ኢትዮጵያ - “የሚወድቁ አገራት” ዝርዝር ውስጥ?!

Failed Statesሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

June 18, 2021

“It’s dangerous to be right when the Government is wrong.”
(ቮልቴር)

ከድህነቷ ጋር እየተንገታገተች ዘመናትን የፀናቸው አገራችን ኢትዮጵያ በየወቅቱ የጦርነትና ረኃብ ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡ በየጊዜውም የህልውና ጥያቄዎችን ትጋፈጣለች፡፡ ችጋርና ድህነት በሰፊው ከተንሰራፋው ጦር ወዳድ ድንቁርናችን ጋር እየተሰናሰሉ የህልውና ውጥረታችን ደልዳላ መሠረትና ምቹ ቀጠና ሆነዋል፡፡ ከህልውና ትግል ለመውጣት ድንቁርናን እና ድህነትን ድል መንሳት አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታ ቢሆንም በየወቅቱ “የድህነት ዘበኛ” እየሆኑ ከአገረ መንግሥቷ መንበር ላይ የሚደላደሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የቁስለቷ ድነት ላይ የሥልጣናቸውን ዕድሜ መራዘም ይመሰርታሉና ሰቆቃችን እንደቀጠለ አለን፡፡

ስለዚህም መንግሥታቱ በሽታችንን ሳይሆን የበሽታውን ምልክቶች በማስታገሻ ማቆየት እንጂ ማከሙን አይፈልጉትም፡፡ አገራችንን ኢትዮጵያን እጅግ አድርገን ለምንወድ ዜጎቿ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ልንንደረደረው በያዝነው የቁልቁለት ጉዞ ሳቢያ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ወቅቶች እንዲሁም በተለያዩ መመዘኛዎችና ምልክቶች የወደቁ አገራት (Failed States) መዘርዝር ውስጥ መግባትን ቀርቶ ለውድቀት በቀረቡና ደካማ ሆነው በመውደቅ ሂደት ላይ ባሉ (Weak and Failing States) አገራት ተርታ መሰለፍን “የሠይጣን ጆሮ አይስማው!” ብለን በሩቅ የምንፀልይበት ክፉ ሟርት ነበር - በነበር ቢቀር!

ከውድቀታችን በስተፊት - ፖለቲካዊ ምልክቶቹ!

ኢትዮጵያውያን ሩቅ ማማተር ሳይኖርብን የቅርብ ጎረቤታችን ሶማሊያ ፈርሶ መቅረትንና የሁለቱን ሱዳኖች ዕጣ ከየመን ጊዜያዊ ሁኔታጋ ደምረን ልንማርባቸው በቂ ነበሩ፡፡ አሻግረን ስንመለከት የሊቢያና ሶሪያን ውድመት ከኢራቅ ፍርሰት ጋር ልንመለከትና ቀልብያችንን ልንሰበስብም ዕድል ነበረን፡፡ ምክንያቶቹ ሊያነጋግረን የሚችለው የቅርብ ጊዜው የመታከም ተስፋ ምክነት ለዚሁ አንድና አይነተኛው ማሳያ ነው።

በቃል ተለምዶ ውዱቅ መንግሥታትን (Failed States) ለመበየን በተገቢነት ሊሟሉ በሚገቡ መስፈርቶችና ቅድመ-ሁኔታቸው ላይ አንዳች አይነት የጋራ ስምምነት ባይኖርም ምሁራኑ ከፈረሱ አገረ መንግስታት (Collapsed States) እና ከወደቁት (Failed States) መካከል የሚገሽሯቸው ደካማና በመውደቅ ላይ ያሉ አገራት (Weak and Failing States) በጅምላ የሚጋሯቸው ጠባያትና በመንግሥቶቻቸው የሚንፀባረቁ ባህሪያት አሉና “Failed states are tense, Deeply Conflicted, Dangerous and Bitterly Contested by warring Factions. Domestically, they cannot safeguard minimal civil conditions such as peace and order, facing serious internal problems that threaten their continued coherence or significant internal Challenges to their political order.” የሚለው ገለፃ አስማሚ ይመስለኛል፡፡

የሥልጣን ዘመናቸው ህጋዊነት ያከተመው የአብይ አህመድ (ኮ/ል) አገዛዝ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ "ሲመቸኝ ዝም ብል ዝም ያልኩ መስሎታል ሲታሰብ ነው'ንጂ ዝም ማለት የታል?!" ከሰኙት ጊዜያዊና ህዝባዊ ዝምታ ጋር መተጋገሉን እንደቀጠለ ነው። ዛሬ አብዝተው የሚያብጠለጥሉት እናት ድርጅታቸው "ኢህአዴግ ቀዳማዊ" ቅቡልነትን በልማት ይመኝ ነበርና እርሳቸውም በዚህ ክሽፈት ላይ የይስሙላ ምርጫን እንደቅቡልነት ማግኛ መንገድ ደምረውበታል።

የመልካም ተስፋ ሽልማትና የዲፕሎማሲው መስክም ማማ ከሆነው የኖቤል ሠላም ሽልማት በወራትና በዓመት ውስጥ እንዘጭ እንቦጭ ብሎ የቪዛ ዕቀባና የምጣኔ ሀብታዊ እገዳን ያስከተለ ጦርነት ውስጥ መግባት አይገመቴ ነው፡፡ ይሄ አሮጌ ዙረት (Vicious Circle) ውስጥ የመመላለሳችን ማብቂያን ርቀት ጠቋሚም ነው፡፡ ተሳልቆውን የሚያደምቀው ደግሞ ከጀመርነው ቁልቁለት የመገቻው መንገድ አይረቤ ፉከራና የባዶ አቁማዳ ቀረርቶ ሆኖ የተመረጠ መምሰሉ ነው፡፡ በተደጋጋሚ በህዝብ የተጠየቀውን የአገራዊ ብሄራዊ ምክክርና ድርድር ጉዳይ ከምርጫ ተብዬው በኋላ የብዙሀን መገናኛዎቻቸው ቀዳሚ አቧራ ማቡለያ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።

መድረኩ የሚመዘጋጀው መሠረታዊ ጥያቄዎችን በሚያነሱና ከፊሉም በፖለቲካና በህሊና እስረኝነት ከተያዙ ፓለቲከኞች ጋር አለመሆኑም የሚጠቁመን አንድ ነገር የሂደትና ውጤቱ ጋርዮሻዊነት የታወቀለትን ተቃራጮቹም በመሠረታዊ ውጤቱ ላይ በአይን ጥቅሻ ወከንፈር ንክሻ የተመቻመቹበትን "ምርጫ" ተከትሎ እንዲከወን የማድረግ ወንበር ከረጋ በኋላ የሚፈፀም ሥነ-ሥርአት (Vicious Circle) እንጂ ከሥልጣን በላይ ለሆነው ዘላቂ የአገር ሠላምና ጥቅም የቀና አይሆንምም ተብሏል።

ከአሮጌው መንገድ ለመውጣት ጀምረው ተስፋ ያስሰነቁን የብዙሀን መገናኛዎችም አንፃራዊ ነፃነታቸውን እየጠበቁ ከመጓዝ ይልቅ ለመጣ ለሄደው መንግሥታዊ ሥርአት ሁሉ ወዶገብ ባሪያ በመሆን ብኩርናቸውን በምስር ይለውጣሉና ጥርጊያቸው በአሮጌው ፍሳሽ ተሞልቷል። በመንግስት አጋርነት ከሚታማው ስብስብ ሳይቀር ተደጋግሞ እንደተነገረን አማራጭ ሀሳቦች ከምንግዜውም በከፋ መልኩና በስልታዊ መንገድ እንዲታፈኑ ሆኗል። የጋዜጠኞች ብዕርና አንደበት ከበአሉ ግርማ ብሂል ተቃርነው ልወደድና "አድር ባይ" መሆናቸውን አስቀጥለዋል። ከፊሎቹም በልኑርበትና ልጆቼን ላሳድግበት ፍርኃት ራስን በራስ ሸብበዋል፡፡

ሊያበቃ ነው ያልነውና ቃል ተገብቶለት የተካደው የሰዶ ማሳደድ ዘመን "ዶሮን በቆቅ" ለውጦና የማድባቱን ዘመን ተሻግሮ በወታደራዊ መለዮ እየተንጎማለለ ነው። የወደቀው የፍትህ ሥርአት የማያውቃቸው ከፍርድ ውጪ የሚደረጉ ማጎሮችና የምፅአተ ነፃ-ግድያዎችን (Extra Judicial and Arbitrary Killings) የደረበ ማሳደድ በርክቷል። ውክቢያና እስራትማ የሰርክ ዜናዎቻችን ናቸው። የድጋፍና የንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ ውዳሴ እንጂ የተቃውሞ ሀሳብም ሆነ ሰልፍ ባልታወቀ የህግ አግባብ "ነብሳችሁ በሠላም ትረፍ!" ተብለው ተቀብረዋል።

ዜጎች ሊቀር ነው ብለን የተሰፍንበትና እነሱም እንደሚቀር እኛን ያስተሰፉበት በፓለቲካዊ ልዩ አመለካከታቸው ሳቢያ ግለሰቦችና ቡድኖችን በአገርና ሠላም ፀርነት መፈረጁ ብሶበታል። ከአሸባሪ፤ ፀረ-ሠላም፤ ፀረ-ልማት፤ ጠባብ፤ ትምክህተኛ.... የመሳሰሉ ፍረጃዎች ላይ አዳዲስ ማሸማቀቂያዎችን ወደፖለቲካ መሰብስበ ቃላቶቻችን አስተዋውቀውናል። ፀረ-ለውጥ፤ የቀን-ጅብ፤ ፀጉረ-ልውጥ፤ ፅንፈኛ፤ ዘረኛ፤ ባንዳ እና የግብፅ ተላላኪ ብሎ የሥርአቱ ተቃዋሚዎች ላይ ቅጥያ መለጠፍ ከገዢው የፖለቲካ ማህበር ወደ መንግሥታዊው መዋቅር ወርዷል።

ተራ-ተርታዎቹም ተቀብለን እያስተጋባነው ለዙሩ መጦዝ አሉታዊ አበርክቷችን ቀላል አልሆነም። ይህንን ፅሁፍ በማገባደድ ላይ ሳለሁ ተዓማኒነቱን እንደተቋም ማስመለስ ያልቻለውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚመሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የህግ ባለሙያ ሆነው ሳለ ከዚህ በፊት በፍርድ ቤት ተወስኖ የተላከላቸውን ውሳኔ “ለማስፈፀም እቸገራለሁ!” በማለታቸው ስንገረም ከሰሞኑ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ የመብት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ለነበሩ ሰዎች የሰጡት ቅጥያ “የጎን ውጋት!” መሆኑን ላስተዋለ የችግሩን መጠንና መዋቅራዊ ጥልቀቱን ለመገንዘብ አይዳግተውም፡፡

ከውድቀታችን በስተፊት - ምጣኔ ሀብታዊ ምልክቶቹ!

ከእነዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎች ጋር በጥቂቶች ካልሆነ በቀር የማይወሳው ምጣኔ ሀብታዊው መውደቅ ይደረባል። አገራችን በሮበርት ኤች.ጃክሰን ስላቃዊ አገላለፁ የተወጋ ሉአላዊነት (Surrogate Ssovereignty) ካላቸው አገራት ነው ምድቧ። ያልተከፈሉ፤ የዕዳ መክፈያ ጊዜያቸውም ያልተራዘመላቸው ውዝፍ እዳዎች ከሚያስጨንቋቸው የአፍሪካ አገራት ስር ነው መዘርዝሯ።

በዚህ የደንባራ በቅሎ ምጣኔ ሀብት ላይ ከሰሞኑ የተጣለብን እቀባና እገዳ ሹማምንቱና ሸቃሎቻቸው በቀጥታ ላይጎድልባቸው ይችላልና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባዩ በኩል "አንዳንድ ስሜታዊ የሆኑ ሰዎች" ተብለው ከተገለፁት አንዱ የነቀዘ አመለካከት ባልደረባ እንደተናገሩት ተፅእኖው "የነቀዘ ስንዴ ነው የሚቀርብን!" ተብሎ ብቻ የሚያልፍ አይደለም። የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት በምጣኔ ሀብታዊ የቴሌኮም እጅ መንሻ ለማካካስ የተኬደበት ርቀት ውጤት የራቀውም ለዚህ ነው።

በሚሊዮን የተገመቱ ምሩቃን ወጣቶቻችንን ከጫትና ተያያዥ ሱሶች አልላቀን ወደስራ ማስገባት ያቃተን ሆነን ሳለ ለመሸጋገሪያ ተብሎ ዓመታትን ቆሞ እንደቀረው የ"አብዮታዊ ዴሞክራሲ" ፕሮግራም ከርእዮተ አለም "ተቸካይነት" በመውጣት ለረዥም አገዛዝ የተመቸ እንዲሆን በመተለም ተቀርፆ "Pragmatism" ሲሰኝ ይደንቃል። ይህ "አገር በቀል" የሚል የዳቦ ስም የተገሸረለት መንገድ እንደቀደመው የልማታዊ መንግስት እሳቤ ሁሉ በአገራችን የሌለውን አስቻይ ሁኔታ በደቡብ ኤዥያ አገሮች ስኬት የሚመነዝር ነው።

አማራጭ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎችን ሲያንስ ለአስር ሲበዛ ለሰላሳና አርባ ዓመታት ከፓለቲካው ምህዳር የመግፊያ ኢህአዴጋዊ ብልጠትም ነው። አብይ አህመድ (ኮ/ል) ይህንን ውጥናቸውን በተደጋጋሚና በተለያዩ አውዶች ነግረውናል። እሳቤው የፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ይዞታ የቆመበትን ምሰሶዎች ምንነት እንዳናውቅ ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ እንዳንጠይቅም የሚያደርግ ነው። በአገር በቀል ስም የተሸፈነው ግራ የተጋባ መርህ የብራችንን ምንዛሪ መጠን ከአሜሪካ ዶላር አንፃር የት እንዳደረሰው ለማወቅ ግሽበቱ በመሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ እንኳን በአስደንጋጭነት መቀጠሉን መረዳትን ይጠይቃል፡፡

ከላይ የጠቀስነው ያልተከፈለ ውዝፍ ዕዳ ለወደቁ አገራት አንድ መስፈርት ሲሆን በደካማና በመውደቅ ላይ ላሉ አገራት ደግሞ ከበቂ በላይ ነውና ቻይና ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉ የአፍሪካ አገራትን አንዳንድ ሀብቶች ለማስተዳደር ዳርዳርታዋን ስለማሳየቷ አይዘነጋም፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመተው የታይታ ስራዎች ላይ የተተኮረበትና ለምርጫው ፍጆታም እየተዞረ የተመረቀበት አካሄድ በህዝቡ ኑሮ ላይ ይልቁንም የዕለቱን እየበላና እያበላ የሚኖረው ሰፊው ድሀ ማህበር ላይ የደገነው ችግር አስከፊ ሆኗል፡፡

ከአገራዊ ውድቀታችን አፋፍ ላይ.... ?!

መንግሥት የምንለው አካል ቀዳሚውና አስፈላጊው ኃላፊነት በተለምዶ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍጆታዎች (Political Goods) በሚባሉት መሠረታውያን ላይ በህዝብ ውክልና መስራትና ለህዝብ ማቅረብ ነው። ከእነዚህ አቅርቦቶች ውስጥም በጅምላ የህዝቦችን በተናጠል ደግሞ የዜጎችን ደህንነት ጠብቆ ማስጠበቅ ቀዳሚ ለኩሉ ነው። ህግና ሥርአትን በህጋዊና ሥርአታዊ መንገድ በማቅናት መልካም አስተዳደርን ማንበር ከመሠረተ ልማት ስራዎች ማሟላትጋ ቀጣዮቹ የመንግሥት ሃላፊነቶች ይሆናሉና "States fail when they are no willing or able to carry out these functions." ይላሉ የሥነ-መንግስት፣ የህግና የፓለቲካ ምሁራኑ።

አገራችን ኢትዮፕያን በአንድ በኩል ወደውዱቅ አገራት ዝርዝር ሊያካትት በሌላው ጎኑ ደግሞ በመውደቅ ላይ በሚገኙ አገሮች ጎዳና ላይ የሚያቆይ፤ ወደን የገባንበት ነው ብዬ ባላምንም በከፊል የብሄር ማንነትን መሠረቱ ያደረገ ፓለቲካ በደካማና በመውደቅ ሂደት ላይ መዘርዝር ውስጥ ለመቆየት አንድ መስፈርት ነው። በሌላ አገላለፅ ከአገራት ፍርሰት በስተፊት ከሚታዩ የመከፋፈል ምልክቶች በሁሴን ባራክ ኦባማ አገላለፅ "ማንነትን መሠረቱ ያደረገ" የተባለለት ብሄርን ያማከለ ስንጥቅ (Identity as a Basic Unit of Social Oorganization) አንዱ ይሆናል ማለት ነው።

በአገረ መንግሥቱ ግንባታና ቅጠላ ላይ በግልፅ የታዩ መግፋትና ማግለሎችን የመንግሥት ሥልጣንን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተቆናጠጡ ሰዎች የሚደርቧቸው ቁርሾዎች ስንጥቁን እያሰፋትና መቻቻሉን እያደፈረሱት ውሻ በቀደደው ጅብ እንዲገባበት ይሆናል። ምሁራኑ “State Failure need not be reserved for cases of complete state collapse, either into civil war or Anarchy but can also be understood as a process involving the weakening of a state’s Capacity to meet its Responsibilities and Provide legitimate Governance.” የሚሉበት አገላለፅ እውነታችንን አቡጎ የሚያስመለክት ይመስለኛል።

አለመታደል ሆኖ ይህንን ስንጥቅ ለመድፈን ችግሮቻችን ላይ አድምተን በመነጋገር፤ አገረ መንግስቱንም አካታች በማድረግ ከ"ህዝቦች" ወደ "ህዝብ" በሂደት ልንደርስ እንችልባቸው የነበሩ መንገዶች ሁሉ ተበለሻሽተዋል። በቃል አሳማሪ ገዢዎቻችን ይህንን አይነት ታሪካዊና ፖለቲካዊ እድሎች መክነውብናል። እኛም እንደህዝብ በተራዳኢነት አክሽፈናቸዋል። ሥልጣን ወዳድና ሥሥታምነት ይገነባሉ የተባሉ ድልድዮችን እንዳይገነቡ አድርጎ መተማመኑን ንዶታል። ግድግዳውንም በጥላቻ ላይ ገድግዶበታል።

ችግራችን ግን ይህ ብቻ አይመስልም። ኮሎኔሉ እንደአፍ ድልጠት ቀለል ተደርጎና ከፖለቲካዊ ብስለትና የልምድ ማነስ እንዲወሰድ በውታፍ ነቃዮቻቸው የተሰራለት ነጥብም በይደር ይቆየናል። ምለውና ተገዝተው ሥልጣን ከያዙበት ህገ-መንግሥትም ሆነ በሁለቱ መፃህፍቶቻቸው ከገለፁት ስብእናቸው ባሻገር የታየው የ"ህዝብ" እና "ህዝቦች" ቁማር ላይ በየትኛውም የፌዴራል ሥርአት ውስጥ የሚኖረውን ጋርዮሻዊ መንታ ሉአላዊነት (Dual Ssovereignty) በመካድ ስለ አገራዊ "ድንበር" እና ክልላዊ "ወሰኖች" መረዳታቸውን የገሩበት መንገድም እጅግ አደገኛ ይመስላል - ከተሞከረ!

ዶናልድ ፖተር የተባሉ የሥነ-መንግሥት ምሁር ይህንን የአገራት ፍርሰትን የሚያማጡና የሚያዋልዱ ምልክቶች ከነሂደታቸው አጠር ግን ደግሞ በጣም ግሩም አድርገው ባቀረቡበትና "State Responsibility; Sovereignty and Failed States" የሚል ርዕስ በሰጡት አንድ ህትመታቸው ላይ ይህንን ትንቢት አዘል መስፈሪያ ኢትዮፕያችንን እያሰቡ የከተቡት እስኪመስለን ድረስ በደነቄታ እናነባለን:-

“Only few of the world’s states can be described as failed or collapsed. But, there are many dozens more that are weak and possible candidates for total failure. They generally share some of the following negative characteristics; a rise in criminal and political violence, a loss of control over their borders, Ethnic Religious or Cultural tensions or Hostilities as well as weak Economy and Declining levels of GDP per capita.”

ሉዓላዊነት ከፓለቲካ ሸቀጦች አንዱ ነውና ድህነታችን "Legal Equality of States" ይሉትን አይነት እኩል አገርነት አሳጥቶን አይቆምም። ወዲያውም ኮሎኔሉ በሸንጎ ውሏቸው "ድሀ አገር ሉአላዊነት የለውም!" ማለታቸውን ይዘን መፈተሹ አይከፋም። ሉአላዊነትን በምሉእነቱ ከመፈለግ ይልቅ እንደቀደመው ዘመን የፖሊሲ ነፃነታችን እንዳይወጋ መጠበቡ ይፈይደን ይመስለኛል።

የብልፅግናው መንግሥት ህጋዊም ህገ-መንግሥታዊም ባልሆነ አካሄድና ከሌሎች አምባገነን የአፍሪካ አገራት ኮርጆ ያራዘመው የሥልጣን ዘመኑ የቅቡልነትን ችግር ደርቦ እየተከተለው ነውና በመጪዎቹ ቀናት ለብቻው ባመቻቸው ደልዳላ ሜዳ አደርገዋለሁ የሚለው "መረፃ" የህግም ሆነ የፓለቲካ ይዞታውን በጊዜያዊነት እንጂ በዘላቂነት አያፀናለትም።

ይልቁንም ይህንን ችግር በሰሜንም በምእራብም ከሚደረጉ አሰቃቂ የእርስ-በእርስ ጦርነቶች ላይ በተደራቢነት ስንመለከተው መንግሥት አገራችን አሁን ካለችበት የደካማና በመውደቅ ሂደት ላይ ካሉ አገራት (Weak and Failing States) ወደ ውዱቅና የፈረሱ አገራት (Failed and Collapsed States) ይዞን እንደሚወርድ ያስገምታል። ከፍርስራሹ ማን አትራፊ ሊሆን እንደሚችል ማንም እርግጠኛ አይሆንም። የአለማቀፍ ድንበሮች አለመከበር የሉአላዊነት መሸራረፍ (Erosion of Sovereignty) ሌላው ምልክት ነው።

የወደቀ ምጣኔ ሀብታችን ላይ የብሄር መቧቀሶች መደመራቸው ሲገርመን ሃይማኖታዊውን ካባ የደረቡ ፍጥጫዎች አክለንባቸዋል። የህግ ማስከበር ዘመቻ ስላቁ ወደለየለት የወገን ጦርነትና የዘር ፍጅት ሲዋረድ ርዝማኔው የደቀነልን ፍርሰትን ነው። እነዚህ ተጠቃሽ መስፈርቶች ሁሉ ለአደጋው ቅርብና ግልፅነት ከበቂ በላይ ማሟያ ናቸውና በፍጥነትና በርብርብ ካልተሰራ የቀጣይ ፈራሽነታችንን ቀሪ ጥቂት ሀሙሶችን ያሳብቃሉ።

ወዲያውም "Possible Candidates for total Failure" የሚለው ሀረግ አስደንግጦን ስለአገር ሲባል አይጢቱን በብልሀት ለማሳለፍ ካልቆረጥን እልሀችን ያፈርሰናል፡፡ ምርጫው ምናልባት ህጋዊ ሽፋንን ላጡት የዓቢይ አህመድ (ኮ/ል) አገዛዝ ሰዎች ህጋዊ ሽፋን የመስጠት ሚናውን ይወጣ ይሆናል፡፡ አገራዊ ዘላቂ ሠላምንም ሆነ ዴሞክራሲን እንደማያዋልድና ነገሮች በዚሁ እንደማይቀጥሉ ግን ለእርግጠኝነት ቅርብ ሆኜ ነው የምፅፈው፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :