ታለ “በአገር ሉዓላዊነት” ስም! (ማጠናቀቂያ - ሁለት በሉ!)

Ethiopia at warሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

August 5, 2021

"...if Humanitarian Intervention is, indeed, an unacceptable assault on sovereignty, how should we respond to a Rwanda, to a Serbrenica - to gross and systematic violations of Human Rights that affect every precept of our common Humanity?..."
 (የኮፊ አናን ጥያቄ)

በቀደሙት ሁለት ክፍሎች “ታለ በአገር ሉዓላዊነት ስም!” በሚል ርዕስ የጀመርነው መጣጥፍ በቀናቶች ልዩነት በብዙ በሚቀያየረው ፖለቲካችን ሳቢያ እነሆ እንደቀጠለ አለ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እስከጥግ ድረስ ሄዶ ችግራችንን በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ስንወተውት ቆይተናል፡፡ ግጭትና ጦርነት አይቀሬ ሲሆን ደግሞ ባልታጠቁና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት በሌላቸው ዜጎች ላይ የትኛውም አይነት ሰቆቃ እንዳይፈፀም ጮኸናል፡፡ ይህንን የጦርነት ህግ እየተላለፉ “ሉዓላዊነት” ላይ ሙጭጭ ማለት ከተጠያቂነት እንደማያስጥል መክረናልም፡፡ አሁን ጥረታችን ፍሬ ያፈራና የሉዓላዊነቱ ጋሻነት ያበቃለት ቢመስልም የምስራቅ እና የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካዊ ሁኔታን ከአቋማችን አኳያ እንመለከታለን - መልካም ንባብ!

“ምስራቅ” እና “ምዕራብ” ያዋጣን ይሆን?!

ቻይናን ለመብላት የብልሀትን አስፈላጊነት ያልተረዱ የአፍሪካ አገራት በቻይና ለመበላት ቀርበዋል፡፡ ሩሲያ ጣልቃ እየገባች ከአሜሪካ ጋር በተፋጠጠችባቸውም ሆኑ የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) በገጠመችባቸው አገራት ድል አድርጋ አታውቅም። የቅርቦቹን እንኳን ብንመለከት ኢራንን እያስከተለችና ቻይናን እያባበለች የዘመተችለት ጨፍጫፊው የአል-አሳድ መንግሥት የፈረሰ አገር ታቅፎ ነው ያለው። የኢራቅን የምታውቁት ነው። ከጎረቤቶቿ ጋር ያለችበት ጦርነትም ይታወቃል ምን እንደፈጠረ። ይህንን ፅሁፍ በማሰናዳበት ወቅት "የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር" የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን የጦር መኮንኑን ባጫ ደበሌን (ጄ/ል) አስከትለው ሞስኮ ናቸው። ወደቱርክም ጎራ ብለዋል፡፡

ይሄ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ!” ፖለቲካዊ ጨዋታ መነሾ ጣልቃ-ገብነትን ሽሽት ብቻ አይደለም፡፡ የበዛ የስልጣን ወዳድነት በሽታም እንጂ፡፡ ዓለማችን ከምስራቅ ወምዕራብ ፖለቲካዊ ምልከታዋ ባትላቀቅም ረገብ ማለቱ አይካድም፡፡ የምስራቁን ጎራ ቻናና ሩሲያ ሲዘውሩት ምዕራባውያኑ ደግሞ በአሜሪካና እንግሊዝ አለቃነት ላይ ተማምነዋል፡፡ ኢትዮጵያችን በውስጣዊ መፈናቀል (Internal Displacement) ዓለምን አስከንድታ በቀዳሚነት የተመዘገበችው ከሰሜኑ የወገን ጦርነት በስተፊት ቢሆንም በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉት ደግሞ የሰብዓዊ ድጋፎች (Humanitarian Access) እንዳይደርሱ የኤርትራን በቀል ጠማሽ ኃይሎች ያካተተው የመንግሥት ሠራዊት ከአማራ ኃይሎች ጋር በማበር እንደሚዘጉ በተደጋጋሚ በተደመጡ ገለልተኛ ዘገባዎች የተረጋገጠ ነው።

በሸኘነው ሳምንት ደግሞ የአፍሪካ የሰዎችና የህዝቦች መብት ኮሚሽን በኮሚቴዬ በኩል አስጠንቼዋለሁ ሲል በቀደሙት የዚሁ ፅሁፍ ሁለት ክፍሎች የወቀስነው የአፍሪካ ህብረት ድምፁን አሰምቶ ነበር። የሪፖርቱን ሙሉ ሀተታ ይህ ፅሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ይፋ ባያደርገውም "የሰሜኑን ጦርነት የጀመረው የፌዴራሉ መንግሥት ነው። ህወኃቶች በሰሜኑ ዕዝ ላይ ጥቃት የፈፀሙት ለዚህ መልስ ነው!" እስከማለት የደፈረ ነበር። የኢትዮጵያችን ፖለቲካ ለትንቢትም እየቸገረ ነውና ህብረቱ የገዢ አባላቱ መደበቂያ የሆነውን "ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ!" ይሉትን ማዋዣ ሰብሮ ይህንን ሲል በወዲያኛው ረድፍ ደግሞ የአውሮጳ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ገዢዎቻችንን ያናገሩትና ፔካ ሔቪስቶ ከዲፕሎማቶቻችን የቋንቋ እጥረት አልያም ኢ-መደበኛ ወግ ቢሆን እንጂ "ፈፅሞ ሊባል አይችልም!" ያሰኘውን የትግራይን ህዝብ መቶ ዓመት ወደኋላ እንመልሳለን ትርክት ይፋ አድርገዋል።

የአፍሪካ ህብረቱን ሪፖርት ሙሉው ሲወጣ በቀጣይ ክፍል የምንመለስበት ይሆናል፡፡ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ሰቆቃዎች በሁለት አንፃር ተመልክቷል፡፡ ምሥራቁ ዓለም በዝምታና በድጋፍ ምዕራቡ ደግሞ በተቃውሞና በድጋፍ እንዲሁም በማስፈራራት፡፡ እ.አ.አቆጣጠር ከ-1954 ጀምሮ ቻይና "The principle of Non-interference" ተብሎ ሊጠቀለል በሚችለውና "አምስቱ መርሆዎች" በሰኝቻቸው ነጥቦች በኩል የምትከተለው በአገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም በምትልበት መርኋ በንግድና ኢንቨስትመንትም ሆነ በፖለቲካና ወታደራዊ መስኮች ለአምባገነን መንግሥታት እገዛ እያደረገች የመሆኑ እውነት አልተደበቀላትም።

ሩሲያ መሳሪያዋን ለአፍሪካ ግጭቶች የምትነግድ ናት፡፡ ቻይናም ከሱዳን መንግሥት ጋር የነበራትን የነዳጅ ሽያጭ ስምምነት አስከትላ በጎረቤት ሱዳን "ጃንጃዊድ" ተሰኝተው በመንግሥት ለሚደገፉ ሚሊሻዎች በማገዟ አስከፊውን ሰቆቃ ዓለም ተመልክቷል። የተመድ ፀጥታው ምክር ቤትም በዛሁ የዳርፋር ግዛት ሰቆቃ ሳቢያ አሁን ኢትዮጵያ ላይ እንደተወጠነው አይነት የመሳሪያ ግዢና ትልልፍ እቀባን (Arms embargo) ጥሎ ነበር። ሆኖም የቻይናዎቹ ገዢዎች ይህንን በመተላለፍና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ቁብ ካለመስጠት የአልበሽር መንግሥትንና በዚሁ መንግሥት የሚደገፋትን ጨፍጫፊዎች የጦር መሳሪያ ሲያስታጥቅ ኖሯል። እንደሩሲያ ሁሉ ቻይናም ይህንን ወቀሳ ልታጣጥለውና የአሜሪካንን ተፅእኖ ለመቀነስ ብትተጋም አልተቻለም፡፡

የአፍሪካ ገዢዎች ይህንን የቻይናን ምንገዶኝ መርህ (Non-perspectivity) የመውደዳቸውና ወደእርሷም የመሰባሰባቸው ብቸኛ ምክንያት ለየአገሮቻቸው ያላቸው የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ቀናኢነት ሳይሆን ሥልጣን ላይ ያለጠያቂ የመክረም አህጉራዊ ልክፍት ነው። ቻይና ሩሲያን እያስከተለች ለተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት (UNSC) በሚቀርቡ እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች ላይ ከአሜሪካ አንፃር የምትሰለፍበት ልምድ አልተቀየረም። ድምፅን በድምፅ የመሻር (Veto Power) መብቶቻቸውን የሚጠቀሙባቸው ውሳኔዎች ቢገለጡ በመቃረንና በድምፀ ተዓቅቦ (Abstaining) ታጅበው የሚገኙ ናቸዉ። አለፍ ሲልም በውጭ ጉዳይ ምልከታና መርኋ (The five Principles of peaceful coexistence) መሠረት በበርካታ የአፍሪካ አገራት ጭፍጨፋዎች ላይ ዲፕሎማሲዋ ከአሸናፊው ጋር መጓዝን እንጂ ዘላቂ ሠላምን ስለማይመርጥ "Wait and see!" ነው።

በእርግጥ ቻይና ምጣኔ ሀብታዊ እገዛዋ እንጂ ፓለቲካዋና ወታደራዊ ጡንቻዋ ከአፍሪካ ጋር አልተዋወቀም። በቀጠናችን የያዘችው የጦር ሰፈር ጉዳይም ያን ያህል አይደለም። ይህ "በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም መርኋ" እናንተም እንዳትገቡብኝ ማለትን የቀፀለ ሲሆን አሜሪካና ምእራባውያኑን ተወዳጅቶ ለመዝለቅ ግን ቢያንስ በመርህ ደረጃ የሰብአዊ መብቶች መከበርን መቀበል ያስፈልጋል። ከዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር አለመጣላትና መንግሥታዊ የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተለም ፖለቲካዊ መስፈርት ይሆናሉ።

በቻና፣ በሩሲያና በአሜሪካ በኩል ከአገራችን ዘላቂ ጥቅምና ሠላም አኳያ የምስራቁን አሰላለፍ መከተል ለሰብዓዊ መብቶች ደንታ ያለመስጠትን ያስከትላል፡፡ የቲቤታውያኑን መንፈሳዊ መሪ ዳላይለማ አለም በመልካም ያውቃቸዋል። እኚህ ሰው ወደደቡብ አፍሪካ ተጉዘው ሌላኛውን ዕውቅ መንፈሳዊ መሪ ዴዝሞን ቱቱ እንዳያገኙ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ በቻይና ቀጥተኛ ተፅዕኖ ቪዛ ሲከለክላቸው ኖሯል። በቦትስዋናም ይኸው ተደግሟል። ቻይና “ከጣልቃ ገብነት ነፃ” ለመምሰል ብትሞክርም በማስፈራሪያ፤ አማፅያንን በመርዳትና በመፈንቅለ መንግሥቶችም ስሟ ተደጋግሞ መነሳቱ አልቀረም።

ወዲያውም "አንዲት ቻይና!" በምትለው መርኋ አገራት በተለይም የአፍሪካ አገራት ለታይዋን ዕውቅና እንዳይሰጡና ዲፕሎማሲያዊም ሆነ የንግድ ሽርክና እንዳይመሰርቱ የምትገፋበት መንገድ አሁን የምንፎክርለትን አይነት "ሉዓላዊነት" የጣሰ ነው። ማስፈራሪያውም እንደምዕራቦቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማቋረጥና ዕርዳታን በመከልከል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በአፍሪካ በሰፊው የገባችበትን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማስታጎልንም ይጨምራል። በተመድ የፀጥታው ም/ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ጥቅም ላይ የምታውልበት አንዱ መሥፈርት ጉዳያቸው ለምክር ቤቱ የቀረቡ አገራት ቻይና ግዛቴ ናት ከምትላት ከታይዋን አኳያ የሚይዙት አቋም መሆኑ የጣልቃ አለመግባት መርኋን ያወድቀዋል።

"እስኪ ምርጫው ይለፍ!" አልፎስ?!

የኢትዮጵያ መንግሥት ህገ-መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የሥልጣን ዘመኑን ካራዘመ በኋላ ምርጫ ለማድረግ ሲጓጓ ኖሯልና ብዙዎች በስጋት ውስጥ ሆነው “እስኪ ምርጫው ይለፍ!” ያሉለትን “ምርጫ” አድርጎ ቅቡልነትን (Legitmacy) ከህዝብ ለመቀበልና ለማግኘት ወጥኗል፡፡ ከምርጫው በፊት ሁሉንም ያካተተና በመንግሥት ሥልጣን ላ ያሉ ሰዎችን ሚዛን ያላስበለጠ “ብሔራዊ መግባባት” ላይ እንዲደረስ ስንገፋ መቆታችን አይዘነጋም፡፡ የአሜሪካ መንግስት አቋምም ይኸው ነበር፡፡ ሆኖም መንግሥት አሜሪካንን ማሳመን ችሎ መድረኩ “ከምርጫው በኋላ” እንዲደረግ አሜሪካ ፍላጎቷን ገልፃለች፡፡

በይደር ቆይተው የነበሩ ጉዳዮች በርክተው የነበር ቢሆንም ምርጫው በአይነቱ የመጀመሪያው ቢባልና በይዘት ከቀደመው የቀጠለ ነውና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን መሠረት አያኖርም። ዘላቂና መሠረታዊ ሠላምንም ያሰፍናል ብዬ አላምንም። የቅድመ ምርጫው ሂደት ብዙዎችን የገፋ እንደመሆኑ ምርጫ የተደረገም አይመስልም። ይልቁንም የኦሮሚያው "ምርጫ" እንዳልተደረገ የሚቆጠር ነውና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከውጤት ገለፃ ጅማሮው ማግስት ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው ለእውነተኛ ምርጫ መዘጋጀቱ ተገቢ ይመስለኛል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ የሚመራት "ፍትሕ" መፅሔት በአንድ ድሮም ዘንድሮም የሥልጣኑ ወንበር ላይ በተደላደለ ቱባ ካድሬ በኩል ከህገ-መንግሥቱ የንግግርና ፅህፈት ነፃነት በተቃራኒ የ"ቅድመ ምርመራ" ዕይታ መሰራቱም ስጋታችንን አንሮታል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያችን "የዘር ማጥፋት ወንጀል አልተፈፀመም!" ማለት አንድም የዚህን ወንጀል ምንነትና የተመድ ህግን መሥፈርቶች ያለማወቅ ሁለትም ከራስ ህሊና ጋር ሲጣሉ ለመኖር መወሰን ይመስለኛል። ነገሮችን ከልካቸው በላይ ማክበድም ሆነ ያለልካቸው የማቅለሉ ፅንፋዊ አቋማችን አንደኛችን በሌላችን ላይ ብሄርን አልያም ሀይማኖትንና ፖለቲካዊ አመለካከትን መሠረት አድርገን በፈፀምናቸው ማንነት ተኮር ጥቃቶች ያለመፀፀታችን ማሳያ ናቸው። ከአዲሳባ ምርጫ ጣቢያዎች አቶ እስክንድር ነጋ የተወዳደሩበትን የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ምርጫ ለየት የሚያደርገው በታሪካዊው ምርጫ-97 ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሣን ያስታወሰ መሆኑ ነው።

ይኸውም እንደብልፅግናው "Pragmatism" ሁሉ አቋማቸው እየዋዠቀ በተለያዩ ማሊያዎች ሲጫወቱ ሰንብተው የብልፅግና ዕጩ ሆነው የቀረቡትን ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ያሸነፉት የቀድሞው ጋዜጠኛ፤ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋችና የአሁን ፖለቲከኛ አቶ እስክንድር ነጋ መሆናቸው ነው። በዚህ ጆን ማርሽ (ዶ/ር) የተባሉ አሜሪካዊ የምርጫ ተመልካች ህይወት ባረፉበት ራዲሰን ብሉ ሆቴል አልፎ ስለመገኘታቸው በተሰማበት ምርጫ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መሪ አቶ እስክንድር ነጋ ታስረው ያሸነፉት መሆኑ በታሪክ ቀዳሚና አነጋጋሪ ያደርገዋል።

ተፎካካሪ ተሰኝተው የተሸነገሉትና ዘበናዩ ታዬ ደንደዓ "መብላቷን ሳታውቅ እጇን ታጠበች!" ሲል የተረተባቸው ተቃዋሚዎቻችን በዝረራ መሸኘት የሚነግረን ብዙ ነገር አለ። በተለይ የአዲስ አበባንና የአማራ ክልልን መሠረታዊ እውነታ ለመረዳት ትርፉ ብዙ ነው። ከመተባበር ይልቅ ተሰባብሮ መቅረቡና ለየብቻና በየተራ "እዬዬ" ማለቱ "አንዱ በአንዱ ሲስቅ ጀንበር ጥልቅ!" ይሉትን ውርደት አዋልዷል። "ዋናው ምርጫው መደረጉ ነው!" መፅናኛ ሊሆን አይችልም። አሸናፊና ተሸናፊውን የበየነና ለአሸናፊው ያደላ ሜዳ ዛሬም በነበረበት አለ። የምርጫ ህጉ "የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት" አሸናፊው ሁሉንም ይወስዳል (The winner takes all) ሆኖ በቀጠለበት ሁኔታ እንኳንስና ተከፋፍሎ ቀርቦ እንዲሁም መንግሥት እንደማያስኮን ለመገንዘብ ፓለቲከኞቻችን ገና መሆናቸው ይገርማል።

ገዢዎቻችንም የምርጫውን በሠላም መጠናቀቅ እንደቀብድ እየከፈሉንና "ዴሞክራሲ ሂደት ነው!" እያሉ ሂደቱን ሳይጀምሩት ለዓመታት እንዲሳለቁብን የመዳረጋችን ምክንያቶች እነዚሁ ተቃዋሚዎች መሆናቸው ደግሞ ግርምቱን ያበረታዋል። የቴአትር መድረክ በተባለችው ዓለም ሁላችንም የየራሳችንን ስንተውን ውጤቱ ቀድሞ ከሚታወቅላቸው የአፍሪካ ምርጫዎች አንዱ ነውና የኢትዮጵያችን ምርጫ አንድ ቁም-ነገር አቶ እስክንድርን ከጭቦ ክስ ነፃ ማውጣቱ ይመስለኛል። ወደነጥቤ ስመለስ “With power comes responsibility” እስከሆነ ድረስ ሥልጣኑን ወድደን ተጠያቂነቱን ልንጠላው አንችልም። አድናቆትና ሙገሳ ብቻ ተብሎ ለምክንያታዊና ተገቢ ትችት ጀርባ አይሰጥም። ምርጫውም ብቻውን ቅቡልነትን አለማረጋገጥ ብቻ ሳሆን ዘላቂ ሠላምን አያዋልድልንም፡፡

ባለንበት ያልረጋ የቀንድ ቀጠና (Volatile Region) ላይ ምሉዕ በኩልሄ ብቻ በሉኝ እያሉ መቀጠል ግጭትን አያስቀርም፡፡ በእርግጥም ቆሞቀሮች እንሁን ካላልን በቀር የሉዓላዊነት ፅንሰ ሀሳብ ቀድሞ ከነበረው እየተቀየረ ስለመምጣቱ ከተባበሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር አንቀፅ 2(7) ድንጋጌ የተሻለ አስረጅ መጥቀስ አያስፈልግም። ቲም ሙራዝ "The African Union's Transition from Non-intervention to Non-indifference: An adhoc Approach to the Rrsponsibility to Protect" መደምደሚያ ላይ እንደተጠቀሰው "The African Union has the right and the Responsibility to Protect." ሆኖም ህብረቱ ከድንዛዜው ነቅቶ ጥየቃ ቢጀምር የገዢዎቻችን "የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ!" ማምለጫ ሸብረክ ማለቱ አይቀሬ ይሆናል። የዳርፉርና የሩዋንዳው ጭፍጨፋ አንቅቶን ይመስላል የተወሰነም ቢሆን እየነቁ ዳግም መተኛት ይስተዋላል።

ምራቂ ወሬ!

በኢትዮጵያችን መንግሥታት በተቀያየሩ ጊዜ ሁሉ የቀደመውን መንግሥት ስራዎች ማበሻቀጥ፤ የመንግሥቱ መሪ የሆኑ ግለሰቦችን ስብዕና እያኮሰሱ የራስን ለማጉላት የመድከም የበታችነት ስሜታዊ ስቅየት የኖርንበት ነው። የቀደሙትን መለያና አሻራዎች ሁሉ እያወደምን ከዜሮ መጀመሩንም ያደግንበት ክፉ ባህል ነው። ብዙዎች ይህ አዙሪት የተሰበረ መስሎን ነበር። ሆኖም የአቶ መለስ ዜናዊ አስረስ ጥላ ይጋርደኛል ብለው የሰጉት ኮሎኔል ዓቢይ አህመድ አሊም እዚሁ ያረጀና ያፈጀ መስመር ላይ ናቸው። ፅሁፍና ንግግሮቻቸውን እንኳ ትተን ከሰሞኑ በሚኒስትሮች ምክሮ ቤታቸው ያስወሰኑትን ውሳኔ ብንመለከት ይህንን እንረዳለን።

ገዢዎቻችን ከየትም የመጡ ሳይሆኑ የእኛው ነፀብራቆች ናቸው። የምናገኘውም የሚገባንን እና እኛኑ የሚመስለውን ነው። ዓቢይ አህመድ በቀደሙት ቃሎቻቸው አብየውናልና የራሳቸውን አሻራ ከማኖር ጎን-ለጎን "መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ" ተብሎ የሚታወቀውን ተቋም ስያሜ ቀይረዋል። አቶ መለስ ስማቸውን በተቋማት በኩል በማስተዋወቅ ረገድ ያን ያክል የሚደክሙ ሰው አልነበሩምና በስማቸው ከተመሠረተው ፋውንዴሽን ሲለጥቅ ይህ ተቋም ብቸኛ መታወሻቸው ነበር። እዚህ ስማቸውን የማልጠቅሳቸው የበርካታ ባዕዳን አገራት ባለውለታዎችን በተቋማት ስያሜ ሳይቀር የምታስታውስ አገር መለስን ለመግደፍ ተቋሙ "የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ" ስለመሰኘቱ ገዢያችን በማህበራዊ የትስስር ገፆቻቸው አሳውቀውናል።

በዚህ አያያዝ አቶ መለስ ዜናዊ ከአስር ዓመታት በፊት በወሳኝ ሰዓት መሠረቱን ያኖሩለትንና ከፊሉን ያስኬዱትን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (Great Ethiopian Renaissance Dam) የሰየሙት ፕሮጀክት የሚፈጥረው ሀይቅ (ግብፆቹ "ናስር ሀይቅ" እንደሚሉት!) በአቶ መለስ ሳይሆን በኮሎኔል ዓቢይ የመሰየም የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የማይገባበት ምክንያት አይኖርም። በእርግጥ ትናንትም ዛሬም በካድሬነት ፀንተው ለሁለቱም ገዢዎች "ንሴብሆ!" እያሉ ሲያሸበሽቡ የምናውቃቸው ሰዎች ከኮሎኔሉ "ዘመኑን የሚዋጅ ማዕከል ለማድረግ መተለም ስላስፈለገ...." አገላለፅ በተቃራኒ አመራሩ በዚህ ተቋም ገብቶ ለመሰልጠን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው እያሉን ነው።

የብአዴኑ አቶ አገኘሁ ተሻገር እዚህ ተቋም በዳይሬክተርነት ሲሾሙም ተጠይፈውት እንደነበርና "ስያሜው ካልተቀየረ አልፈቅደውም!" ስለማለታቸው እዚሁ ገፃችን ላይ በዜና መልክ መዘገቡ አይዘነጋም። ተቋሙንም አመራሮቹንም ሳውቃቸው ብዙዎቹ በሰልጣኝነት ከፊሎቹ ደግሞ በደህና አበልና በአሰልጣኝነት ይጋፋ የነበሩ ናቸው ደርሼ ፃድቅ ልሁን የሚሉን። በዳግማዊ ምኒሊክ ስያሜ ከቤተ-መንግሥቱ ጀምሮ በዓፄ ምኒሊክና በእቴጌዎቹ ዘውዲቱ ወጣይቱ የሚጠሩ ተቋማትንስ ስም ልንቀይርላቸው ነው? የቀዳማዊ ኃይለሥላሴና የኮሎኔል መንግሥቱን እንኳ አመናምነነዋል። ታሪክን እንቀበለዋለን ወይስ እንጣላዋለን? በታሪክ አጋጣሚ ክርስትና የመንግሥትም የቤተ-መንግሥትም ሀይማኖት ነበርና በይሁዳ አንበሳነት ተሰይመው ከምናውቃቸው የሀውልት ቅርሶች ባሻገር በቤተ-መንግሥቱ አጥር ዙሪያ የሚታዩትን መስቀሎች እንዲሁም መስቀል ያለባቸውን የዘውድ ምልክቶች እየነቀልን ልንጥላቸው ነው ወይስ ምን ልናደርጋቸው አስበን ይሆን?! ከእንዲህ አይነት ዙረት አለመላቀቃችን ያሳዝናል፡፡

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :