ታሪኩ እንዳጠየቀው - ማነው እየሄደ እየሞተ ያለው?!

Tariku Gankasi Dishtaginaሪያድ አብዱል ወኪል (የህግ ባለሙያ)

November 14, 2021

“እኔ የምፅፈው ማንንም ለማስደሰት አይደለም። ማንንም ለማሳዘንም አይደለም። ሙግት ለመፍጠርም አይደለም። ውይይት ለማካሄድ ነው። አተካሮ ለመፍጠር አይደለም። የሰከነ ሀሳብ ማንሸራሸር ቢቻል ብዬ ነው…. በአጭሩ የሰከነ ውይይት ለመፍጠር ነው።”
(ጋሽ አሰፋ ጫቦ - የትዝታ ፈለግ)
 
አገራችን ወደቀውስ ከመግባቷ በፊት ጀምሮ ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በፖለቲካዊ ንግግሮችና በሁሉን አሳታፊ ድርድር በመፍታት በኢትዮጵያ ብልጭ ብሎ በርቶ የተዳፈነውን የለውጥ ተስፋ በሙሉ እንዳናመክነው ይልቁንም ወደትክክለኛው መስመር እንዲመለስ በዚሁ ገፅ እና በአገራችን የህትመት ብዙኃን መገናኛዎች በኩል ስናሳስብ ቆይተናል፡፡

አለመታደል ሆኖ ለውጣችን ከህዝብ ሠላምና ከአገራችን ዘላቂ አንድነት ይልቅ በሥልጣን ወዳዶች የእርስ በእርስ ትንቅንቅ እና በዋነኝነትም በኢህአዴጋውያን በኩል እንዲከሽፍ ሆኗል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት በኢፌዲሪ የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የህወኃት ቡድን ጥቃት ማድረሱን በውድቅት ሌት የነገረን ቢሆንም ይህ ሚስጥር ወደፊት የሚጣራ መሆኑና ታሪክ የሚፈርደው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ “ህግ ማስከበር!” በሚል ስያሜ የተገባበት ዘመቻ ወደእርስ በእርስ ጦርነት ከፍ ካለ እነሆ አንደኛ ዓመቱን ተሻግሯል፡፡

በሸኘነው አንድ ዓመት ብዙዎች ሞተዋል፡፡ ተገድለዋል፡፡ ተገዳድለዋል፡፡ በነበረብንና በቀዳሚነት በያዝነው የውስጥ መፈናቀልና ስደት ላይ ሌሎች ሚሊዮኖችን ደምረንበታል፡፡ የክረምቱንና የመዝሪያውን ወራት ከዚህም ከዚያም ከብቶችን በመግደል፤ እህልን ያለምንም ጡር አይፈሬነት በማቃጠል፤ ታታሪውን ገበሬም ወደዘመቻ በመስደድ ችግርና ረኃብን አክለንበታል፡፡ በዚሁ ላይ ይህንን አይነቱን ኋላ-ቀርነታችንን እንድንተው የሚያሳስቡ ድምፆችን በማፈን ተሳልቀንበታል፡፡ አሁን የደረስንበት ስንደርስ አንደኛችን ለሌላችን ያለን ልክ-አልባ ጥላቻ፤ የመበቃቀል ፍላጎትና ያለመተማመን ስሜት እጅግ ገዝፏል፡፡

እንጠይቅ - ማነው እየሄደ እየሞተ ያለው?!

ምንም እንኳን የውስጥ ለውስጥ የፍጥነት መንገድን እንዲያካትት ሆኖ በ-2008- መጀመሪያ ዕቅዱ የተጠናቀቀ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪነት እና በዓቢይ አህመድ (ኮ/ል) ጥሩ የፕሮጀክቶች ክትትል ብቃት አሁን አምሮበት የምናየው የመስቀል አደባባይ (አብዮት አደባባይ) ለብልፅግና ሰዎች ተደራቢ ጥቅምም ይዞ መምጣቱ አይካድም፡፡ ይኸውም የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይደረግ ሁሏቀፍና ሥልታዊ ክልከላ በተደረገበት የአምባ-መግነን ድባብ ውስጥ በዚሁ አደባባይ በርካታ የድጋፍ ሰልፎችና የመንግሥት ምስረታም ተካሂዶበታል፡፡

እዚሁ አደባባይ ላይ ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በንግግርና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ጦርነትን የሻቱ በመቶ ሺዎች የተቆጠሩ የመዲናችን ነዋሪዎች በተሰበሰቡበት ነው እንደስሙ ታሪክ ሊሰራ አንድ የደቡብ ሰው ወደመድረክ የተከሰተው፡፡ ይህን ሰው እኛም ዓለምም ያወቅነው በፍቅርና በሠላም ስብከቱ እንጂ በግጭትና ጦርነት ጠማቂነቱ አልነበረም፡፡ እናማ ዕውቁን የሬጌ ሙዚቃ ስልት አቀንቃኝ ሮበርት ኔስታ ማርሌይ ሁለቱን የወቅቱ ተቀናቃኝ የጃማይካ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እጅ ለማያያዝ የደፈረበትን አይነት ድርጊት ደገመውና ግለቱን አቀዘቀዘው፡፡

ሙዚቀኛው ታሪኩ ጋንካሲ ጥቁር ለብሶ መጥቶ ጥቁር መልበስ ይበቃናል ሲል በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እየተላለፈ በነበረው መሰናዶ ምስቅልቅላችንን ለማጠየቅ ጀገነ፡- “እኔ አልዘፍንም! ልዘፍንም አይደለም የመጣሁት፡፡ በደስታም በኃዘንም መዝፈን ብቻ ነው እንዴ?! የቱ ጋር ቆሜ ልዝፈን?! የቱ ጋር ቆሜ ልዘምር?! የቱ ጋር ቆሜ ልናገር?! እንደዚህ ተጣቧል ሰፈሩ፡፡ እኔ የምዘፍነው የለም፡፡ የምናገረውም የለም፡፡ በዘፈኑም ካልተማርን፤ በመዝሙሩም ካልተማርን፤ የሚዘፈን ነገር የለም አሁን፡፡ የሚዘመርም ነገር የለም አሁን፡፡በመዝሙሩም አልተማርንም። በቤተክርስቲያን በሚያስተምሩም በቄሶችም አልተማርንም። በፕሮቴስታንት ሃይማኖት አባቶችና ፓስተሮች በሚያስተምሩት ካልተማርን፤ ሙስሊሞች በሚያስተምሩንም ካልተማርን ዘፈኑም አያስተምረንም… ምን አለ ብዬ ነው ምዘምረው?! ሁሌ ጥቁር መልበስ አያምርብንም፡፡ ይበቃል! ጥቁር መልበስ ይበቃል፡፡”

ታሪኩ ጋንካሲ በዚህ ልክ ጀግኖ ለሠላምና ለድርድር ጥሪ አድርጓል፡፡ በዚህም በእነ “ግፋ በለው!” ተቃውሞ የገጠመው ከዚያው መድረክ ጀምሮ ነበር፡፡ ታሪኩን የተቃወሙና የዘለፉት የጥበቡ ሰፈር ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ትክክልነቱን ደፍረው የገለፁም አሉን፡፡ “ዲሽታ-ጊና!” የተሰኘውንና ከአሪ ብሔረሰብ ቃል የተያዘውን ተወዳጅ ሙዚቃውን “ጁንታ-ጊና!” ብለው ለማጠልሸት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በአንፃሩ ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በቃሉ “እስኪ ተዋደዱ ይያያዝ እጃችሁ በልዩነታችሁ፤ አለበለዚያማ በምን ያስታውቃል እኛን መውደዳችሁ?!” ይሉትን መልካም ፍካሬ በቃል ቢነግረንም በተግባር ስንጠብቀው ሊኖረው የከበደውንና አንድም ቀን ሊያወግዘው ያልፈለገውን የወገን ጦርነት (Civil war) እና መፈናቀል ብሎም ጥቁር መልበስን ታሪኩ ሆኖና ኖሮት አሳይቶናል፡፡

እናማ ከመድረክ አመራረጡና ከአለባበሱ ጀምሮ በመላ አገሪቱ ሚሊዮኖችን በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት እና በተመሳሳይ ሰዓት በመላው አገሪቱ በሚታይበት መድረክ ላይ ጀግንነትን መስራት ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ አገሩ ሁሉ ከልሂቅ እስከደቂቅ የጦርነት ችቦን በሚያቀጣጥልበት ሁኔታ ሠላምና ዕርቅን የሚሰብክ ሰው ከእርጉማን ተቆጥሮ በቃላት ውግ፤ በዛቻና ማስፈራሪያ መወገሩ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ውርደትም ሆኗል፡፡ እንደ አውራ ዶሮው ታሪክ በጩኸታቸው ሌላውን ቀስቅሶ መሸኘት እንጂ እነሱ ሊሄዱና በጦርነት ቀጠና ውስጥ ለአንድ ቀን ቀርቶ ለአንድ ሠዓት እንኳን መቆየት የማይፈልጉ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከወዲሁ የሌላ አገር ዜግነትና ቪዣቻውን አመቻችተው መንገድ ቢጀምሩም የድኃውን ልጅ እነሱ ለማይገቡበት ጦርነት ሲማግዱ ማየት በእጅጉ አስተዛዛቢና ኢ-ሰብዓዊነትም ነው፡፡

ሌሎችን የሚያዘምቱ ግን ራሳቸው የማይዘምቱ ወገኖች እንደሚደግፉት ገዢያችንና እንደዘፋኚቷ ሁሉ “Walk your talk!” ሲባሉ “ዘራፍ እወዳለሁ ሠላምም አልጠላ!” ነው መልሳቸው፡፡ ጦርነትና ግጭት ለአንድ ቀን በተራዘመ ቁጥር በየቦታው ስለሚቃጠለው የገበሬ ቤት፤ ስለሚገዳደለው፤ በርኃብ ስለሚሞተውና ከቀዬው ስለሚፈናቀለው ወገንም የሚያሳስባቸው ነገር የለም፡፡ እናማ የመጨረሻ ግባችን ምንድነው?! ማነው እየሄደ እየሞተ ያለው?! በጠላትነት የፈረጅነውን አካል የማናሸንፈው ከሆነስ የመውጫው መፍትሄው ምን መሆን ይኖርበታል?! ብሎ መጠየቅና ለሚሆነውም መዘጋጀት መልካም ነው፡፡

ሁለቱም ወገኖች ከሚያሳዩት እብሪት፤ ከሚሰብኩት ጥላቻና ከጦርነታቸው እንዲወጡ ከተፈለገ የሰሙትን ሁሉ በደፈናው ከማስተጋባት ባሻገር የእያንዳንዱ ዜጋ ነቅቶ መጠየቅ መቻል ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ጦርነት የሚፈታው ችግር ኖሮ ካለማወቁም በላይ በጦርነት የሚያልቀው ድኃው ወጣት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ለዚህም ነው ከዓመታት በፊት አሁን ዓቢይ አህመድ (ኮ/ል) ስማቸውን ደጋግመው የሚጠቅሱላቸው መንግሥቱ ኃ/ማርያም (ኮ/ል) ከህዝብ ለተነሳላቸው የማነው እየሄደ እየሞተ ያለው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ “እናንተም እንዳላችሁት…. እየተለቀመ ወደዘመቻ የሚሄደው የድኃው ልጅ ነው፡፡” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በእርግጥ ከላይ የጠቀስነው ሙዚቀኛ አርሶ አደርነቱን ባይክደውና ቢኮራበትም “ገበሬ!” መባል ክብር እንጂ ስድብ መሆኑን ለመረዳት የሰነፉ ጥቂት ከተሜ ነን ባዮች ይህንን ቀፅለውለታል፡፡ አለመማርን ነውሩ ሊያደርጉበት ሲንተፋተፉም “መማሩንስ ተምረሃል ማስተዋሉን ግን ዘንግተሃል!” መባሉን ረስተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ደጋግመን የጠቀስነው ጆርጅ በርናንድ ሾው “Beware of false knowledge; it is more dangerous than ignorance!” ማለቱ፡፡

በስደት ኑሮው ሳለ የዛሬ ሰባት ዓመት ህይወቱ ያለፈቸረው አብዮታዊ ገጣሚ ኃይሉ ገ/ዩሐንስ “ዲግሪማ ነበረን!” እንዲል ደጋግመን እንዳልነው በሠላምና ግጭት አፈታት ዙሪያ ጥናት አለኝ የሚልና የሠላም ኖቤል ሽልማትን በቀብድነት የወሰደ ሰው የሚመራት አገር የወትሮው አንፃራዊ ሠላሟ እንኳ እንደራቃት አላስተዋሉም፡፡ ማስተዋሉንና በጭፍን አድናቆት ከተሞላው ቅዠታቸው መንቃትና ዙሪያ-ገባቸውን ማስተዋል የሚፈልጉም አይመስልም፡፡ ከቅዠት ጋር ከመኖር ረፍዶም ቢሆን ነቅቶ እውነትን ማየትም ያረፈደ ግን ያልቀረ ጥበብ ነበር፡፡

እነሆ በወሬ ሳይሆን በግንባር ጦርነትን የሚያውቀው የታሪኩ ጋንካሲ ታሪካዊ ንግግር፡- “…ጆሯችን ደማ! ለምንድነው ለመሞት ብቻ ወደ ፊት የምንለው?! አሁን ወጣቶች አይሂዱ፡፡ ሽማግሌዎች ይሂዱ፡፡ ድንጋይ ያንሱና ሳር በጥሰው አናታቸው ላይ ይዘው፡፡ በሽምግልና ይሻላል። አፈ-ሙዙ ይበቃል! መፍትሔ የለውም! መዋጋትን እኔም ተዋግቻለው ከወንድምህ ጋር ነው ሲባል ግን ጎንበስ ብዬ ብቻዬን ሄድኩ፡፡ ተውኩ። ደም አላስተማረንም፣ ጉልበት አላስተማረንም። የኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር የሁሉም ደም ትኩስ ነው፡፡”

እንጠይቅ - መጨረሻችንስ የት ይሆን?!

ወደግጭትና ጦርነት የገባንበት ትክክለኛ ምክንያትና የየተረኮቹ እውናዊነት ለጊዜው ቆይቶን ተስፋ ከተጣለባቸው ተቋማት አንዱ የነበረውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በኃላፊነት እንዲመሩ ወንበር ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ የሆነው የቀድሞ የሠማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ተስፋዬ “የጦርነቱ ምክንያት ሲወገድ” ሠላም እንደሚወርድ መግለፃቸውን አድምጫለሁ፡፡ ይህንን አባባል የፖለቲካ ሀሁ የማያውቅ አንድ ዜጋ ቢጠቀመው ላይገርም ቢችልም በወንበር ላይ የተሾመና ከዚህ በፊት በአንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመሳተፉ “ጠላት” ሆኖ የነበረ ግለሰብ ሲናገረው ግራ ይሆናል፡፡

የሌላው ወገናችንን ህመም እንደራስ ህመምና ችግር መውሰድ ቢያቅተን እንኳ በሌላው ህመም እየሳቅን፤ ህመሙም እኛጋ ቢደርስ እንኳ ብለን መድኃኒት ከመፈለግ ይልቅ በሚሊዮን ተፈናቃይ ነፍስ-ውጪ ነፍስ-ግቢ ኑረት ላይ የስላቅ ጨው እየነሰነስን እንጨትም በቁስሉ እየሰደድንበት መኖር ተመርጧል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የመሆንን ዕድል አጊኝታ ዕድሏን ለፖለቲካ አቋማ አሳልፋ የሸጠችው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳንና የሙዚቀኛውን ታሪኩ ጋንካሲ ገጠመኞች ተማስሎ ለማሳየት ሃሳቡን ጠቅሼ የዛሬ ፅሁፌን ልቋጭ፡፡

ደፍሬ “ምርጫ” በማልለው የቅርጫ-2014 የመራጮች ምዝገባ ማብቂያ ላይ “የምርጫ ካርድ ማውጫ የመጨረሻ ቀን ዛሬ ነው… አብረን እናጠናቀው፡፡” በማለት በማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ “ዲሽታጊና” የተባለውን ሙዚቃ ተጋብዞ እንደነበርና ግብዣውም “የጎን ውጋት” ተብለው በወቅቱ የፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ብቻ የተዘለፉትንም የጨመረ ነበር፡፡ ዝርዝሩ ቆይቶን በዘመነ ኢህአዴግ ወ/ት ብርቱካን በስዊድን ሀገር ባደረገችው ንግግር መነሾ ምክንያት ይቅርታ እንድትጠይቅ ስትገደድ “ቃሌ!” በሚል ርዕስ በወቅቱ የፖለቲካ ገበያውን ትመራ በነበረችው “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ ሐተታዋን በማስነበብና የምትለውጠው አቋም እንደሌለ በመግለፅ ለድጋሚ እስር ተዳርጋ ነበር፡፡

ያን ጊዜ የወ/ሪቷ ፖለቲካዊ ፀብ ከህዝብም ሆነ ከመንግሥት ሳይሆን ከኢህአዴጋውያን ጋር ብቻ ነበርና ተፅዕኖው የከበደ አልነበረም፡፡ ሙዚቀኛው ታሪኩ ጋንካሲ ግን አያያዛችን ከሚያስፈራውና በተደጋጋሚ ካስጠነቀቅነውና በዚያው መድረክ ላይ ከተስተዋለው የህዝብ አፋኝነት፤ የመንግሥት አስተዳደር፤ እንዲሁም ስምና መሪውን ቀይሮ በዚያው አፋኝነቱ ከቀጠለው ኢህአዴጋዊው የብልፅግና አደረጃጀትና ሹማምንት ጋር ሆነ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጋር መጋፈጡ ደግሞ የጀግንነቱን ጥግ ያስመለክተናል - ቀላል አይደለምና፡፡

ገዢው ሰውዬና ፓርቲውም ሆኑ መንግሥትና ደጋፊዎቹ እንዲሁም የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት ሰጪና-ከልካዮቹ በተከታታይ ዘምተውበት ራሱን በገጠር እንዲደብቅ ሆኗል፡፡ ብዙዎች ቢረዱለትም ሳይወድ በግዱ “ይቅርታዬን ተቀበሉኝ!” ሲል እንዲናገር ሆኗል፡፡ የታሪኩን ታሪክ ጊዜ የሚገልፀው ታሪክ እስኪፈርደን ድረስ በቃሉ እንሰነባበት፡- “የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሁሉም ነገር ይቅርታ እኔ የእናንተ አብራክ ክፋይ ነኝ፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ነኝ። እኔ አሸባሪውን ቡድን ለመደገፍ በማሰብ የተናገርኩት ነገር የለም፡፡ እናም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተንበርክኬ ይቅርታ እጠይቃለሁ!”

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

_____________________________
ኢዜጋን በሶሺያል ሚድያ ይከታተሉ

ለኢትዮጵያ ዜና፣ ለመዝናኛ ቪድዮዎች፣  የሚከራዩና የሚሸጡ ቤቶች፣ ለክላሲፋይድስ ኢዜጋ ፌስ ቡክ ገፅ ይከታተሉን

ለአዳዲስ ዜናዎች እና ሌሎች አስቸኳይ መረጃዎች በ ኢዜጋ ትዊተር ይከታተሉን

ለ አዳዲስ ስራዎች እና የኢትዮጵያ ዜናዎች የ ኢዜጋ ሊንክደን ገፅ ይከታተሉን


  እትምContact News Editor

Name :
Email :
Phone :
Message :
ezega
ከላይ የሚታየው ጽሁፍ ያስገቡ :