ኢትዮጵያ ከዓቢይ አህመድ ዓሊ… በኋላስ?! (ቀዳሚው ክፍል)

ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
October 21, 2021

“Those who cannot remember the past are condemned to repeat it.”
(ጆርጅ ሳንታያና፤ ስፔናዊ አሰላሳይና ደራሲ)

After Abiy Ahmedይሄንን ፅሁፍ ሳሰናዳና ይህንንም ርዕስ ስሰጠው “ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” የማለቱን የጭቆና ቀንበር በወዶ ገብነት የሚጫኑ የሥልጡኑ ዘመን ቆሞ ቀሮችን ማሰቤ አልቀረም፡፡ ብዙዎቹ የዚህ እሳቤ ተጋሪዎች ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር ያላቸው ፀብ ላይ በአመክንዮ ያልታገዘና በምልከታ ችግር የሚሰቃይ ስሁት የአገር ወዳድነት (Patriotism) ይስተዋላልና፡፡ሳያጠይቁ መቀበልን አልወደውም፡፡ በስራ ቀናት ሳይቀር ህዝባዊ አደባባዮችንና አማራጭ ያልተበጀላቸውን መንገዶች እየዘጉ የሚደረጉ “የድጋፍ ሠልፎችን” የማብዛቱ ነባር ባህል ቀየር ተደርጎበአጃቢነት ሲካተት ደግሞ መገረሜ በእጅጉ ይጨምራል፡፡

የኩነቱ መደጋገም ይልቁንም በከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶችና በአስተዳደሩ የወረዳ አደረጃጀቶች በኩል አበል እየተሰፈረና ትራንስፖርት እየተመቻቸ መስከንተሩ ቀጥሏል፡፡ በህዝብ ስም ከህዝቡ የሚሰበሰበው የቀረጥ ገንዘብም የወረዳውን አደረጃጀት ተጠግተው “ሰልፍን እንጀራቸው ላደረጉ” እናትና አባቶች እንዲሁም “ወጣቶች” ፈሰስ መደረጉን እንደቀጠለ በሩቅ ሳይሆን በቅርበት አስተውያለሁ፡፡ ይህ ድግግሞሽም በቅርቡ ከውጪ ጉዞው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ዕይታውን ማስመልከት የቀጠለውን “እያዩ ፈንገስ” አንድ በኢህአዴግ ላይ ዕውን ሲሆን የታዘብነውን ፖለቲካዊ ሟርት ደጋግሞ ያስታውሰኛል፡-

“በጨረቃ ችሎት - ፀሐይን በመክሰስ
በሞቅታ አንቀፅ - ፍርድን በማድበስበስ፤
እመነኝ ወዳጄ - አትድንም ከመፍረስ!”

ኢትዮጵያውያን የመንግሥት ለውጥ ታሪካችንን ስናስተውል አንዱን ሥርዓት ጥለን ሌላኘውን ስንናፍቅ፤ ያንን የጠላነውንና የጣልነውን ከማስወገድ ባሻገር ወዳቂውን ሥርዓት የሚተካውንና እኛ “የተሻለ” እንደሆነ የምናምንለትን ሥርዓት በመገንባቱ ረገድ ታሪክ ተደጋጋሚ ክሽፈቶቻችንን ነው የሚያስነብበን፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋናቸውን ሲነጠቁ ግርግር ለወታደር አመችቶ በትረ መኮንኑን ወስዷል፡፡ መኮንኖቹ “ጊዜያዊ” ብለው ዓመታትን የዘለቁበት ሥልጣን በኢህአዴግ ነፍጥ ታግዞ ሌላ ዘራፊና አምባገነናዊ ሥርዓትን ተክሏል፡፡ ኢትዮጵያ የኤርትራ ግዛቷንና የባህር በሮቿንም እንድታጣ ሆኗል፡፡

ኢህአዴግ በጥቅምና በፍርኃት ትስስር ላይ ያስቀጠለውን ሥርዓት በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በተሰራ ጭቦ እንዲሁም በዋነኝነት በኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴና በአማራ ክልል ወጣቶች እገዛ የማረም ዕድል ተገኝቶ የነበር ቢሆንም ሥርዓቱን ከመጣል ያለፈና በድል ማግስት የተያዘ ግብ ባለመኖሩ አሮጌዎቹ ኢህአዴጋውያን ስያሜና መሪያቸውን ቀይረው ያንኑ ግብራቸውን እንዲቀጥሉበት ሆኗል፡፡አሁን በሀገረ አሜሪካ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው “27 ሲደመር 2... ኢትዮጵያ - አዲስ አምባገነናዊ ሥርዓትን በማዋለድ ሂደት” በተሰኘውና በእስር ቆይታቸው ወቅት ባዘጋጁት መፅሃፍ በኩል ይህንኑከፖለቲካዊ ታሪክና ልምዳችን ያለመማር ችግራችንን አውስተው ይህንን አስነብበውናል፡-

“አንድ ህዝብ አንድን ለውጥ ለማግኘት ፈልጎ ትግል ሲያካሂድ ከአሸናፊነት በኋላ ሊያገኘው ስለሚችለው ተጨባጭ ለውጥ አስቀድሞ ማሰብና መጨነቅ የሚያስፈልገው ወደዚህ አይነቱ የባሰ ጣጣ ውስጥ ላለመግባት ነው፡፡ አንድን ህዝብ ከሌላ ህዝብ በበለጠ ብልህ ወይም አዋቂ ሊያስብለው የሚችለውም በዚህ ረገድ የሚኖረው የማስተዋል አቅም ነው…… ችግሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ አይነቱ አስተሳሰብ አልታደልንም፡፡ ሁልጊዜም ጭንቀታችን ስለምንጥለው ወይም ስለምናስወግደው መንግሥት እንጂ በምትኩ ስለምናገኘው እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ሆኖ አያውቅም፡፡” (ገፅ-182)

አቶ ልደቱ ይህንን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ህዝብን እንደህዝብ ደካማ ጎን ያለው ስለመሆኑ ለመንገር ፖለቲካዊ ትክክለኝነት (Political correctness) ከሚያነቅፋቸው ፖለቲከኞቻችን በተቃራኒ “ኢትዮጵያን እያፈረሱ ኢትዮጵያ አትፈርስም!” ማለትን ይተቻሉ፡፡ በምትኩም ከፖለቲካ ባህታውያኑ አትፈርስም ይልቅ የገባንበትን የኢህአዴግን መፍረስ የተከተለ የአገር መፍረስ ሂደት እንዴት አድርገን በጋራና በርብርብ ማስቆም እንደሚኖርብን መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን አቁማዳ የመቀየርሂደት አብዮታዊው ገጣሚ ኃይሉ ገብረዩሐንስ (ገሞራው) “ጥሬው እስኪበስል የበሰለው የማረሩን” አይቀሬነት ከመግለፁ እኩል እንዲህ ይቀኘዋል፡-

“ስልቻ ቀልቀሎ - ቀልቀሎ ስልቻ
ማን ከማን ተሸሎ - ሁሉም አራሙቻ፤
ቀልቀሎ ስልቻ - ስልቻ ቀልቀሎ
ማንን ይመርጡታል - ማን ከማን ተሽሎ”

የኢህአዴግ ፍርሰት አገራችንን ይዞ ለመፍረስ ጫፍ በደረሰበት በዚህ ወቅት ብዙዎች የሥርዓቱን መውደቅ ብንናፍቅና ምዕራባውያኑም አቋማቸውን ከዚሁ ጋር የከረከሙ ቢመስልም “ኢትዮጵያ ከዓቢይ አህመድ…. በኋላስ?!” ስለሚለው ጥያቄ ዛሬም እምብዛም የተጨነቅንበት አይመስለኝም፡፡ ይህ ማለት ኮሎኔሉ እንዲህ በቀላሉና በቅርቡ ሥልጣናቸውን ይለቅቃሉ ወይም መልቀቅ አለባቸው ማለትም አይደለም፡፡

በዚህ አገላለፅ ማንሳት የተፈለገው ነጥብ ዓብይ አህመድ (ኮ/ል) ሥልጣናቸውን ይልቀቁ የሚሉ ፖለቲከኞቻችን የሚያቀርቧቸው አማራጮች (Political offers) ምንድን ናቸው? ምንስ ያህል የታሰበባቸውና አገራችንን ወደሠላሙ መንገድ የሚመልሱ ናቸው? ሁለቱን የአገዛዝ ሥርዓቶች ከማስታረቅና አንዱ ሌላውን ሰዶ ከማሳደድ የሚያተርፉን ናቸው ወይ? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎችን እንዲያስተናግድ የተተለመ ነው፡፡ እንጂማ ኮሎኔሉ በ “መደመር” በኩል የሚሽኮረመሙበትን የሥልጣን ጥም በ “እርካብና መንበር” በኩል እንቅጩን ነግረውናል፡፡

በተለይ በአጠራር ተለምዶ “አሀዳውያን” እና “ፌዴራሊስቶች” በመባል የተማከለውንና ያልተማከለውን የአገዛዝ ዘይቤ በሚተልሙት መካከል ያለው ትግግሎሽ መታረቂያ ማዕከሉን ባላበጀበት በዚህ ሰዓት የሚደረገው መንግሥታዊ ለውጥ ላይ ስምምነት አለመፈጠሩ ደግሞ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ወንድም ጀዋር ሲራጅ ሙሐመድ በተለያዩ ወቅቶች ተናግሯቸው ከተደመጡ ቁም-ነገሮች አንዱ “ህዝብ ነፃነቱን ይፈልጋል፡፡ ከነፃነቱ በላይ ግን በደህንነት መኖርን ይሻል። ይህንን በህይወትና አካላዊ ደህንነት የመኖር ፍላጎት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ለሥልጣን ማደላደያ እንዳይጠቀሙበት እሰጋለሁ…” የሚለው ይገኝበታል፡፡

እዚህ ግድም ጃዋርን ስለምን “ወንድም” ትለዋለህ የሚል ቅሬታ ባይጠፋም እዚያም “ስፓንሰር” እየተደረጉ ይጠመቁ የነበሩ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚከሰቱ ግድያና መፈናቀሎች ከወራት መጥፋት በኋላ እንደአዲስ የማገርሸታቸውን“ጥቁምታ” ማጤኑ አይከፋም፡፡ ወዲያውም የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ውስጥ ለመፍታት ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር ሁሉ ችግር የለብኝም፡፡ ይልቁንም ሌላ መተኪያ የሌላትን አገሬን አንድነት የምጠብቀውም የሃሳብ ልዩነቶችን በግድያና አሻጥራዊ እስራት እንዳልሆነ በደንብና ከአንደበቴ ሳይሆን ከልቤ ስለማምን ነው፡፡

ከተከዜ ማዶ - ዘመድ አለኝ ማለት?!

ጦርነትን መጀመር ሊቀል ቢችልም መጨረሱ ግን የማይቻል አልያም በጣም የከበደ ነው። በፖለቲካዊ ንግግርና ድርድሮች ሊፈቱ ይችሉና ይገባቸውም የነበሩ ልዩነቶች ማብቂያ አልባ የወገን ጦርነት ውስጥ ሲከቱን “አበጀህ… ግፋ በለው!” የሚሉቱ በዝተው አስተውለናል፡፡ ኢትዮጵያችንን እጅግ አድርገው እንደሚወዷት ይናገሩ የነበሩ ሰዎች “ትግራይ ትገንጠልልን!” ሲሉ ማድመጥም ሆነ በወዲያኛው ሌላ ጫፍ “ሀገረ ትግራይን እንመሰርታለን!” የሚሉ ድምፆች እንግዳነትና ረባሽነታቸው ያለፈበት መስሏል፡፡

በአንዳንድ ቦታ ከታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቃን ጀምሮ እስከነዚሁ ዩኒቨርስቲዎች መምህራንና ልኂቃን ድረስ ይሄ መፈክር በይፋ መደመጡ የገባንበትን ፖለቲካዊ ድንዛዜና የመለያየት ጥግ አስመልካች ይመስሉኛል፡፡ የጎረምሶቹ የነገር ማስተዋል በዕድሜና ሁሏቀፍ ዕውቀት ወብስለት ማጣት ሊመካኝ ቢችልም “የምሁራኑ” ሁናቴ ግን እጅግ አድርጎ ያሳስባል፡፡ ለዘመናት “አንቀፅ-39 ካልተሰረዘ አገራችን ኢትዮጵያ መበታተኗ ነው፡፡ ሲሉ ከርመው ድንገት የዚሁ አንቀፅ ወዳጅ ሆነው ሲገኙ ለአድማጭ ተመልካቹ ግራ ያጋባል።

በተቃራኒው ለዓመታት የአንቀፅ-39 ደጋፊዎች የሆኑቱ ድጋፋቸውን ባያነሱም የትግራይን መገንጠል አጀንዳ ሲያጮሁ እምብዛም አይደመጡም። የፊተኞቹ ስለትግራይ መገንጠል ሲናገሩ “ኦሮሚያስ?አማራስ? ሶማሌስ? ይገንጠሉ ወይ?” ቢሏቸው ፊታቸው ይጠቁራል። የገመዱ መተርተር ጅማሮ ብቻ እንጂ ፍፃሜ ያለው አይመስላቸውም። ወይም ያንን ደፍረው ማስተዋል አይፈልጉም፡፡ የኋለኞቹ መገንጠል አማራጫቸው ካልሆነ ስለምን አንቀፁ እንዲሰረዝ እንደማይፈልጉ ሲጠየቁ “ምናልባት...” የሚል ስጋትን ከማስቀመጥ ውጪ በቂና አሳማኝ ምክንያት አያቀርቡም። ከሁለቱም የሚከፋው ግን በመንግሥት ተቋማት በኩል የኮሎኔሉን ንግግር ተከትሎ እየተኬደበት ያለው መንገድ ነው፡፡

ከጦርነቱ የመውጫ ዘዴ (Exit strategy) እንኳን በወጉ ሳያበጁ ወደ ጦርነት መግባታቸው ሳያንስ በየፊናቸው ሽንፈታቸውን በትግራይ ህዝብና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በሚገለፅ ዘለፋ ለመካስ መሞከር ያለንበትን አሳፋሪ ወቅትና አመራር ገላጭ ነው፡፡ ዓቢይ አህመድ (ኮ/ል) “የመገናኛ ብዙኃን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላበረከቱት አስተዋፅዖ” ለማመስገን ጋዜጠኞችን ጠርተው በነበረበት መድረክ ከተናገሯቸው አሳፋሪ ንግግሮች አንዱ “ህዝቡ ነው እየወጋን ያለው!” የሚለው ይገኝበታል፡፡ በዚያኛው ወገንም አጀንዳው ይኸው ነበር፡፡

ይህም አልበቃ ብሎ በገዛ አገሩ “መንግሥት” በበዛው ህዝብና በተቋማቱ ሳይቀር ፊት የተዞረበት የትግራይ ህዝብ ከዚህም ብሶ “ወገኔ” ያለው አካል ከባዕድ ጦር ጋር በአንድ ሆኖ ሲወጋው ተፍቶት የነበረውን ወያኔን እንደብቸኛ አማራጩ ቢወስድ ትክክል የማይሆንበት አመክንዮ ሊኖር እንደማይችል እየታወቀ ዓቢይ አህመድ (ኮ/ል) ይህንኑ ንግግራቸውን በእንደራሴዎች ምክር ቤት ደግመውታል፡፡

የትግራይ ወገናችን በብዙ ተስፎበትና በደስታ ተቀብሎት የነበረውን ያህል ባለፉት ዓመታት “ዓይንህን አያሳየኝ!” ያለበት ምክንያትስ ምን ይሆን? ብሎ የመረመረ አላጋጠመኝም፡፡ ትግራዋይ ወገኖቻችን ንግድ ቤቶቻቸው በፖለቲካዊ ስሌት ሲዘጋ፤ መንግሥታዊ ድጋፍና መሪነትን በተላበሰ የቂም በቀል መነሾ ለህገ-ወጥ እስሮችና ብሔር ተኮር ልየታ (Ethnic profiling) ሲዳረግ ዝምታን የመረጥን ብዙዎች ነን፡፡ በሌላ መልኩ ለአገራችን መገነጣጠል የበኩላችንን አድርገናል ማለትም ይሆናል፡፡

አሁንና ሰሞኑን “ደጀን”እየተባለ የሚሞካሸው የአማራ ክልል ህዝብና መንግሥት በነገው ቁማር ምን እንደሚባል አብረን የምናየው ቢሆንምከአገሪቱ ሳቢ (Vibrant) ከተሞች አንዷ የነበረችው መቀሌን ለገጠር ከተማዋ በሻሻ ተምሳሌት አድርጎ ከማሳደግ ይልቅ “መቀሌን ከበሻሻ እኩል አድርገናታል!” ብሎ ከድኃ አገር ጥሪት ቢልዮን ዶላሮችን ለጦር እየገበረ በተሳልቆ የሚሸልል ገዢ በሚዘውራት አገርና ይህንን አይነቱን እብደትና የቂም-በቀል ፈቀቅ አያደርግ ጉዞ አድንቆ በጭብጨባ የሚያጅብ እንጂ በጥያቄ የሚያፋጥጥ “ጋዜጠኛ” በእብደታችን ውስጥ አንጠብቅም።

ከሙያውና ሙያዊ ሥነ-ምግባር ተለያይቶ ለመጣ ለሄደው አድር-ባይ ብዕሩን የሚያስገዛ ጋዜጠኝነት ለኢትዮጵያ እንግዳ ክስተት ባይሆንም በዚህ ደረጃ መዛቀጡ ግን “እንገነባዋለን” ለምንለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትልም በጣም አስጊ ይመስለኛል። በአንድ ወገን ጭፍን ድጋፍ ያበደ ባለሙያ ለሌላው ወገን ጭፍን ጥላቻ ቢያዳብርም አያስደንቅም። ትግራይ ብቻዋን እንደማትፈርስ ይልቁንም ከኢትዮጵያችን ቀሪ አዕማዶች የአንዱ መከላት ሁላችንንም አናግቶ እንደሚበትነን ለ“ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!” ሀሳዊ ፎካሪዎች ማስረዳቱ ይደክማል።

የተከዜ ድልድይ መሰበር ተነገረን እንጂ ማን እንደሰበረው ተመስጥሯል፡፡ ከሰሞኑ ድልድዩ በትግራይ ኃይሎች ተገንብቶ ብንመለከተውም ከሌሎች መገናኛ ብዙኃን የተሰማ ነገር የለም፡፡ በምልኪና ገጠመኞች ባላምንም የድልድዩ መጠገንም ሆነ ጥገናው በትግራይ ኃይሎች መሆኑ የግንኙነታችንን በሙሉ አለመቋረጥ ይጠቁመኛልና አልጠላውም፡፡ ከተረቶቻችን በአንዱ ቤቷን አቃጥላ “አሁን ገና በራልኝ!” እንዳለችው አይነት አቃጥሎ የመሞቅ ጤና ማጣት ውስጣችንን አምሶታልና እዚህ ግድም አንጋፋውን የአደባባይ ምሁርና የሠብዓዊ መብቶች ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን አፈሩን እንዲያቀልላቸው ከመመኘት ጋር ልንጠቅሳቸው ሆነ፡፡

ፕሮፌሰሩ ዛሬ ከጋዜጠኝነት ይልቅ አራማጅነት (Activism) መለያው የሆነውን “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ያነብቡ እንደሆነ በጋዜጣው ባልደረባ ተጠይቀው ሲመልሱላት እንዲህ በማለት ነበር በቀጥታ ያልተኳኳለውን እውነታ ያስቀመጡት፡- “ምን አዲስ ነገር ለማግኘት? … እናንተም ብትሆኑ መንግሥት የአቋም መዋዠቅ ውስጥ ሲገባ ትበረታላችሁ፡፡ መንግሥት ሲነቃነቅ አቅም ታገኛላችሁ…. ደግሞም ከእናንተ ይልቅ የግሉ ፕሬስ ደፋር ፅሑፎችን ይዞ ስለሚቀርብ አነባለሁ፡፡ የግሉ ሚዲያ ወኔ አለው፤ እናንተ ጋር ያለው የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡”

እንደ መቆዘሚያም…. እንደ መሰናበቻም!

ለዘመኔ ወጣቶች መልካም አርዓያ ይሆናል ብዬ የማምንበትና በቀደመው ሥርዓት ከ“ዞን ዘጠኝ” አባላት ጓዶቹ ጋር ስለዴሞክራሲና ሠብዓዊ መብቶች ሰቆቃን የተቀበለውጋዜጠኛና የመብቶች ተሟጋች በፍቃዱ ኃይሉ ፅሁፎች አስተማሪነታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በፍቃዱ በዶቸዌሌ ገፅ ላይ “በወል ሽንፈት የየብቻ ለቅሶ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው የግል አስተያየት የሠላምና ፍትህን ማህበራዊነት ጠቅሶ በፖለቲከኞቻችን ለመነጋገርና ድርድር መስነፍ ሳቢያ አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ መዘፈቃችንን ፅፏል፡፡

በዚህ ሳቢያም “አንዳንዶች ከግጭት ስጋት የተረፉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው፤እነርሱም የምቾት ቀጠና ውስጥ ገብተው ለጎረቤቶቻቸው ችግር ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል ይላሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር የተኩስ ልውውጡ አዲስ አበባ አልደረሰም እንጂ የኃይለ ቃላት ልውውጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችንም ማቃቃር ከጀመረ ቆይቷል፡፡” በማለት ትዝብቴንና ትዝብቱን ካጋራ በኋላ የወል ሽንፈታችንን በጋራ መፍትሄ እንድንቋጨው ሃሳቡን አጋርቷል፡፡ በፅሁፍ አይሁን እንጂ ባበደ ሥርዓተ ማህበር ውስጥ ጤና ሆኖ ያስተዋልኩት ሌላኛው ብርቱ ሰው ደራሲና ጋዜጠኛ ሠለሞን ሹምዬ እንደሆነ ከዚህ በፊት የሰጠሁትን ምስክርነት ዛሬም አፅንቻለሁ፡፡

የአንዳችን ህመም ለሌኛችን ደስታ ሆኖ እየቀጠለ የጋራ አገር ትኖረናለች ወይም በዚችሁ የጋራ አገር ላይ አብረን እንዘልቃለን የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ቢሆንም በቀጣዩ ፅሁፌ ይህንኑ ጉዳይ ጦርነትን ባህል እና ጨዋታ ካደረገው ታማሚ ምልከታችን ጋር አሰናስ እስክመለስበት በተከታዩ የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ርዕሳችንን እንቋጥረው፡፡ ከሰሞኑ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አዳራሽ በተካሄደው ዘጠነኛው ዓመታዊ የበጎ ሰው ሽልማት መርኃ ግብር ላይ በኪነጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ የሆነው ደራሲ፤ ገጣሚና ወግ አዋቂ በዕውቀቱ ሥዩም በስብስብ ግጥሞች መድብሉ በኩል በእነዚህ ስንኞች “ሉላዊነት” ሰኝቶ በአራት ስንኞች እና በሌላ አንፃር ቀንብቦታልና እነሆ፡-

“የጋራችን ዓለም
የጋራችን ሠማይ፤
የብቻችን ህመም
የብቻችን ስቃይ!”

- ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :