ኢትዮጵያ ከዓቢይ አህመድ ዓሊ… በኋላስ?! (ሁለተኛው ክፍል)

After Abiy Ahmed 2ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
October 21, 2021

“If history repeats itself and the unexpected always happens, how incapable must Man be of learning from Experience?”
(ጆርጅ በርናንድ ሾው)

ጦርነት እና የነባሩ “ባህላችን” አበርክቶ!
 
በቀደመው ፅሁፍ የነካካነው የ“ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” ነባር “ኢትዮጵያዊ” ባህል ከትውልዳችን ዕሴቶች ጋር መቃረኑ፤ ለፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ግቦች ብሎም ለሥልጣን መደላድል ሲባልም የጦር ባህልን ዋነኛ መሳሪያው ማድረጉ ሺህ ዓመታትን እንደተሻገረ የተለያዩ የታሪክ ወፖለቲካ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ የኢህአዴግ ሥርዓት አልባና ህግን ያልተከተለ ፍርሰት ጦሱ ለአገራችንም ተርፎ እነሆ ጦርነትን ቀዳሚው ምርጫችን እንዳደረግን በአዝማናት መካከል ቀጥለናል፡፡

ይህን የጦር ባህልን ያለመግራታችን ብዙ እንደሚያስከፍለን ቢታወቅና በዚህ መጣጥፍም ልንነካካው ቀጠሮ ብንይዝለትም ሙዚቀኞቻችንና ግጥሞቻቸው በዚሁ የ“ገዳዬ ገዳዬ…” እና “ኸረ ጎራው!” ይሉት ባህላችን ውስጥ ታሽተው የመጡ በመሆናቸው ይህንን አይነቱን የተሳሳተ አልያም ጊዜ ያለፈበት የአገር ወዳድነትና አርበኝነት (Patriotism) ዕይታ እና አጓጉል ጀብደኝነት ከ“ሥርዓተ ማህበሩ” ሲጋት ያደገ የኔ ዘመን ወጣኒ የፉከራና ቀረርቶውን ዓላማና ምንጭ ሁሉ ሳያጠይቅ እንደወረደ ከመቀበል ይልቅ ይህንን የባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) ግጥም ቢያጣጥም እንደሚበጀው እጠቁማለሁ፡-

“እነሱም ይላሉ - ከተኮስን አንስትም
እኛም እንላለን - ቃታ አናስከፍትም
እንዲህ ብለን… ብለን የተገናኘን’ለት
አሞራ ተሰብሰብ - ትበላለህ ዱለት፡፡”

ኢትዮጵያችን ከዓለም ተነጥላና ዓለምም ዘንግቷት ሺህ ዓመታትን እንደኖረች በታሪክ ፀሓፊያን ተከትቦ የማንበባችን ምስጢር የጦርነት ይልቁንም ለንግሥና ሲባል ዕጩ ገዢዎች በየወገኑ እየገፋፉ የሚያደርጉት የማስገበር ፍልሚያ ቀዳሚው እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚሁ ባህል ሳቢያ በሠላም መኖር ለአገራችን ህዝቦች የሩቅ ህልም ሆኖ ቀርቷል ቢባልም ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ሳቢያም ነባሩ ባህላችን ጦረኛን የሚያጀግን፤ ገዳይንም የሚያሞግስ ሆኗል፡፡  የደም ቃና ያላቸው ዜማዎች የመገናኛ ብዙኃኖቻችንን የአየር ሞገድ ሞልተዋል፡፡ ሰርክ ጧትና ማታ “ተነሳ ተራመድ!” የሚል ሽለላና ቀረርቶ ማድመጥ ኹነታችን ከሆነም ሰነበተ፡፡

የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ የአገራችን የዘመናት “ትዕምርት” ሆኖ የኖረው የአንበሣ ምልክት በብዙ ውዝግብ ውስጥ ሆኖም ቢሆን በ“ጣዖስ/ፒኮክ” ሲቀየር ባልደግፈውም ዘላቂ ሠላምንና የምልከታ ልውጠትን ካስከተለ መልካም እንደሚሆን ግምት ነበረኝ፡፡ የጥንቷ ሠንደቅ ዓላማ ከእንቅልፏ ተቀስቅሳም አይተናልና በደራሲው ቃል ብረት እንጂ ልብ ያልተቀየረ ስለመሆኑ ታዝበናል፡፡ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ጦርን መግራት እንደሆነ የሚነግረን የ“ጦር አውርድ” ደራሲው በዕውቀቱ ሥዩም በቅርቡ ተመሳሳይ አቋሙን አስነብቧል፡፡

ሆኖም በተለያዩ የታሪክ ምስክርነቶች “ጦረኛ ህዝቦች” መባላችን በፉከራ እየታጀበ ሲነገረን አድገናልና ጦር ወዳድ ያልሆኑ ሠላማውያንን (Pacifist) ሱሪ በምናስታጥቀው አባታዊው ሥርዓት (Patriarchy) መመሰላችንና የዚህን ምሰላ ተቃራኒም በቀሚስ ለበስነት፤ በፈሪነት እና በእንስታይ ፆታ ውስጥ እንዲወከል ማድረጋችን የተለመደ ነበር፡፡ እነሆ ከብዙ አብነቶች ውስጥ አንድ ሁለቱን እንደማሳያ፡-

“ወንድ ልጅ ተወልዶ - ካልሆነ እንዳባቱ
ቀሚስ አልብሱና - አውሉት ከቤቱ፡፡”
           ****
“ወንድ ልጅ ተወልዶ - ካልሆነ እንዳባቱ
ስጡት አመልማሎ - ይፍተል እንደናቱ!”
           ****

ይህ ነባር የጦረኝነት ባህላችን ስለነፃነታችን የራሱ አበርክቶ እንደነበረው የማይካድ ቢሆንም በዘመናዊ እሳቤዎችና የዴሞክራሲ እሴቶች ሳይገረዝ መቀጠሉና በስሁት የአገር ወዳድነት መታጀቡ የራሱን ችግር አዋልዷል፡፡ በቀጣዩና የዚህ ርዕስ መጨረሻ በሆነው ፅሁፍ የምንመለስበት ቢሆንም ይኸው የተኳሽ ወዳድነት ባህላችን እንዲህ ይከተላል፡-

“ገዳይ ገዳይ ያልሽው - አባትሽ አይገድል
ገዳይ ገዳይ ያልሽው - ወንድምሽ ያልሽው
አርሶ ያብላሽ እንጂ - ሆድሽ እንዳይጎድል፡፡”
           ****
“ገዳይ እወዳለሁ - ገዳይም አልጠላ
ሲደክመኝ አርፋለሁ - በጎፈሬው ጥላ!”

በእርግጥ ሠላም ስለተፈለገ ብቻ አይመጣም፡፡ ሠላሙ ስለመዝለቁ እርግጠኛ ባንሆንም ሠላምን ለጦርነት ዝግጁ በመሆን ማረጋገጥ እንደሚቻል የሚሰብኩም አሉ፡፡ አበሳዋ የበዛባት ታማሚ አገራችን ለህመሟ ትክክለኛ ያልሆኑ መድኃኒቶችን በሚሰጧትና “ፈፅሞ አልታመመችም!” ሲሉ እውነታውን በሚክዱ ልጆቿ ሠላሟ ታውኳል፡፡ አስደናቂው ነገር አገራችን ሠላሟን ያጣችው በግጭቶች አፈታት (Conflict resolution) ተመርቄያለሁ የሚል ገዢ በሚዘውራት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ በመሳሪያ የሚመጣ ዘላቂ ሠላምና እስከወዲያኛው በኃይል የሚፈታ የፖለቲካ ልዩነት እንደማይኖር ዓለማችን ከበቂ በላይ ማስተማሪያዎች አሏት፡፡

የነገር አያያዛችን ያለማማር፤ ከእኛው የቀደመ የታሪክ ማህደርም ሆነ ከሌሎች ውድቀት ለመማር አለመቻላችን ሲታይም ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ እየሆነ እንደብርጭቆው መሰባበር፤ እንደውኃውም ያለመታፈስ መከተሉን እንዘነጋለን፡፡ በጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ እርግጥ ቢሆንም “መማሩንስ ተምረሃል ማገናዘቡ ይጎድልሃል!” ለእነሱ የተተረተ የሚያስመስሉና የቀደመ መልካም ስም ያላቸው ሰዎቻችንን ማስታዘቡ አልተገታም፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በጭቦ እና በጉልበት ትክክል ነው (Might is right) መርህ ስንታገለው መኖራችንን የዘነጋ “ችግራችንን በመድፍ እንፍታው!” ሲሉ መስማትም ሆነ “በጦርነት ብቻ ነው ይህንን ችግራችንን የምናልፈው!” የሚልን ምክር በሙሉ ልቦና የሚያደምጥ መብዛቱ አሳሳቢና የዕውቀትን ምንነትም የሚያጠያይቅ ይመስለኛል፡፡ ከአውዳሚ የወገን ጦርነት ማግስት የምታጓጓ ሳትሆን በችጋርና ረኃብ የተጎዳች፤ በበቀል መፈላለግ የሰከረች አገር እንደምትፈጠር አልገባንም፡፡

ከጦርነቱ… ማን ምን ሊያተርፍ?!

እንደየአውዱ ለሠላምም ለጦርነትም የሚተረጎም ቢሆንም በዕውቀቱ ሥዩም “በራሪ ቅጠሎች” በተሰኘ ስራው ስር ባካተተው “ጦር አውርድ” በኩል ይህንን ምልከታ በኪናዊ ለዛ ከመተቸት ባሻገር ጦርን መግራት የጥበቦች ሁሉ መነሻ ስለመሆኑ አሳይቶናል፡፡ “ጦር አውርድ” ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪያቸውን ቢያቀርቡም በአንድ በኩል አብረው የጦርነቱን አታሞ ሲደልቁ በመክረማቸው አልያም ስለሠላም በሚዘምሩበት አንደበትና ለሠላም በሚያሸበሽቡ እጆቻቸው መልሰው የጦርነቱ ቀንደኛ አጋፋሪ በመሆናቸው የትውልዱን ጆሮ ተነፍገው የማህበሩን ተሰሚነትም አጥተዋል፡፡

ከሁሉም ሲከፋ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች እና እንደተቋም “የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ” በቀደመ የተለጣፊነት መንገዳቸው በመቀጠላቸው ከወትሮው የተለየ ውጤት አላመጡም፡፡ የመከራችን ማብቂያ ገና እንደሆነ የሚገለፅልን ግን ገዢያችንና ጃግሬዎቻቸው የእስካሁኑን ውድመትና የየወገኑን ስቅየት “የልምምድ ጦርነት” ለማለት ስቅቅ እንዳላላቸው ስናስተውል ነው፡፡ ከወራት በፊት ከድኃዋ አገር ጥሪት ከወታደራዊ ወጪዎች በመለስ ከመቶ ቢልዮን በላይ ለሰሜኑ ጦርነት ወጭ መደረጉን ሲናገሩ ማድመጣችንም አይዘነጋም፡፡

ድንዛዜው አልለቀቀንምና የሠላሙ መንገድ ተመርጦ ይሄ ሀብት በጤናው ዘርፍ ብቻ እንኳን ምን ያህል መሠረተ ልማቶችን ይሰራ እንደነበር የሚጠይቅ የለም። ባለፋት ወራት ይህንን የጥላቻ ህመም፤ ይህንን የበቀል በሽታ ከመሀል እስከዳር አገር አስተውለናል። ባልሰለጠኑና እንደ ኢትዮጵያችን ባሉ የሶስተኛው ዓለም አገራት በገዢነት የሚፈራረቁ የፖለቲካ ማህበራትና ግለሰቦች ፖለቲካዊ ትርፍን ያስገኝላቸው እንጂ በምንም ነገር ላይ አጀንዳ ፈጠር አፍ-ዕላፊዎችን እንደሚያራግቡ ግልፅ ነው፡፡ እጃቸውን በየዘርፉ ከማስገባት እንደማይመለሱ፤ የየአገራቱ መንግሥታዊና አገራዊ ሥርዓቶችም በወጉ ተሰርተው ያላለቁ በመሆናቸው ይህንን እንደሚፈቅዱ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል፡፡

በአንድ አጋጣሚ ለዙፋኑ የቀረበ ግለሰብ የአገሩን ህልውናና ሉዓላዊነት የሚፈታተን ቀይ መስመር ውስጥ እንኳን እንዳሻው ቢሆን ከዚህ በመለስ ብሎ የሚመልሰው ህግና አሰራር እንዳይኖር በራሱ ህግ ይሆናል፡፡ በቀደመው ክፍል ከጠቀስነው የአቶ ልደቱ ፅሁፍ በተደማሪነት እዚህ ግድም አቶ ሞላ ዘገየን ምስክርነት መጥራቱ የተሻለ መስሎኛል፡፡ የቀድሞ የክቡር ዘበኛ ሠራዊት አባል የነበሩትና ብዙዎች በ“ውይይት” መፅሔት እና ሌሎች ህትመቶች ላይ የፅሁፍ ተሳትፏቸው የሚያውቋቸው አቶ ሞላ ዘገየ “አብዮት ወይስ ሪፎርም?” የተሰኘች አነስተኛ መፅሀፍ አሳትመው ነበር፡፡ በዚህ የኦሮሞ ተቃውሞ (Oromo Protest) የመጨረሻ ሰሞን ስራቸው የኢህአዴግ ፍርሰት የአገርን መፍረስ እንዳያስከትል በብርቱ አስጠንቅቀዋል፡፡

ለዚህም መፍትሄ ያሉት አገራችን አብዮትን የምትሸከምበት ጫንቃ ስለሌላት ሪፎርም ማካሄድና ሪፎርሙንም ኢህአዴግ ራሱ መምራት እንደሚኖርበት ጠቁመው ነበር፡፡ የህግ ባለሙያ ሆነው የቀድሞ ባለሥልጣናትን በመወከል የተከራከሩት አቶ ሞላ ዘገየ የጥቂቶች ፈላጭ ቆራጫዊ ሥርዓት እምዳላዋጣንና ለዘመናት እንደሞከርነው ሲመሰክሩ የአልበርት አንስታይንን “እብደት ማለት አንድን ነገር በተመሳሳይ መንገድ እየሞከሩ የተለየ ውጤትን መጠበቅ ነው!” የሚሉ ይመስላል፡፡ አስከትለውም የቀደመውን ነገር ሁሉ በዜሮ እያሰሉ እንደአዲስ ከመጀመር አባዜ ተላቅቀን በተጀመረው መልካም ነገር ላይ እየደመርን እንድንሄድ ያስታውሳሉ፡፡

በእርግጥ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው!” የሚሉትን እንርሳቸውና ከሁለቱም ኢህአዴጎች በኩል የጦርነቱ ዝግጅት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ከሁለቱም ወገን የእባብ ለእባብ መስታከክና ካብ ለካብ መተያየቱም የከረመ ነው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸውን ቀመር ሰርተውና ወታደራዊ የጡንቻ መተያያን አስቀድመው የገቡበት ጦርነት ቢሆንም አሸናፊ የማይኖርበት መሆኑ በዝሆኖች ፀብ የሳሩን መጎዳት ማስተረቱ አይቀሬ ሆኗል፡፡ እየደጋገመ አገራችንን የሚጎበኛት ሰው-ፈጠር ድርቅና ጦርነት-ወለድ ረኃብ በላያችን ላይ ማንዣበቡም ለዚሁ ነውና እነሆ የምጣኔ ኃብት ባለሙያና ፖለቲከኛው አቶ ሙሼ ሰሙ የሠላም መልዕክት፡-   

“በጦርነት አሸንፎም ሆነ ተሸንፎ ልቡ የፈቀደውን ያደረገ ሥርዓት፤ መንግሥት ወይም ቡድን በዓለም ላይ የለም፡፡ ይዋል ይደር ጦር አውርድ ባዮች እርስ በእርሳቸው ተጫርሰውና ህዝብ አጫርሰው አቅማቸው ሲሟጠጥና ጉልበታቸው ሲዝል ሁሉም ወደ ድርድር ጠረጴዛ መምጣታቸው አይቀርም፡፡ የትናንት አሳዳጅ የዛሬ ተሳዳጅ፤ የዛሬ ተሳዳጅ ደግሞ የነገ አሳዳጅ፤ ትናንት ግፍ ተፈፅሞብኛል ባይ ዛሬ ግፍ ፈፃሚና ሂሳብ አወራራጅ ተራ በተራ በመሆን ሁላችንም በአዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን እንደምንዳክር በተግባር እያየነው ነው፡፡ ጦርነት መፍትሄ አይሆንም፤ ሆኖም አያውቅም!”

አይ… እማዬ!

አምባገነንነት ለአህጉራችን አፍሪካም ሆነ ለቀጠናችንና ለአገራችን ከቅርሶቻችን እኩል ዕድሜ የጠገበ ችግር ነው፡፡ ችግሩ ግን ብቻውን የአንድ ጨቅላ አልያም የአንድ ቡድንና መንግሥታዊ ሥርዓት ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ግለሰቡ አልያም ቡድኑ አምባገነን እንዲሆን ከዝምታው ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን የሚቸር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ይኖራል፡፡ ይኸውም በተለያዩ ምክንያቶች የሚከማች ሲሆን ከጥቅም ባለፈ የዕውቀት ማነስና ገዢዎቹ የሚነግሩትን ሳያጠይቅና ሳያላምጥ የሚውጠው በቁጥር የሚበዛ በመሆኑ ነው፡፡

በቅርቡ የክብር ዱክትርናውን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተቀበለው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን “ኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ በሰጠው አልበሙ ይህንን በንዑስ ርዕስነት የተጠቀምኩትን አገላለፅ እያስዘመተና “አይ እማዬ!” እያለ የአህጉራችንን ችግር መንቀሱ ለዚህ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያችን ባሉ በትምህርት እጦት ድንቁርናና ተምሮም በማገናዘብ ማነስ ችግር ለዘመናት የተመቱ አገራት (Countries ploughed by ignorance) ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር እንዲህ በቀላል መተዋወቅም ሆኖ ተግባብቶ መዝለቅ ይሆንላቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

የትምህርት ተደራሽነቱም ሆነ የትምህርት ጥራቱ ጉዳይ ሳይስተካከል ያሏትን ትምህርት ቤቶች በጦርነት በምታወድም አገር እንኳንስና የፊደል ሽፍታው ዶክትሯል በፊደልም ተሞርዷል የምንለው ሳይቀር ካልዶከተረውና ፊደል የተሳሳተ እሳቤዎችን ሞርዶ ካልገረዘለት ሰው እኩል ነውጥን ሲናፍቅና የፖለቲካ ችግሮችንና የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶችን በጦርነትና በመድፍ ብቻ እንድንፈታ ሲያማክር በዕድሜያችን ለማየት በቅተናል፡፡

በእርግጥ የተኮተኮትንበትን የጠቅላይነት የፖለቲካ ባህል (Zero sum Game Politics) በቶሎ ልናመልጠው አንችልም፡፡ ኢህአዴግ የዚህ ክፉ ውርስና ባህላችን አስቀጣይ እንደመሆኑ ዛሬ በነብስ ተወራርደው ለውጥን እንዳመጡ የሚነግሩን በእውነታው ግን ህዝብ ታግሎ ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከተላላኪነት ወደፈላጭ ቆራጭነት የቀየራቸው አካላትም ዴሞክራሲን ከአንደበት ሽንገላ ባለፈ ሊኖሩበት እንደማይሹ ግልፅ ሆኗል፡፡ በኮሎኔሉ “ተፎካካሪ” እየተባሉ የሚኳሹቱም ቢሆኑ ከዚሁ ሚስጥራዊ፤ የተለየ ሃሳብና አዲስ ነገርን ከመ-ጦር ከሚፈራ ሥርዓተ-ማህበር የተገኙ፤ የማህበሩም አካልና የነባሩ ልማድ ሰለባ ናቸውና ነው በውስጠ-ፓርቲ ዴሞክራሲ እጦት እንደአሜባ ሲባዙ የምናያቸው፡፡

የእነዚሁ ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት አዲስ ፓርቲ አዋልደውም የሊቀ-መንበሩን ቦታ የሚይዙት ይኸው በአገራችን በሽታ ለሆነው ልጓም አልባና ያልተገደበ ሥልጣን ያላቸው መሻት ነው፡፡ ይህ ልክፍት ከሌሎች ስራን እንደመናቅና ክብርን ብቻ እንደመፈለግ ከመሳሰሉት ነባር ልማዶቻችን ጋር እየተዳመረ የዓለም ጭራ አድርጎናል፡፡ አቶ ሞላ ዘገየ አውጳውያኑም እንዲህ አይነቱን ጦረኛ ባህል ኖረውበትና ጎጂነቱን አስተውለውታል ይሉናል፡፡ በምትኩም ይህንን ባህልና ነባር ልማድ አሽቀንጥረው በመጣል ለተቀረው ዓለም አርዓያ የሆነ የፖለቲካና ምጣኔ ሀብታዊ ልማት ወዕድገት ገንብተው ማሳየታቸውን ይመሰክራሉ፡፡

ሲቀጥሉም እንደጋዜጠኛና ገጣሚ በፈቃዱ ሞረዳ ሁሉ “በእኔ ዘመን ማንም አሳዳጅ ማንም ተሳዳጅ አይሆንም!” ይሉትን የአድብቶ ማረድ ቃልኪዳን እንደሚያዘክሩ እንዲህ ያጠይቃሉ፡- “ኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ላይ ናት፡፡ ሕዝባችን በፖለቲከኞች መካከል፤ በተለይ በሥልጣን ላይ ባሉት ኃይሎች አካባቢ በሚታየው ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ ምክንያት በእጅጉ ግራ ተጋብቷል…. ለመሆኑ መቼ ነው ከአፍርሶ የመገንባት አዙሪት የምንላቀቀው? መቼ ነው ከሴራና የመጠፋፋት ፖለቲካ የምንፈወሰው? መቼ ነው አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ፤ አንዱ ገራፊ ሌላው ተገራፊ መሆናችን የሚያቆመው?” እርስዎ የዚህ ፅሁፍ አንባቢም ራስዎን ይጠይቁ፡፡ እኔም የዚህ ፅሁፍ አሰናጅ ስለሰዶ ማሳደድና ዶሮን በቆቅ የመለወጥ ፖለቲካችን ራሴን እጠይቃለሁ - መቼ ይሆን?! እኮ መቼ?!!!

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :