ኢትዮጵያ ከዓቢይ አህመድ ዓሊ በኋላስ?! (ወግ መቋጫ)

After Abiy Ahmedሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)
November 14, 2021

“In peace, sons bury their fathers. In war, fathers bury their sons!”
(ሄርዱተስ፤ ግሪካዊ የታሪክ ሰው)

ሥልጣኔያችን… ቢሰለጥንስ?!

ኢትዮጵያችን የረዥም ጊዜ ሥልጣኔ ያላት አገር ስለመሆኗ ሲነገር መስማት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በሸኘናቸው ዓመታት አላስፈላጊና የማይናፀር ፉክክር ውስጥ እየተገባም “እነሱ አገር ከመሆናቸው በፊት እኛ መንግሥት ነበርን!” በማለት አሜሪካንና አውሮጳውያኑ ምሳሌ ሲደረጉም አስተውለናል፡፡ በመሰረቱ ሆኖ በመገኘት፤ በምግብ እህል ራስን በመቻል፤ በፖለቲካ ሥልጣኔና ዴሞክራሲያዊ ዝማኔም የዚያኑ ያህል በመግፋትና በቁሳዊ ብልፅግናም ካልታጀበ “ነበረን” ማለቱ ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ነበረን ለምንለው ነገር ሁሉ ያለንን ካልደመርንለት ትናንት ላይ ቆሞ-ቀርነታችንን እና የታሪክ ምንጣፍ ላይ ተኝተን መቅረታችንን ከማጋለጥ የተሻገረ ርባና ይኖረዋል ብዬም አላምንም፡፡

በቀደሙት የዚህ ፅሁፍ ክፍሎች የሥልጣን መወጣጫው፤ ርክክባችንም ሆነ ሥልጣንን የማስጠበቁ አካሄዳችን ያለመሰልጠኑ ዋነኛ ምክንያት በአንበሳነት መስለን የምንወክለው የጦር ባህላችን እንደሆነ አውስተን ከታሪክ ሰበዞቻችንና ከሥነ-ቃሎቻችንም ጠቃቅሰናል፡፡ ታሪክን ማወቅ ጥሩ ማስተዋሉም ጥበብ ነው፡፡ ጥሩ መካሩ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ “ታሪክን መማር ለሁሉ ሰው ይበጃል፡፡ ለቤተ-መንግሥት መኮንን ግን የግድ ያስፈልጋል፡፡” በማለት ይህም አስፈላጊነቱ ከትናንቱ መጥፎ ታሪክ እየተማሩ እንዲያስተካክሉ ነው ይሉናል፡፡

በእርግጥም ዕውቁ የታሪክ ምሁር ኤድዋርድ ሀሌት ካር “ነበር” እና “ነው” የሚታረቁበትን የታሪክ አረዳድ “If you don’t know History you don’t know anything. You are a leaf that doesn’t know it’s part of a tree.” በማለት ሲገልፀው በጥቁር ህዝቦች የነፃነት እንቅስቃሴዎችና የትግል ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ማርክስ ጋርቬይም “There’s no future for a people who deny their past.” ስለማለቱ ይወሳል፡፡ አለመታደል ሆኖ እኛም ገዢዎቻችንም ከታሪክ የተማርነው እምብዛም እንደሆነ ደጋግመን ያሳየንባቸው አጋጣሚዎች በርክተዋል፡፡

ለታሪካችን ካለን ፍቅርና በታሪካችን ካለን ኩራት እኩል በመጥፎ የታሪካችን ኹነቶች ላይ ልናፍርና ቢያንስ ድግጋሜውን ልንቀንሰው የሚገባ ስለመሆኑ እነሆ የነጋድራስ ምክርና ጥያቄ፡- “የእኛ የኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪክ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍፁም የሆነ ሠላም አግኝተን አናውቅምና… በመላው ዓለም ሠላም ሲሰፋና አዕምሮ ስትበራ እኛ በጭለማ እንኖራለን… ምነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንቅልፍህ መቼ ትነሳለህ? በዓለም ላይ የሚደረገውን ነገር ለማየትስ ዓይንህን መቼ ትከፍታለህ?” በእርግጥም የአያቶቻችን ዘመን ችጋርና ርኃብ በእኛ በልጅ ልጆቻቸው ዘመንም አለመነቀሉና መታወቂያችን ሆኖ መቅረቱ ሊያብከንክንና ሊቆጨንም በተገባ ነበር፡፡

የእርስ በእርስ መተላለቃችን አንዳችን የሌላኛችንን ትርክትና ችግር ለማክበር ብቻ ሳይሆን ሲቻል ለማጥፋት ይኸውም የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ርዕሰ ብሔር ታቦምቤኪ እንደገለፁት “Failure to deal with Diversity” ሳይቻል ደግሞ ብዝኃነትን ለመሸፈን (a politics of diversity blindness) እንሞክራለን እንጂ አንደኛችን ሌላኛውን ወገን ለማድመጥ እንኳ አለመፍቀዳችን፤ ፀጉርን አጎፍሮ መሸፈትና ቀረርቶን በስልጡኑ ዘመን እንኳ ማንበራችን ያለመሰልጠናችን ማሳያ ሆኖ ዛሬም እነሆ የዘራፍ ፖለቲካና ዲፕሎማሲያችን ቀጥሏል፡፡ በቀደሙት ፅሁፎች የጠቃቀስናቸውም ሆኑ ተመዝግበው የቆዩ ሥነ-ቃሎቻችን “ኸረ ጥራኝ ጫካው ኸረ ጥራኝ ዱሩ…” ተኮር ሆነው ባሉበት አሉ፡፡

ተደጋጋሚና ዓለም ያወቀለትን ውሸት፤ ጥላቻንና አጓጉል ተስፋዎችን በመልካም ቃላት እየለበጠና እያመረተ የሚያከፋፍል ግለሰብ በበበጎነት በሚጎላበት ማህበረ ሥርዓትና ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥም የጥላቻና የሐሰተኛ ንግግሮችን በአዋጅ እቆጣጠራለሁ የሚል ሃሳብ መኖሩ ቢያስደንቅም በችግራችን ላይ ችግርን ስለመደመሩ የሚካድ ፍሬ ነገር አይደለም፡፡ በጋራችን አገር ላይ አንዱ ለአገር በጎ አሳቢና ዋና ዜጋ ሌላው በአገር ላይ ክፉ አሳቢና ተጠርጣሪ ተደርጎ እንዲሳል የሚሰራው ስራ መንግሥታዊ መዋቅርንና የአውርቶ አደሮችን ስሁት ንግግሮች ይዞ እስከቀጠለ ችግራችንም እየተባባሰ ይቀጥላል፡፡

እዚህ ግድም በተደጋጋሚ የገለፅኩትንና “ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት…” ይሉትን እጅ የመታጠብና ኃጥያትን ለአንዱ ብቻ የመለከክ አዝማሚያ በጥብቅ እንደምቃወመው መግለፅ ይጠበቅብኛል፡፡ በነበሩን ጥሩ ነገሮች ላይ ሌሎች ጥሩ ነገሮችን እየደመርን መጥፎዎቹን በመቀነስ መጓዝ እንጂ ያለንን ሁሉ እያፈረሱ እንደአዲስ በመገንባት መጠመድ ለቀደሙት አገዛዞችም ያልበጀ አካሄድ ነውና፡፡ ይህንን ኢህአዴጋውያኑ ሁሉ የተጨማለቁበት ግን ደግሞ ለይቶ የመምታቱን ጲላጦሳዊ አካሄድ የምቃወመውም የኢህአዴጋውያን ችግር አገራችንን ለማፍረስ የሚበቃ ችግር በመሆኑ ነው፡፡

የዚያን ሰሞን የሳልቫኪርን መወድስ ተከትሎ ለንጉሡ እና ለደርጉ ዘመን ገዢዎች አጨብጭቦ ያስጨበጨበው የኢህአዴግ መዋቅር ሲያጨበጭብለት ኖሮ እጅ የነፈገውን “መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ” ተፍቆ “የአፍሪካ ልህቀት ማዕከል” መሆኑን ከዚህ በፊት እዚሁ ገፃችን ላይ መተቸታችን አይዘነጋም፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ እዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኘውና በ1952 የተቋቋመው “አግዓዚያን” ቤተ-ትምህርት በመዲናዋ ከንቲባዋ ወደ “አዲስ ምዕራፍ” ሲቀየርና በተወሰነ መልኩም ተቃውሞ ሲገጥመው አይተናል፡፡ ይህም ብዙ ከተሰፍንለት ባለው ላይ እየደመሩ የመሄድ አካሄድ በእጅጉ የተቃረነ ክፉ ጥንስስ ስለመሆኑ አንወሻሽም፡፡

ይህንን አይነቱን አይረቤ አሰራር ለመተቸት ሠላሙ በቀለ ገብረኢየሱስ የተባሉ የህግ ባለሙያ ቃላቶችን ልዋስ፡፡ እኚህ ደራሲ “ሕግን እንወቅ” በሚለው አነስተኛ መፅሃፋቸው አንዱ ገፅ ላይ ይህንን ሲሉ ይነበባሉ፡- “ሥልጣኔና ብልፅግና በባዶ ሁኔታ አይሠራም፡፡ ከባዶና ካልነበረ መፍጠርና መሥራት የእግዚአብሔር ሥልጣንና ችሎታ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ያለውንና የተደረሰበትን ባህልና ሥልጣኔ መልካሙን ይዞ፤ ክፉውንና የማይጠቅመውን አስወግዶ፤ በተገኘውና በተደረሰበት ዕውቀት ላይ አዲስ ጨምሮ መራመድ ያሻል፡፡ ያለዚያ ሥራው ሁሉ የእንቧይ ካብ ይሆናል፡፡” (ገፅ፡-12)

መቼ ይሆን… ?!

በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የዴሞክራሲ ባህላችን ኋላቀርነት አንዳችን የሌላኛችንን ሃሳብና እምነት ለማድመጥና መታገስ አለመፍቀድ ብቻ ሳይሆን ተቃራኒ ሃሳቦችንና ድምፆችን በሙሉ አጥፍተንና ሁሉንም ጠቅልለን ካልያዝን ያስተዳደርን እስከማይመስለን ድረስ እንሄዳለን፡፡ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የቡዳ ፖለቲካ” ከሚሉት እንዲህ አይነቱ ነገራችንን ሁሉ የእምቧይ ካብ የማድረግ ፖለቲካ ወጥተን ፖለቲካችንንም ሆነ ሥልጣኔያችንን እንድናዘምን ከእኛ የተለዩ ድምፆች ሁሉ ባንወዳቸውና ባይስማሙን እንኳ መደመጥ እንደሚኖርባቸው አያጠራጥርም፡፡

ከሸኘናቸው ሳምንታት በአንዱ ጋዜጠኛ፤ ደራሲ፤ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋችና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዚደንት የሆነው አቶ እስክንድር ነጋ በፍርድ መንዛዛትና በሀሰት ምስክሮች ከተፈጠረበት ችግር በተጨማሪ በእስር ቤት ውስጥ በደረሰበት ድብደባ ሳቢያ የፍትህ ሥርዓታችን ዳግም መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሆኖም የፍትህ መጓደል በሁላችንም ላይ የተደገነ አደጋ ስለመሆኑ ተዘንግቶ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ሰው “Injustice anywhere is a threat to justice everywhere!” ከሚለው ሥልጡንና ሰብዓዊ መርህ ባፈነገጠ መልኩ በድብደባው ላይ ሲሳለቁ ተስተውሏል፡፡

ህወኃትን በተመለከተ “አንተም እርጉም ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ እንደገና ዳቦ እሳት ለቀቀብህ!” ልንል ብንችልም የትግራይ ህዝብ ስቅየት ላይ መሳለቅና በቁስሉም እንጨት መስደድ፤ በህዝቡም ላይ የወረደውን መከራ አለመቃወም ከወዴት እንዳመጣነው ይኸው እየደነቀኝ አለ፡፡ ዳሩ “ሰሚ ነው እንጂ ተቸጋሪ፤ ደንቆሮ መልካም ኗሪ!” ሆኖ ብዙዎች እስክንበስል ብሱሎቻችን ተብከንክነዋል፡፡ አለማወቅ ላይ ሥልጣን ሲደረብበት ደግሞ ጉዳቱም በዚያው ልክ ከፊ ነውና ነው በተደጋጋሚ የጠቀስኩት ኃይሉ ገ/ዩሐንስ (ገሞራው) ይህንን ብሎን አልፏል፡-

“በመንቃት ላይ ባሉ - ፍጡራን መካከል
ህይወት የምንለው - እንደጥሬ እህል፤
በኑሮ ምጣድ ላይ - ቢቆላ ቢማሰል
የበሰለው ያርራል - ጥሬው እስኪበስል፡፡”

እንደጋዜጠኛና ገጣሚ በፈቃዱ ሞረዳ ሁሉ “በእኔ ዘመን ማንም አሳዳጅ ማንም ተሳዳጅ አይሆንም!” ይሉትን የአድብቶ ማረድ ቃልኪዳን “ሳናጣራ አናስርም፤ አስረን ማስረጃ አናፋልግም!” ይሉትን አሁን በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የምናየውን ተሳልቆ የሚሞግቱት አቶ ሞላ ዘገየ እንዲህ ያጠይቃሉ፡- “ኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ላይ ናት፡፡ ሕዝባችን በፖለቲከኞች መካከል፤ በተለይ በሥልጣን ላይ ባሉት ኃይሎች አካባቢ በሚታየው ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ ምክንያት በእጅጉ ግራ ተጋብቷል…. ለመሆኑ መቼ ነው ከአፍርሶ የመገንባት አዙሪት የምንላቀቀው? መቼ ነው ከሴራና የመጠፋፋት ፖለቲካ የምንፈወሰው? መቼ ነው አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ፤ አንዱ ገራፊ ሌላው ተገራፊ መሆናችን የሚያቆመው?”

እርስዎ የዚህ ፅሁፍ አንባቢም ራስዎን ይጠይቁ፡፡ እኔም የዚህ ፅሁፍ አሰናጅ ስለሰዶ ማሳደድና ዶሮን በቆቅ የመለወጥ ፖለቲካችን ራሴን እጠይቃለሁ - መቼ ይሆን?! እኮ መቼ?!!! በእርግጥ ይሄ ጥያቄ የብዙዎች ነውና ጋዜጠኛና ደራሲ ደምሴ ፅጌም “መቼ ይሆን?” በሚለው ስራው በኑረታችን ውስጥ የጎደለውን ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር የመጣላት አባዜ አስመልክቶናል፡፡ ጦርነታችንን ለማስቆም ስንት ሚሊዮን የወጣባቸው መሠረተ ልማቶች መውደም ይኖርባቸዋል? “ረኃብ ስንት ቀን ይፈጃል?” እንዲል ባለቅኔው ስንት ሰው በርኃብና ጠኔ፤ በጦርነትና የግጭት አዙሪት መሞትና በፆታዊ ድፍረት መዋረድ ይጠበቅበታል? ምን ያህል ዕርዳታና ልመናስ ከጥይትና መሳሪያ ግዢ ተርፎ ውድመቱን ለመገንቢያ ይበቃን ይሆን? ከዚህ ሁሉ መቂያቂያም በኋላስ እንኳን እኛ ልጆቻችን በሠላም ይኗኗሩ ይሆን?! ዛሬ እየከፈልን ያለነው ዕዳስ የቀደምቶቻችንን አርቆ ያለማየት አይነግረን ይሆን?!

ስልጡኖቹ አገራት ከአውዳሚ የጦርነት ታሪካቸውና ዓለማችን ካስተናገደቻቸው የጦርነት ሰቆቃዎች ተምረው በገዛ አገራቸው ጥቅም ላይ ሳይቀር የፀረ-ጦርነት ንቅናቄ (Antiwar movement) ሲያካሂዱ የእኛ ቆሞ መቅረት ያሳዝናል። ገዢያችን በአንድ በኩል ሠላም ምንም አይነት ዋጋ ቢከፈልላት ይገባታል እያሉን “Walk your talks!” ሲባሉ በወታደራዊ መለዮ ብቅ የሚሉት ኮሎኔል ከድኃዋ አገር ጥሪት ላይ መቶ ቢልዮኖችን ስለሥልጣናቸው ደህንነትና ዘለቄታ ለማውደም ሁለቴ አያስቡም።

ፖለቲካዊ ንግግርንና ድርድርን ያላስከተለ “ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ” የመሠረተ ልማቶችን መከፈትና የሰብዓዊ ተራድዖ መንገዶችን ከርችሞ ከርቀት የሚፎክር መሆኑን ስናስተውል ከዕረፍት መልስ ዳግም የመግጠም ነገር ስለመኖሩ እንደገመትነው እነሆ ቀጣዩ ዙር ውድመት እየተካሄደ ነው፡፡ በዶክተርነት ጀምረው በኮሎኔልነት የቀጠሉት ዓቢይ አህመድ “የውስጥ ግጭታችን ተራዝሞ የደከመች ኢትዮጵያን ለማየት ያሰፈሰፉ ኃይሎች ከበውናል።” ሲሉና ለቤተ እንደራሴዎች አባላት ሲናገሩ ቢደመጡም አገዛዛቸው ከአንዱ ቀውስ ወደ ሌላው እየመራ እዚህ ይዞን ወርዷል፡፡

አንዳንድ ጊዜ አማራጮቻችንን በጊዜ አጢነው በትግረኛው ብሂል “ስለምጣዱ ሲባል አይጢቷ ትለፍ!” ባዮችን በአፍቃሪ-ህወኃት ሲያስፈርጅም ይስተዋላል። ገፋ ተደርጎም ያሰቃየህን አካል በመውደድ አባዜ (The Stockholm Syndrome) ፖለቲካችን እንደተሞላ ተፅፎ አንብቤያለሁ። ሰው ፈጠር ርሀብ (Manmade starvation) በሁለቱም ወገን ብዙዎችን እያመሰቃቀለና ይልቁንም የወሎውን አካባቢ ከጥንት እስከአሁን እያዳረሰ ባለበት ሁኔታ ለሠላም አይረፍድም ቢባልም በደንብ ሲረፍድ አይተናልና ዝምታዬ ኃጥያት ይሆናል። የጦርነት ጥሩ የሠላምም መጥፎ እንደሌለው በሚነገረው ሙሉ አማኝም አይደለሁም፡፡ ዛሬ ጦርነቱን በመሽረፈትነት የሚያርገበግቡ፤ ዛሬም የማይዘምቱ ግን የሚቀሰቅሱ ብሎም ከውድመቱ ለማትረፍ አድብተው የሚጠብቁ መኖራቸውን ማሰብ ግን ህሊና ያሳምማል።

ለምን እንደሆነ በማይገባንና አተራረክንም በሚያዛባ መልኩ እየተዛባ በሚገለፀውና ከንጉሥ ወነገሥቱ ዘመን ጀምሮ እንደአሁኑ ሁሉ ለይስሙላም ቢሆን የተካሄዱትን ምርጫዎች ሁሉ ያስካዱት ምርጫዎችም ሆኑ “ስድስተኛው” እንደሆነና “ዓለምን ያስተማረ…” ተብሎ በስሁት ምስክርነቶች የተሞካሸውን የምርጫ ውጤት ማሳያ እናድርገው፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ከተደመጡት አስተያየቶች መካከል “ህዝብ በሠላም ወጥቶ መግባት ስለሚፈልግ…” ገዢውን እንደመረጠና ዳገት ላይም ፈረስ ላለመቀየር እንደሆነ ተደምጧል፡፡

በእርግጥ ህዝብን በመሰረታዊ ነገሮች ላይ ጠምዶት ለቆው ብልፅግና ስለሠላሙ ሲል ህዝብ ነፃነቱን ቢተውለት እንግዳ አይሆንም፡፡ ሆኖም የቅርጫውን ውጤት ብቻ ለቅቡልነት (Legitimacy) በመስፈርትነት መውሰድ የማይቻልባቸውና ህጋዊነቱ “Regain” ተደርጓል ተብሎ በጅቡቲው ገዢ የእንኳን ደስ ያለህ አገላለፅ ልክ የማይኬድባቸው ሁኔታዎች አሉ። ወዲያውም ኮሎኔሉ እንደነገሩን “ሙከራ” የተባለውም መንግሥትን በምርጫ መቀየር የማያስችል ስለሆነም ነው። እኔም ትያቄውን ያነሳሁት ለዚሁ ነው፡፡ እስከመቼ እየተገዳደልን እንዘልቀው ይሆን? ከኮሎኔል ዓቢይ አህመድ አሊ በኋላስ የስልጣን ርክክባችን እንዲሁ ጠብ-መንጃ እንደወደረ ይቀጥል ይሆን???

እርግጥ ነው ዓቢይ አህመድ እንደሌሎች ገዢዎቻችን ሁሉ ምልክቶቹን እንጂ የፖለቲካ ህመማችንን ለማከምና ለመፈወስ ፈቃደኝነቱም ችሎታውም እንደሌላቸው ይልቁንም መሰንበቻ ስለማድረጋቸው ባለፉት ዓመታት ከበቂ በላይ ተረጋግጧል። ኮሎኔሉ በምክር ቤት ሪፖርታቸው ኤርትራን ከመገንጠል ያላስቀረውን ጦርነት ሲተቹ ቢደመጡም በትግራይ ጉዳይ ያንኑ ሂደት እየደገሙት ስለመሆኑ ግን አይነግሩንም፡፡ አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው በ“ለውጡ” መጀመሪያ ወራት “የማስጠንቀቂያ ደወል” በሚል ዓብይ ርዕስ ስር የኮሎኔሉን እና ሚሃይል ሲርጌዬቤች ጎርባቾቭን እያናፀረ የተመለከተበትን መፅሀፍ አቀብሎን ነበር።

በተለይ የራስ በራስ ትድድርን በተመለከተ የተሰጡት ህገ-መንግሥታዊ ዋስትናዎች መሸራረፍ በቅራኔና ቁርሾዎች ለተሞላች አገር የሚያተርፍላት ብቸኛ ነገር ቢኖር የ“አዲዮስ ሶቭየት ህብረት” አይነት እንደሚሆን በማስጠንቀቅም ፅፏል። የነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ መሆን ጅማሬም በኢትዮ-ኤርትራው ውዝግብ ላይ ከጉዳዩ ባለቤቶች አንዱ የሆነውን የትግራይ ህዝብንና መሪ ድርጅቱ ህወኃትን “ገለል ያደረጉ” አካሄዶች ስለመሆናቸው ይገልፃል።

የኢህአዴጋውያኑን ፖለቲካዊና የዘረፋ ኃጥያት በሙሉ ለህወኃት ሰዎች ሰጥቶና በላዩም ላይ ትግራዋይ የሆነውን ሁሉ በመተንኮስ ከላይ እስከታች የሚታየው መረባረብ የፈጠረውን የተገፊነት ስሜት ማቀጣጠያ ያደርገዋል። “በቅርቡ ከወደ ትግራይ የሰማነው በእኩልነት ተከባብሮ አብሮ የመኖር ወይም የመበታተን ደወል ወደ እልህና ቁጣ የሚነዳን ሳይሆን በእጅጉ በትህትና ዝቅ እንድንልና ለድርድርና ለውይይት ራሳችንን እንድናቀርብ የሚያስገድድ አደገኛ ደወል ነው።” በማለትም እንደጀዋር የቀደመ ማስጠንቀቂያ ሁሉ የዓቢይና የህወኃት እልህ መጋባት ወደ ጦርነት እንዳያድግ ይማፀናል።

ደራሲው በእነዚሁ የመጨረሻ ገፆች ላይ “በቀጥታ ለዶክተር አቢይ” ሲል ባስተላለፈው መልዕክት ትግራይ እንድትገነጠል በቃልም በተግባርም እየተደከመበት የቆየውንና አሁን በግላጭ የሚቀነቀነውን አካሄድ በተቸበት የአገርዎን አድኗት ተማፅኗዊ አገላለፅ ልሰናበታችሁ:- “የመጨረሻው ፈተናዎ ግን ከህወኃትና ከትግራይ ህዝብ አቅጣጫ እነሆ በፊትዎ ተደቅኗል.... በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተቋጥሮ የነበረውን ስሜት አርግበው ሁለቱን ህዝቦች ወደ አንድ ማምጣት የቻሉ መሪ ነዎት። ኤርትራን አምጥቶ ትግራይን ማጣት ግን ከኪሳራዎች ሁሉ ታላቅ ኪሳራ ነው።”

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትም



Contact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :