, a Roman Jurist)

በቀደመውና “ታለ በሉዓላዊነት ስም!” የሚል ርዕስ በሰጠነው መጣጥፍ “ሉዓላዊነት” ምን ማለት እንደሆነና እንዳልሆነ ጭምር በማሳየት የአህጉረ አፍሪካችን ገዢዎች “በሉዓላዊነት ስም” ዜጎቻቸው ላይ እያደረሱት ያለውን ዘርፈ ብዙ በደል ለመመልከትና ዘመኑ እያለፈበት ስለመምጣቱም ተጠቋቁመናል፡፡ የሉዓላዊነትን ተራማጅ ፍቺ መነሻ በማድረግ አገራችንን ጨምሮ ወንበሯን ያገኙ አምባገነን መንግሥታትን ክሽፈት እየነቃቀስን ዛሬም እንቀጥላለን፡፡ በዚህም የ“ዓለማቀፉ ማህበረሰብ” ሚናና የጣልቃ-ገብነቱን ሁኔታ እናወሳሳለን - መልካም ንባብ!

“ሉዓላዊነት” እንደ መብትም - እንደ ግዴታም!

በህገ ፍልስፍናው ዙሪያ ስለ “ሉዓላዊነት” በቀደመው ክፍል ያወሳናቸው ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው ቁጥራቸው ቀላል ተብሎ ሊናናቅ የማይገቡ ሰዎች ገዢው የፖለቲካ ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉባዔ ሲቀመጥ በድጋሚ ተስፋቸው ማንሰራራት ጀምሮ እንደነበርና አዲስ አይነት መግለጫ ለመስማትም ጆሯቸውን አቅንተው፤ ልቦናቸውን አብርተው እንደነበር አስተውያለሁ፡፡ የሆነው ግን እንደተለመደውና በተቃራኒው ነው፡፡

አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የስምዖን ልጅ አቶ በረከት ቀዳማዊው ኢህአዴግ 100% በመቶ “አሸናፊ” መሆኑን ባወጀበት “የ2007 ምርጫ” መነሾ በከተቡትና “ናዳን የገታ ሩጫ” የሰኙትን መፅሀፍ ያስታወሰ አንድ ነገር እውን ሆኗል፡፡ ይኸውም እነአቶ በረከት በዚያ ዝቅተኞቹን የምርጫ መስፈርቶች እንኳ ባላሟላ የጨረባ ምርጫ ወቅት ከወዳጆቻቸው ጋር ሲኳረፉ የአሁኑን አይነት አምባገነንነትን የመደገፍ ግላዊ ጉዟቸውን “ኢየሱሳዊ” ከሚያደርጉት የሪፐብሊካኑ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ድጋፍ ተችሯቸው ነበር፡፡ ሴናተሩም እንዳሁኑ ሁሉ በገዢውና በፓርቲው ልሳኖች ጀግነው ታይተው ነበር፡፡

ያ ሁሉ ሩጫ ግን ህዝባዊ ናዳውን መግታት ሳይችል ቀርቶ አቶ በረከትን በእግረ ሙቅ አሳስሮ ከዘብጥያ ጥሏል፡፡ የቀድሞ ወዳጆቻቸውን የሥልጣን መንበር ቢያቆናጥጥም እርካብ በእግራችን ሳይጠልቅ እንዳሻን እንሁን ማለትን መርጠዋል፡፡ የዲፕሎማሲያችን ውድቀት በአፍሪካ ቀንድ የመንግሥተ አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ (US Special Envoy for the Horn of Africa) ከሆኑትና የአገራቸውን አቋም ከሚያስተጋቡት ጄፍ ፌልትማን ይልቅ ሴናተር ጂም ኢንሆፍን የሚንከባከብ ሆኗል፡፡ እኚህ ሴናተር:- “The Government of Ethiopia has taken significant steps to Re-gain a Democratic process that is fair and respectful of Human Rights.” በማለት አምባገነናዊውን ምርጫ-2007- ማሟሟቅ ላይ እንደነበሩና “HR-2003” እንዳይፀድቅ የተሟገቱ የአምባገነኖች ወዳጅ ስለመሆናቸው የአሁኖቹ የኢህአዴግ ቅሪት ገዢዎቻችን የሚያውቁት ነው፡፡

ፌስቡክን በመጠቀም ቀዳሚ ከሆኑ የመንግሥት መሪዎች አንዱ በሆኑት ዓቢይ አህመድ (ኮ/ል) “ወደ ሁለተኛ ቤትዎ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ!” የተባለላቸው እኚህ ሰው ሊቀይሩ የሚችሉት ነገር ባይኖርም “Strong US Presence in Africa is Critical to our National Interest.” ለማለት ሁለቴ ማሰብ እንዳላስፈለጋቸው “ሉዓላዊነትን” ጋሻ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎቻችን ቢገነዘቡት ኖሮ ቀዝቀዝ ይሉ እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ሴናተሩን በማወደስና መልዕክተኛውን በመርገም የሚመጣ ለውጥ አይኖርም እንጂ ቢኖር እስካሁን በመጣ ነበር፡፡

ጦርነቱን በድርድር አስቁሙ፤ የኢ-ሰብዓዊ ሰቆቃዎቹ ዋና አራማጅ የሆነውን የሻዕቢያ ጦርን ጨምሮ የአማራ ክልል ኃይሎችን አስወጡ፤ ለሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅፋት አትሁኑ ለሚለው ጉትጎታ ምላሹ “ግድቡ የኔ ነው!” መፍትሄ አይሆንም፡፡ ይሄ ማለት ግን አሜሪካ ይዛ የመጣችው አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት ብቻ ያነገቡ ናቸው የማለት ጅልነት አይደለም፡፡ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ከቀደመው የዶናልድ ትራምፕ “ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች!” ከሚለው ንግግር የቀጠለ ዓላማና ዒላማ እንዳለው የተሰወረ አይደለም፡፡

ይህንን የሚደግፍ ጤናማ ኢትዮጵያዊም አይኖርም፡፡ ሆኖም ይህንን የምንገልፅበት መንገድ በትግራይ ወገኖቻችን ላይ የሚወርደውን መከራ በመቃወምና አሜሪካኖቹን መግቢያ በማሳጣት እንጂ በቀደመው ጦርነት ስለመላው ኢትዮጵያ ሲሉ ጋሻ የሆኑትን ትግራውያን ዛሬ አሳልፎ “ለበቀል ማወራረጃነት” በመስጠት አይደለም፡፡ በእርግጥ ከአሁኑ ካሣ መጠየቅ የጀመረው ሻዕቢያ እንዲህ በቀላል ጦሩን ከኢትዮጵያ ያስወጣል የማለትን ዘበትነት አልዘነጋሁም፡፡ እዚህ ግድም የአፍሪካ ህብረት “የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ!” በሚል ፍካሬ ንቅናቄ በጀመረበት ወቅት የያዘውን መሪ ቃል ማውሳቱ ግድ ይሆናል - Silencing the Guns!

የአፍሪካ “ህብረት” እንደ አፍሪካ “አንድነት”

የአፍሪካ ህብረት የአምባገነኖች ማህበር ነውና ህብረቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ተክቶ ሲቆም ሊያስሽላቸው ከወጠናቸው ነጥቦች አንዱ ይኸው የ“ሉዓላዊነት” ሽፋንን የተመለከተው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ልውጠት በፖለቲከኞቹ አገላለፅ “From the Policy of Non-Interference to Non-Indifference” ቢባልለትም በሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በጎረቤታችን ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ዳርፉር ብሎም በማዕከላዊቷ አፍሪካ ሪፐብሊክ የደረሱ ፍጅቶችን የተመለከተበት መንገድ የቀድሞው አይነት ሉዓላዊነት እሳቤ ላይ ተቸንክሮ መቅረቱን በይፋ ያጋለጠ ነበር፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም (UNSC) ቢሆን ከዚሁ የተሻለ አልሆነም ስለፍጅቶቹ፡፡

የህብረቱ መተዳደሪያ ህግ (Constitutive Act of the African Union) አራተኛው አንቀፅና ሰባተኛው ድንጋጌ በጦር ወንጀሎች፤ በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎችና በዘር ማጥፋትን በመሳሰሉ ወንጀሎች ላይ የጠራ ፖሊሲ ያለው ቢመስልም ብዥታውን (Policy Dilemma) ያልለየ በመሆኑ ጣልቃ ላለመግባት በሚያደርጋቸው ዝምታዎች ብዙ ንፁኃን ሰለባ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ሆነ የፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በያዝ-ለቀቅም ቢሆን ከላይ በህብረቱ ህግ የተጠቀሱት አይነት ወንጀሎች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስለመፈፀማቸው አሳውቀዋል፡፡

እንዲያውም የህግ ማስከበር ነው በተባለው ዘመቻ የተያዙ የህወኃት አመራሮች ላይ ከሚቀርቡ ክሶች አንዱ የእርስ በእርስ ጦርነትን ማነሳሳት (Instigating Civil War) የሚለው መሆኑ ጉዳዩን ላልተረዱ ግልፅ ያደረገ አነጋገር ነው፡፡ ህብረቱንና የህብረቱን ፀጥታ ምክር ቤት ድምፅ የበላው ጅብ ግን እስካሁን አልጮኸም፡፡ የቀድሞው የናይጄሪያ ሰብዓዊ መብቶች ብሔራዊ ኮሚሽን ሰብሳቢ የነበሩት ቺዲ ኦዲንካሉ ከወራት በፊት https://africanarguments.org በተባለው ገፅ ላይ “The situation in Ethiopia is a Unique War and The African Union Has a Legal Duty to Silence the Guns” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ሐተታ የኢትዮጵያና የናይጄሪያን ተማስሎ በቢያፍራ እና በትግራይ በማናፀር ህብረቱ በቃሉ መሠረት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን እንዲፈታ ጠይቀው ነበር፡፡

በፅሁፋቸውም ነገርዬው የወገን ጦርነት (Civil War) እንጂ ህግ ማስከበር (Law Enforcement) ሆኖ እንደማይዘልቅ አሳውቀው:- “What is happening in Tigray is war or, to use the language of international humanitarian law, “armed conflict.” International law knows broadly two types of armed conflict: internal armed conflict (more popularly called civil war) or international armed conflict, which describes a war between two or more countries.” የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱትና እንደሉዓላዊነት ሁሉ ግጭቶችን መፍታትም በህብረቱ ህገ-ደንብ መብትና ግዴታ (conflict resolution is both a duty and a right.) ስለመሆኑ አውስተው ነበር፡፡

የአገራት “የውስጥ ጉዳይ” ሲባል?!

የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ገዢው የፖለቲካ ማህበርና አንደበት የሆኑላቸው የመገናኛ ብዙኃን “ሉዓላዊነት” ሲሉ እንደሚመቻቸው ከሚያቀርቡት ቃል ባልተናነሰ “በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት” የሚል ሐረግ ይጠቀማሉ፡፡ የቻይና፤ ሩሲያ፤ የቱርክና ኢራንን ደጅ ሲጠኑም ይታያሉ፡፡ የእነርሱን ጣልቃ-መግባት ግን ህወኃትም በሥልጣን ሳለ ይፈልገው እንደነበረው ይፈልጉታል፡፡ እርግጥ ነው ቻይና “Policy of Non-Interference” መርህን ትከተላለች፡፡ መሪዋም ዢም በፖለቲካዊና ምጣኔያዊ ድጋፏ ረገድ “No Political Strings Attached.” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አምባገነን የአፍሪካችን መንግሥታትም ይሄ ገለፃ ሰርግና ምላሻቸው ነውና እየሄዱ ቻይና ጉያ ስር በመሸጎጥ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ዜጎቻቸው ላይ ይጭናሉ፡፡ በአገራችን ግጭቶች ውስጥ እጃቸውን የዶሉና በውስጥ ጉዳያችንም ጣልቃ የገቡ አገራትን ጉዳይ ሳንፈታ ሌላ እንግዳ የመጋበዙ አደጋ እየታየን አይደለም፡፡ የምዕራብ-ምስራቁ ጎራ ሙሉ ለሙሉ አለመፍረስም ቀንዳችን ላይ የሚደቅነው አደጋ እንደተጠበቀ ሆኖ የገባንበትን እሳት አራግቦ ለፍጅት ሊዳርገንና ያለአሸናፊ በሚደረግ ውጊያ ውስጥ ሊያዘልቀን እንደሚችል መገንዘቡ ተገቢ ነው፡፡

በኢትዮጵያ መጥቷል ትበሎ ለተቀለነሰው “ለውጥ” የአገራት ውስጣዊ ጉዳይ ሆነው የማይቀሩ ነገሮች አሉና የአሜሪካ ምልመላና ሹመት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ መርጦ ዓቢይ አህመድን (ኮ/ል) እንዳላስቀመጠ ይታወቃል፡፡ ዛሬ እንደፍላታም ጎረምሳ ባንዲራ ካላቃጠልን የሚሉትም ቢሆኑ በዚሁ የአሜሪካ ጣልቃ-ገብነት ከኢህአዴግ በትራዊ አገዛዝና ከእስር ቤት ማጎሪያዎች እንደተላቀቁ መርሳት አይገባም፡፡ በቄሮና ፋኖ ድንጋይ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ጣልቃ ገብነትም አንዱ ከሥልጣን ወርዶ ሌላው ሥልጣን እንደተሰጠው ተደጋግሞ መነገር ይኖርበታል፡፡

በዙሪያችንና በአፍሪካ ቀንድ ላይ የቀጠለውን የኃያላኑ መሳሳብ ለእኛ በሚጠቅም መልኩ ለማስኬድና በድልም ለመወጣት የውስጥ ሠላም ከአንድነት ጋር መኖሩ በመሠረታዊ ግዴታነት የሚያስፈልጉን ጊዜ ላይ ብንሆንም ለቀናዒው መንገድ ገና ነን፡፡ ከዕቀባው በፊት ሱዳን በግብፅ ተመልምላ ጓሯችንን ማረስ ጀምራለች፡፡ ከመንግሥታችን ቅቡልነት መውደቅጋ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች “ለውክልና ጦርነቱ” ሊያንገራግሩን እንደሚችሉ መጠበቅም መልካም ነው፡፡ የኬንያ የቀድሞ ፓርላማ አባልና ምክትል አፈ-ጉባዔ የነበሩት ፋራህ ማሊም ያለንበትን አደገኛ ሁኔታ የገለፁበትን ቃል እዚህ መድገሙ አስፈላጊ ይመስለኛል:- “Egypt is frantically trying to build a friendly wall around Ethiopia…. Unfortunately, we are witnessing the Beating of drums of war in Horn of Africa. African Desist Wars.” በማለት ነበር እውነታውን ያስቀመጡት፡፡

የሱዳንና ግብፅ ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምዶችን፤ የልምምዶቹ ቦታዎች ድንበር ቀረብነትና ተለማማጆቹም ወደግብፅ ሳይመለሱ ሱዳን የመቅረታቸው አደገኝነት ብዙ ነው፡፡ ለሁሉም አደጋ የሚያጋልጠን ግን ውስጣዊ ይዞታችን ነው፡፡ የባዕድ አገር ሠራዊት ሆኖ ለበቀል የገባው የኤርትራ ጦር መውጣት ይኖርበታል፡፡ አሁናዊውን ሁኔታ ለማስጠበቅም የአማራ ክልልም ሆነ ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች በሙሉ ከምዕራብ ትግራይ መሳባቸው የግድ ነው፡፡ በአካባቢው የሚኖረው ህዝብ አስተዳደራዊ ፍላጎቱን በህዝበ-ውሳኔ እስኪገልፅ ድረስ የፌዴራሉ መንግሥት ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ መወሰን ይኖርበታል፡፡

ህወኃት ከኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች የተለየ የትኛውንም ኃጢያት ቢሸከም እንኳን እንዲህ በቀላሉና በ-17-ቀናት ኦፕሬሽን እንኳንስና ከትግራይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጪ አደርገዋሁ፤ ከታሪክም እፍቀዋለሁ ብሎ ማሰብ በራሱ ከአጉል ጀብደኝነት ጥንውት የተሸለ ስም አይገኝለትም፡፡ ወዲያውም ህወኃት እስካልተወገደ ድረስ የትግራይ ህዝብ ቢራብና ቢሰቃይ ምን-ገዶኝ የማለትን ዋጋ ዛሬ ላንረዳው እንችል ይሆን እንጂ መክፈላችን ግን አይቀሬ ነው፡፡ አገርን ከመንግሥት፤ መንግሥትን ከገዢ የፖለቲካ ማህበር መለየት ተስኖን የንጠላ ግድግዳውን የምናጠብቀው ከሆነ ዕጣችን ፍርሰት ላይ ብቻ አይቆምም፡፡

To withdraw or not to withdraw?!

በዘመነ ሉላዊነት ዓለም ከእያንዳንዱ አባል አገር የሚጠይቃቸው የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የነፃ ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎችና ነፃነቶች አሉና ሉዓላዊነት እንደ መብት (Sovereignty as a Right) ብቻ ተወስዶ መንግሥታት በግዛቶቻቸው ያልታጠቁ ዜጎቻቸውን መሠረታዊ መብቶች ሲጥሱና በሰው ሰራሽ (Man Made Starvation and Famine) ርሀብ ሲያዳክሙ ብሎም “እስካልመጣሁባችሁ ድረስ የእኔን ጉዳይ ለእኔው ብቻ ተውልኝ!” ይባልበት ዘመን ቀርቷል፡፡ ለደህንነትና ለሰብዓዊ ጉዳዮች (For the Sake of Security and Humanitarian Concerns) ጣልቃ ገብነትን የሚፈቅዱ ህግጋቶችን አለማችን አበጅታለች፡፡

ሐረጉ በትክክል ማንን ይመለከታል የሚለው ነጥብ ይቆየንና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ (The International Community) እንዲህ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአንድ በኩል መንግሥታዊ ኃላፊነትና ግዴታን በአግባቡ ባለመወጣት (Sovereignty as a Responsibility) በሌላ በኩል ደግሞ መብቶችን ባለማክበር ያስጠይቃል፡፡ ጥየቃውም እንደ ነገሩ ሁኔታ እስከ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የደፈረ እርምጃን ሊያስወስድ ይችላል፡፡ ይህም መንግሥታት ላይ የሚደረግ ጫና ተፅዕኖው የታወቀ ቢሆንም አገራት ላይ እንደተደረገ ወይም እንደሚደረግ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቆጠር አይሆንም፡፡ በገዛ አገሩ ዜጎች ላይ በይፋ ያልተጋበዘ የሌላ አገር ጦርን ጣልቃ ገብነት የፈቀደ መንግሥት “Absolute Supremacy over Internal Affair” ያጣልና ይህንንም ተከትሎ “Absolute Right to Govern it’s People” አይኖረውም፡፡

ስለ “ሉዓላዊነት” ፅንሰ ሃሳብ ስንነጋገር እንደጠቀስነውም ይህ መንግሥት ከጣልቃ ገቢው ፍላጎትና ጥቅም (Interest) ፈፅሞ ሊርቅ አይችልምና የሚመራውን አገር ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ በሚከት ሁኔታ መንግሥታዊ ሉዓላዊነቱንም ይነጠቃል፡፡ በዚህ ረገድ የድንበሮቻችን አለመከበር ብሎም በወታደራዊ ሀይል መያዝና በድፍረት መወረር "ሉአላዊ ነን!" እያልን በምንጮኸው መጠን የሚሰፍረን አይደለም። የሻእቢያ ሠራዊት አሁን ለሚያደርሰው የግፍ በቀላዊ ሰቆቃ ትናንትን እንደሚያጣቅስ ማስተዋል በቂ አስረጅ ነው።

አልገባም ሲባል ተከርሞ መግባቱ ይበልጥ እየተጋለጠ ሲመጣ የአልገባምንም የገብቷልንም በአንድ ጊዜና በአንድ ሰው አንደበት ለማስረዳት የተኬደበት ርቀት ገርሞ ሲገርመን ራሱን ለመከላከልና ከተደገነበት የደህንነት ስጋት የተጋበዘው የሻእቢያ ጦር "ከትግራይ እየወጣ ነው!" በተባለ ማግስት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች መታየቱ ያለንበትን የችግር ገዘፍ ጠቋሚ ነው። በቀድሞው ደርጋዊ የድንቁርና ብሂል መሠረት "አሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ የግድ ነው!" እየተባለ በህወኃት የአሳዳጅነት ዘመንም ሆነ በህወኃት የተሳዳጅነት ዘመን ከመከራ ያልራቀውን የትግራይ ህዝብ ለሰው ፈጠር ርሀብና ችግር ብሎም ለጦር ወለድ ሰብአዊ ሰቆቃ መዳረግ ይቅር የማይሉት ስህተት ስርየትም የሌለው ወንጀል ይሆናል።

እርግጥ ነው ሠይጣንን ወደራስ መጋበዝ ከራስ የማስወጣቱን ያህል አይቀልምና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባዩ "አንድ ቀን ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን!" ሲሉ መደመጣቸው ከፊሉ ልግጫ ከፊሉ ደግሞ መራር እውነታችን ነው። በአንድ ሰሞን ታይታ የጠፋውና የተግባቦትና መረጃ ስልጠት ስራውን ከቀድሞው "የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት" የወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ፕሬስ ሴክሪቴሪያት በቢልለኔ ስዩም በኩል በሰጠው መግለጫ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ "ለሚመለከተው አካል" በኢትዮፕያ መንግሥት በኩል ጥያቄው ስለመቅረቡና ሂደቱም እንደተጀመረ ተነግሮ ነበር።

መግለጫው ያልተብራሩ ነገሮችን ከመያዙጋ ከወር በፊት በኢትዮፕያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊርማ ለኤርትራው አቻ እንደተላከ ተነግሮ በወሬ የቀረውን ጥያቄ ትርጉም አልባነት ከሚያስታውሰን በቀር ፍሬ አይኖረውም። ይህንን ፅሁፍ በማሰናዳበት ውቅት “To withdraw or not to withdraw, that is the question!” የሚል አማራጭ የቀረበለት የኤርትራ ጦር ምዕራብ ትግራይን ብቻ ለቆ እንደወጣ “Eritrean Press” ቢዘግብም ዘገባው ሊመጣ ያለውን መዓት ለማዘግየት የተለመ እንጂ ከእውነታው የራቀ ስለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በዝምታችን የግፎቹ ተባባሪዎች እንደምንሆን የሚነግረን ፕላቶ ዝምታን እንደመቀበል ይቆጥረዋል፡፡ ስለሥልጣን ታጥቀው ለሚተጋተጉት ጉዳያችን ላይሆን ይችላል፡፡ ሁለቱንም እንደየአግባቡ መተቸትም መብታችን ነው ግን እንዴት ባልታጠቁ ንፁሀን የትግራ ወገኖቻችን ላይ የሚጨክን ስብዕና እንዳዳበርን አልተያዘልኝም፡፡ ጀርመንን ያዋሀዳት ኦቶቮን ቢስማርክ "Never believe anything in politics until it has been officially denied." እንዳለው ይህ ሰቆቃ በይፋ በመንግሥት ቢስተባበልም ዓለም ሰምቶት ለእርምጃ ተዘጋጅቷል፡፡ በቀጣዩ ፅሁፍ በእንደዚህ አይነት ሰቆቃዎች ወቅት ስለሚካሄዱ ጣልቃ-ገብነቶች እስከምንነጋገር ሊዮ ቶልስቶይን እንካችሁ፡- “If you feel pain, you are alive. If you feel other people’s pain you are a human being.” (Leo Tolstoy)

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :