ታለ “በአገር ሉዓላዊነት” ስም! (ማጠናቀቂያ - ሶስት በሉ!)

Tigray warሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

August 5, 2021

“State sovereignty implies responsibility, and the primary responsibility for the protection of its people lies with the state itself. Where a population is suffering serious harm, as a result of internal war, insurgency, repression, or state failure, and the state in question is unwilling or unable to halt or avert it, the principle of non-intervention yields to the international responsibility to protect.”
(Report of the International Commission on Intervention and State Sovereignty, The Responsibility to Protect: Core Principle one)

ሉዓላዊነት የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች እየጣሱ መደበቂያ ሊሆን እንደማይችል ለማሳየት የጀመርነው ህግን ይልቁንም ዓለማቀፉን ህግ መነሾው ያደረገው መጣጥፍ እነሆ ሊያበቃ ሆነ፡፡ በቀደሙት ክፍሎች ከሉዓላዊነት የምንነት ፅንሰ ሃሳብ አንስቶ እስከ የአፍሪካችን ባህርያተ መንግሥታት ድረስ ዘልቋል፡፡ የአህጉራችን መንግሥታት ከጥንት እስከዛሬ የሰው ልጆችን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አክብሮ ከማስከበር ይልቅ መንበራቸውን ማደላደል ቀዳሚ አጀንዳቸው ይሆናልና ይህንን የሚቀናቀን ወገንን ሲያስሩና ሲገድሉ ለሚደርስባቸው ጫና ጋሻ የሚያደርጉትም ሉዓላዊነትን ነው፡፡

በሂደት አሁን አገራችን የገባችበትና አንድ ጊዜ “የህግ ማስከበርና የህልውና” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የሠላም ማስከበር ዘመቻ” እየተባለ የሚስተባበለውን ይፋ የወጣ የወገን ጦርነት (Civil War) ስንቃወም ቆይተናል፡፡ በጦርነቱ ውስጥም ቢሆን የማይጣሱ መሠረታዊ የሠብዓዊ መብቶችን በመተላለፍ ከዘር ልየታ (Ethnic profiling) ጀምሮ ለተከሰቱ ሰቆቃዎች በኃላፊነት ሊጠየቁ የሚገባቸውን ስንነቅስ መቆየታችን አይዘነጋም፡፡ እነሆ በዚህ የመጨረሻው ክፍል መርሆዎቹን ግድ እየሆነብን ከነህግ ቋንቋው የጠቃቀስንለትን የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ሚናና የዓለማቀፉን ህግ አሁን ኢትዮጵያችን ከዘቀጠችበት ምስቅልቅል አኳያ እንዳስሳለን - መልካም ንባብ!

የአምባገነኖች ዕድር - እና ኃላፊነቱ?!

ከሥልጣንና ከኃይል ጋር ተጠያቂነት ያብራልና (With power comes responsibility) ሥልጣኑ ተወዶ ተጠያቂነቱ ሊሸሽ አይችልም። አለመታደል ሆኖ አፍሪካ ውስጥ ሥልጣንህን ስታጣ ሁሉን ነገር እንድታጣ ሥርዓታቱ ግድ ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሥልጣን ዘመን ለተፈፀሙ ወንጀሎች ጥየቃው በህግና ሥርዓታዊ መንገድ ሳይሆን እንደተረኛው የመሣሪያ ምርጫ የጭካኔ ልክ የሚወሰን ነው፡፡ “ጣልቃ አለመግባት” እና የሌላውን ሉዓላዊነት ማክበር አንዱ የአገረ መንግሥታት ኃላፊነት ሲሆን የአገራትን "Territorial integration" ማክበርም የዓለማቀፉ ህግና ፖለቲካዊ ተዋስዖ ሌላኛው ጠቅላላ መርሆ (General principle) ነው።

የኒውዮርክ ታይምስ አንጋፋ ጋዜጠኛ ስለመሆኑ የሚነገርለትና “The Africans” በተሰኘው መፅሃፉ የሚታወቀው ዴቪድ ላምብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራትን አይቷል፡፡ በዚሁ መፅሃፉም በአፍሪካ ዓመታዊ የገዢዎች ጉባዔ ላይ በየዓመቱ ሲገናኙ ሞቅ ያለ ሠላምታና ትቅቅፍ የሚታይበት ምክንያት ከመገልብጠ መንግሥት፤ ከግድያና አመፅ ተርፈው በሥልጣን መቆየታቸውን ሲያከብሩ ነው የማለቱ እውነታ እንደቀጠለ ነው፡፡ የአንድ ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሰብሳቢ የነበሩትን የሳሊም አህመድ ሳሊም ግጭቶችን በመተንበይ የማንቃት፤ ሲፈጠሩም መከላከልና በሠላማዊ መንገዶች የመፍታት ውጥን ይታወሳል፡፡

ይህ ውጥን በ "መጠነኛ ጣልቃ ገብነት" መታጀቡ የማይቀበሉት ብቻ ሳይሆን ከላ በጠቀስነው የግዛታዊ ደህንነት ሽፋን አስቆጥቶ እንቅልፍ የሚነሳቸው አምባገነኖች የአፍሪካችን መለያዎች ነበሩ። ይህ ውጥን በተግባር መሬት ረግጦ ድርጅቱን ወደ ህብረትነት ሲቀይረውና የህብረቱ ሚናም "from Non-intervention to Non-indifference" ሊቀየር ጀምሮ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ህገ-መንግሥታዊና ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች የመንግሥት ሥልጣንን መያዝና ማራዘምን የህብረቱ ህግ በብርቱ ሲኮንን ሉዓላዊነትም ጋሻ ሆኖ እንደማይቀጥል ገልጿል፡፡

ሆኖም የአገዛዝ መሠረቱ ጉልበት ሆኖ በቀጠለባት አህጉራችን “መገልብጠ መንግሥት” ዛሬም ጀብዱ ነው። የጠቀስነው የህብረቱ ህገ-ደንብ (Constitutive Act of the African Union) እና ቻርተሩ በውስጥ ግጭቶች ሳቢያ ስለሚፈናቀሉ ሰዎች መብቶች (Rights of Internally Displaced Persons) ያካተቷቸው ድንጋጌዎች ቢኖሩም ከአህጉሪቱ በቀዳሚነት ስለተመዘገበው መፈናቀላችን እያዩ አላዩም። የህብረቱ አባል አገራት ለህብረቱ በእንደዚህ አይነት ምስቅልቅል ወቅት ጣልቃ እንዲገባ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል ቢባልም የአባል አገራቱ ገዢዎች ተሰብስበው ይህንኑ ይሁንታቸውን በውሳኔ እንዲደግፉት ይጠበቃልና በምናውቀው ምክንያት አሳይቶ የመንሳት ጨዋታ ይሆናል - የእከክልኝ አክልሀለሁ!

ዛሬ "በሰብዓዊነት ሽፋን" ሉዓላዊነታችን እየተጣሰ ነው የሚሉት በአንድ አፍሪካዊ ምሁር አጠራር የአምባገነኖች የአገዛዝ አጋርነት ዕድር (Allies of Dictatorship) የሆነው የአፍሪካ ህብረት "ዝም አይነቅዝም" ላይ ነው። የህብረቱ ፀጥታ ምክር ቤትም በአህጉራችን ሠላም ላይ እንዲሰራ ቢጠበቅበትም በኢትዮጵያችን ምስቅልቅል እንኳን ዝምታን መርጦ የደረሰበት ዓለማቀፍ ውግዘት ነው፡፡ ህብረቱ በድርጅትነት ሳለ ሊያስቀራቸው ሲችል የሰነፈባቸውን ስህተቶች መማሪያው አድርጎ በህገ-ደንቡ አራተኛው አንቀፅ መሠረት ሉዓላዊነትን እንደመብት ብቻ ሳይሆን እንደ ህጋዊ ኃላፊነት ቢቀበልም ለተግባራዊነቱ ሰንፏል፡፡ በጦር ወንጀሎች (War Crimes) በዘር ማጥፋት (Genocide) እንዲሁም በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈፀሙ (Crimes against Humanity) ተብለው ሊጠቃለሉ የሚችሉ ወንጀሎችን ለማስቆምና ጣልቃ ገብቶም የሰቆቃዎቹ ኃላፊዎችን ለአህጉሩ ፍርድ ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ነበረው - ቢሰራበት!

ዓለማቀፉ ማህበረሰብ - እና ኃላፊነቱ!

በእርግጥ ይህንን አይነቱን ጣልቃ ገብነት በሰብዓዊነትም ቢሆን የማንጋብዝበት ምክንያት ብዙ ነው። ከግድባችንና ካለንበት ፖለቲካዊ ቀጠና አኳያ ጣልቃ ገብነቱ ከሰብዓዊነት ወጥቶ ወደ ውስጣዊ ፖለቲካችን እንዳይዞር ያሰጋልና። የተቋማቱን ጠንከር ያለ ጣልቃ ገብነት የምንደግፈው ጦርነቱ ያስከተለውንና የሚያስከትለውን ሰብዓዊ ሰቆቃ እንዲያስቀርልን ቢሆንም የታጠቁ ኃይሎች በበረከቱበት ሁኔታ እንደየፓለቲካዊና ጥቅማዊ ውድጅናዎች አሰላለፍ እየተቀየረ እንዲያጥር የምንመኘውን ሰቆቃ ሊያረዝምብን ይችላል ብሎ መስጋቱም ተገቢ ነው፡፡ ምንም እንኳን ችግሮቻችን ሁሉ ከፖለቲካዊ ቅራኔዎቻችን የሚመነጩ በመሆናቸው መፍትሄያቸውም "ፓለቲካዊ" እንዲሆን ስንጮህና ስንፅፍ ብንከርምም የመግባባት ዴሞክራሲ መክኖብናል።

እንደ አገር አብሮ የመቀጠል ተስፋችን አብሮ እንዳይመክን "ጩኸቴን ብትሰሙኝ...." እንዲል ጋሽ ጥላሁን ገሠሠ ጩኸታችንን ቀጥለናል፡፡ ስጋታችን ከመቅረት እኩል የሆኑ ወይም ከዚያም የከፉ ማርፈዶች በመሀል ከባድ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ነው። የተመድ ፀጥታ ም/ቤት ያረፈደባቸውና ከእልቂቱ በኋላ ግን የተፀፀተባቸው ወቅቶች አሉ። በቅርቡ የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ሩዋንዳን ሲጎበኙ ስለምዕራቡ ዓለም ማርፈድ ይቅርታ መጠየቃቸውን ያጤኗል፡፡ በሸኘነው ሳምንት ሐምሌ 11/1995 መደበኛ ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈፀመበት ዕለት በየዓመቱ የሚዘከረው ስምንት ሺህ ያህል የሰርብ ሰቆቃ ተጠቂዎችን ዓለም በፀፀት ውስጥ ሆኖ እንዳስታወሳቸው አይዘነጋም፡፡

የዓለማቀፍ ህጎች አባት (the Father of international law) የሚባለው ሁጎ ግሮሺዬስ እና ሌሎች የዘርፉ ምሁራን የሰብዓዊ ጣልቃ ገብነትን ሲደግፉ ብቻ ሳይሆን ሠብዓዊ ግዴታ መሆኑንም ሲጠቅሱ ኖረዋል። ሁጎ አለፍ ብሎም "a right vested in human nature" ነው የሚለው። የተመድ ቻርተር ራስን ለመከላከል ከሚደረግ የአገራት ምላሽ በቀር ኃይልን መጠቀም (use of force) አስገዳጅ ሲሆንና በተናጠል ሳይሆን በተመድ ቁጥጥር ስርና በፀጥታው ምክር ቤት በኩል እንዲሆን ያስገድዳል። ይሄ ሂደት ግን ምንም እንኳን ለሉዓላዊነት አቀንቃኞች ቢመችም በሂደቱ ምላሽ ሳያገኙ ቀርተው ለከፋ ቀውስ ሲዳረጉ ዓለም ያስተዋላቸው ሰቆቃዎችን ለማስቀረት "Just war" የሚባለውን ነቢብ ይዞ ያስተዋወቀንን ተቋም እዚህ ልንጠቅሰው ግድ ይሆናል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ለተመድ ጉባዔ "Millennium Report" ሲያቀርቡ አባል አገራት በአገር ሉዓላዊነት እና በሰብዓዊ ጣልቃ ገብነት መካከል አማካይ መቆሚያ (Common Ground) እንዲፈለግ አሳስበው "...if Humanitarian Intervention is, indeed, as unacceptable assault on sovereignty, how should we respond to a Rwanda, to a Serbrenica - to gross and systematic violations of Human Rights that affect every preecpt of our common Humanity?" ሲሉ የጠየቁት ኮፊ አናን ጣልቃ ገብነቱ የዘፈቀደ (Arbitrary) እንዳይሆን ጠይቀዋል፡፡ ሉዓላዊነትን መደበቂያ የሚያደርጉ አምባገነኖችም የሚያደርሷቸው ሰቆቃዎች ያለጠያቂ እንዳይቀሩ አሳስበው ነበር፡፡

በዚህም መሠረት በካናዳ መንግሥት አቀናጅነት "Responsibility to Pprotect" በተባለ ሀሳብ ስር የተመድ ፀጥታው ም/ቤት ውሳኔ ላይ እንዲደርስና የመብት ጥሰቶቹን እንዲገታ ያስችለዋል ያለውን መንገድ ዓለማቀፉ የሰብዓዊ ጣልቃ-ገብነትና የአገራት ሉዓላዊነት ኮሚሽን (International Commission on Intervention and State Sovereignty) የተባለው ተቋም “The Responsibility to Protect” በሰኘው ሪፖርቱ በኩል ለዓለም አስተዋወቀ። በዚህም መሠረት የተመድ ፀጥታ ም/ቤትን ፈቃድ የሚጠቅስ ከሚመስለው የተገቢ ሥልጣን (Right Aauthority) ጀምሮ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብነት በቂ ምክንያት (Just Cause) ከቅን ልቦና (Right intention) ጋር መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት ጠቅሶ ምክረ ሃሳቡን አቀረበ፡፡

ይህንንም ከዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ሲከተል የሚደረግ የመጨረሻ አማራጭ (Last resort) እንዲሆን በመጠቆም ከተገባም በኋላ ቢሆን በተመጣጣኝ ኃይል ተገማች የሠላም ሁኔታን በመፍጠር መውጫ ስትራቴጂውን ይተልማል፡፡ በእርግጥ ሉዓላዊነትን "Hhypocrisy of a Government" ሲሉ የሚተቹት ምሁራን ጣልቃ ገብነቱን ቀለል የሚያደርጉትን ያህል የሉዓላዊነት ባለጋሻዎች ደግሞ ይህ አሰራር በሂደት የአገራትን ሉዓላዊነት የሚቀናቀን አጉል ልምድ (Dangerous Precedent) እንዳይፈጥር ይሰጋሉ። ጣልቃ ገብነቶቹ በጊዜ ገደብ የተቀነበቡ አለመሆናቸውና የግልፅ ዓላማ (Clearly puted Objectives) አለመኖር ከራሳቸው ውስጣዊ ችግርጋ እየተዳመረ ፍርሰትን ያስከተለባቸው አገራት ስለመኖራቸው  አይስተባበልም።

ለጣልቃ ገብነቱ መነሾ የሚሆነው የከፋ ሰብዓዊ ሰቆቃ (Large scale Humanitarian Crisis) በማን መለኪያና በምን ያህል መጠን መሆን እንደሚኖርበት ግልፅ ያለ ነገር አለመኖሩም ተደራቢ ችግር ነው፡፡ የፀጥታው ም/ቤት ፈቅዶና ከረፈደ ጣልቃ ገብቶም የከሰረበት ወቅት አለ። ለመፍቀድ ሲያንገራግር በመዘግየቱ የከሰረበት ወቅትም አለ። የኮሚሽኑ መርህ ለተመድ ከተዋወቀና አስገዳጅ ህግ ባይሆንም በሪዞሉሽን ታጅቦ ለጠረፔዛ ከበቃ እነሆ ዓመታትን አስቆጥሯል። መርሁንም ከመብት ወደ ኃላፊነት በማሻገር ግቡን ጣልቃ የሚገባባቸውን አገራት መንግሥታት መቀናቀን ሳይሆን የሲቪያሉን ደህንነት መጠበቅ እንዲሆን ተስማምቷል።

እርግጥ ነው የአገራቱ መንግሥታት "Manifestly failing to protect their population" ይሉትን መሥፈርት ቢያሟሉም ይህ የጉባዔው አቅርቦት በፀጥታ ም/ቤቱ ካልፀደቀ ከሀሳብነት አይዘልም። በተደጋጋሚና በተለያዩ አገራት እንዳስተዋልነውም ፀጥታ ም/ቤቱ ያላፀደቃቸው ጣልቃ መግባቶች ከሰብዓዊነት አኳያ ተገቢነት ቢኖራቸውም የህጋዊነት ጥያቄ ተነስቶባቸዋል። እዚህ ግድም ከአንባብያን ከህገ-ፍልስፍናው አኳያ ብቻ ሳይሆን ከሠብዓዊነትና ከህግ የቱ መቅደም ይኖርበታል የሚል ጥያቄ ቢነሳ ክርክሩ መቋጫ አጥቶ የተንጠለጠለ ነውና ሰብዓዊነትን የማይጋፉ ህግጋትና ህግጋትን የማይጣላ ሰብዓዊነት ቢኖረን መመኘቱ አይከፋም፡፡

የሆነው ሆኖ መንግሥታችን ዛሬም ድረስ በትግራይ ያለው "ህግ የማስከበር ዘመቻ" እንጂ የወገን ጦርነት (Civil war) እንዳይደለ በመንገር ችክ ብሏል፡፡ የኬሚካል ጦር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ሪፖርቶች ከመኖራቸውና ሻዕቢያም ቀዳሚ ተጠርጣሪ ከመሆኑ ጋር ሰብዓዊ ዕርዳታዎች እንዳይደርሱ እንቅፋት መፍጠሩ ቀጥሏል፡፡ ይህ ነው ወሰንህ ያልተባለና በሴቶች ኢትዮጵያውያት እንኳን በአግባቡ ያልተወገዘ የእህቶቻችን ጩኸትም አልተረሳም፡፡ ሰው ሰራሽ ረሀብ (Forced starvation from sieges) የገዘፉ ማፈናቀሎችና ግድያዎች (Killing and Displacement) ዛሬም በቦታቸው ናቸው፡፡ በመዲናችን የብሔር ልየታው (Ethnic profiling) በመንግሥታዊ መዋቅር እየታገዘ ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ብቻ ለእስራትና ለንግዶቻቸው መዘጋት ተጋልጠዋል፡፡

በመርህ ደረጃም ቢሆን ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ከደፈና ጣልቃ ገብነት ይልቅ መንግሥታቱ ዜጎቻቸውን ከሰቆቃዎች እንዲጠብቁ (Prevention than Reaction) ጫና መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ማለት ግን ወታደራዊው ጣልቃ ገብነት በመጨረሻ አማራጭነት ተቀመጠ ማለት እንጂ ከመዘርዝሩ ወጥቷል ማለት አይሆንም። የአገራት ለመብቶች ያላቸውን ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት ማሳያ ሆኖ በቅድሚያ በራሳቸው በኩል ግዴታ ሆኖ በኃላፊነት እንዲፈቱት፤ ሲቀጥል ድጋፍ እንዲደረግላቸው፤ ሲሰልስና የግድ ሲሆን ደግሞ ጣልቃ ተገብቶ ችግሩ እንዲፈታ ይሆናል፡፡

ይሄ ብዙዎች በዩኒቨርሲቲው መነሾ "The Brookings Doctrine" እያሉ የሚጠሩት ኃላፊነት ተለምዷዊውንና በዓለማቀፍ ህግ የዌስትፋሊያ ስምምነት መሠረት "ሉዓላዊ አገራት አንዳቸው በሌላኛው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም" ይሉትን መርህ በመገዳደር ያለንበትን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በደንብ በሚያውቀው ፍራንሲስ ዴንግ እና ባልደረቦቹ የቀረበ ሲሆን "Sovereignty as Responsibility; Conflict Management in Africa" በተሰኘውና በኋላ ላይም ወደ መፅሐፍነት ባደገው ስራ የተዋወቀ ነው። አገራት በዓለማቀፍ ህግጋትና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ስለሰብዓዊ መብቶች ባስቀመጧቸው መለኪያዎች መሠረት ለውስጣዊ ችግሮቻቸው መፍትሄ የማያበጁ ከሆነ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ቀጣዩ ኃላፊ (Residual Responsibility) ሆኖ መፍትሄ ያበጅለት ዘንድ ግዴታው ይሆናልና፡፡

ያለንበትን ቀጠና ጠንቅቆ የሚያውቀው ፍራንሲስ ዴንግ ተለምዷዊውን የዓለማቀፍ ግንኙነትና የሥነ-መንግሥት ፖለቲካዊ ምህዳር ሲሞግት ሉዓላዊነትንም ውጫዊ ጣልቃ-ገብነትን በመቃወም ብቻ የሚገለፅ እንዳይደለና ይልቁንም አገራትና መንግሥታቶቻቸው ላይ አዎንታዊ ኃላፊነትን (Positive Responsibility) የሚጥል ስለመሆኑ ያወሳል። ይኸውም የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚው ኃላፊነት የአገሩ መንግሥት ቢሆንም ያ መንግሥት ኃላፊነቱን (The primary responsibility) መወጣት ሳይችል ሲቀር (Unable to) አልያም ሳይፈልግ ሲቀር ወይም አባባሽ ሲሆን (Unwilling to) ዴንግ "Broader Community of States" የሚላቸው አገራትና ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ላይ ይህንን ግዴታ የመወጣት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል ይላል።

ታለ “በሉዓላዊነት” ስም - ሲጠናቀቅ!

የዓለም አካል ነንና ወዲያውም ሉላዊነት (Globalization) ሉዓላዊነትን (Sovereignty) በሚቀናቀንባት ዓለም እንደከዚህ ቀደሙ ዓለምን ረስተንና በዓለምም ተዘንግተን ከዓለም ተነጥለን ልንኖር አንችልም፡፡ ዓለምን ሁሉ እኛ ላይ የሚያደባና ከእኛ ጥቅም በተፃራሪ የቆመ አድርጎ ማሰቡም ስህተት ነው፡፡ መንግሥታት በዜጎቻቸው ላይ ወንጀልን ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙም ከዓለማቀፋዊ ተጠያቂነት የአገራቸው ሉዓላዊነት ሊየስጥላቸው አቅሙን አጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት የአገራችን ሹማምንትን ያገኘው የማለፊያ ክልከላና የጉዞ እገዳዎች (travel bans) ከሚጠበቀው የሀብት እግድና ትልልፍ (seizure of the assets of the governments ringleaders) እንዲሁም የተመረጡ ተላኪ ምርቶች ክልከላ (targeted sanctions of a states exportable products) እስከ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ (Arms embargo) ድረስ የዘለቀው ልምጭ በቀጣይ ህጋዊና ፖለቲካዊ ጫናዎችን አስከትሎ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጣልቃ-ገብነትን እንዳይጋብዝ የመንግሥትነት መንበሩን ዕድልና ጊዜ የጣለላቸው ሰዎች ሊያስቡበትና ለራሳቸው ሲሉ ጨው ሊሆኑ ግድ ይላቸው ይመስለኛል፡፡

አለመታደል ሆኖ “ዓለምን ያስተማረ…” የተባለለትና ስላቁ ያላበቃው ምርጫም ሆነ ጉልበት ሁሌም ትክክል ነው ጥቅም ሲታከልበት (Might is Right) ይሉት መርህ ከኮሎኔል ዓቢይ አህመድ ጀምሮ ባሉ ኢህአዴጋውያን በኩል አሁን ላለንበት ዝቅጠት ዳርገውናል፡፡ ቁልቁለታችንን ከዚህ ሊያከፋው የሚችለው ግን ማህበራዊው ኪሰራችን እንደመሆኑ የጋራ ጎጇችንን ነዋሪ አልባ ልናደርጋት ከጫፍ የመድረሳችንን ነባራዊ ወአሁናዊ እውነታ ተከታዩ የ“ኗሪ አልባ ጎጆዎች” መድብል ይጠቁመን ይመስለኛል፡፡ እንግሊዝኛ ፅንሰ-ሃሳቦችን ግድ እየሆነብኝ የጠጠቀምኩበትን መጣጥፍ እካችሁ በበዕውቀቱ ሥዩም አንዲት ዘለላ ግጥም እንሰናበታት፡-

“ማጭድ ይሆነን ዘንድ - ምንሽር ቀለጠ
ዳሩ ብረት’ንጂ - ልብ አልተለወጠ፤
ለሳር ያልነው ስለት - እልፍ አንገት ቆረጠ፡፡”

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :