ኢትዮጵያ ከዓቢይ አህመድ ዓሊ… በኋላስ?! (ሶስተኛው ክፍል)

After Abiy Ahmed 3ሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
October 21, 2021

“Educating the mind without educating the heart is no education at all.”
(አርስቶትል)

ፈር ማስያዥያ…!

በቀደሙት ሁለት ክፍሎች በኪናዊ ስራዎች እያዋዛን የተመለከትነውን የ“ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” ልማዳዊ እንከናችንን ዛሬም መሞገት እንቀጥላለን፡፡ አባባሉም እንደሚል “ንጉሥ ሞተዋል… ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” ሆኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሥልጣን ከኢህአዴግ ወደ ኢህአዴግ ቢሆንም ሥልጣንን የመያዣውና የማስቀጠያው መንገድ ከብልፅግና ወይም “ከዓቢይ አህመድ ዓሊ…. በኋላስ?” እንዴት ሊሆን ይችላል ወይም ምን አይነት መሆን ይኖርበታል የሚለው ነጥብ ላይ ዛሬም አለመግባባታችን ለነገ ሌላ ዙር የግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳይዶለን መስጋቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ከእነዚያ ፅሁፎች በኋላ ዘላቂ ሠላምንና መግባባትን እንደማያመጣ ለእርግጠኝነት ቀርቤ የምናገርለት የመንግሥት ምስረታ “ፈጣሪ ይርዳን!” ተብሎ በኢህአዴጋዊው የመናገር እንጂ ያለመስማት ትምክህት ተጀምሯል፡፡ የአንድ አፈር አፈሮች የሆንን ኢትዮጵያውያን በወገን ጦርነት ስር መኖራችን ይብቃ የሚለው ደራሲና ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም መግቢያችን እንዲሆን ወደድኩ፡፡ ኤፍሬም “የተዘጋበት ቁልፍ” በሚለው የሶልያና ግጥሙ በኩል አባት በልጁ ላይ በቆለፈበት በር ምሰላ ትውልዷ ሁሉ እያንኳኳ በሚኖርባት አህጉረ አፍሪካ የበር መክፈቻው ቁልፍ ከዚያው ከጓዳዋ የጠፋ ቢሆንም “አህጉራዊ መፍትሄ” የሚባለው የጠፋውን ቁልፍ አፋልጎ ማግኘቱ ላይ ሳይሆን በሩን መስበሩ ላይ እንደሆነ ይሰኛል እንዲህ፡-

“እናም በዚች አገር
መፍትሄ ሚባለው
ቁልፉን ማግኘት ሳይሆን
በሩን መስበር ላይ ነው፡፡”
የትውልዶች ወግ!

ትውልዴ የቀደመውን ትውልድ “መዝሙር” እየዘመረና ያንኑ የፖለቲካ ኑረት እየደጋገመ እንዲኖር የተፈረደበት መስሏል፡፡ አንድም የቀደመውን ፖለቲካ ከመውቀስ አልዳነም፡፡ ሁለትም የራሱን ደለል፤ ፖለቲካዊ ምልከታና የፖለቲካ ማህበር አደረጃጀት አበጅቶ ለዘመኑ የሚመጥን ፖለቲካ ማደርጀት አልቻለም፡፡ በዚህ መሀል እንደተተሰፈው ባለው ላይ እየደመሩ የመቀጠል ሳይሆን የተገነባውን ሁሉ የማፍረስና እንደገና የመጀመር ፖለቲካ ጥርጊያውን ቀጥሎበታል፡፡ ይህም ከእርሱ ለቀደመው ትውልድ ፖለቲካና የፖለቲካ ባህል እንዲገብር ያደርገዋል፡፡

አገኘሁ አሰግድ “ማፍረስ እንደባህል” በሰኘው መጣጥፉ “what is in a term? A historical and linguistic examination of the revolutionary terminology: yiwdem, “let it be demolished, down with,” 1974-1977” የሚለውን የስሜነህ አያለሁ እና ቢኒያም ሲሳይን የጋራ ጥናት ስራ በመጥቀስ የ“ይውደም” ባህል ብዙ እንዳሳጣን ያትታል፡፡ መልካም የሚመስለው የ“ኢትዮጵያ ትቅደም!” ፍካሬ ሐረጉን የሚያበቃው “አቆርቋዧ ይውደም!” ላይ ቢሆንም ይሄ ቃል ለገዢው የፖለቲካ ማህበር ተቀናቃኝ የሆኑት ላይ ሁሉ እየተለጠፈ ያልወደመ ነገር እንዳልነበር ፅፏል፡፡

ፖለቲካዊ ልምምዶቻችን ሁሉ የጦርነትና የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ መሆኑን የተረዱት ገዢያችንም ከፕሮቶኮል ደንብ በላይ ናቸውና በወታደራዊ መለዮና ቀይ ቦኔት በመታየት ይህንን የህዝብ ሥነ-ልቦና ይዘውበታል፡፡ በእርግጥ “ምነው ፈጣሪዬ ጠላት ነሳኸኝሳ?” ይሉ የነበሩ ነገሥታት እንደነበሩ በተከተበላት አገር ገድሎ “የፍየል ወጠጤ…” የሚል ሥርዓትን ቢያስከትል አይገርም ይሆናል፡፡ ሰፊው የማህበረሰባችን ክፍል ያልተማረ መሆኑ እዚህ አለመማር ላይ ሥልጣን (Power) ተጨምሮበት “ሠላም ይሻለናል!” የሚሉ ባለሥልጣናት ሲገኙ እንኳን በተለመደው ፍረጃ በማዋከብ ዝም ማሰኘት ነባር ፖለቲካችን ነው፡፡

በእርግጥም ይህ ዘመናትን ያስቆጠረ የፖለቲካ ባህላችን በየትውልዶች መናናቅ ታጅሎ ከ“ህወኃት ይውደም!” ወደ “ትግራይ ትገንጠልልን!” ከፍ ብሏል፡፡ ትግራይን ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ለመገንጠል የሚጥሩትን የትግራይ ወገኖቻችንን በምንተቸውና በምንወቅሳቸው ልክ ትግራይ ከኢትዮጵያ ትነጠልልን የሚሉቱን የመሀል አገር ጥላቻ ወላጆችም በልኩ መተቸት ተገቢ ነው ብዬ በፅኑ አምናለሁ፡፡ ያለችን አንዲት አገር እርሷም “ኢትዮጵያ!” እንደመሆኗ በሀገር አንድነት ላይ ከየትኛውም አይነት ይሉኝታ ርቄ ይህንን ለመመስከር አልሰንፍም፡፡

ያለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር ነውና ከተራው ዜጋ አንስቶ በአገር ውስጥም ይሁን በውጪ አገራት ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩቱን “ምሁራን” ትግራይ እንድትገነጠል ሲሰብኩ መተቸት ልክ ይሆናል፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ልዩነታችንን ከጥንት እስከነገ የምንፈታበት መንገድ ከእኛ ትውልድ በተቃራኒው ቦታ ላይ ቆሟል ያልነውን ሰው በመሞገትና በህዝብ ድምፅ ወሳኝነት ሳይሆን በሴራና በመጠላለፍ፤ በማሳጣትና በማሰደድ፤ በማሰርና በመግደል ይህንንም በመሳሰሉ መንገዶች ላይ ፀንቶ የቆመ ነው፡፡ ይህ “የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ!” አይነት ጠፍቶ የማጥፋት እና የመደምሰስ የተከታታይ ትውልዶች አካሄድ ደግሞ ማህበራዊ ትስስራችንን አላልቶት ከጤነኛው የእኛና እነሱ ትርክት ወደታማሚው ገፍቶናል፡፡

ተቋማት ተቋማት ተቋማት…. !

ባለፉት ዓመታት የነፃና ገለልተኛ ተቋማት ግንባታና መጠናከር ላይ ብዙ ብለናል፡፡ በቀደመው ፅሁፍ የጠቀስናቸው የህግ ባለሙያው አቶ ሞላ ዘገየ “በብዙዎቹ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባልዳበረባቸው አገሮች፤ በተለይ በአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አለመተማመን አለ፡፡ ጠንካራና ገለልተኛ ሀገራዊ ተቋማት ስለማይገነቡ በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ሥልጣናቸውን ቢለቁ በሠላም የሚኖሩበት ዕድል ስለመኖሩ ጨርሶ እርግጠኖች አይደሉም፡፡” (ገፅ-114) በማለት ወደመንበሩ መወጣጫው እርካብና ከመንበር መፈንገያው ልጓም ከጥንት እስከዛሬ አንድ አይነትነት ያልተለየው ሴራና ጭቦ፤ ግድያና መገልብጥን ጨምሮ አይነቱ የበዛ ህዝባዊ የአመፃ መንገድ በመሆኑ ላለንበት እውነታ አብቅቶናል ይሉናል፡፡

ስለዚህም ይላሉ አቶ ሞላ ሲቀጥሉ “ሁሉን ዓቀፍ ብሔራዊ የንግግር ጉባዔ” በማድረግ ችግራችንን መፍታትና ተቻቻይ የፖለቲካ ባህልን መገንባት እንችላለን ይላሉ፡፡ ይህንን ልዩነት በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ያስችሉ የነበሩት ፍርድ ቤቶች የአስፈፃሚው አካል ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተቀባይና አቤት-ባይ ሆነው የፍትህ እና ርትዕ ሚዛኑ ባጋደለባቸው አገራት ዜጎች ዋስትናዬ የሚሉትን አካል እንዲያጡ ማድረጉም ተደባይ ችግር ይሆናል፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ብቻ ሳይሆን የወገን ጦርነትን በመባረክ የሚያስጀምሩና የሚያስቀጥሉ ሆነዋል፡፡

ቀለም ከመቀባባትና መለዮን ከማዕረጉ ጋር ከመለወጥ የተሻገረ ነፃ የፖሊስ፤ የዓቃቤ መንግሥት ወገዢ ፓርቲ ሳይሆን የእውነቱ ዓቃቤ-ህግ እንዲሁም የአገር ደህንነት ተቋማት መገንባትን በተመለከተም አቶ ሞላ “የህገ-መንግሥት ሪፎርም” የግድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ለተቋማት ግንባታና መጠናከር በቂና ቀዳሚ ትኩረት ሳንሰጥ በዚሁ ፅሁፍ ቀዳሚ ክፍል ላይ ከአቶ ልደቱ አያሌው ተውሰን ኢትዮጵያችን መንግሥትን ስለመጣል እንጂ ያ መንግሥት ከወደቀ በኋላ  ማለትም “ከመንግሥት ለውጥ በኋላስ?” መኖር ስለሚገባው ዓይነተ መንግሥት ስምምነቱ እንደሌለን የአሜሪካዊውን ሄንሪ ኪሲንጀር ስራዎች በመስበዝ አስረጅ ያቀርባሉ፡፡

በእርግጥም ቸስተር ኤ.አርተር “Men may die, but the fabrics of free institutions remains unshaken” ማለቱም ለዚሁ ነውና የነፃ ተቋማት ምድረ-በዳ በሆኑ አገራት ሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ማስወገድ ጦሱ የበዛና መዘዙም ለብዙ ጊዜ የሚመዘዝ እንደሆነ ጠቅሰው “አምባገነኖችን ማስወገድ መቻል እና አዳዲስ ተቋማትን መገንባት ጨርሶ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ “ከመንግሥት ለውጥ በኋላስ?” የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ በቂ እና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መልስ ሳያገኝ፤ ሁሉም “ከለውጥ በኋላ” በሚል መንፈስ መንጎዱ መዘዘኛ እና ውድ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄድ ነው፡፡” ሲሉ ዘግይተን ዋጋ ያስከፈለንን ግብ አልባ አመፅ ያወሳሉ፡፡

አቶ ሞላ ዘገየ የበለፀጉ በሚባሉትና ባልበለፀጉ አገራት መካከል ስላለው መሠረታዊ ልዩነት ሲያነሱ ፖለቲካዊ ተቋማት (Political institutions) የሚሏቸውን ሶስት ማዕዘኖች ያነሳሉ፡፡ ብዙኃኑ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በበኩላቸው ዘመናዊ ሀገረ መንግሥትም፤ የሕግ የበላይነትም፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም መገንባት አልቻሉም፡፡ በሀገራችን እና ከላይ በጠቀስኳቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች የሚስተዋለው ትልቅ ችግር እነዚህን ሶስት የፖለቲካ ተቋማት አመጣጥኖና ሚዛናቸውን ጠብቆ ያለመገንባት እና በእነዚህ ተቋማት አማካይነት የጋራ እሴቶችን ያለመፍጠር ችግር ነው፡፡” በማለት ዜጎች ሁሉ ያለልዩነት የሚጋራወቸውን የጋራ እሴቶች (Shared values) ያልገነባን በመሆኑና የገነባናቸውም በአንድ ወገን እሴትነት የሚፈረጁ እንዲሁም የሌላውን እሴቶች ከመምጣት የሚከለክሉ በመሆናቸው ከችግር የመውጫችንን ጊዜ እንዳረዘሙት ያወሳሉ፡፡

በእርግጥ በጥሩ ንግግሮችና የተስፋ ምገባዎች ጥሩ እንቅልፍ ተኝተው የሚያድሩና እምነታቸውን ከተቋማት ይልቅ ግለሰብ ላይ ያደረጉ ወገኖቼ መብዛታቸውን አስተውያለሁ፡፡ ሆኖም “ትናንትም ሆነ ዛሬ የሀገራችን መሠረታዊ ችግር የእነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት አለመኖር እና በእነዚህ ተቋማት መደላድልነት ኢትዮጵያውያን የሚጋሯቸው የጋራ እሴቶች አለመገንባታቸው ነው፡፡ ዘመናዊ ሀገረ መንግሥት መገንባት አልቻልንም፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም መመስረት አልቻልንም፤ የሕግ የበላይነት የተከበረበት ሥርዓት መመስረት አልቻልንም፡፡ መሠረታዊ ችግሮቻችን እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ሳይኖሩ የጋራ እሴት ብሎ ነገር ቀልድ ነው፤ ብሔራዊ መግባባት የሚባለውም ከተራ ዲስኩር ያለፈ ትርጉም አይኖረውም…. ” ይላሉ ደራሲው፡፡ (ገፅ-115)

ሲቀጥሉም ማሳረጊያና የችግሮቻችን ሁሉ ማሰሪያ የሚያደርጉት ይህንኑ ሃሳብ ነው፡፡ “እነዚህን መሠረታዊ ተቋማት መገንባት ካቻልን የጋራ እሴት መፍጠር አንችልም፡፡ እንደህዝብ የምንጋራቸውና የሚያስተሳስሩን የጋራ እሴቶች ከሌሉን ደግሞ፤ ሁልጊዜም ባለመተማመንና በጥርጣሬ ላይ ነው የምንኖረው፡፡ አቅም ያለው ደካማውን እያስገበረ፤ ደካማውም እንዲሁ ሲሳካለትና አቅም ሲያገኝ መልሶ ጊዜ የጣለውን እየተበቀለ የሚሄድበት የጥፋት አዙሪት እንዲቆምና ለሁላችን የምትሆን ዘመናዊ፤ የሕግ የበላይነት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡” (ገፅ-24)

በቀጣዩና ለዚህ ፅሁፍ ማጠናቀቂያ በሚሆነው ክፍል እስክመለስ ድረስ ዛሬም እንደተለመደው በገላጭ የግጥም እንሰነባበታለን፡፡ አበባው መላኩ “ከራድዮን” የተሰኘ የግጥሞች ስብስብ መድብል አለው፡፡ የተመረጡ ግጥሞችንም በንባብ እንካችሁ ያለበትን ሲዲ አንዘነጋውም፡፡ እርግማን ሆኖብን በአበሻ ምድር ላይ ደግ እንደማይበረክት የሚነግረን ይህ ገጣሚ ከእነዚህ ስራዎቹ በአንዱ “እስከማዜኖ” ይለናልና እነሆ አንስተን ከጣልናቸው ሃሳቦች አኳያ አሰላስሉትማ፡-

“…ከዚህ የቀን ጎዶሎ ነው
ከዚህ ክህደት በኋላ
ከተራራው አናትና
ከግርጌ በቆመው መሃል - መተማመኑ የላላ፡፡
የአዳም የልጅ ልጅ ሁሉ - ምን ቢጀግን ምን ቢያቅራራ
ምን ደግ ንግርት ቢያስነግር - ምን በማዕረግ ቢጠራ
“ይገድሉኝ ይሆን?” እያለ ነው - ውረድ ሲሉት የሚፈራ፡፡
እናም መውረድ ሞቱ ነው - አንዴ ደርጉን ከወጣ
ውረድ ሲሉት በመውረዱ ነው - ወንድሙም ህይወቱን ያጣ፡፡
በእርግጥ ለምን ይወርዳል - መውረድስ ማንን ጠቀመ
የወረደውን መግደሉ - ለዘለዓለሙ ካልቆመ???”

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :